Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአገራችን ባንኮች የትርፍ ድርሻ ምጣኔ ከዓለም አንደኛ ነው›› አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ

በእያንዳንዱ የብር ኖት ላይ ‹‹ላምጪው እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል›› የሚለው መልዕክት ሥር ወረድ ብሎ አንድ ፊርማ በጉልህ ይታያል፡፡ ከፊርማው ሥር በአማርኛ ‹‹ገዥ›› በእንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹Governor›› የሚል ጽሑፍ ይነበባል፡፡ እነዚህ ቃላት በሌሎች አገሮች የገንዘብ ኖቶች ላይም የተለመዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የብር ኖት ላይ ፊርማቸውን የሚያኖሩት የወቅቱ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ላይ ፊርማቸውን የምናየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ባንኩን እየመሩ ያሉት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ናቸው፡፡ አቶ ተክለወልድ የባንኩን ትልቁን የኃላፊነት ቦታ ከተረከቡ ከ12 ዓመታት በላይ ቢሆናቸውም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋና መዘውሮች ከሆኑት መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ከተቀላቀሉ ግን 30 ዓመታትን ሊደፍኑ ነው፡፡ ወደ ብሔራዊ ባንክ የመጡትም በባንኩ ሪሰርች ዲፓርትመንት የሪሰርች ኦፊሰር በመሆን ነበር፡፡ ከዚያም ሲኒየር ሪሰርች ኦፊሰር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ በዚሁ ዲፓርትመንት ውስጥ የሞኒተሪና ባንኪንግ ዲቪዥን ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢኮኖሚክ ሪሰርችና ሞኒተሪ ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የግል ፋይናንስ ተቋማት እንዲቋቋሙ ሲፈቀድ፣ ለእነዚህ ተቋማት ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የሚተዳደሩበትን ደንብና አሠራር ከመቅረፅ እስከ መቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠውን አዲስ ሱፐርቪዥን በዳይሬክቶሬት እንዲመሩ፣ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ዛሬ የፋይናንስ ተቋማት የሚተዳደሩባቸውን ሕግጋት ከመቅረፅ እስከ ማስፈጸም የሚደርሰውን ሥራ አከናውነዋል፡፡ በዚህ የኃላፊነት ቦታቸው ለዓመታት ከቆዩ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እንዲሆኑ፣ ከዚያም የባንኩ ገዥ በመሆን እንዲሠሩ ተሹመው እስካሁን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ አቶ ተክለወልድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ከመቀላቀላቸው በፊት በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ረዳት ኤክስፐርት ሆነው ማገልገላቸውም ይጠቀሳል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት በመምህርነት ሠርተዋል፡፡ ከፋይናንስ ዘርፉ ጋር የተቆራኘ አገልግሎታቸው ጅማሬ ለማስተርስ ዲግሪያቸው ከመረጡት የመመረቂያ ጽሑፍ ይጀምራል ሊባል ይችላል፡፡ የመመረቂያ ጽሑፋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሞኒተሪ ፖሊሲ ሁኔታና አጠቃላይ የገንዘብ አቅርቦቱ ምን ይመስላል የሚለውን ጉዳይ የፈተሸ ነበር፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል ወደ ብሔራዊ ባንክ ለመምጣታቸው አንዱ ምክንያት ይኸው ጽሑፍ ነው፡፡ በስታትስቲክስ፣ በኢኮሜትሪክስና በፋይናንሻል ማኔጅመንት ሦስት ዲግሪዎችን ያገኙት አቶ ተክለወልድ በማክሮ ማኔጅመንት፣ በፋይናንሻል ፕሮግራሚንግ፣ በባላንስ ኦፍ ፔይመንት፣ በሞኒተሪ ስትራቴጂና በመሳሰሉት ትምህርቶች ከሰባት በላይ ዲፕሎማዎችን አግኝተዋል፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ጉዳዮች አሻራቸውን ካሳረፉ ባለሙያዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ተክለወልድንና የሚመሩትን ባንክ የተመለከቱ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ በተወሰኑ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በተለይም የፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡    

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ በተለይም የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት እንዴት ሊገለጽ ይችላል? 

አቶ ተክለወልድ፡- ብዙ ጊዜ እንደ ዓለም ባንክ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና እኛም ስናጠና እንዳየነው በደርግ መውደቂያ አካባቢ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተንኮታክቶ ነበር፡፡ እንደዚያ ተንኮታኩቶ የነበረውን ኢኮኖሚ ለማንሳት ፈታኝ ነበር፡፡ ከ1984 እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ የመወቅራዊ ማስተካከያ ፕሮግራም ከዓለም ባንክና ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ጋር በመሆን ሠርተናል፡፡ ወደ ነፃ ገበያ ለመግባት ብዙ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የማረጋጋትና ኢኮኖሚው እንዲያንሠራራ መደላድሎችን ከመፍጠር ባሻገር፣ ኢኮኖሚውን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ብዙ ይቀረን ነበር፡፡ ግን በዚያም ወቅት ቢሆን በአሥር ዓመት ውስጥ ከ4.5 በመቶ ያላነሰ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዋናነት መሠረት የተባለውና ኢኮኖሚው ዕድገት ማምጣት የቻለው ከ1994 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- 1994 ዓ.ም. በተለይ የዕድገቱ መንደርደሪያ ተደርጎ የተወሰደበት ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ተክለወልድ፡- በዋናነት እንደ ምክንያት አድርገን ማየት ያለብን የአሥር ዓመታት ዕውቀት ተሰባስቦ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ በኩል የአስተሳሰብ ለውጦች በመፈጠራቸው ነው፡፡ ተሃድሶ ተብሎ በሚጠራውና ጥርት ባለ መንገድ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት፤ በምን መልክ መሄድ አለበት? የሚለው ነገር በበለጠ ቅርፅ ይዞ ሊወጣ በመቻሉ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ነፃ ገበያ ፖሊሲ ነው የምናራምደው፡፡ በዚያ ማዕቀፍ ለመሥራት ግብርና መር  ኢንዱስትሪን መሠረት በማድረግ ይሠራ ነበር፡፡ ለድህነት ቅነሳና ለመሳሰሉት ከነአይኤምኤፍ ጋር በመሆን መወዋቅራዊ ማስተካከያ ፕሮግራም ውስጥ መግባት የግድ ነበር፡፡ በዚህ መካከል ብዙ ተሠርቶ 4.5 በመቶ የሚሆነው ዕድገት መጥቷል፡፡ በደርግ ጊዜ የነበሩትን ሥራዎች በማስቀረት ዋጋ የሚወሰኑ ገበያ የመፍጠር ሥራዎች ሁሉ ተሠርተዋል፡፡ ይህም ቢሆን የጠራ የኢኮኖሚ አቅጣጫና የመጨረሻው ግባችን ደግሞ ምንድነው? የሚለው ሁሉ መልስ የሚሰጠው አጀንዳ የተቀረፀው በ1994 ዓ.ም. ነው፡፡ የግብርና ልማት ስትራቴጂና ፖሊሲ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲና የመሳሰሉት  ስትራቴጂዎች የተቀረፀበት ነው፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች መድረስ አለብን ብለን ያስቀመጥንበት ጊዜ ስለነበርም ነው፡፡ 1994 ዓ.ም. የጠቀስኩት ይህንን ለማድረግ ስትራቴጂ የተቀመጠውም ያኔ ነው፡፡ አሁን እየተወራ ያለው ስለጂቲፒ 1 እና 2 ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ በዚሁ መሠረት የተቀረፁትን ዕቅዶች ለማሳካት የፋይናንስ ሥርዓቱ ምንድነው የሚያግዘው? በወቅቱ በነበረው ዕቅድ መሠረት ግብርናውን ለማሳደግ ለማዳበሪያና ለመሳሰሉት በምን መልኩ ነው ብድር ማዘጋጀት አለብን? ተብሎ ዕቅድ ተቀምጦ የተሠራበት ነው፡፡ በተጓዳኝም መሠረተ ልማት የተስፋፋበት ነበር፡፡

አሁን ወደ መጀመሪያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተገባውም በዚያን ወቅት በተጣለው መሠረት ነው፡፡ በዚህ ዕቅድም ኢኮኖሚው ባለሁለት አኃዝ ዕድገት መምጣት አለበት ተብሎ ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ ማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ መሆን አለበትና ለዚህም ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረግ ያለበት ግብርናው ነው፡፡ ግብርናው ከሰባት እስከ ስምንት በመቶ ማደግ አለበት፡፡ የአርሶ አደር ግብርና፣ ሜካናይዜሽንና ሌሎችም መጠናከር አለባቸው ተብሎ ተቀምጦ በዚሁ መሠረት ተሠርቷል፡፡ በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትም የወጪ ንግዱ ገቢ ከግብርና መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በተገኘው የውጭ ምንዛሪ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ማስፋት እንደሚቻል፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ግን ከሌሎችም የሚገኘውን በማቀናጀት የኢንዱስትሪ ልማቱን ማስፋት አለብን ብለን ለዚህ ደግሞ መሠረተ ልማቶችን ማስፋት ቁልፍ ነው ብለን የሠራነውም በዚሁ ዕቅድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያው የዕድገት ዘመን የተገኘው ውጤት ተሳክቷል ማለት ይቻላል?

አቶ ተክለወልድ፡- በአምስት ዓመቱ የመጣው ዕድገት ከአሥር በመቶ በላይ ስለሆነ የተሳካ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ሁሉ ውጤት መገኘት ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ እንደገለጹልኝ ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ የፋይናንስ ዘርፉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ ይህ አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ተክለወልድ፡- ኢኮኖሚውን በሦስት ደረጃ እንኳን ብናይ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ አሉ፡፡ እነዚህ ዘርፎች የተቀመጠላቸው ግብ ሊያሳኩ የሚችሉት ፋይናንሱ ሲኖር ነው፡፡ ያለፋይናንስ የሚካሄድ ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ ለግብርናውም፣ ለኢንዱስትሪ መሠረተ ልማትና ተያያዥ ለሆኑ ዘርፎች ሁሉ ያለፋይናንስ የትም ሊኬድ አይችልም፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ የሚባለው ራሱ ከንግድ ጀምሮ ከሥር ላይ ያለው ሥራ ሊከናወን የሚችለው ፋይናንስ ሲኖር ነው፡፡ የመጀመሪያውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስንቀርፅ  የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ዋነኛ ተግዳሮት ይሆናል ብለን ፋይናንስ ነው፡፡ ይህንን ተግዳሮት ለማለዘብ በሁለት መልክ እንሠራለን ብለነው የገባንበት፡፡ አንደኛውና ዋነኛው አገራዊ ፋይናንሲንጉን ማስፋት ነው፡፡ ለዚህም ቀዳሚ ሆኖ የተወሰደው የአገር ውስጥ ቁጠባን ማስፋት ነው፡፡ ይህም ቁጠባ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ቁጠባዎች ብለን በመለየት የሠራንበት ነው፡፡ ይኼ ቁጠባ የሚገለጸው በፋይናንስ ሴክተር በኩል ነው፡፡ ይህንን ቁጠባ ለማሳደግ ዕቅድ ይዘን ሠርተናል፡፡ አንደኛ ቁጠባውን ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት? ሲባል የአገራችን የፋይናንስ አገልግሎትና ተደራሽነቱ ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ፣ ቢቆጥብም በባንክ ሳይሆን በሌላ በኩል መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ለምሳሌ በሬ በመግዛትና በመሳሰሉት ነው የሚቆጠበው፡፡ ይህንን ለመለወጥና ቁጠባውን ለማሳደግ የምንችለው የባንክ ተደራሽነትን በማስፋት ነው ብለን፣ ባንኮች ተደራሽነታቸውን በገፍ ማሳደግ ይኖርባቸዋል በማለት ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ የባንክ ቅርራጫፎች ቁጥር ቢያንስ ከ25 እስከ 30 በመቶ ማሳደግ አለብን ብለን ነው ያቀድነው፡፡ ይህንን በማድረጋችን ከጠበቅነው በላይ ተሳክቶልናል፡፡ አንዱ መገለጫ ይህ ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- በዚህ መንገድ ቅርንጫፎች ማሳደጉ በቁጠባው ላይ ምን ያህል ለውጥ አመጣ? ኢኮኖሚው ላይ ያሳረፈው አሻራ እንዴት ይታያል?

አቶ ተክለወልድ፡- ልመጣልህ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም. 680 አካባቢ ብቻ የነበረው የቅርንጫፎች ቁጥር በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ 2,800 ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ 3,900 ደርሷል፡፡ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም 1,600 ቅርንጫፎች መድረስ ቻሉ፡፡ ያቀድነውን  ተግባራዊ በማድረጋችን የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ፡፡ በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከነበረው ወደ ስድስት እጥፍ አደገ፡፡ በቁጠባው መጨመር የተሰጠው የብድር መጠን ወደ አምስት እጥፍ ጨመረ፡፡ ይህ ማለት በመጀመሪያው ዕቅድ ዘመን ከጠበቅነው በላይ ፋይናንስ ተሰብስቦ ብድር ተሰጥቷል፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ማለት ነው፡፡ ነገሩ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ሌላው ያደረግነው ነገር ኢኮኖሚው ኢንዱስትሪ መር መሆን አለበት ስላልን ለማኑፋክቸሪንግና ለመሳሰሉት የረዥም ጊዜ ብድር ይስጥ የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የተሰበሰበውን ገንዘብ በምን ዓይነት መልክ ነው ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ማድረስ የምንችለው በማለት፣ የሌሎች አገሮችን ልምድ ዓይተን ብዙ ጊዜ ሲጮህበት ወደነበረውና በኋላ ላይ ወደተሳካው ጉዳይ ገባን፡፡  

ሪፖርተር፡- ከእያንዳንዱ ከሚሰጥ ብድር 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ ማዋል ወደሚለው አሠራር ማለት ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- አዎ፡፡ ባንኮቹ ቅርንጫፎች እስካስፋፉና ገንዘብ እስከሰበሰቡ ድረስ ይኼ ገንዘብ ደግሞ አንድ አካባቢ ብቻ ከሚውል ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ አዲስ ሥራ እንዲፈጠርና ገቢ እንዲጨምር አድርገን ድህነት እንዲቀንስ ለማድረግና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ዋናው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የረዥም ጊዜ ብድር ይፈልጋል፡፡ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ ይህንን ለመተግበር ባንኮችን ሳይጎዳ ሌሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የብሔራዊ ባንክ ሰነድን እንዲገዙ ማድረግ አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ሁልጊዜ ከሚሰጡት ብድር 27 በመቶ ለሰነድ ግዥ እንዲያውሉ፣ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ ለልማት ባንክ በመስጠት ባንኩ ለማኑፋክቸሪንግና ለመሳሰሉት እንዲያበድር በማድረጋችን በዚህ ረገድ የነበረውን ማነቆ ፈትተናል፡፡ ይኼ ትልቁ መፍትሔ ነበር፡፡    

ሪፖርተር፡- ይህ አሠራር ወይም መመርያ ግን የግል ባንኮቹን ስለመጉዳቱ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ተፅዕኖ አላሳደረባቸውም?

አቶ ተክለወልድ፡- ይህንን በማድረጋችን ብዙ ሲወራ ነበር፡፡ ግን ምንም ነገር አልተፈጠረም፡፡ ጥናትም አስጠንተን የሠራነው ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ ተግባራዊ ከማድረጋችንም በፊት የእነ ህንድን ልምድ ዓይተን ነው መመርያውን ያወጣነው፡፡ ዝም ብለን የገባንበት አይደለም፡፡ አሠራሩ እኛ የጀመርነውም አይደለም፡፡ የእኛም ብቻ አይደለም፡፡ እንደነ ህንድ ያሉ አገሮች አሁንም እየሠሩበት ነው፡፡ እንዲያውም የህንድ 40 በመቶ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- በ27 በመቶ ታስቦ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ገንዘብ በባንኮቹ እጅ ቢኖር፣ የበለጠ ማበደር ችለው የበለጠ ትርፍ እንዲያገኙ አያደርግም ነበር? ባላቸው ልክ ያለማበደራቸው ጉዳት አይደለም?

አቶ ተክለወልድ፡- ጉዳት እንዳላደረሰ ለማሳየት ከዓለም፣ ባንክ ከአይኤምኤፍ፣ ከባንክ ኅብረተሰቡ ጋር ብዙ ተከራክረንበታል፡፡ እኛ አጥንተን ምንም የተጎዱበት ነገር የለም ብለን ነው ያስቀመጥነው፡፡ ወደዚህ ዕርምጃ ከመግባታችን በፊት ባደረግነው ጥናት ባንኮቹ ከሰበሰቡት ገንዘብ ብድር የማይሰጡበት ጊዜ ብዙ እንደነበር አረጋግጠናል፡፡ በዚያን ወቅት የሰበሰቡት ገንዘብ በሙሉ ለብድር እያዋሉት አልነበረም፡፡ እንዲያውም እኛ ሳናዛቸው በቁጠባ ከሰበሰቡት ገንዘብ ወደ 13 እና 14 በመቶ የሚሆነውን ብሔራዊ ባንክ ያስቀምጡ ነበር፡፡ ኤክሰስ ሪዘርቭ ማለት ነው፡፡ ይህንን አየንና ይቀጥል ብለን ወስነናል፡፡ እነሱ ብር ይሰበስባሉ፡፡ የት ያደርጉት ነበር? እንዲያውም ቁጠባ ማሰባሰቡን ይተውት ነበር፡፡ ምክንያቱም የሰበሰቡትን ብድር ካልሰጡ ለቆጣቢ የሚሰጡትም ገንዘብ ያጡ ነበር፡፡ ይህ ማለት ቆጣቢውንም እያበረታታም ነበር፡፡ ሌላ ችግርም ይፈጥር ነበር፡፡ ስለዚህ የወሰድነው ዕርምጃ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደ ማለት ነው፡፡ ቁጠባ እንዲበረታታ አድርገናል፡፡  ቅርንጫፍ እንዲስፋፋ ያበረታታ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ‹ኤክሰስ ሪዘርቭ› መጥቶ ተበዳሪ እስከሌለ ለምን ቅርንጫፍ ይከፍታል? ለምን? እኔ ጋ አስቀምጡ ብሎ ይተናነቃል? ስለዚህ በዚህ ዕርምጃችን ባንኮች ራሳቸው እንዲያበረታቱ አድርገናል፡፡ ለምሳሌ አሁን ካሉት 3,900 ከሚሆኑት የባንክ ቅርንጫፎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የግል ባንኮች ነው፡፡ 20 ሺሕ የነበረው የባንክ ሠራተኛ አሁን ከ100 ሺሕ በላይ መሆን የቻለውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ባንኮች እንዲወዳደሩ አድርገናል፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት የባንኮች ዋነኛ ውድድር ቁጠባ መሰብሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የ27 በመቶ መመርያ ተግባራዊ መሆን ብዙ ጠቀሜታ አስገኝቷል፡፡ ነገር ግን ይባል የነበረው የባንኮች ትርፍ ይወድቃል፣ ቅርንጫፍ ማስፋታቸውን ይገታል፣ የፋይናንሻል ተደራሽነቱ ችግር ላይ ይወድቃል የሚለው ወሬ ሁሉ አልሆነም፡፡ መመርያው የባንክ ባለአክሲዮኖች የሚያገኙትን የትርፍ ድርሻ ስለሚቀንስና ባንክ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያበረታታ ስለሚሆን መጨረሻ ላይ የፋይናንስ ዘርፉ ችግር ላይ ይወድቃል ሲባልም ነበር፡፡ ግን ይህ የተባለው ሁሉ በጭራሽ አልሆነም ማለት ነው፡፡       

ሪፖርተር፡- ስለዚህ 27 በመቶው መመርያ ለለውጥ ምክንያት ሆኗል እያሉኝ ነው ማለት ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- አዎ፡፡ ለለውጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ የባንኮች የትርፍ መጠን ይቀንሳል የተባለውም እኮ አልሆነም፡፡ እንዲያውም የአገራችን ባንኮች የትርፍ ድርሻ ምጣኔ ከዓለም አንደኛ ነው፡፡ 100 ብር አክሲዮን ያለው ሰው 40 ብር ትርፍ ያገኛል፡፡ ይህ በዓለም የሌለ ነው፡፡ ከፍተኛ ተብሎ የሚጠቀስ የትርፍ ድርሻ ነው፡፡ ገና በሚያድጉ አገሮች እንኳ ትልቁ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 20 በመቶ ነው፡፡ ወደ ትልልቆቹ አገሮች ብትሄድ የትርፍ ድርሻው አምስትና ስድስት በመቶ ነው፡፡  ስለዚህ መመርያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ሰጠ እንጂ የተባለውን ጉዳት አላመጣም፡፡ ብዙ ነገር ለውጧል፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ የባንኮች አትራፊነት በዚህን ያህል ደረጃ ትልቅ ነው የሚባለው ለምንድነው? ከሆነስ ለምን ከፍተኛ የትርፍ ድርሻ የተገኘበትና ጥሩ አትራፊ ሆነው የዘለቁበት ሚስጥር ምንድነው?

አቶ ተክለወልድ፡- ይህንን ትርፍ በሁለት ከፍለን ማየት አለብን፡፡ በባንክ ሥራ የአገር ውስጥ የባንክ ሥራና ዓለም አቀፍ የባንክ ሥራ አለ፡፡ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት፣ የኢንፖርት ኤክስፖርት ሌተር ኦፍ ክሬዲት ሥራ ይሠራሉ፡፡ ይህ ሥራ ኮሚሽን አለው፣ ገንዘብ አለው፡፡ እኛ ዘንድ ያለው ኢንፖርተር ሁለት ነገር ያደርጋል፡፡ አንደኛ ዕቃ አምጪው ገንዘብ የለውም፡፡ አሥር ሃያ በመቶ የሚሆን ሊኖረው ይችላል፡፡ ከዚያ ለኢንፖርት ዕቃ መጀመሪያ ብድር ይበደራል፡፡ ይህ ለባንኮቹ የገቢ ምንጭ ነው ማለት ነው፡፡ ላበደሩት ብድር 16 እና 17 በመቶ የወለድ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ከዚያ በኋላ አስመጪው ዶላር ይገዛል፡፡ በራሳቸው ገንዘብ ዶላር ይገዛቸዋል፡፡ በዚህ ግዥና ሽያጭ መካከል ባንኮቹ ደግሞ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ ከዚያ የሌተር ኦፍ ክሬዲት ኮሚሽን ክፍያ ያገኛሉ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ተደምረው በኢንፖርትና በኤክስፖርት 40 በመቶ ትርፍ የሚገኝበት ይሆናል፡፡ አሁን አሁን ቀነሰ እንጂ ከዚህም ይበልጥ ነበር፡፡ በዶላር ላይ የሚሟሟቱት ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርት ኢንፖርቱ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ስለሆነ ትልልቅ ባንኮች ከውጭ ኮረስፖንዳት ባንክ ጋር ሲገበያዩ አልከፈለም የሚል መጥፎ ስም የለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሚገባ ስለሚከታተል ማንኛውም ኮረስፖንዳንት ባንክ ከእነርሱ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን ዶላር ባይኖራቸው እንኳን ‹‹ላይን ኦፍ ክሬዲት›› በሚባለው አሠራር ገንዘብ ሰብስበው እስኪያመጡ ድረስ ያ ባንክ ዕቃ እንደገዙ የሁለት ወራት ጊዜ ይሰጣል፡፡ ይህ መተማመን አለ፡፡ ዶላር እስኪመጣ ድረስ ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ በጨበጣ ጭምር እየተሠራም ጠርቀም ያለ ትርፍ ይገኛል፡፡ ሌላው የብድር ትርፍ ነው፡፡ ለ27 በመቶ ብድር ወለድ አነስተኛ ነች እንጂ ከዚህ ውጪ ከሚሰጡት ብድር ጥሩ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ የሚሰጡትን ብድር እንደፈለጉ ያድርጉ ብለን አንስተንላቸዋል፡፡ እንደፈለጉ ያድርጉ ብለናል፡፡ ስለዚህ ከሚሰጡት ብድርም ጥሩ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ ባንኮች ለቆጣቢዎች የሚከፍሉት ወለድ አምስት በመቶ ነው፡፡ ሲያበድሩ ደግሞ እስከ 17 በመቶ ወለድ ይጠይቁበታል፡፡ በዚህ መሀል ወደ አሥራ አንድ ብር ያህሉ ትርፍ ነው፡፡ ወጪያቸው ሦስት በመቶ አይሞላም፡፡ ለቁጠባ በሚከፍሉትና ለብድር በሚጠይቁት ወለድ መካከል ያለውን ህዳግ ብሔራዊ ባንክ መቆጣጠር አልፈለገም፡፡ 27 በመቶው ተቀንሶ በቀሪው ተቀማጭ ገንዘባቸው የሚያገኙት ትርፍ በጣም ብዙ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የግል ባንኮች በአብዛኛው ብድር የሚሰጡት ለአገልግሎት መሆኑም ለትርፋቸው ዕድገት አንድ ምክንያት ነው፡፡ አገልግሎት አካባቢ ያለውን ነገር ደግሞ ያው የምናውቀው ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ምንድነው የሚታወቀው? ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?

አቶ ተክለወልድ፡- የንግድ አሠራሩንና የመሳሰሉትን ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መለስተኛ የሆነች ጥናት ስናይ አስመጪዎቹ ከውጭ የሚያስገቡት ዕቃ ዋጋ አንድ ሰው ዕቃ ቢገዛ ኮስት ኢንሹራንስና ፍሬይቱ (CIF) ተያይዞ እስከ ጂቡቲ ድረስ ያለው ዋጋ አለ፡፡ ከጂቡቲ በኋላ ያሉ ወጪዎች አሉ፡፡ ጉምሩክም የሚያስከፍለው ክፍያ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ተደምሮ ያለውን ‹ኢንፖርት ፓሪቲ ፕራይስ እንለዋለን፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ዕቃ የሚፈጀውን ዋጋ ይዘን መርካቶ ሄደን ስንት ይሸጣል ብለን ስናይ በጣም የተለየ ነገር ይገኛል፡፡ አንድ ዕቃ አጠቃላይ ወጪው ተደማምሮ የሚኖረው ዋጋና ገበያ ላይ በሚሸጥበት ዋጋ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በሌላው አገር አንድ ዕቃ ፈጀ ተብሎ ከሚገለጸው ከጠቅላላ ወጪው የምትጨምረው ግፋ ቢል አሥር በመቶ ወይም 15 በመቶ ነው፡፡ እኛ ጋ ግን ከፈለገ መቶ በመቶ ያደርጋል፡፡ እጥፍ ጭማሪ አድርጎ ይሸጣል፡፡ የትርፍ ህዳግህን ማሰብ ያለብህ ‹ኢንፖርት ፓሪቲ ፕራይሷ› ከወጣች በኋላ እዚያ ላይ ጭማሪ አድርገህ የምትሸጠው በአብዛኛው አምስት በመቶ አክለህ ነው፡፡ አንዳንዴ እስከ አሥር ሊሄድ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትርፍ ህዳግ ሥሌቱ መነሻ ምንድነው?

አቶ ተክለወልድ፡- ‹ኢንፖርት ፓሪቲ ፕራይስ› ይዘህ እስከ አሥር በመቶ ማትረፍ ትችላለህ ሲባል፣ የምታገኘው ትርፍ በባንክ ቆጥበህ ከምታገኘው የወለድ ክፍያ ትንሽ ከፍ ማለት ስላለበት ነው፡፡ ሠርተህ የምታገኘው ትርፍ በባንክ ከቁጠባ ከሚታሰበው ወለድ ማነስ የለበትም፡፡ ይህ ከሆነ ገንዘቡን አስቀምጦ ወለድ መብት ይቻላል፡፡ ሥራ ከሠራህ ግን ለቁጠባ ከሚታሰብልህ ከወለዱ እጥፍ ማግኘት አለብህ ማለት ነው፡፡ በዓለም እየተሠራበት ያለው ይህ ነው፡፡ ሥሌቱም ገንዘብ በባንክ ባስቀምጥ ምን ያህል ወለድ አገኛለሁ? ሥራ ብሠራ ምን ያህል አገኛለሁ ብለህ ነው የምትሠራው፡፡ የወለዱን እጥፍ ዋጋ ይዘው ይሠራሉ፡፡ እኛ ጋ ግን እንዳልኩህ ነው፡፡ ‹ኢንፖርት ፓርቲ ፕራይሱ› አንድ ሺሕ ብር የሚጨርስ አንድ ዕቃ አንድ መቶ ብር ጨምረህ አንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር ብትሸጥ ከአንድ ዕቃ አንድ መቶ ብር አተረፍክ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ አንድ ሺሕ ጨርሶ መርካቶ የደረሰ ዕቃ ሁለት ሺሕ፣ ሦስት ሺሕ ብር ሊሸጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ የባንክ ወለድ 17 በመቶ ይሁን ከዚያም በላይ ምንም ግድ አይሰጣቸውም፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ያ ሁሉ ነገር የሚወድቀው ሸማቹ ላይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም? ኢኮኖሚያዊ ቀውስስ አያስከትልም?

አቶ ተክለወልድ፡- እሱን እመለስበታለሁ፡፡ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ገንዘቡ በአንድ ሰርክል ሄዷል ማለት ነው፡፡ እነሱ በዚህ መንገድ ያገኙትን ትርፍ ወደ ባንክ ይወስዳሉ፣ ባንኩ እንደገና ያበድረዋል፡፡ በዚህ መንገድ ስለሚሠራ ይተረፋል፡፡ ከባንክ ወደ ብድር፣ ከብድር ክፍያ ወደ ባንክ እያለ ይሽከረከራል፡፡ እንዲህ እያደረገ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ዋናው ችግሩ ይህ ሲሰፋ ግሽበት  ያመጣል፡፡ እኛ ጋ ግን የግሽበት ቅርጫትዋ በአብዛኛው ከምግብ ጋር የተያያዘች ስለሆነች ይህንን ይደፍቃል ማለት ነው፡፡ የግሽበቱ አካል የሆነው ምግብ 47 በመቶ ነው የሚይዘው፡፡

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ዘርፍ በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን ስኬት ነበር ተብሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱስ?

አቶ ተክለወልድ፡- በፋይናንስ ዘርፉ ያልተሳካው ብለን የምናስቀምጠው የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን ካልሆነ በስተቀር ሌላው ተሳክቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የወጭ ምንዛሪ ግኝት ያልተሳካው ለምንድነው? በተለይ የወጪ ንግዱ በተፈለገው መጠን አልሄደም?

አቶ ተክለወልድ፡- በውጭ ምንዛሪ ግኝትም ቢሆን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ስንል ኤክስፖርት ብቻ አይደለም፡፡ የወጪ ንግድ፣ ‹ኤክስፖርት ኦፍ ሰርቪስ› አለ፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አለ፡፡ ሬሚታንስ አለ፡፡ ብድርና ዕርዳታም አለ፡፡ ከዚህ ሁሉ ያልተሳካው የወጪ ንግድ ነው፡፡ በተቀመጠው መልክ አልሄደም፡፡ ከወጪ ንግድ ብዙ ይጠበቅ ነበር፡፡ ከግብርና እስከ 65 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ ነበር፡፡ የግብርናው ከወጪ ንግድ አንፃር ሲታይ ለገበያ የቀረበው ምርት በመጠን በጣም ጨምሯል፡፡ ነገር ግን በሁሉም ረገድ የዓለም ገበያ ዋጋ ወድቋል፡፡ የበለጠ ዋጋው የወደቀው ብዙ ወደ ውጭ የምንልካቸው የግብርና ምርቶች ናቸው፡፡ ዋጋው በመውደቁ ደግሞ የቱንም ያህል የምርት መጠን ብንጨምርም አልሆነም፡፡ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆነ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ምርት ዋጋ መውደቁ በአብዛኛው ተጠቃሚ አድርጎናል፡፡

ሪፖርተር፡- የምርቶች ዋጋ በዓለም ላይ መውደቅ ኢትዮጵያን እንዴት ተጠቃሚ ያደርጋል?

አቶ ተክለወልድ፡- እንደተባለው የምርት ዋጋ መውደቅ በኤክስፖርቱ በኩል ተጠቃሚ አላደረገንም፡፡ ኤክስፖርቱን በ20 በመቶ እናሳድጋለን ብለን እንዳቀድነው አላደገም፡፡ ካሰብነው ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር አጥተናል ማለት ነው፡፡ የዋጋ መውደቁ ግን ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጠቃሚ አድርጎናል፡፡ ለምሳሌ ነዳጅ ብቻ በውጭ ምንዛሪ እናገኛለን ብለን ያሰብነውን አቻችሎ ከዚያ በላይ እንድናገኝ አድርጓል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነዳጅ መቀነስ በዓመት ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንድናገኝ አድርጎናል፡፡ ስለዚህ ከወጪ ንግዱ የፈለግነውን ያህል አላገኘንበትም እንጂ በዋጋ መውደቁ ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ ይህም መታየት አለበት፡፡ የብረታ ብረት ዋጋም በ50 በመቶ አካባቢ ወድቋል፡፡ ስለዚህ ከዚህም ብዙ ሚሊዮን ዶላር አትራፊ ሆነናል፡፡ ከእጥፍ በላይ ተጠቃሚ ሆነንበታል፡፡ ምክንያቱም በእኛ ኢኮኖሚ አጠቃላይ የካፒታል ዕቃዎች ከውጭ ነው የሚወጡት፡፡ እነዚህ በሙሉ ዋጋቸው ከ30 በመቶ በላይ ወድቋል፡፡ የእኛ ኢምፖርት ከአጠቃላይ የምርት መጠናችን (GDP) ወደ 23 በመቶ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቅማችን ይበልጣል፡፡ እኔ ሳስበው ኤክስፖርት በ40 በመቶ ቢያድግ እንኳን ይኼ አጋጣሚ ባይፈጠር በምን ዓይነት መንገድ ፋይናንስ ማድረግ እንችል ነበር? የዓለም ዋጋ ባይወድቅ በኢኮኖሚው ላይ በጣም ተፅዕኖ ይፈጥር ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ በአጋጣሚ የተገኘ ዕድል ነው፡፡ ይህ ሁሌ አይሆንምና ከዚህ በኋላ ምንድነው የሚሆነው? የውጭ ምንዛሪ በጣም ችግር አለ፡፡ በወረፋ እንኳን ማግኘት ተቸግረናል እየተባለ ነውና ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ምን ታስቧል?

አቶ ተክለወልድ፡- ኤክስፖርት ላይ ያለው ግብርናው በራሱ እየሄደ ነው፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ፡፡ ማዕድናትም ዋጋቸው ወድቆ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረውን በአጋጣሚ የተፈጠረውን ዋጋ ትተን ብዙ አምርተን ያልነውን ገንዘብ ለማግኘት መሥራት ነው ያለብን፡፡ እንዲህ ያለው ነገር በአሥርና በሃያ ዓመታት አንዴ የሚመጣ ነው፡፡ ወርቁንም ሌላውንም ብዙ ማምረት ነው፡፡ ብዙ ቢሊዮን ብር ያመጣሉ የተባሉት ማዕድናት ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ በኩል ደግሞ እንደ ሐዋሳ ካሉት ፓርኮች አንድ ቢሊዮን ያስገባሉ ተብሏል፡፡ ከዚህ ግማሽ እንኳን ብናገኝ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ መሥራት ነው፡፡ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ ማኑፋክቸሪንግ ላይ የተጀመሩት ጅምሮች ወደ ሥራ መግባት አላቸው፡፡ ለእነዚህ እንግዲህ ብድርና የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ሌሎች የምንሰጣቸው የማበረታቻ ካሮቶች ብዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ተሰጠ የተባለውን ካሮት ያህል በተፈለገው መጠን አልተጓዙም፡፡ አሁንስ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

አቶ ተክለወልድ፡- አሁንማ ሒደት ላይ ስለሆኑ ለምን አላገኘንም ማለት አንችልም፡፡ ይህ ሁሉ ገንዘብ የፈሰሰበት ነገር ፍሬ ማሳየት አለበት፡፡ እንደ ብሔራዊ ባንክ እያለቁ ያሉት ሥራዎች ወደ ፍሬ መግባት አለባቸው፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል በኩልም እንዲሁ ግልገል ጊቤ ሦስት አልቋል፣ ሌላውም እያለቀ ይሄዳል፡፡ ቢያንስ በዓመት 600 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር በኤክስፖርት እናገኛለን ብለን ይዘናል፡፡ ሁሉም በመንገድ ላይ ነው እንጂ ብዙ የምንጠብቀው አለ፡፡ አሥር ቦታ ስኳር የጀመርነው እኮ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብለን ብቻ አይደለም፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታማ አምስትም ይበቃል፡፡ ይህ ሁሉ የተሠራው ለኤክስፖርትም ታስቦ ነው፡፡ ሁሉም ግን እየተሠራ ነው፡፡ እንደ መንግሥትም መስመር ላይ ያሉትን ማስጨረስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሌላውን ማሰብ፡፡ ይኼ በአጭር ጊዜ ካለቀ በኤክስፖርቱ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ይመጣል፡፡ አለበለዚያ ኤክስፖርቱን አሳደግን ከተባለ እንኳን ሊገኝ የሚችለው ሁለትና ሦስት ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ ፋብሪካም አይበቃም፡፡ ጥያቄው ይኼ አይደለም፡፡ እኛ አደገ የምንለው ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው የውጭ ምንዛሪ ሲያስገኙ ነው እንጂ፣ ነገ ቡናና አበባ አሥርና 15 በመቶ አደጉ በሚለው ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ ሳይቆራረጥ የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ ይገባል እንጂ አንድ ጊዜ ንፋስ አመጣሽ ሆኖ ሌላ ጊዜ ዘጭ የሚል ከሆነ ማክሮ ኢኮኖሚውንም መምራት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ተስፋችን ያ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከእኛ አገር ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አገሮችም ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡት ምርት በኤክስፖርት ገቢ የሚሸፈን የለም፡፡ ኤክስፖርቱ የሚሸፍነው ግፋ ቢል ከአሥር እስከ 15 በመቶ ነው፡፡ አካሄዱም ይህንን 30 በመቶ ከዚያ 40 በመቶ እያደረጉ መሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የወጪ ንግድ ገቢው ማነስ ብቻ አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ከማባሉት አንዱ የሆነው የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ገቢም ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ትንሽ ነው ይባላል፡፡ እንዲያውም ወደ አፍሪካ ከሚገባው ቀጥታ የወጪ ኢንቨስትመንት ገቢ የኢትዮጵያ ድርሻ ሦስት በመቶ እንኳን አይሞላም ይባላል፡፡ ይህ አንድ ክፍተት አይሆንም?

አቶ ተክለወልድ፡- እንግዲህ የአፍሪካን ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በሁለት ከፍለን ማየት አለብን፡፡ በአፍሪካ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚባለው ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ቴሌኮምና ፋይናንስ ነው፡፡ ይህንን ከወጣህ የእኛን 0.5 በመቶ እንኳን አይደርስም፡፡ ይህንን ጉዳይ በጥልቀት ካላየኸው እውነታውን ይሸፍናል፡፡ ቴሌኮም በእነሱ ስለተያዘ ይህንን ያህል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አለ ነው የሚባለው፡፡ ባንኩም እንደዚያ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሰውን የሳስታል፡፡ ጭምብል ነው፡፡ ሌላው ነዳጅና ማዕድን ነው፡፡ የአፍሪካ ‹‹FDI›› የሚባለው፡፡ እዚህ ውስጥ ማኑፋክቸሪንግና ሌላ ነገር የለም፡፡ ቴሌኮም፣ ባንክና ማዕድን ነው፡፡ ለዚህም ነው ይኼ ሁሉ ነገር ሆኖ እንኳን የአፍሪካ አገሮች ዕድገታቸው ከአምስት በመቶ ያላነሰ ጥሩ ዕድገት እያገኙ ነው ተብሎ የነበረው፡፡ ነገር ግን ዕድገታቸው አካታች አይደለም፡፡ ሁሉንም በደረጃ ተጠቃሚ በሚያደርግ አይደለም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ዕድገቱ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ አይደለም፡፡ ጥቂቶችን የሚጠቅም ነው፡፡ ልማታዊ የተባለ መንግሥት ሁሉ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ሙጭጭ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ብዙ ዕውቀት አይፈልግም፡፡ ብዙ ሰው ይቀጥራል፡፡ ብዙ ገንዘብ ስለሚያስገባ አካታች ነው፡፡ ሰው እያደገ ወደ መካከለኛ ገቢ የሚሄድ የሚችለው በዚህ ነው፡፡ ለማንኛውም የአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በጥንቃቄ የሚታይ ነው፡፡ እኛ ጋ ግን ይኼ በሌለበት ሁኔታ እያደገ ነው የመጣው፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንቱ በየዓመቱ እያደገ መጥቷል፡፡ በአጠቃላይ አገራዊ ምርት ሦስት በመቶ ደርሷል፡፡ በማኑፋክቸሪንጉም ሆነ በሌላው አለ፡፡ ግን ይህንን ለማስፋት አሁንም እየተሠራ ነው፡፡ አሁን ባለው መረጃ እንኳን ባለፉት አራት አምስት ዓመታት ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የተገኘው ገቢ ከኤክስፖርት ከተገኘው ይበልጥ እንጂ አያንስም፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በአምስት ወራት ምን ያህል ተገኘ?

አቶ ተክለወልድ፡- የተገኘው ወደ 950 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከወጪ ንግድ የተገኘው ደግሞ ወደ 760 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሲታሰብ ሌላው ማጠናከር ያለብህ ‹ኤክስፖርት ኦፍ ሰርቪስ› የሚባለውን ነው፡፡ ቱሪዝምን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብን በዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀንሷል እንጂ የቴሌኮም ሁሉ እንዲበረታታና ገንዘብ እንዲያስገኙ ማድረግ ነው፡፡ በጣም ትልቅ ገንዘብ የሚያመጡ ስለሆነ የእነዚህ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ በዓመት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚያመጡ ናቸው፡፡ ሌላው ዋናው ሬሚታንስ ነው፡፡ ሪሜታንሱ በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሬሚታንስ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከወጪ ንግድ ከሚገኘው በላይ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ አምስት ወራት ከሬሚታንስ የተገኘው ገቢ ከወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ በላይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በነበረው ችግር ውስጥ ሆነን እንኳን የሬሚታንስ ገቢ ጨምሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው ችግር ወቅት የተገኘው ሬሚታንስ ይቀንሳል፣ ወይም ቀንሷል ሲባል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በእርግጥ ጨምሯል?

አቶ ተክለወልድ፡- አዎ ጨምሯል፡፡ በችግሩ ምክንያት አልቀነሰም፡፡ እንዲያውም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ተገኝቶ ከነበረው የሬሚታንስ ገቢ ጋር ስታነፃፅረው እንኳን በአሁኑ በአምስት ወራት ውስጥ የተገኘው በ7.7 በመቶ ጨምሯል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር የቀነሰው የኤንጂኦ ሬሚታንስ ነው፡፡ ይህም የቀነሰው ካለፈው ድርቅ ጋር በተያያዘ ወደ መደበኛው ሄዷል፡፡ ሌላው ከብድርና ዕርዳታ ነው፡፡ ከብድርና ከዕርዳታ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም ጨምሯል፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ካሉ ምንጮች ነው የውጭ ምንዛሪ የሚገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የዚህን ያህል ከሆነ እጥረቱ ለምን ተከሰተ?

አቶ ተክለወልድ፡- እንደዚያ የሚባል ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ ባለፉት አራት ወራት 5.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከኤክስፖርት የተገኘው ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት አምስት ወራት ለገቢ ዕቃ የወጣው 5.6 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የግል ሴክተሩ ብቻ 3.3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎችን አስገብቷል፡፡ ለሜጋ ፕሮጀክቶችና ለመሳሰሉት መንግሥት ያስገባው ዕቃ 2.3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንንም ለገቢ ዕቃዎች በአራት ወራት የዋለውን የውጭ ምንዛሪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስታነፃፅረው የግል ዘርፉ የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ መሆኑን ነው፡፡ ካለፈው ዓመት የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ተሰጥቷል፡፡ ይህ ማለት ግን ጥያቄ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ በአራት ወራት ብቻ 3.3 ቢሊዮን ዶላር ዕቃ የግል ዘርፉ አስገብቷል ስንል፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ቀርቧል ማለት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩትን ጉዳዮች እናውቃለን፡፡ ያ ሁሉ ነገር በነበረበትና ትንበያው ገኖ በወጣበት ጊዜ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ይጠፋል፣ ዳያስፖራውም ገንዘብ አይልክም የተባለውን ነገር በሙሉ አሰባስበህ ስታየው እዚህ ግባ የማይባል ችግር ነው የፈጠረው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የተፈጠረው ችግርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያሳደረው ተፅዕኖ የለም?

አቶ ተክለወልድ፡- በዚያን ጊዜ የተፈጠረው ችግር በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ትንሽ ያመጣው ነገር ቢኖር ብላክ ማርኬት ትንሽ ከፍ እንድትል አድርጓታል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም የጥቁር ገበያው ዋጋ ጨምሯል፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ አያሳይም?

አቶ ተክለወልድ፡- ዋናው የትንበያ ሥራ ስለሆነ ነው እንጂ የውጭ ምንዛሪ ጠፍቶ አይደለም፡፡ በዚያ በችግሩ ጊዜ የተፈጠረ ነው፡፡ ያው ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ አገሪቷ እንዲህ ሆናለች በማለት የሌለ ነገር አውርተው አንዴ ዋጋውን አወጡትና ሁሉም ዶላር መግዛት ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ከፍ አለ፡፡ አገር አማን ከሆነ በኋላም ቀጠለ፡፡ እኛ አገር አንዴ የተሰቀለ ዋጋ ቶሎ ወደ ኋላ ስለማይወርድ ነው፡፡ በዚያ ሁኔታ ስለቀጠለ ሰው ይህንን ይዞ ሁልጊዜ የውጭ ምንዛሪ ተመኗ ከፍ ብላለች ያስብላል፡፡ መቼና በምን? የሚለውን ሰው ስለማያይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የእያንዳንዱን ባንክ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ስታየው ከአምናው የተሻለ ነው፡፡ ሁሉም ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ገቢ አምና በአምስት ወራት ካገኙት ገቢ በዘንድሮው በጀት ዓመት በአምስት ወራት ያገኙት ገቢ የተሻለ ነው፡፡ አሁን ባንኮች እኛን ተጫናችሁን የሚሉት ለማኑፋክቸሪንግ  ቅድሚያ ስጡ የሚል መመርያ ስለወጣ ነው፡፡ አሁን ሰንጠረዡን ስናይ ለውጡን ታያለህ፡፡ የኢትዮጵያ ንገድ ባንክ ብቻ 800 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል፡፡ ይህ ከአምናው ከ200 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ አምና ደግሞ መመርያውን ስለቀየርን ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን የግል ባንኮች ናቸው ያገኙት፡፡ ስለዚህ እንደ ድሮው ጫጫታ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የለም ከተባለ ለምን የጥቁር ገበያው ምንዛሪ ጨመረ?

አቶ ተክለወልድ፡- የውጭ ምንዛሪ እውነታው የጠቀስኩልህ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በመርካቶ ለምን ይህንን ያህል ወጣ የሚለውን ምክንያታዊ ሆኖ ማየት ነው፡፡ ስለዚህ መርካቶ ላይ የሆነው መስከረምና ጥቅምት ላይ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ደላላው ነገሩን በማስጮኹ ነው፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አይመጣም፣ ዳያስፖራው ገንዘብ አይልክልህም፣ ዶላር የለም፣ ኤክስፖርቱ ይወድቃል፣ ብድርም የሚሰጥ የለም የሚሉ ወሬዎች ሲወሩ ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለታወጀም ማዕቀብ ስለሚኖር ገንዘብ አይሰጥም ስለተባለ ገንዘብ የያዘ ሁሉ ዶላሩን ለመግዛት ስለተሯሯጠ ነው፡፡ አሁን ተረጋግቶም እያለ ደግሞ ደላላው በዚያ ወቅት የሰበሰበውን ዶላር መሸጥ አለበት፡፡ ከሸጠም ደግሞ በቅናሽ ዋጋ ስለሚሆን ቁጭ ብሎ መጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ተነስቶ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ዋጋውን ሊጨምር ይችላል ወደሚል ወደ ሌላ ነገር መሄድ ተጀመረ፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጠረ ችግር አለ ከተባለ በተወሰነ ደረጃ የብላክ ማርኬት መጨመር ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ የሚያነፃፅሩት ከጥቁር ገበያው ዋጋ ጋር ነው፡፡ ከእኛ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ግን ያቆማሉ፡፡ ከዚህ ተነስተን የውጭ ምንዛሪ ተመኑን እንዲቀንስ እናድርግ ቢባል ጥፋት ነው? ልማት? ተንባዮቹ ካደረጉት ነገር ተነስተህ የኢኮኖሚክ ምክንያታዊነትን ሳታይ የእነሱን 25 እና 26 አደርጋለሁ ብለህ ብትሄድ ጥፋት ነው የሚለውን ነገር ነው የምታየው፡፡ በእርግጥ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ኤክስፖርቱን ያበረታታል የሚባለው ትክክል ነው፡፡ እኛ ጋ የኤክስፖርት መጠኑ ነው የወደቀው? ወይስ ዓለም አቀፍ ዋጋ ነው የወደቀው? ኤክስፖርት እንዲበረታታ የውጭ ምንዛሪ ተመን ታሸሻለህ የሚባለው ምክንያት ሲኖር ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የቀነሰውና መጠኑንም ጨምረን ልክ ነው፡፡ ግን የትኛው ነው የበለጠ ጥቅም ያለው? ይህንን በማድረጋችን ኢኮኖሚው ላይ ሚዛን የሚደፋው የትኛው ነው? ብለህ ነው የምታየው፡፡ ከዋጋ አንፃር ማለት ነው፡፡ ካፒታል ዕቃ በሙሉ እኮ ከውጭ ነው የምናመጣው፡፡ የግል ዘርፉም ሜጋ ፕሮጀክቱም ዶላር እዚሁ አንድ ሆኖ አንተ ዶላር እዚህ ስትጨምር የአገር ውስጥ ዕቃዎቹን በጣም ነው ውድ የሚያደርጋቸው፡፡ የካፒታል ዕቃ አገር ውስጥ ካለ የአገር ውስጥ የካፒታል ዕቃዎቹን ገዝቶ ያኛውን ይተዋል ነው፡፡ ኢንፖርት ይቀንሳል ነው፡፡ የእኛ ገና ኢንፖርት የሚቀንስበት ሎጂክም የለም፡፡    

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ተክለወልድ፡- የግድ ካፒታል ዕቃ መምጣት ስላለበት ነው፡፡ የካፒታል ዕቃ ካልመጣ ሁሉም ነገር ይቆማል፡፡ ምክንያቱም የካፒታል ዕቃ ማምረት ስላልጀመርን ነው፡፡ ስለዚህ ካፒታል ዕቃዎቹ ጋ ያለውንና የአገር ውስጥ ዋጋን ከፍ ታደርጋለህ፡፡ ስለዚህ 50 ሚሊዮን ብር የሚበደር ሰው 60፣ 70 ሚሊዮን ብር እንዲበደር ታደርጋለህ ማለት ነው፡፡ ይህንን ብድር ዝም ብለህ የምትሰጥ ከሆነ ደግሞ ግሽበት ይሆናል፡፡ ዕቃው መምጣቱ አይቀርም፡፡ ግን ዋጋው ውድ ሆኖም ብር ትረጫለህ፡፡ ዕቃው ሲገባ የአገር ውስጥ ዋጋው ይጦዛል፡፡ ይህ ግሽበት ያመጣል፡፡ ግሽበት ደግሞ የደሃ ሰው ጠንቅ ነው፡፡ ግሽበት ያልታሰበና የማይታወቅ ታክስ ይሆናል ይባላል፡፡ ስለዚህ ችግሩ እሱ ጋር አይደለም፡፡ ሸማቹ ላይ ነው፡፡ ሸማቹ ላይ ደግሞ ግሽበት ትፈጥራለህ፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋ እንዳይሆን ታደርጋለህ ማለት ነው፡፡ ማኑፋክቸሪንግን ትንሽ ፈቀቅ ማድረግ ፈልገህ ሌላውን ኢኮኖሚ ታበላሻለህ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን በተደጋጋሚ እንደሰማሁት እርስዎም እንደገለጹት የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ከዚህ በኋላ ብዙ ይጠበቅባቸዋል እንዴት?

አቶ ተክለወልድ፡- የፋይናንስ ሴክተሩ ከዚህ በኋላ ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ዓይነት አካሄድ ቅርንጫፎቹን በማስፋት ብቻ አይቆምም፡፡ አንደኛ የፋይናንስ ተደራሽነቱና ተጠቃሚነቱ መስፋት አለበት፡፡ ኢኮኖሚው በሚገባ እንዲያንሰራራ ከተፈለገ መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የተቀመጠውን ራዕይ ከግብ ለማድረስ፣ ሌሎች መንግሥት የሚሠራቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዋናነት በፋይናንስ ዘርፉ አካባቢ ያለው የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ከመቼውም ጊዜ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እንዴት ይገለጻል? ብዙ ይጠበቅባቸዋል ከተባለ ምን እንዲያደርጉ ይፈለጋል?

አቶ ተክለወልድ፡- ይህ ማለት በአፍሪካ ደረጃም ብታይ ኢትዮጵያ ገና የባንክ ተደራሽነት የሌለባት ተብላ ነው የምትታየው፡፡ ስለዚህ ተደራሽነት ስንል ቅርንጫፍ ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ አንዱ አካል ቅርንጫፍ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከአምስት ኪሎ ሜትር ባልራቀ ቦታ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማግኘት አለበት፡፡ በቅርቡም በወኪል ባንክ፣ በሞባይል ባንክ፣ በክሬዲት ባንኪንግ፣ በኤትኤምና በመሳሰሉት መንገዶች ኤሌክትሮኒክ ባንኪንግም ሆነ ሌሎቹ በዓይነትም በመጠንም መስፋት አለባቸው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር በእኛ አገር ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ከተጠቃሚነት አንፃር ጥራት ያላቸውና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ አገልግሎቶችን ማቅረብ ሁሉ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ደግሞ ቁጠባ፣ ብድር፣ ክፍያ፣ ሐዋላ፣ የመድን ሥራዎች የመሳሰሉትን የፋይናንስ ሴክተር ምርቶች የሚባሉትን ያጠቃልላል፡፡ ይህንንም ዝም ብሎ አቅርቤያለሁ ማለት ሳይሆን ጥራት ያለውና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በዋናነት መሥራት ያለባቸው ባንኮች ናቸው፡፡ ባንኮቹ እነዚህን ሥራዎች ከሠሩ ለባንክ ተደራሽ የሆነ ኅብረተሰብ ይፈጠራል፡፡ ይህ ከተፈጠረ ደግሞ ከፋይናንስ ዘርፉ ውጭ የሚዘዋወር ገንዘብ ጥቂት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ የሚሰበሰበው ገንዘብ ነው ለኢንቨስትመንት ውሎ የሥራ ዕድል የሚፈጥረው፣ ድህነትን የሚቀንሰው፡፡ ይኼ ሲሆን ጥቃቅንና አነስተኛ ሁሉ ገንዘብ እንዲያገኝ ታደርጋለህ፡፡ አዲስ ሥራ እንዲፈጥር ታደርጋለህ፡፡ ይህ ከሆነ ብድር ንብረት በማስያዝ ብቻ ሳይሆን ቬንቸር ካፒታል የሚባለውን አሠራርም ታሰፍናለህ፡፡ ዕውቀትህን ይዘህ መጥተህ ብቻ ገንዘብ የምትወስድበት ማለት ነው፡፡ ይህንን እንጀምራለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ብድር ያለማስያዣ ማለት ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- ቬንቸር ካፒታል ከዩኒቨርሲቲ ተምሮ ዕውቀት ይዞ መጥቶ ይህንን ልሠራ ነው ብድር ስጠኝ ካለና ትክክለኛ ከሆነ ማስተናገድ ነው፡፡ ስለዚህ ዕውቀት ይዘህ ዝም ብለህ እንዳትቀመጥ ይደረጋል፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ሁሉ ራሱን አሻሽሎ ወደ ላይ እንዲሄድ ታደርጋለህ ማለት ነው፡፡ በዚህ ኢኮኖሚው ያድጋል፡፡ ሥራ አጥ እንዲቀንስ የሚያደርግ ጭምር ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው በፋይናንስ ዘርፉ ስለሆነ ትልቅ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ስኬት ታጥቆ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ እኛም የፋይናንስ አካታችነት ብሔራዊ ስትራቴጂ እየቀረፅን ነው፡፡ ለዚህም ቴሌ፣ መብራት ኃይልና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ሁሉ ሊሟሉ ይገባል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኅብረተሰቡን ማስተማር ነው፡፡ አንድ የዓለም ባንክ ጥናትን ምሳሌ ልጥቀስልህ፡፡ ጥናቱ የተለያዩ ሰዎችን በማነጋገር የተሠራ ነው፡፡ ለምንድነው የባንክ አገልግሎት የማትጠቀሙት? ተብለው ሲጠየቁ 78 በመቶዎቹ የሰጡት ምላሽ ትንሽ ገንዘብ በቁጠባ ማስቀመጥ ይቻል እንደሆነ ትንሽ ብድር የሚሰጥ ስለመሆኑም የማውቀው ነገር የለም ነበር ያሉት፡፡ ይህንን ምላሽ የሰጡት አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ጭምር ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ትንሽ ገንዘብ ይዞ ወደ ፋይናንስ ተቋማት መምጣት እንደሚቻል፤ ትንሽም ብድር ማግኘት እንደሚቻል፣ ግንዛቤ የለም ማለት ነው፡፡ በዚሁ ጥናት ላይ ወደ 12 በመቶ አካባቢ የሚሆኑት ተጠያቂዎች ደግሞ ባንክ የሚያገኙበት ቦታ ራቅ ስለሚል ለምን እዚያ ሄጄ ገንዘብ አስቀምጣለሁ የሚል ነው፡፡ ይህንን ስታይ ግንዛቤ ማስጨበጡ አንድ ነገር ሆኖ ዜጎች ወደ ፋይናንስ ተቋማት እንዲመጡ የማድረጉ ሥራም በዋናነት የሚያርፈው በፋይናንስ ተቋማቱ ላይ ነው፡፡  ይህንን ለማድረግ ደግሞ ካፒታላቸው በጣም ማደግ አለበት፡፡ አሁንም ከተባለው በላይ እጅግ በጣም ካፒታላቸው ማደግ አለበት፡፡     

ሪፖርተር፡- ባንካችን ካፒታላችሁን ሁለት ቢሊዮን ብር አድርሱ ብላችኋል፡፡ ይህንን ለማሟላት ሊፈተኑ የሚችሉ ባንኮች ይኖራሉ፡፡ ካፒታላቸውን ማሳደግ አለባቸው የሚባለው ቀደም ብሎ ከተጠቀሰው ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረግ ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- እሱም ትንሽ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ካፒታሉ እጅግ በጣም ካልተጠናከረ ትንንሽ ቢዝነሶች ውስጥ ስትገባ የአደጋ ሥጋሩ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ብድር የመመለስ ሥጋት ሊኖር ስለሚችል ይህንን ሪስክ መሸከም የሚችል ካፒታል ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮችን እኮ በቅርብ ጊዜ ገበያውንየተቀላቀሉት ባንኮች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ለማድረስ ሊፈተኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ይታያል፡፡ ስለዚህ ከዚህም በላይ ካፒታላችሁን ማሳደግ አለባችሁ ከተባሉ ሊያስቸግራቸው ይችላል፡፡ ምናልባት በተለያየ መንገድ ሲገለጽ እንደቆየው አንዳንድ ባንኮች ወደ ውህደት እንዲገቡ የማድረግ ሐሳብ አላችሁ ማለት ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

አቶ ተክለወልድ፡- እንግዲህ አሁን ምንም ነገር ማለት አልችልም እንጂ፣ አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ በመንግሥት ውሳኔ ካገኘና ጊዜ ከተሰጠ በኋላ ውህደት ግዴታ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ውህደቱን እንዴት ማስኬድ ታስቧል?

አቶ ተክለወልድ፡- የያዙት ገንዘብ እኮ የሕዝብ ነው፡፡ የእነሱ አይደለም፡፡ እንግዲህ ባንኮች በአሁኑ ወቅት በቁጠባ የሰበሰቡት ከ467 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ የግልና የመንግሥት ባንኮችን ካፒታል ሲታይ ደግሞ ወደ 30 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው ያላቸው፡፡ ይህንን ካፒታል ብትቀንስ ቀሪው 437 ቢሊዮን ብር የሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ገንዘብ በተገቢው መንገድ እንዲሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና መንግሥት ማንኛውም ነገር ያደርጋል ማለት ነው፡፡በመጀመሪያ ግን ካፒታል ማድረግ አለበት የሚለው ነገር መተግበር አለበት፡፡ ካፒታሉ ማደግ አለበት ከተባለ ምን ያህል? በምን ያህል ጊዜ ነው? የተባለው ካፒታል ደረጃ መድረስ ያለባቸው የሚለው ተጠንቶ ለሁሉም ይገለጻል ማለት ነው፡፡ በተባለው ጊዜ የተባለውን ካፒታል ማድረስ ያልቻለ በቀጣይ ምን ይሆናል ለሚለው፣ አንዱ ባንክ እንደፈለገ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የሕዝብ ባንክ ነው እያልኩህ ነው፡፡ ስለዚህ ውህደት በራሱ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ሦስት ዓመት የፋይናንስ ቀውስ ሲከሰት ቀውሱ ናይጄሪያንም ሲመታት፣ በናይጄሪያ የነበሩ 90 ባንኮች ተዋህደው አሥር ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ግዴታም ሊሆን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አቶ ተክለወልድ እስካሁን ያለው ሁለት ቢሊዮን ብር አድርሱ ነው፡፡ አሁን ከእርስዎ እንደተረዳሁት ደግሞ ካፒታላቸውን ከዚህ በላይ ማድረስ እንደሚኖርባቸው ነው፡፡ ይህንን ይችላሉ?

አቶ ተክለወልድ፡- ካፒታላችሁን ሁለት ቢሊዮን ብር አድርሱ ቢባሉም በዚህ ቀን ብለን ስላልነገርናቸው፣ ከዚህ በኋላ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር አድርሱ ወይም ከዚያም በላይ ያድርጉ የሚለውን ለመወሰን እያጠናን ነው፡፡ ሁለት ቢሊዮኑ ላይ አልቆምንም፡፡ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በታች ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ካፒታል ማሳደግ እንዳለባቸው አሳውቀናቸዋል፡፡ ጥናቱ ሲያልቅ ይህንን ያህል ካፒታል በዚህን ጊዜ ማድረስ አለባችሁ ብለን እንወስናለን፡፡ ያንን በተባለው ጊዜ በማያደርስ ባንክ ቀጣዩ ዕርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ያኔ የሚታወቅ ይሆናል፡፡ በጥቅሉ ግን ውህደት የውዴታ ግዴታ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ግዴታም ሊሆን ይችላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የውህደት ጉዳይ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ሐሳቡን ሲያንሸራሽሩ የነበሩም አሉ፡፡ ነገር ግን ባንኮች ይዋሀዱ ሲባል አንድ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ የብዙ ባንኮች አመሠራረት በአካባቢ ልጅነት አንዳንዴም በብሔር፣ ወዘተ. የሚመስል ነገር አለ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አንዱን ከአንዱ ጋር መዋሀዱ ከባድ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡

አቶ ተክለወልድ፡- አንዳንዴ በአካባቢ ልጅነት ተሰባስቦ የተቋቋመ ነው ይባላል፡፡ ይህ ስምም ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ የምናውቀው ግን የፋይናንስ ቢዝነስ ለትርፍ ተብለው የተቋቋሙ እንጂ የፖለቲካ ድርጅት አይደሉም፡፡ ሁለተኛ የአካባቢ ማኅበረሰብ ዕድር አይደሉም፡፡ ለትርፍ የተቋቋሙ ሼር ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ምንም ይሁን ምን ጊዜው ሲደርስ እናያለን እንጂ እከሌ እከሌ ነው የሚባል ነገር የለም፡፡ ዋናው አራት ነጥቡ የባንኪንግ ቢዝነስ ማለት ሰዎቹ ያቋቋሙት ትርፍ ለማግኘት እንጂ የሰንበቴ ማኅበር አይደለም፡፡ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም፡፡ ይኼ የእክሌ ይኼ ደግሞ የእንቶኔ የሚባል ነገር የለም፡፡ እኛ በይባላሉ አንሄድም፡፡     

ሪፖርተር፡- ባንኮች ካፒታል ማሳደግ ይኖርባቸዋል ከተባለ አንዱ መንገድ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲገቡ መፍቀድ ነው ይባላል፡፡ በአጠቃላይ ዳያስፖራው የውጭ ዜግነት ያለውም ቢሆን በፋይናንስ ዘርፉ እንዲገባ ለማድረግ የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ተክለወልድ፡- ካፒታል ለማሳደግ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነህ የሚያግድህ ነገር የለም፡፡ አሁን የባንኮች ካፒታል ከትንሽ ተነስቶ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ አሁን የሚያገኙትን ትርፍ ሁሉ ለካፒታል ማሳደጊያ ቢያውሉ 40 በመቶ ትርፋቸውን ወደ ካፒታል ቢያዞሩ ኖሮ፣ እስካሁን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ይደርስ ነበር፡፡ ስለዚህ የካፒታል ችግር የለም፡፡ አንደኛ ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያዊ ደም ኖሯቸው የውጭ የዜግነት የወሰዱ ሁሉ በፋይናንስ ሕጉ የውጭ ዜጋ ናቸው፡፡ ለሌሎች የውጭ ዜጎችና ኩባንያዎች የከለከልንበት ምክንያት ለእነሱም ለሌላውም ይሠራል፡፡ በተናጠል የውጭ ዜጎች እንዳይገቡ የተከለከለበት ምክንያት አለው፡፡ በየትም አገር እያደገ ባለ ወይም እየቆጠቆጠ ባለ ኢኮኖሚ ላይ የባንኪንግ ቢዝነስ በጣም ትርፋማ ነው፡፡ ያውም ለአገር ውስጥ ብቻ ወይም ለዜጎች ብቻ ገድበህ ማለት ነው፡፡ ሌላ ተወዳዳሪ ቢኖር ለውጭ ቢፈቀድ ኖሮማ ከ17ቱ ባንኮች አንዱ ሊቀር ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ ዘርፉን ገድበን ባለንበት ሰዓት በግለሰብ ደረጃ ይግቡ የሚባሉትን እንዲገቡ ካደረግህ፣ አሁን እንደምናየው አንድ መቶ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን 40 ብር ትርፍ በየዓመቱ፣ አንድ ሚሊዮን ያለው 400 ሺሕ ብር እያገኘ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ይህ ምን ችግር አለው?

አቶ ተክለወልድ፡- ችግሩ ይህንን ገንዘብ ማግኘታቸው አይደለም፡፡ ይህ ገንዘብ መጨረሻ ላይ ወደ ዶላር ይቀየራል፡፡ አንድ ጊዜ እዚህ ውስጥ ካስገባህ በኋላ ገንዘቡን ወደ ዶላር አትቀይር ማለት አይቻልም፡፡ ልክ ቆርቆሮ ፋብሪካ እንዳቋቋመ የውጭ ሰው ዶላሩን ይዞ እንደሚሄድ ማለት ነው፡፡ ሌላው የውጭ ባንኮችና የውጭ ሰዎች እንዳይገቡ የተከለከለው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ አቅማችን ውስን በመሆኑ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅማችን ካደገ ግን እነሱ በፈለጉ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ቢወስዱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንገጫገጭ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ሊኖር አይገባም ነው፡፡ ስለዚህ ለእኔ ትልቁ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ለእነሱ የሚሆነውን ይህንን ዓይነት ነገር ፈጥረናል ወይ ነው፡፡ ይህንን ባለማድረጋችን በእነሱ በኩል የተለየ ነገር አላይም፡፡ ይህንን ለማድረግ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ እኛማ እያሰብን ያለነው በጂቲፒ 1 ያሰብነው ስምንትና አሥር ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ምንዛሪ ቢመጣ ኖሮ ይህንን ማሰብ እንችል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ለውጭ ዜጎች ያለመፈቀዱ አንዱ ሥጋት የውጭ ምንዛሪ ያስወጣል ከሚል ነው ማለት ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- ዶላሩ መውጣቱ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ባለን አቅም ያለውን ዶላር ለማኑፋክቸሪንግና ለሌሎች ጉዳዮች ማዋል ያለብንን ዝም ብሎ ተቀምጦ ለሚገኘው ትርፍ እናውላለን ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋ ሆነህ ሥራ መፍጠር እየቻልክ ለተቀመጠ ገንዘብ የዶላር ችግር ያለብን አገር ሆነን ዶላር እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡ የአገሪቷ የዶላር አቅም የተደላደለ በሚሆንበት ጊዜ ትፈቅዳለህ፡፡ የግዴታ ነው፡፡ የውጭ ተቋማት በመግባታቸው ውድድሩም ቴክኖሎጂውም ስለሚመጣ ኢኮኖሚው ብዙ ነገር ያገኛል፡፡ ነገር ግን ለዳያስፖራዎቹ ይህ እስኪፈቀድ ለእነሱ እኮ ብዙ ነገር ፈጥረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ተክለወልድ፡- አንደኛ ሊዝ ፋይናንሲንግ ፈቅደናል፡፡ ሊዝ ፋይናንሲንግ የባንክ ሥራ ነው፡፡ ብድር በዕቃ መስጠት ማለት ነው፡፡ አገር ውስጥ ገብቼ ለኢኮኖሚው እጠቅማለሁ ካለ ብድርን በካሽ በሚሰጠው አሠራር ውስጥ ለመግባት ትንሽ ትቆያለህ፡፡ እስከዚያ ብድር በዕቃ በሚሰጠው የባንክ ሥራ ትኖራለህ ሲባል ለምንድነው እንቢ የሚባለው? ኢኮኖሚውን ጠቅሜ ራሴንም እጠቅማለሁ ከተባለ ያኛው እስኪፈቀድ በተፈቀደው ሥራ ቢሠራ እኮ መማርያ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ወጣም ወረደ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የፋይናንስ ዘርፉ ለዳያስፖራውም ሆነ ለሌላው መፈቀዱ አይቀርም?

አቶ ተክለወልድ፡- እንዴት ይቀራል? በምንም ተዓምር አይቀርም፡፡ ይፈቀዳል፡፡ አንደኛ በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ለመድረስ የሚል ራዕይ አስቀምጠህ እዚያ ደረጃ ከደረስክ በኋላ አገር በቀል የፋይናንስ ተቋም ብቻ ይዘህ አትቀጥልም፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እኮ መዋቅራዊ ለውጥ አምጥተን ነው ወደ 2017 ዓ.ም. መድረስ ያለብን የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት ኤክስፖርቱ በአብዛኛው በማኑፋክቸሪንግ መምጣት አለበት፡፡ የኢንዱስትሪው ድርሻ ወደ 30 በመቶ መድረስ አለበት፡፡ ትራንፎርሜሽን አምጥተን ለመድረስ ነው፡፡ ይህ ማለት የውጭ ምንዛሪም በገለጽኩልህ መንገድ ይመጣል፡፡ የውጭ ምንዛሪው ችግር ለ40 እና ለ50 ዓመታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ግን እንደ አሁኑ ሆኖ እዚህ ትርፍ ያመጣው ሰው ሁሉ ሲወስድ እንደ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዋ! የምትልበት ደረጃ ላይ አትደርስም፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ የውጭ ዜጋ ቢገባ ተጨማሪ እሴት የሚጨምር ነገር ያመጣል እንጂ፣ ለውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብቻ አይመጣም የሚል ሐሳብ ስላለ ነው፡፡ ዕቅዳችን ትራንስፎርሜሽን ነው፡፡ ዝም ብለን 2017 ይደረሳል፣ አጠቃላይ ምርት ሲካፈል ለሕዝብ ብዛት ብለን አንድ ሺሕ ወይም አንድ ሺሕ አንድ መቶ ዶላር ሳንደርስ መካከለኛ ገቢ ላይ እንደርሳለን በሚል ተራ ሥሌት አይደለም፡፡ ለዚህ ለዚህማ ጂቡቲም እኮ በዝቅተኛ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ላይ ነች፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አይደለም መድረስ የምንፈልገው፡፡ ትራንስፎርምድ የሆነ ነገር ይዞ በመግባት ነው፡፡ ሙጭጭ ብሎ አሁን ፋይናንሻል ሴክተር ላይ ካልተገባ የሚባለው ሌላ ችግርም ያመጣል፡፡     

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ችግር?

አቶ ተክለወልድ፡- ለምሳሌ አሁን የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) ላይ ድርድር እያደረግን ነው፡፡ በዓለም ንግድ ድርጅት ደግሞ ለአንዱ የሰጠኸውን ለሌላውም መሰጠት አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊ ደም ስላለው እሱን ግባ ብዬ ቻይናዊውን ወይም አሜሪካዊውን ከልክያለሁ ማለት አትችልም፡፡ ከከፈትክ ለሁሉም ነው የምትከፍተው፡፡ ድርጀቱ ደግሞ ይቺን ነገር ቅርቅር አድርጎታል፡፡ ይህም አለ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አንድ አክሲዮን የገዛ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ቢለውጥ ምንድነው የሚሆነው የሚለው ጉዳይ ሲያከራክር ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር እያጋጠመ ነው፡፡ ምን እየተደረገ ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- ዋናው ነገር ኳሱ በሰውየው እጅ ነው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለኢትዮጵያዊ ብቻ የተፈቀደ ሥራ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን አልፈልግም ብለህ ስትወጣ ለኢትዮጵያዊ የተሰጠውን ነገር መልሰህ ነው ኢትዮጵያዊ የማትሆነው ማለት፡፡ ዋናው ቁልፍ ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ላልሆኑት የማይሰጠውን ጥቅም አግኝቷል፡፡ አሁን ደግሞ እሱ ኢትዮጵያዊ አልሆንም ብሎ አውጆ ወጥቷል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሲያገኝ የነበረውን ጥቅም መመለስ አለበት፡፡ ይህ አውቶማቲክ ነው፡፡ ለእኛ ከገዛ በኋላም ቢሆን የውጭ ዜጋ ከሆነ የውጭ ዜጋ ነው፡፡ እንዲያውም ለእኔ የበለጠ ችግር ያለበት እሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ላልሆነው ጓደኛው የተከለከለውንና ኢትዮጵያዊ ሆኖ ያገኘውን ዕድል አሜሪካዊ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ያገኘውን መብት ማስተላለፍ ነበረበት፡፡ ከዚህ ቀደም አንዳንዶች እኔ ዜግነቴን ቀይሬያለሁና ለእከሌ አሳልፋለሁ ብለው በይፋ ለጠየቁ ሁሉ ፈቅደናል፡፡ ለልጆቼ ይሆን ብለው የጠየቁትን ሁሉ ፈቅደናል፡፡ ይቆይ እንጂ ይህንን ጥያቄ ላቀረቡ ሁሉ ማድረግ ያለባቸውን ምክር ሰጥተናል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...