Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የቅድመ ሰው ዘር መገኛ አዲስ ገጽ

በሸዋዬ መርን

ኢትዮጵያ በዓለም ቀዳሚና ገናና የዓለም ሥልጣኔ ቁንጮ በመሆን የምትጠቀስ አገር፣ የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ብርቅዬ ቅርሶች ባለቤት ናት። የ13 ወራት የፀሐይ ብርሃን ባለፀጋ የገነት ተምሳሌት፣ የዋህና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ መኖሪያ፣ በልዩነት ውስጥ የአንድነት ተምሳሌት፣ ለዘመናት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች የጀግኖች ምድር፣ የታቦተ ጽዮንና የግማደ መስቀሉ መገኛ እንቁ ምድረ ኢትዮጵያ።

በዘመናችን ካሉ ኃያላን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በላቀ ደረጃና በዓለም ላይ ከተፈጠሩ የሰው ልጆች የፈጠራ ውጤቶች፣ በተለይ ደግሞ የኪነ ሕንፃ ጠበብቶች በቀደምትነት እየመሩ ያሉ ውስብስብና ከአዕምሮ በላይ የሆኑ የምህንድስና ባለቤት መሆኗን የሚመሠክሩ አንድ ወጥ ከሆነ ድንጋይ የተፈለፈሉ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት (ላሊበላ)፣ አክሱምና የጎንደር ቤተ መንግሥት ኪነ ሕንፃዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

 ምሥጋና ለቀደሙት ባለብዙ ጥበብ እሳቤ ባለቤቶች አባቶቻችን ይሁንና እነዚህ ተዓምራዊ ቅርሶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝብ ቅርስ ሆነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት ከተመዘገቡ ሰንብተዋል። እስካሁን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች 11 የደረሱ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ሦስቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት፣ የጁገል ግንብ፣ የታችኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ኦሞ፣ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ ከሚዳሰሱት ይመደባሉ፡፡ መስቀል ደመራ፣ ፊቼ ጨምበላላና የገዳ ሥርዓት ደግሞ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት የማይዳሰሱት ቅርሶች ውስጥ ይመደባሉ።

እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ አገራችን ግሩም ድንቅ የሆኑ ሌሎች የቱሪዝም መስህብ ቦታዎች እንደነ ሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የባሌ ተራሮች፣ ነጭ ሳር፣ ስሜን ተራሮች፣ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ (ከደብረ ብርሃን በስተሰሜን 145 ኪሜ) በጓሳ ተራራ ላይ የምትገኝ፣ አርባ ምንጭ የአዞ እርባታ፣ ጣና ሐይቅና ላንጋኖ ጥቂቶቹ ናቸው።

እነዚህ ቅርሶች የማንነታችን መገለጫዎች፣ ብሔራዊ ኩራቶቻችን፣ የኢኮኖሚያችን ዋልታዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ምንጮቻችን ብሎም አንድነታችንን የሚያጠነክሩ የህልውናችንና የታሪካችን መሠረቶች ናቸው። ስለሆነም እንደ ዓይናችን ብሌን ጠብቀን በአግባቡ ልንከባከባቸውና ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ የሞራል ግዴታ አለብን።

በቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሦስቱ ‘መ’ዎች ምንዛሪዎች

በአንድ ቦታ ወይም ጊዜ ቱሪዝም ተካሄደ/ሆነ ለመባል ሦስቱ ነገሮች የግድ መሟላት ይኖርባቸዋል። በማንኛውም ሁኔታ አንድ አገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ብሎም ዘርፉን ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና መደገፍ ካለበት እነዚህ ሦስት የማይነጣጠሉ የቱሪዝም ምንዛሪዎች (Components) ላይ መሥራት ይኖርበታል።

የመጀመሪያው ጉዳይ የቱሪዝም መስህብ (Attraction) ቦታችን የሚመለከት ሲሆን ታሪካዊ ቅርሶች፣ ባህላዊ ምግብና መጠጦችን፣ ባህላዊ ዳንሶችን፣ ቋንቋዎች፣ የአኗኗርና የአመጋገብ ሥነ ሥርዓቶችና ሁነቶችን የሚያካትት በሙሉ መስህብ ተብሎ ይጠቃለላል። ስለዚህ እነዚህ የቱሪስት መስህቦች በሌሉበት ስለቱሪዝም ማውራት ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ እንደሚባለው የአገራችን ብሒል ይሆናል ማለት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የቱሪዝም አካል ደግሞ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ይወስነዋል። ምክንያቱም አንድ ቱሪስት በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ የቱሪስት ቦታዎችን ሲጎበኝ በቆይታው መሠረታዊም ፍላጎቶች የሚባሉትን እንደ ምግብ፣ የሆቴል አገልግሎትና የመሳሰሉትን መስተንግዶዎች (Accommodations) ካላገኘ ወይንም ዝግጁ ካልሆኑ በስተቀር የውጭ ምንዛሪን የማግኘቱ ጉዳይ የህልም እንጀራ ሆኖ መቅረቱ አያጠራጥርም።

በመጨረሻ ደረጃ ለቱሪዝም ዕውን መሆን ወሳኝ ሚና የሚጫወተው መገናኛ መንገዶች/ተስማሚነት (Amenity) የሚባለው ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮው በሄደበት ቦታና ጊዜ የሚስማማው የአየር ንብረት፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የግብይት አገልግሎቶችን እስካላገኘ ድረስ ምንም ያህል የሚያስደንቅ ጥበብ፣ ቅርስ ወይም ቦታ ቢጎበኝ በቆይታው አለዚያም በጉዞው ወቅት ወይም ከደረሰ በኋላ ከድካሙ የሚጠግነውና የሚያዝናናው አገልግሎትና ምቾት ካላገኘ፣ በፈቃዱ ለስቃዩ ብር እንደማይከፍል ዕሙን ነው። ስለዚህ በተለያዩ የቱሪዝም ቦታዎቻችን መዳረሻ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ፣ ዘመናዊ ሆቴሎችና መዝናኛ ማዕከላት ሊሟሉ ይገባል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉባትና የዘርፉን ህልውና ከሚወስኑት ጉዳይ አንዱ ሆኗል።

ቱሪዝም ለአገራዊ ኢኮኖሚ ያለው አስተዋፅኦ

ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እየተባለ የሚጠራው ቱሪዝም ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መሻሻል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ግን ከሴክተሩ በሚገኘው የገቢ መጠን ይወሰናል። ቱሪዝም በዓለም ላይ አንደኛው በተለይ ለታዳጊ አገሮች የኢኮኖሚ ምንድግና (Economic Transformation) ከፍተና አስተዋፅኦ እያበረከተ መጥቷል።

ይህን በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የቱሪዝም ዘርፉን ከማስተዋወቅና የውጭ አገር ጎብኝዎችን ልብና ኅሊና ከማማለል ሥራ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መሄድ እንዳለበት የዘርፉ ባለ እሳቤ ልሂቃን ያሳስባሉ።

በተለይ በታዳጊ አገሮች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መቀጨጭና የሚፈለገውንና የሚጠበቅበትን ያህል የገቢ ምንጭ ላለማስገኘቱ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ችግሩ በተለይ በአፍሪካ ሥር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አፍሪካን በረሃብ የተመታችና የችግሮች ቤት፣ በብጥብጥና በበሽታ የተወረረች አድርጎ መመልከት ዋነኛ ምክንያቱ ነው፡፡ እውነታው ግን አፍሪካ የብዙ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ባለቤት፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛና የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን በአግባቡ አለመረዳት ነው።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚዳስሱ የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ 2.9 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ታገኛለች። እ.ኤ.አ. በ2015 ቱሪዝም ለአጠቃላይ ብሔራዊ ምርት 9.2 በመቶ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ 8.4 በመቶና 2.9 በመቶ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ  አስተዋፅኦ እንዳበረከተ መገንዘብ ይቻላል።

ለዚህ መሠሰሉ አስተዋፅኦ ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፉ የሚመጥን ዘመናዊና ምቹ የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጠንካራ ትስስር ፈጥሮ መሥራትን ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዷ ከቱሪዝም ዘርፍ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ይህን ግብ ለማሳካትና በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነዱ ላይ የተለያዩ የማስፈጸሚያ ስልትና አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሀብት ለተቀረው ዓለም በሚገባ ማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባንን የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማጠናከርና ማብዛት፣ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎችን በብዛትና በጥራት መጨመር የመሳሰሉትን ዋና ዋና አቅጣጫዎች በማስቀመጥ እየተሠራ ይገኛል። እነዚህን ሁሉ ተግባራት ለማከናወን በአገር አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ካውንስል የተቋቋመ ሲሆን፣ በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይልና በጥናትና ምርምር የተደገፈ  የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለመምራት የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላትን ለማጠናከር ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የቱሪዝም ዘርፉን ማስተዋወቂያ መንገዶች

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ቱሪዝም በተለይ ለወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ትልቅ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም፣ ድህነትን የመቀነሻ አንዱ መንገድ እንዲሁም ለሰብዓዊ ልማትና ለአካባቢያዊ ሥነ ምኅዳራዊ  ደኅንነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተለያየ መንገድ ለአገራዊ ኢኮኖሚው መሻሻልና ዕድገት ጉልህ  ሚና ቢኖረውም፣ ዘርፉ ግን የተለያዩ  ፈተናዎች ተደቅነውበት ይስተዋላል ። የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የተደራጀ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ሥልቶች አለመቀየሳቸው፣ በዘርፉ የተካነ የሰዉ ኃይልና የድጋፍ ማነስ ችግሮች መኖር ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም  ዘርፉን በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቁ ረገድ ብዙ መጓዝ ቢጠበቅምባትም፣ በአሁኑ ወቅት በመጠኑም  ቢሆን  እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች ። ቱሪዝምን ለውጭ ጎብኚዎች የመሸጥ ጥበብ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም  የሚከናወን ይሆናል። ከእነዚህም ውስጥ የመተዋወቂያ ጉዞ ማዘጋጀት፣ ብሔራዊ ግሎትም (Nation Branding)፣ ሮድሸው፣ የንግድ ትርዒት፣ ዲጂታልና የኅትመት ውጤቶችን  በመጠቀም ማስተዋወቅ ይቻላል።

በጣም የተሻለ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መንገድ የሚባለው የመተዋወቂያ ጉዞ ማዘጋጀት ነው። ይህ መንገድ የሚከናወነው ለውጭ የጉዞ ወኪሎች፣ ጋዜጠኞችና ቱር ኦፕሬተሮች ወደ ተለያዩ የአገራችን የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ጉዞ እንዲያደርጉ በማመቻቸት የሚደረግ ሥልት ነው ። ይህን የማስታዋወቂያ  መንገድ መጠቀም የረጅም ጊዜ ተፅዕኖ ለመፍጠርና እነዚህ የጉዞ ወኪሎች፣ ጋዜጠኞችና ቱር ኦፕሬተሮች በቱሪስት መዳረሻዎች ያዩትን ድንቅ የተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ስለቱሪዝም  ኢንዱስትሪው በጎ ጎን በመጻፍ፣ በመናገርና ኢትዮጵያን በቱር ፓኬጃቸው በማስገባት ብሎም ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለተከታዮቻቸው በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሪያ ሥልት መሆኑ ይነገራል።

የኅትመት ውጤቶችን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን የማስተዋወቅ ዘዴ ደግሞ በዝቅተኛ ወጪ ብዙ ሰዎችን መድረስ የሚስያችል የቱሪዝም መሸጫ ጥበብ ነው። እነዚህ የኅትመት ውጤቶች ውብ የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን፣ ፎቶግራፎችና ዲዛይኖችን ሆነው በተለያዩ አገሮች ለሚገኙ ቱሪስቶችና የጉዞ ወኪሎች የሚሰጡ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽኖች ላይ መሳተፍ ሌላው የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መንገድ ነው። የዚህ ማስተዋወቂያ ሥልት ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ የታደለቻቸውን የተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶቻችንን ለውጭው ዓለም ማስተዋወቅ ብሎም የአገሪቱን ገጽታ መገንባትን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህ የንግድ ትርዒት ላይ በዘርፉ የተሠማሩና የሚያገባቸው ባለድርሻ አካላት የሚባሉት አገር በቀል የጉዞ ወኪሎች፣ ቱር ኦፕሬተሮች፣ የሆቴል ባለቤቶችና ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጋራ በመሳተፍ በትርዒቱ ከሚሳተፉ አቻዎቻቸው ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያግዛል።

በዚህች ሉላዊና በቴክኖሎጂ በመጠቀች ምድር ላይ አካላዊ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ዘዴ ብቻ ዋጋ ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ለአጠቃቀም ቀላልና ብዙ የዓለማችን ቱሪስቶችን በቀላሉ መድረስ የሚያስችል የደረጃውን የጠበቀና ተደራሽ ድረ ገጽ መገንባት ያስፈልጋል (Twitter, Facebook, YouTube and Blogs)፡፡ እንዲሁም የሞባይል ኦፕሊኬሽኖችን በማልማት ቱሪስቶች በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው መረጃዎችን ስለኢትዮጵያ ብሎም ስለቱሪዝም ሀብቶቻችን በማውረድ እንዲጠቀሙ ማድረግ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ማንኛውም ሰውና አገር የትኛውንም ዓይነት የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ሥልቶችን ቢጠቀምም ቅሉ፣ በጣም የተለየና የማንኛውንም ሰው ቀልብ ሊገዛ የሚችል የግንኙነት ሥልት መፍጠሩ አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ”Nation Branding” (ብሔራዊ ግሎትም) መሠረታዊ የሆነ የአገር መለያና የሰዎችን ልብና ኅሊና ለመግዛት የሚስችልና አዲስ አቀራረብን በመያዝ ቱሪስቶችን የማማለያ ሥልት ነው።

አዲሱ የኢትዮጵያ መለያ ”Land of Origins” (የሰው ዘር መገኛ) በዚህች ዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው ይህን ሀረግ ሲሰማ ከሦስት ሚሊዮን ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የእነ ሉሲና ሀዳር አገር የሰው ልጅ መገኛ፣ ኢትዮጵያ የዘር ግንዱ አንድ ተብሎ የሚቆጠርባት ባለውለታው መሆኗን ለማሰብ ይገደዳል።

ቱሪዝም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከሌሎች ሴክተሮችና ከሰፊው ኢኮኖሚ በላቀ ደረጃ በፍጥነት እንዲያድግ ይጠበቃል። ስለዚህ ቱሪዝም የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ፍትሐዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥቅሞችን ለዜጎች ማበርከቱን ይቀጥላል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles