Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የበግ ቆዳ ለሰሚው እስኪያስገርም የረከሰው በምን ምክንያት ይሆን?

የዘንድሮው የገና በዓል የቀንድ ከብቶች ገበያ እንደቀደሙት በዓላት የተጋነነ ዋጋ የሚጠራበት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ የበሬ፣ የፍየልና የበግ ዋጋ ቀንሶ ታይቷል፡፡

ከበርካታ ሸማቾች የሰማሁት አስተያየትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የበዓሉ ዕለት በአቅራቢያዬ ወደሚገኝ በግ ተራ በመሄድ የተመለከትኩትም ይህንኑ አረጋግጧል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ፊቱ የዋጋ ጥሪያቸው የሚያስበረግግ አልነበረም፡፡ ጥሩ የሚከራከር ሸማች ሦስት ሺሕ ብር የተባለውን እስከ 2000 ብር አስቀንሶ ሲገዛ ተመልክቻለሁ፡፡ የበግ ነጋዴዎቹም ቢሆኑ እንደ ቀድሞ ከጠሩት ዋጋ ላለመቀነስ ድርቅ አይሉም፡፡ ለማንኛውም በዘንድሮው የገና በዓል የከብት ገበያ ከቀደሙት በዓላት የተሻለ ነበር፡፡ ለምን የተለየ ሆነ የሚለው ጥያቄ ብዙ ሊያነጋግር ይችላል፡፡ በገፍ ከብት በመግባቱ ነው? ወይስ ኪሳችን በመድከሙ የተፈጠረ? ወይስ ሌላ ምክንያት ሊጠቀስ ይችል ይሆን?

ምላሹ ይቆየንና በዘንድሮው የገና በዓል በተሻለ ዋጋ ይዘን የገዛነው በግ ከታረደ በኋላ የገጠመኝ አንድ ነገር ብዥታ ፈጥሮብኛልና እሱን ላውጋ፡፡ ብዙዎቻችን ከተሜዎች በጉን ገዝቶ ማምጣቱ ላይ እንጂ ባርኮ መበለቱ ላይ የለንበትም፡፡ ስለዚህ ከበጉ ጋር አራጅ ወይም ገፋፊ ይዞ መምጣት የተለመደ ነው፡፡ የዛሬውን አያድርገውና የአራጅ የጉልበት ዋጋው ቆዳ ነበር፡፡ ቆዳውን ሽጦ ገንዘቡን ለራሱ ይወስዳል፡፡ ይህ ክፍያውን ያረደበት፣ የበለበት ዋጋው ነውና፡፡ ካልሆነም የወቅቱን የቆዳ ዋጋ መሠረት በማድረግ የተወሰነ ገንዘብ ካልተጨመረለት በቀር አራጅ ቆዳውን ከወሰደ ለጉልበቱ ዋጋ ተከፈለው ማለት ነው፡፡

አሁን አሁን አራጆች በጥሬው እየጠየቁ ነው፡፡ የአራጅ ዋጋ ከ100 እስከ 150 ብር ደርሷል፡፡ እንደ ቀድሞው የቆዳ ዋጋውን አስልቶ መክፈል አይታሰብም፡፡ በተለይ ዘንድሮ ለአራጅ የሚከፈል የጉልበት ዋጋ ቆዳ ሰጥቶ ለመደራደር አያስችልም፡፡ በአስደንጋጭ መጠን ሲጨምር የነበረው የቆዳ ዋጋ የቀድሞውን አሠራር ሰብሮታል፡፡ ለእኛም ብዥታ የፈጠረብን ይህ አጋጣሚ ነበር፡፡

እስከ 200 ብር ያወጣ የነበረ የበግ ቆዳ፣ በአሥራ አምስት ብር ሲሸጥ ምን ተከሰተ ማለት የማይቀር ነው፡፡ በግሌ የበግ ቆዳ በዚህ የወረደ ዋጋ የተሸጠበትን የቅርብ ጊዜ አላስታውስም፡፡ እንዲያውም ቆዳው ይሸጥና ወይንና አረቄ ይገዛት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የዘንድሮው የበግ ቆዳ ግን ቄጤማ ለመግዣ እንኳ ያለመብቃቱ ነገር የቆዳ መሸጫና መግዣ ተመኑ ጤናማነትን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡

ዋጋው ለምን ወረደ የሚለው አከራካሪ ቢሆንም፣ እንደ አገር ካሰብነው የዋጋው መውረድ በመልካም አጋጣሚነቱ ለመመልከት የሚያስችል ቀዳዳ ቢኖርም፣ የቆዳ አቅርቦት ዕጥረት አለብን በማለት በየዓመቱ ሪፖርት የሚያቀርቡ የቆዳ ፋብሪካዎች፣ እጅግ በረከሰ ዋጋ ጥሬ ዕቃ እንዲሸምቱ አስችሏቸዋል ማለት ግን ይቻላል፡፡ በቆዳ ዋጋ መወደድ መግዛት የሚገባቸውን ያህል እንዲገዙ ማስቻሉም እንደ መልካም አጋጣሚ ሊታይ ይችላል፡፡ ችግሩ ግን ቆዳ ረከሰ ሲባል በየቤቱ ዕርድ ያከናወነ ሁሉ ሥጋውን ከቆዳው ለማላቀቅ ግዴለሽ ካልሆነ በስተቀር ለቆዳ ተቀባዮች መልካም ዕድል ሆኖ መገኘቱ ጥሩ ነው፡፡ አሁንም የቆዳ ዋጋ ለምን በዚህን ያህል ደረጃ ወረደ ለሚለው ጥያቄ ሙያዊ ትንታኔ ያሻዋል፡፡ ለአገሪቱ የቆዳ ኢንዱስትሪ መሠረታዊ የሆነውን የጥሬ ቆዳ አቅርቦት ትልቁ ችግር ጥራት በመሆኑ ይህንን ጥራት ለማምጣት ሰሞነኛ ተመኑ ብዙ መንገድ የሚያስጉዝ አልመሰለኝም፡፡ በተለይ የጥሬ ቆዳው ዋናው ምንጭ የበዓላት ወቅት ስለሆነ ቆዳን ሳይበላሽ ማቅረብ አገርን መጥቀም ጭምር እንደሆነ በማስመዝገብ በጥራት ችግር ምክንያት የሚቀርበውን ሰበብ አስባብ ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡

ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊገኝበት የሚገባው ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ሊያስገኝ ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ በብዙ መንገድ ርቆ መገኘቱን ሲጠቅሱ ነበር፡፡ ከዋና ዋና ግድፈቶች ውስጥ የአቅርቦት ዕጥረት አንዱ ነው፡፡ የቆዳ መሸጫ ዋጋ ንሯል የሚሉ በርካታ ንትርኮች ይደመጡ ነበር፡፡ ጥራት ያለው ቆዳ እንደልብ ያለመገኘቱንም ለቆዳ ኢንዱስትሪ ራስ ምታት ሆኖ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ከውጭ እስከማስመጣት ማድረሱም ተነግሯል፡፡ ነገር ግን የቆዳው ዋጋ መውረዱ ብቻ ሳይሆን ጥራት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይ በበዓላት ወቅት እርዱ ላይ ብዙ መሠራት አለበት ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሸማቾች ለሥጋው የሚሰጡትን ትኩረት ለቆዳውም እንዲሰጡ ለማድረግ አንዱ አጋጣሚ ቆዳው ጥሩ ዋጋ እንዲያወጣ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የቆዳ ዋጋው መውረዱ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ይታወቅ ይሆን? ለበጎ ከሆነ ይሁን ከማለት ውጭ ምን ይባላል? 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት