Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አማራጭ ድምፆች እንዲደመጡ የፖለቲካው ምኅዳር ይከፋፈት!

ያለንበት ዘመን በጣም ከመራቀቁ የተነሳ ዓለም በፈጣን የለውጥ ሒደት ውስጥ ናት፡፡ ምጡቅና ነፃ የሆኑ አዕምሮዎች የፈጠሩዋቸው ቴክኖሎጂዎች የዓለምን የሥልጣኔ ግስጋሴ እያፋጠኑት ሲሆን፣ ምርትና ምርታማነትም በጣም እየጨመሩ ነው፡፡ አዳዲስ ትኩስ ሐሳቦች በአመቺ ሁኔታዎች ውስጥ ሲንሸራሸሩ፣ የሰውን ልጅ ድካም የሚቀንሱና ሕይወቱን ቀለል የሚያደርጉለት የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ይፈጠራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ በሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች ውስጥ ለጥጠን ስናየው፣ ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ ለአገር ብልፅግናና ለሕዝብ የኑሮ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች አዳዲስ አስተሳሰቦችና ዕውቀቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ዘመን ያለፋባቸውን አመለካከቶች የመጠቀሚያ ጊዜው እንዳለፈበት ምግብ ወይም መድኃኒት በማስወገድ፣ ያለንበትን ሥልጡን ዘመን የሚወክሉ አዳዲስ አማራጮችን ማስተናገድ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

ከየትም ይምጡ ከማንም ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ አማራጭ የፖለቲካ ድምፆች መደመጥ አለባቸው፡፡ ‹‹አንድ አይነድ፣ አንድ አይፈርድ››  የሚለው አገራዊ ምሳሌ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታን አስፈላጊነት አመላካች ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዝግትግት ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ተከፋፍቶ አማራጭ ድምፆች እንዲሰሙ፣ ዴሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ከንድፈ ሐሳብነት ተላቆ ገቢራዊ እንዲሆን፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የአገር መለያ ባህልና ጌጥ መሆኑ እንዲረጋገጥ፣ ለአገራቸው ዘለቄታዊ ህልውናና ለዴሞክራሲ ግንባታ ራዕይ ያላቸው ዜጎች በአደባባይ በነፃነት እንዲታዩ፣ ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅሙ የታፈኑ ሐሳቦች ያላንዳች መሰናክል እንዲንሸራሸሩ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሠበት ሥርዓት እንዲፈጠር፣ በሕግ የበላይነት ብቻ የምትተማመን አገር እንድትኖር፣ ወዘተ አማራጭ ድምፆች የሚሰሙበት መድረክ ይመቻች፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩት መሠረታዊ መብቶች በተግባር ተከብረው ዜጎች ለአገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከልብ መነሳት ያስፈልጋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠረው በጠመንጃ በሚገኝ ሥልጣን ሳይሆን፣ የሥልጣኑ ባለቤት በሆነው ሕዝብ ይሁንታ ብቻ ነው፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ፉክክር  በፍትሐዊነት ሲከናወን ዴሞክራሲ የምር ሥርዓት ይሆናል፡፡ የሕግ የበላይነት በትክክል መከበሩ ይረጋገጣል፡፡ በቂምና በጥላቻ አረንቋ ውስጥ የሚዳክረው የአገሪቱ ፖለቲካ ትንሳዔ ያገኛል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሥልጡን አካሄድ ደግሞ መቀራረብ፣ መነጋገር፣ መከራከር፣ መደራደርና መግባባት የግድ ነው፡፡ ፖለቲካው አሁን ካለበት አሳዛኝና አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ ወጥቶ ቂምና ጥላቻ እንዲወገዱ፣ የፉክክር ስሜቱና ግለቱ ከሕገወጥነትና ከፅንፈኝነት ተላቆ የሕዝብ ፈቃድ የሚፈጸምበት እንዲሆን አማራጭ ሐሳብ ያላቸው ያላንዳች ገደብ ይስተናገዱ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብቶች ከወረቀት ጌጥነት ተላቀው ለሥልጡን የፖለቲካ ሒደት ሁሉም ወገን ራሱን ያዘጋጅ፡፡ ከፅንፈኝነትና ከጭፍን ጥላቻ ምንም አይገኝም፡፡ ዴሞክራሲም በዚህ አሳዛኝ መንገድ ተገንብቶ አያውቅም፡፡ የእስካሁኑን አሳዛኝ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ይጀመር፡፡

ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ሳይቀሩ በኃላፊነት ስሜት በመነሳት ለሕዝብ ፈቃድ የሚገዛ ዓውድ እንዲፈጠር መትጋት አለባቸው፡፡ ለአገር ይጠቅማል የተባለ ሐሳብ ከየትኛውም አቅጣጫ ሲሰነዘር እንዲደመጥ፣ መድረክ እንዲያገኝና ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡ ይጥቀምም አይጥቀምም መዳኘት ያለበት በሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ ያሻውን የመምረጥ፣ የማያሻውን የመጣል ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት በመሆኑ ሁሉም የአገሪቱ ሰላማዊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያላቸውን አጀንዳ ይዘው በነፃነት የሚቀርቡበት ምኅዳር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምኅዳር እንዲኖር ደግሞ ገዥው ፓርቲ ትልቅ ኃላፊነት ሲኖርበት፣ ተፎካካሪዎቹም የዚያኑ ያህል በኃላፊነት ስሜት በመነሳሳት ለሒደቱ ማማር እገዛ ማድረግ አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገነባ ሥርዓት እንደመሆኑ መጠን፣ በትንሹም ቢሆን የተቃና ጉዞ  እንዲኖር መስዕዋትነት መክፈል ይገባል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነትም ሆነ እርስ በርሳቸው ከመጠላለፍ አባዜ በመላቀቅ ለሒደቱ ማማር የበኩላቸውን ያድርጉ፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር በአንክሮ ስለሚመለከት ለሕዝብ ዳኝነት ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡

በእርግጥ ገዥው ፓርቲና በተቃውሞ ጎራ የተሠለፉት ኃይሎች እስካሁን የመጡበት መንገድ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምኅዳሩን ዘጋግቶ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መላወሻ ማሳጣቱና በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች እንዳይሆኑ አድርጎ ፓርላማውን መቆጣጣሩ፣ የአገሪቱ የተበላሸ ፖለቲካ አንድ ገጽታ ማሳያ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ፓርቲዎቹ እንዲንኮታኮቱና እንዲበታተኑ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ሌላው አሳዛኝ ገጽታ ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ለአልፎ ሂያጅ መንገደኛ ጭምር እንስኪያስገርምና እስኪያስተክዝ ድረስ ተበላሽቷል፡፡ አሁን ባለቀ ሰዓት አዲስ ተስፋ መፈንጠቅ ቢጀምርም፣ የተሠራው ሥራ ግን የራሱን ጥላ እያጠላ አለመተማመን መፍጠሩን ማንም አይክድም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተቃውሞው ጎራ በራሱ ችግር የፈጠራቸው ደግሞ ፖለቲካውን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡ ይህን ነው የሚባል አማራጭ ለማቅረብ ካለመቻል አንስቶ እስከ ዳያስፖራው የገንዘብ ድጋፍ ድረስ የነበረው ውስጣዊ ሽኩቻ፣ በፓርቲ ፕሮግራም ላይ የሠፈሩትን ዓላማዎች ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ የሌሎች አጀንዳ ተሸካሚ  መሆን፣ ከመጠን ያለፈ የገንዘብ እጥረት በፈጠረው ጥገኝነት አቅመ ቢስ መሆን፣ የግለሰቦች ተክለ ሰውነት ያለመጠን መግዘፍ፣ ከዓላማ አንድነት ይልቅ በአኩራፊነት ብቻ መሰባሰብ፣ የአባላትና የደጋፊዎች ንቃተ ህሊና አለመጎልመስ፣ መድረኩ በሙሉ ቢዘጋጋም እንኳን ቤት ለቤት በመሄድ ሕዝቡን ማግኘት ያለመቻል ስንፍና፣ ፖለቲካን የትርፍ ሰዓት ሥራ ማድረግ፣ ወዘተ የድክመት መገለጫ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ እነዚህን ድክመቶች አስወግዶ ሕዝብ በሚፈልገው ቁመና ላይ መገኘትና አማራጭ ድምፅ መሆን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ያለበለዚያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራን ለሚችሉት መተው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ድረስ በተዘረጋ የተለያየ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖር፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ አስተሳሰቦችና የመሳሰሉት ባለቤቶች ቢሆንም በአመዛኙ በሥነ ልቦና አንድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን ኩሩና ጀግና ሕዝብ አስተባብሮ ይህችን አገር ከድህነት ማጥ ውስጥ ማውጣት እጅግ በጣም ቀላል ሥራ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የሚፈልገው ብቁ አመራር ብቻ ነው፡፡ በተለይ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉ የፖለቲካ ኃይሎች ይህ ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብ የሚፈልገው አገሩ ሰላም እንድትሆንለት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊት እንድትሆን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲከበርባት ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖርባት ነው፡፡ ፍትሕ በተግባር የተረጋገጠባትና ዜጎቿ በነፃነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ጦር አውርድ የሚሉ፣ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚሻረኩ፣ ሥልጣንን ሙጥኝ ብለው አገር የሚዘርፉ፣ ልዩነቶቹን እያጋነኑ የሚከፋፍሉትንና አገሩን ለጥፋት የሚዳርጉትን ይፋረዳቸዋል፡፡ ይህ ጨዋና ጀግና ሕዝብ ልዩነትን ሳይሆን አንድነትን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን፣ ከሃዲነትን ሳይሆን ጀግንነትን የጋራ መገለጫው ያደረገ ተምሳሌታዊና አርዓያነቱ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ጭምር በደሙ ያረጋገጠ ወደር የሌለው ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ለአገርና ለሕዝብ የሚመጥን አጀንዳ አለን የሚሉ ዜጎችም ሆኑ የተደራጁ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለውን አላስፈላጊ ቅራኔ ፈትተው ለብሔራዊ መግባባትና ድርድር ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ከምንም በላይ ይህንን ኩሩ ሕዝብ ያክብሩ፡፡ በዚህም አማራጭ ድምፆች በደንብ እንዲደመጡ የፖለቲካው ምኅዳር ይከፋፈት! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...