ሲካዳ የሚባሉት አንበጣ መሰል ነፍሳት ከአንታርክቲካ በቀር በሁሉም አህጉራት ውስጥ ይኖራሉ። ፒሪዮዲካል ሲካዳ የሚባለው ዝርያ የሚገኘው ግን በሰሜናዊ ምሥራቅ አሜሪካ ብቻ ሲሆን እነዚህ ነፍሳት የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎችን ለረጅም ጊዜ ሲያስደንቁ ኖረዋል።
ጄደብሊው ዶት ኦርግ እንደዘገበው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፒሪዮዲካል ሲካዳዎች በፀደይ ወራት በድንገት ብቅ የሚሉ ሲሆን የሚቆዩትም ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው። ፀሐይ ላይ በሚቆዩበት አጭር ጊዜ ውስጥ የወጣትነት ቆዳቸውን ይቀይራሉ፣ ጆሮ በሚያደነቁር ድምፅ ይዘምራሉ፣ ይበራሉ፣ ይራባሉ ከዚያም ይሞታሉ። ቀጣዩ ትውልድ ብቅ የሚለው ደግሞ ከ13 ወይም ከ17 ዓመት በኋላ ሲሆን ይህም እንደ ዝርያቸው ይለያያል።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ነፍሳቱ የሚያደርጉትን ለማወቅ የእነዚህን ነፍሳት ለየት ያለ የሕይወት ዑደት መረዳት ያስፈልጋል። ፒሪዮዲካል ሲካዳዎች ብቅ ካሉ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ተቃራኒ ፆታዎች ይገናኙና እንስቶቹ ከ400 እስከ 600 የሚደርሱ እንቁላሎችን በቅርንጫፎች ቅርፊት ውስጥ ይጥላሉ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ነፍሳት ይሞታሉ። በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንቁላሎቹ ይፈለፈላሉ፤ ከዚያም እጮቹ ከዛፎቹ ወደ መሬት ይወድቁና አፈሩን ሰርስረው በመግባት ከመሬት ሥር መኖር ይጀምራሉ፤ እዚያም የቁጥቋጦዎችን ወይም የዛፎችን ሥሮች በመምጠጥ የሚያገኙትን ፈሳሽ እየተመገቡ ለዓመታት ይኖራሉ። ከ13 ወይም ከ17 ዓመታት በኋላ አዲሱ ትውልድ ብቅ ይልና ወላጆቹ የተከተሉትን ዑደት ይደግማል። የፒሪዮዲካል ሲካዳዎች የሕይወት ዑደት በእንስሳት ዓለም ታይቶ የማያውቅ እንቆቅልሽ ነው።
ኔቸር የተሰኘው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደሚገልጸው፣ የእነዚህ ሲካዳዎች ውስብስብ የሕይወት ዑደት ‹‹የሳይንስ ሊቃውንትን ለብዙ መቶ ዘመናት ግራ ሲያጋባ ኖሯል። ስለ ነፍሳት የሚያጠኑ ሊቃውንት፣ የእነዚህ ነፍሳት ልዩ የሕይወት ዑደት በዝግመተ ለውጥ አማካይነት እንዴት እንደመጣ ለመረዳት አሁንም እየጣሩ ነው፡፡››