Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየአሊ ካይፋ ሙዚቃዊ አበርክቶ

የአሊ ካይፋ ሙዚቃዊ አበርክቶ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲነሳ በርካታ ድምፃውያን፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች፣ አቀናባሪዎችና ፕሮዲውሰሮች ተያይዘው ይጠቀሳሉ፡፡ በየዘመኑ የነበራቸው አበርክቶ ተደማምሮ በሙዚቃው ዕድገት ከፍተኛ ሚናም ተጫውቷል፡፡ ፊት ለፊት ከሚታዩት የዘርፉ ባለሙያዎች በስተጀርባ ካሉት መካከል አሊ ካይፋን ማሳንት ይቻላል፡፡ ስለ አሊ ከተጻፉ ጽሑፎች መካከል በኢትዮጵያ ኦብዘርቨር ዶት ኮም የተነበበው ይጠቀሳል፡፡ ‹‹አሊ ካይፋ ዘ ማን ሁ ቢውልት ኢትዮጵያስ ሞታውን›› በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ ከአሊ ጋር በጥምረት ስለሠሩ ሙዚቀኞችና ስለእሱም ሙዚቃዊ አበርክቶ ያትታል፡፡ ጸሐፊው አረፋይኔ ፋንታሁን ከአሊ ጋር በስካይፕ፣ ከፍራንሲስ ፋልሴቶ ጋር በኢሜይል ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ተመርኩዞም ስለ አሊ ሥራዎች አቅርቧል፡፡ ጸሐፊው ‹‹ኤ ኰንቨርሴሽን ዊዝ ሚስተር አሊ ካይፋ፤ ሲያትል ኮሚኒቲ ሚዲያ›› እና ‹‹ሰን አዋርድ ፎር ኢትዮጵያስ ሌጀንደሪ ሚውዚሽያን መሐሙድ አህመድ ባይ ኢትዮ ዩዝ ሚዲያ›› አጣቅሷል፡፡

በጽሑፉ እንዳሰፈረው፣ አሊ አብደላ ካይፋ ወይም በብዙኃኑ እንደሚጠራው አሊ ታንጎ፣ ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወይም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ለአበርክቶው ዕውቅና በመስጠትም ፍራንሲስ ፋልሴቶ በኢትዮጲክስ ተከታታይ የሙዚቃ ስብስብ ውስጥ ሥራዎቹን አካቷል፡፡ አሊ ታንጎ ከመድረክ በስተጀርባ ያለውን አስተዋጽኦ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ድንቅ ሥራዎች ላይም መመልከት ይቻላል፡፡

እ.ኤ.አ. 1970ዎቹ፣ 1980ዎቹ እና የ1990ዎቹ የአዲስ አበባ የሙዚቃ ድባብ የጀርባ አጥንት የሆነው አሊ ካይፋ ስኬታማ ሥራዎች የተመረኮዙት በማዋቅር ችሎታውንና በሙያዊ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ነው፡፡ ካይፋ ሪከርድ ሌብልም በኢትዮጵያ ስኬታማው ሪከርድ ሌብል ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ተወዳጅነትን ያተረፉ ዕውቅ ሙዚቃዎችም ፕሮዲውስ ተደርገውበታል፡፡

- Advertisement -

አሊ ከኢትዮጵያዊት እናትና የመናዊ አባት ጅማ ውስጥ ተወለደ፡፡ ወጣት ሳለ ግማሽ ቀን እየተማረ በተቀረው ጊዜ አባቱ በተሰማራበት የቡና ንግድ ያግዝ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ እግር ኳስ ይወድ ነበርና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ተላቅሎ ከዕውቆቹ ነፀረ ወልደሥላሴና መንግሥቱ ወርቁ ጎን ለጎን ተጫውቷል፡፡ ወንድሙ አህመድ በክር ክለቡን እንዲቀላቀል አበረታቶት ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ከጀመረ በኋላ በችሎታው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እንዲጫወት ተደርጓል፡፡

የአሊ አባት ጠንካራ የቤተሰባዊነትና የታታሪ ሠራተኝነት ስሜትን በማስረጽ ልጆቻቸውን አሳድገዋቸዋልና ልጆቻቸው የአባታቸውን ፈለግ ተከትለዋል፡፡ የአሊ ወንድም ዘመንኛውን ሴኮ ሰዓት ከውጪ ያስመጣ ነበርና ‹‹መሐመድ ሴኮ›› የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለት ነበር፡፡ የአሊ የቡና ንግድ ሲዳከም የሶኒ ወኪል ሆኖ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ያስመጣ ጀመር፡፡ የጌታቸው ካሳን ትዝታ በሰማበት ቅጽበት ግን በሙዚቃ ፍቅር ወደቀ፡፡ ወደ ሙዚቃው ቢዝነስ ለመግባትም ወሰነ፡፡ የእናቱን ካሊፕሶ ሙዚቃ ቤት ወደ ታንጎ ሙዚቃ ቤት የለወጠው በ1970ዎቹ መባቻ ሲሆን፣ ከሦስት አሠርታት በላይ መገኛው ይህ ሙዚቃ ቤት ነበር፡፡

አሊ ወቅቱን ሲገልጸው፣ ‹‹ሱቄ መሀል ፒያሳ ከአምሐ ሐራምቤ ሙዚቃ ፊት ለፊት ነበር፡፡ ብዙ የአምሐ ሪከርድ ሙዚቃዎችን እሸጥ ስለነበር ስለሙዚቃው ቢዝነስ መረጃ ሰጥቶኛል፤›› በማለት ነው፡፡ ሙዚቃ የመቅዳትና ፕሮዲውስ የማድረግ ፍላጎቱ የተጠናከረውም በዚህ ወቅት ነበር፡፡ በእርግጥ የወቅቱ የሙዚቃ ገበያ አምሐ እሸቴና ፊሊፕስ ኢትዮጵያ የገነኑበት ነበር፡፡ አሊ መጀመሪያ ሙዚቃ ሊቀዳ ሲነሳሳ ያሰበው መነሻው የነበረው ጌታቸው ካሳን ነበር፡፡ ጌታቸው ግን ከሐራምቤ ሙዚቃ ቤት ጋር ለመሥራት ስምምነት ገብቶ ስለነበር ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ለመሥራት ሕጋዊ ሒደቶችን መከተል ጀመረ፡፡ ካይፋ ሪከርድስ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ዕድገት የተጫወተው ሚና መነሻውም ያ ወቅት ነበር፡፡ በግንባር ቀደምትነት በሸክላ ከተቀዱት ሙዚቃዎች መካከል የዓለማየሁ ቦርቦር ‹‹በላዬ በላዬ›› ይጠቀሳል፡፡ ‹‹እንደጠበኩት ባይሆንም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል፤›› ሲል አሊ ስለ ሥራው ይገልጻል፡፡ በቀጣይ እንደ ዓለማየሁ መስፍን፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ታምራት ፈረንጅ፣ ሙሉቀን ታደሰና አሰለፈች አሽኔን የመሰሉ ዕውቅ ሙዚቀኞች ሥራዎችን ቀድቷል፡፡

ዳኒ ኤ መኰንን ‹‹ኢትዮ ግሩቭ ኦን ዘ ወርልድ ስቴጅ ሚውዚክ፣ ሞቢሊቲ፣ ሜዲቴሽን›› በተሰኘው የጥናት ወረቀት እንዳሰፈረው፣ ከ1976 እስከ 1978 በሸክላ የተቀዱት ሙዚቃዎች በኢትዮጲክስ 13ኛው ሲዲ ላይ ‹‹ጎልደን ሰቨንቲስ›› ወይም ‹‹ወርቃማዎቹ 70ዎቹ›› በሚል ተካተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. 1974ቱ አብዮት በኋላ አምሐ ሪከርድ ተዘግቶ ባለቤቱ አምሐ እሸቴ ወደ አሜሪካ አቀና፡፡ አዳዲስ ሙዚቃ የማግኘት ፍላጎት ሰፊ ነበርና ካይፋ ሪከርድስ ፍላጎቱን ለማሟላት አማራጭ ሆነ፡፡ ከ1978 ወደዚህ ካይፋ ከሸክላ ዋጋው አነስ ወዳለው ካሴት ተዛወረ፡፡ የወቅቱን ከፍተኛ የሙዚቃ ፍላጎት የተረዳውና በትክክለኛው ሰዓት ትክክኛው ቦታ የተገኘው አሊ ፕሮዲውስ ካደረጋቸው ሙዚቃዎች መካከል የአሊ ቢራ፣ የንዋይ ደበበ፣ የሐመልማል አባተ፣ የኪሮስ ዓለማየሁና የሶፍያ አፅብሃ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በካይፋ ሪከርድስ ስኬታማ ጉዟቸውን ከጀመሩ ድምፃውያን አንዷ አስቴር አወቀ ናት፡፡ አሊ እንደሚለው፣ ለዋልያስ ባንድ ሴት ድምፃውያን ሲመለመሉ ከመጡት አንዷ አስቴር ነበረች፡፡ ‹‹ትልቅ ተስፋ እንዳላት ስላሰብኩ ከኔ ጋር መሥራት ትፈልግ እንደሆነ ጠየኳት፡፡ በወቅቱ በጊዜያዊነት አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ትሠራ ነበር፡፡ ሐሳቤን ተቀብላ ሥራዎቿን በሸክላ መቅዳት ጀመርኩ፤›› ይላል፡፡ ድምጿ ጎልቶ አይሰማም በሚል ሰዎች ቅሬታ ስላቀረቡ ከውብሸት ፍሰሐ ጋር እንድትለማመድ ቦታ እንደሰጣቸውም ያስታውሳል፡፡ ቤቱ በሰጣቸው ቦታም ለዓመት ተለማምደዋል፡፡ ‹‹ኦሪጂናል ካሴት ስቀዳላት ሙዚቃዎቹ በአጥጋቢ ሁኔታ ተሠርተው ነበር፡፡ ኮከብ ድምፃዊ ለመሆን እንደተፈጠረች አውቅ ስለነበር ሥራዎቿን በሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስተዋወቅ አስላስፈለገኝም፤›› ይላል፡፡ ከዚያ በኋላ ለአስቴር አራት ካሴቶችና ሁለት ነጠላ ዜማ ሠርቷል፡፡

ከአሊ ዕውቅ ፕሮዳክሽኖች ውስጥ ከኢትዮጵያ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራጨው ዘመናዊ ሙዚቃ የመሐሙድ አህመድ ‹‹ኧረ መላ መላ›› ይጠቀሳል፡፡ ከካይፋ ሪከርድ ጋር ከሠሩ በኋላ ተወዳጅነትን ካተረፉ ድምፃውያን አሊ ቢራም ተጠቃሸ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 1966 ክብር ዘበኛን የተቀላቀለው አሊ ቢራ፣ በ1977 ነበር ከካይፋ ሪከርድስ ጋር የሠራው፡፡ ‹‹አሊ ቢራን መጀመሪያ ስተዋወቀው ዕውቅናው በትውልድ አገሩ ድሬዳዋ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ሥራዎቹን መቅዳት ባልፈልግም አጥብቆ ሲጠይቀኝ ተስማማሁ፡፡ ሥራው በአስገራሚ ሁኔታ አዲስ አበባ ውስጥና በአገሪቱም በአጭር ጊዜ ዕውቅናን አገኘ፡፡ የምሽት ክበብ መሥራትም ጀመረ፤›› ይላል፡፡

በ1977 አሊ የኪቦርዲስቱን ኃይሉ መርጊያ በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ቀድቷል፡፡ ኃይሉ በዕውቆቹ ዋልያስ ባንድና ሙላቱ አስታጥቄ ታጅቦ ነበር፡፡ አሊ የኃይሉን ዕድገት ያስተዋለው ባንዱ ሲጫወት እንደ ታዳሚ በሚመለከትበት ወቅት ሲሆን፣ የአቀናባሪና ፒያኒስቱ ግርማ በየነንም ተሳትፎ ይጠቅሳል፡፡ ከሦስት አሠርታት በኋላ ሥራዎቹን ፕሮዲውሰሩ ብራየን ሺምቪትሶ አግኝቶ ዳግም ታትሟል፡፡

ሌላው ከአሊ ጋር የሠራው ድምፃዊ ንዋይ ደበበ ከአሊ የተገናኘው በ1985 ነበር፡፡ በወቅቱ ንዋይ በግጥም ደራሲነትና ድምፃዊነት ሲኒማ ራስ ይሠራ ነበር፡፡ አሊ ሁኔታውን ሲገልጽ፣ ‹‹በወቅቱ ታዋቂ የነበረው የፀሐዬ ዮሐንስ ‹‹ያዝ ያዝ›› ግጥም የጻፈውና ያቀናበረው እሱ ነበር፡፡ ሌሎች የሙዚቃ ፕሮዲውሰሮች የድምፁ ጉልበት ለአብዮት ሙዚቃ እንጂ ለፍቅር ዘፈን አይሆንም በሚል አልተቀበሉትም፡፡ ከዚያ የንዋይን አልበም ስቀዳ ዕውቅ ሆነ፤›› በማለት ይናገራል፡፡ ‹‹እሸት በላሁ›› እና ‹‹የጥቅምት አበባ›› በአጭር ጊዜ ከተወደዱ ሥራዎቹ መካከል ሲሆኑ፣ ሥራው በወራት 10,000 ኮፒ በላይ ተሽጧል፡፡ ንዋይ ደበበ ወደ ዕውቅና እንዲመጣና ሥራዎቹ ተደማጭነት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድም ከሚያመሰግናቸው መካከል አሊ ካይፋ ተቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡

እ.ኤ.አ. 1973 እስከ 1977 ድረስ አሊ 53 ሥራዎች ፕሮዲውስ አድርጓል፡፡ በርካታ አማተር ድምፃውያንን ለዓለም አቀፍ ዕውቅና አብቅቷል፡፡ በሙዚቀኞች ዘንድ በታማኝነትና በቀናነት በጎ ስምም አትርፏል፡፡ አሊ ፕሮፌሽናል ስቱዲዮዎች ባለመኖራቸው ምክንያት ጥራታቸው የወረደ ሥራዎች መቅረባቸውን ግን አይክድም፡፡ ‹‹በቂ መሣሪያም ስላልነበረን የጥራት ደረጃቸው የወረደ ሥራዎች ነበሩ፤›› ይላል፡፡ የተሻሉ መሣሪያዎችን ከውጪ ለማስገባት ወታደራዊው መንግሥት እንዳልፈቀደም ያክላል፡፡ በውጪ ምንዛሪ ክፍፍል ረገድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደነበሩ ይነገራቸው ነበር፡፡ ከዚህ ችግር በተጨማሪ ዘርፉን የሚፈታተነው ስርቆትም አሊን አውኮታል፡፡ አዳዲስ ሙዚቃ ቤቶች ሲከፈቱ ችግሩ እየጎላ ሄደ፡፡ በአገር ውስጥ ሪከርድ ሌብሎች ኦሪጂናል ያልሆኑ ካሴቶች ኅትመትም ተስፋፋ፡፡ ‹‹አዳዲስ ካሴት ስለቅ ሌሎች ሙዚቃ ቤቶች ያለፈቃድ አባዝተው በሱቃቸው ይሸጡታል፤›› ይላል፡፡ በዚህ ሳቢያ በሪከርዲንግ ሌብልና ሙዚቀኞች የሚያገኙት ጥቅም ውስን ነበር፡፡

‹‹የስርቆሹ መጠን ከፍ ማለቱ ከቢዝነሱ ለአራት ዓመት እንድወጣ አስገደደኝ፡፡  ሕገወጥ በሆነ መንገድ ሥራዎቼን በድጋሚ ፕሮዲውስ በማድረግ የተሰማሩ ጥቂት ሙዚቃ ቤቶች ነበሩ፡፡ እኔም እንደነሱ ኅትመታቸውን በሱቄ በመሸጥ ብድሩን መክፈል ጀመርኩ፡፡ በሕገወጥ መንገድ መሄድ ባለቤቱ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነበር፡፡ በሥራዬ ተናደው ሁለቱ በጠበቃዬ በኩል ጠየቁኝ፡፡ ሆነ ብዬ የኔን ሪከርዶች ከመደብራቸው ሳስገዛ በሕገወጥ መንገድ ያሳተሟቸው ሥራዎቼ የነሱ ስም ተለጥፎባቸው ተገኙ፡፡ ከዚህ በላይ ማስረጃ ስለሌለኝ ለ15 ዓመታት ድካሜ የሚከፍሉኝ ከሆነ ለአራት ዓመታት ያጡትን እንደምከፍላቸው ገለጽኩላቸው፡፡ መልስ አልነበራቸውም፤›› ይላል፡፡

ወታደራዊው መንግሥት በእጅጉ ባየለበት ወቅት ወደ አሊ ስለሚያመሩት ግለሰቦች ፍራንሲስ ፋልሴቶ ሲገልጽ፣ ‹‹ብዙዎቹ ሱቁ ሄደው የአሜሪካና የእንግሊዝ ፊልሞችና የቲቪ ፕሮግራሞች ይከራዩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ በመንግሥት በሚተዳደረው ቴሌቪዥንና ሬዲዩ በሚሰራጨው የሶሻሊስት ፕሮፓጋንዳ ተሰላችተው ነበር፤›› ይላል፡፡

ፍራንሲስ ፋልሴቶ ከአሊ ሥራዎች መካከል ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያቀረባቸው አሉ፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ወዳጅነት እስከዛሬም ዘልቋል፡፡ ከፍራንሲስ ፋልሴቶ በተጨማሪ ለቀድሞውና ሮሃ ባንድም አሊ ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ የረዥም ጊዜ አጋሮቼ የሚላቸው ሰላም ሥዩምና ጂኦቫኒ ሪኮ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አሊ ታንጎ አሁን 74 ዓመቱ ሲሆን፣ ሲያትል ዋሽንግተን ውስጥ ይኖራል፡፡ ሙዚቃ ቤቱ ታንጎ ግን ዛሬ ላይ የለም፡፡ የመጨረሻ ካሴቱ የታተመው በ1990 ሲሆን፣ በወቅቱ ከፍተኛ ዕውቅና ያገኘው የጌታቸው ጋዲሳ ‹‹ይፈላ ቡና ይፈላ ሻይ›› ነበር፡፡ አሊ በመጀመሪያ ወደ የመን ከዚያም አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት ልጁ አብዲ ሙዚቃ ቤቱን አትክልት ተራ አካባቢ ለማስቀጠል ሞክሮ ከአምስት ዓመት በላይ አልዘለቀም፡፡ አሊ የ13 ልጆችና በሙዚቃው ረገድ የመቶዎች የሙያ አባት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያ ሙዚቃን እንደሚከታተልም ይገልጻል፡፡ አዲሱ ትውልድ ባህላዊና ዘመናዊ ዘዬ በማዋሃድ የሚሠራውን ሥራ እንደሚያደንቅም ያክላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...