Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ምዕመናን በከተራ ዕለት (ጥር 10 ቀን 2009...

የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ምዕመናን በከተራ ዕለት (ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም.) ታቦታቱን በዝማሬ ሲያጅቡ

ቀን:

መቼም የማይሻር ታላቅ ንጉሥ

ሁሉንም የሚጥል

ሁሉን የሚያነሳ ጊዜ ነው፣ ወቅት ነው፡፡

ከወደቁ ኋላ

ዳግም ለመነሳት ምክንያቱ ዘመን ነው፡፡

ነገር ግን

በጊዜ ምክንያት ሕይወት የምንላት

ለአንደኛው ድህነት ለሌላኛው ሀብት

መሆኗን ሲያስተውል

ባለ ፀጋ ያርምም አብዝቶ ዝም ይበል!!

ምክንያቱም

በሀብቱ በከብቱ

ትምክህትን ሊያደርግ ለርሱ አይገባም፡፡

(ደግሞም)

በጊዜ ምክንያት

ፍፁም የቸገረው ያጣ ድሀም ቢኖር

አይዘን አያልቅስ አምላኩን አያማር፡፡

በዚህ መሀል ግና

ለምንድን ነው ብሎ የሚጠይቅ ሰው ካለ

 እኛም እንላለን

ዘመን እንዳነሳ ዘመን እንደ ጣለ

ያነሳውን ሲጥል

የጣለን ሲያነሳ መቼም የማይሻር ጊዜ የምንለው ታላቅ ንጉሥ

አለ፡፡

  • ኤፍሬም ሥዩም ተሰማ ‹‹ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና›› (2006)

******

ጊዜ አለው . . .

ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለመረዳት፣ ላለመረዳት፣ ለመሳሳት፣ ለመስተካከል፣ ቀና ለማለት፣ ለመጉበጥም፣ስኳር ከሰማይ የሚረግፍበት ዘመን አለ፣ ጥብስም የሚመለክበት፣ የመጠጣት ጊዜ አለው፣ የመጥመቅ ጊዜ አለው፣ ጠጥቶም የመሽናት፣ የመውለድ ጊዜ አለው፣ የማደግም ጊዜ አለው፣ የመጎርመስም ጊዜ አለው፣ ጎርምሶ የመውደድም፣ ብስክሌት የመጋለብ፡፡ የጋለቡትንም የመስበር፡፡ የሰበሩትንም የመጠገን፡፡ የጠገኑትን መልሶ የመጋለብ፡፡ ጊዜ አለው በሬ የሚያርስበት፡፡ ለስጋም ወደ ገበያ የሚነዳበት፣ ከገበያም ተወስዶ የሚታረድበት፡፡ ጊዜ አለው ወደ ጥብስ የሚለወጥበት፡፡ ጊዜ አለው ማዕዳችን ላይ የሚከነበልበት፡፡ ጊዜ አለው ዲያቆን መሆን፣ ጊዜ አለው ነጋዴም መሆን፣ በተፃብኦ ማፍቀር እሱም አልፎ በቀን ሕልም መውደድ፣ ቀለበትን የማጣት እሱንም መልሶ የማግኘት፣ ጊዜ አለው ለማፍቀርም፣ ጊዜ አለው አፍቅሮ ለመለያየትም ጊዜ አለው ገመና ገመና ላይሆን፡፡ ጊዜ አለው ግዙፉ አውድ ረቂቅ አውድ የሚሆንበት፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው ይላል ይሄ እዝራ ታዚና……

አዳም ረታ ‹‹መረቅ››

* * *

‹‹በሚቀጥለው ሚልንየም ትምህርት ይሆነኛል››

በአገራችን በተከናወነው የሚልንየም በዓል አከባበር የተለያዩ በጎ ነገሮች  ተሠርተዋል፡፡ የሚልኒየሙን በዓል ምክንያት በማድረግም ስማቸውን የተከሉ፣ ኪሳቸውን ብቻ ሳይሆን ከረጢታቸውን በገንዘብ የሞሉ በርካታዎች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ቢሆንም ከአቅም በላይ ትርፍ ለማግኘት ብለው በርካታ ገንዘብ ካፈሰሱ በኋላ ‹‹ያፈሰሱትን ሳያፍሱ›› አተርፍ ባይ አጉዳይ የሆኑም አሉ፡፡

ቦሌ አካባቢ ነው አሉ አንዲት ወ/ሮ ለሚሊንየሙ ብለው ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ለማከራየት በማለት በተንጣለለው ግቢያቸው ውስጥ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አሥር ክፍሎች ያሠራሉ፡፡ በናፍቆት ሲጠብቁት የነበረው የሚሊንየም በዓል ቢደርስም በዶላር አከራየዋለሁ ብለው የሠሩት ቤት በብር የሚደፍረው ጠፋ፡፡ በዚህ እርር ድብን ያሉት ወይዘሮ ጠላት ለምን ይደሰታል ከሚል ሰው እንዲሰማቸው ጮክ በማለት ‹‹ግድ የለም ለሚቀጥለው ሚልንየም ትምህርት ይሆነኛል›› አሉ፡፡

ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር ‹‹ኅብረ ብዕር ሦስተኛ መጽሐፍ›› (2009)

* * *

እንዲህም!

  • በልብ ውስጥ ትክክለኛነት /ንጽህና/ ካለ፣ . . .

በጠባይ ውስጥ ውበት ይኖራል፡፡

  • በጠባይ ውስጥ ውበት ካለ፣

በቤት ውስጥ ስምምነት ይኖራል፡፡

  • በቤት ውስጥ ስምምነት ካለ፣

በአገር ውስጥ ሥርዓት ይኖራል፡፡

  • በአገር ውስጥ ሥርዓት ካለ፣

በዓለም ላይ ሰላም ይኖራል፡፡

  • እሴት ተኮር ትምህርት ማለት በልጆች ውስጥ ሰብዓዊነትን፣ ለሌሎችና ለአገረ መቆርቆርን ማስረፅ ነው፡፡
  • አንድ ግለሰብ ሀብቱን ካጣ ምንም አላጣም፣ ጤንነቱን ካጣ የሆነ ነገር ያጣል፣ ነገር ግን ጠባይ ካጣ ማንኛውንም ነገር ያጣል ይባላል፡፡

ትርጉም ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ምርጥ ሐሳቦች›› (2009)

* * *

የፓርላማ አባሏ ሚስቶች ባሎቻቸውን ወሲብ እንዲከለክሉ ጠየቁ

በኬንያ ፓርላማ የሞምባሳ ከተማ ተወካይ የሆኑት ሚሺ ምቦኮ ባሎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ጫና ለመፍጠር ሚስቶች ወሲብ እንዲከለክሏቸው ማሳሰባቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ ሴቶች ይህ ልትከተሉት የሚገባ ዓይነተኛ ስትራቴጂ ነው፡፡ በቃ የምራጭ ካርዳቸውን እስኪያሳይዋችሁ ድረስ ግንኙነት ከልክሏቸው፤›› ብለዋል፡፡ ተወካይዋ እንደሚሉት ይህ ለተቃዋሚዎች ድምፅ ለማግኘት ጠቀሜታም ይኖረዋል፡፡

በኬንያ ወሲብ ክልከላን እንደ ኃይል መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. 2008 ላይ የሴቶች መብት አቀንቃኞች የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሙአይ ኪባኪና ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እርቅ ያሰፍኑ ዘንድ ጫና እንዲፈጠር ሚስቶች ባሎቻቸውን ወሲብ እንዲከለክሉ ጥሪ አድርገው ነበር፡፡ በኬንያ ዘንድሮ ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ የሚያበቃው የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

* * *

የሮበርት ሙጋቤን ሞት የተነበዩት ፓስተር ተያዙ

የ92 ዓመቱ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በመጪው ዓመት 2010 ዓ.ም. ጥቅምት 6 ቀን እንደሚሞቱ የተነበዩት ፓስተር ለእሥር ተዳረጉ፡፡ የፓስተሩ ጠበቃ እንደተናገሩት ለደንበኛው ትንቢቱን የነገራቸው እግዚአብሔር ሲሆን፣ ፖሊስ ደንበኛቸውን ቢይዛቸውም እውነቱን ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ ብዙ ጊዜ ስለሞታቸው የሚወራባቸው ሙጋቤ ለጉዳዩ በቀልድ መልክ ሲመልሱ ከክርስቶስ በላይ ብዙ ጊዜ በትንሣኤ ከሞት ተነስቻለሁ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ፓስተሩ ሚስተር ሚትሲ የተከሰሱት የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን በማንቋሸሽ ነው፡፡

 * * *

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...