Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መኪናን ቅንጦት ያደረጉ የመንግሥት ሕጎች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዱሮው ዘመን፣ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ወዲህ ኦፔል፣ ታኖስ፣ ዶጅ፣ ሲትሮይን፣ ሮልስ ሮይስ፣ መርሴዲስና ሌሎችም ባለስም መኪኖችን እያሽከረከሩ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ፈልሰስ ማለት ለዘፈን የሚያበቃ መደነቅን ያተርፍ ነበር፡፡ ‹‹ይሏል ዶጇ ፏፏ…››ን ያስታውሷል፡፡

በበርካቶች የከተማ ነዋሪዎች ዘንድ የግል መኪና ባለቤት መሆን ቅንጦት መሆኑ ካበቃለት ብዙ ዘመን ተኩሷል፡፡ ይበልጡን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በሚታየው የትራንስፖርት እጥረትና መንግሥትም በሚከተለው የትራንስፖርት አቅርቦት ሥርዓት ምክንያት ከባድ የትራንስፖርት ችግር በየመንገዱ ይታያል፡፡ በዝናብና በፀሐይ ወራት ትራንስፖርት ፈላጊ ሕዝብ እንደ እባብ ሽንጥ የረዛዘሙ ሠልፎችን ሠርቶ የሚያሳፍረውን መኪና በጉጉት ይጠብቃል፡፡

በዱሮው ዘመን መኪናው ሳይሆን መኪናውን ማሽከርከር የሚችለው፣ ፈቃድ ያለው ሰው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ መኪናው በመንግሥት ሆን ተብሎ በሚጣልበት ታሪፍና ግብር ምክንያት ውድ አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው መኪና የሚገዛ ገንዘብ ኖሮት የሚገዛውም ጥቂት ነበር፡፡ ይህም ቢባል ግን በተለይ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ደመወዝተኛ የሆነ ሰው ለብድር ከመሥሪያ ቤቱ አጽፎ በሦስት ሺሕም አለያም በአምስት ሺሕ ብርም እንደ አቅሙ ዘመን አመጣሽ መኪኖችን ይገዛ እንደነበር በርካቶች ያወጋሉ፡፡ በዚህ ዘመን ግን መኪና ቅንጦት ነው የሚለው ፈሊጥ እንዳለ ነው፡፡

መንግሥት ከአምስት ዓይነት በላይ ታክስ ከውጭ በሚገቡ አዲስም ሆኑ ያገለገሉ መከኖች ላይ ይጥላል፡፡ እንደ መኪናው የፈረስ ጉልበት እየታየም የታክስ ምጣኔው ከፍ ይደረጋል፡፡ በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ ሆነ ተብሎ ጥቂት የመኪና ባለንብረቶች እንዲኖሩባት ያደረገች አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ነች ማለት ይቻላል፡፡

ይኸው የአገሪቱ ሁኔታ ያስገረመው ኬንያዊው የቢቢሲ ዘጋቢ፣ ኢማኑኤል ኢጉንዛ ‹‹ለመሆኑ በኢትዮጵያ የመኪናን ዋጋ እንዲህ ውድ ያደረገው ምንድን ይሆን?›› ሲል ዘግቧል፡፡ መቶ ሚሊዮን እንደደረሰ ከሚገመተው ከሕዝብ ቁጥር ውስጥ መኪና ያለው ሰው ብዛት 700 ሺሕ ገደማ ብቻ እንደሆነ የመንግሥት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም ማለት ከእያንዳንዱ አንድ ሺሕ ሰው ውስጥ ሁለቱ ብቻ (ለአኃዝ ሲባል እንጂ ሁለትም አይሞሉም) የመኪና ባለንብረት መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ይህ አኃዝ ካቻምና ይፋ ከተደረገው ከድሎይት አማካሪ ኩባንያ ድምዳሜ ጋር የሚያስማማ ነው፡፡ ይህ ኩባንያም ይህንኑ እውነታ ሪፖርት ማድረጉን ዘጋቢው አጣቅሷል፡፡

መንግሥት ባስቀመጠው የታሪፍና የጉምሩክ ቀረጥ ምክንያት፣ አስመጪዎች ለማጓጓዣ፣ ለወደብና ለመሳሰሉትን ወጪዎች ከመሸፈን አልፈው ትርፋቸውን አክለውበት በአዲስ አበባ እየተሸጡ ያሉት ያገለገሉም አዲሶቹም መኪኖች ዋጋቸው አይቀመስ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለአንድ ቪትስ መኪና የሚጠየቀው ዋጋ እንደ መኪናው ቀለምና ይዞታ ከ250 ሺሕ ብር በላይ ሆኖ ይገኛል፡፡

ይህም ማለት ከ10 ሺሕ ዶላር በላይ ሆኖ ይገኛል፡፡ በርካታ የጃፓን ያገለገሉ መኪና መሸጫ ድረ ገጾች ግን እነዚህን ጃፓን ሠራሽ መኪኖች ከአንድ ሺሕ ዶላር ወይም ከ23 ሺሕ ብር (በወቅቱ ምንዛሪ) ባነሰ ዋጋ እንደሚሸጧቸው በይፋ ይታወቃል፡፡ ይህ ዋጋ ግን በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በዚህ በ23 ሺሕ ብር ወይም በአንድ ሺሕ ዶላር መኪና ገዛሁ ብሎ አስመጪው ደረሰኝ ቢያቀርብለት እንዲሁ እንደማይቀበለው ከሚከተላቸው አሠራሮች መረዳት ይቻላል፡፡

በገቢዎችና በጉምሩክ ባለሥልጣን የታሪፍ ኦፊሰር የሆኑትን አቶ ካሳዬ አየለ እንደጠቀሱት፣ መቶ ከመቶ የሚደርሱ አምስት ዓይነት የቀረጥ ስሌቶች በንግድም ሆነ በግል መኪኖች ላይ ይጣላል፡፡ ይህ ግን ቅድሚያ ተሰጧቸውም ሆነ ከታሪፍ ነፃ ተደርገው የሚገቡትን እንደማይወክል አቶ ካሳዬ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሉ ተሽከርካሪዎች ቢበዛ ከአሥር ከመቶ ያልበለጠ ቀረጥ እንደሚጣልባቸው የገለጹት አቶ ካሳዬ፣ ሌሎች መኪኖች ግን እንደ የሞተራቸው የጉልበት አቅም ከ60 እስከ 100 ከመቶ ቀረጥ ይጣልባቸዋል ብለዋል፡፡ እንደ ሔኖክ ደምሰው ያሉ መኪና ነጋዴዎች በአገሪቱ የመኪና ንግድ ውስጥ ትልቁ ፈተና ይኸው የመንግሥት አይቀመስ ቀረጥ መሆኑን ሳይገልጹ አላላፉም፡፡

ይህ በመሆኑም በብዙዎች ዘንድ አማራጭ የማይደረጉት አነስተኞቹ ቶዮታ ቪትዝ መኪኖች ከ250 ሺሕ በላይ እንዲወጣባቸው ቢያስገድድም፣ በኬንያ ግን ከዚህ በግማሽ ያነሰ ዋጋ እንደሚጠየቅባቸው የቢቢሲው ዘጋቢ አስታውሷል፡፡

መንግሥት ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ በሚገጣጠሙ ለመተካት ባይሆን እንኳ ከውጭ የሚገቡትን መጠን ለመቀነስ በማሰብ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካዎችን እንዲመሠርቱ ማበረታቻዎችን በመስጠት ደግፏል፡፡ ይሁንና መገጣጠሚያዎቹ የሚሸጡበት ዋጋም ቢሆን፣ ከሚገመተው በላይ ከፍተኛ ቀረጥ ተጥሎባቸው ከውጭ ከሚገቡት አኳያ ሲታይ ይህ ነው የሚባል የዋጋ ልዩነት እንደማይታይባቸው በርካቶች ይገልጻሉ፡፡

ከዋጋቸው ባሻገር በመኪኖቹ ጥራት፣ በመለዋወጫ አቅርቦትና በመሳሰሉት መስኮች በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙት ላይ በርካቶች ዕምነት አጥተው ይታያሉ፡፡ የቢቢሲው ኢማኑኤልም ሆነ ሪፖርተር ከዚህ ቀደም ያነጋገራቸው የሊፋን ሞተርስ ኃላፊዎች በአገሪቱ ያለው ገበያ ብዙም እንዳልተዋጠላቸው፣ መንግሥትም ቢሆን ያገለገሉ መኪኖችን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክል አሠራር መከተል ሲገባው ያንን ባለማድረጉ እየተቸገሩ እንደሚገኙ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ60 ከመቶ በላይ የቶዮታ ሥሪት አዳዲስና አሮጌ መኪኖች እንደሚሽከረከሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንደ ቶዮታ ያሉና በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ የሚጣልባቸው ሞዴሎች የቱንም ያህል ውድ ቢሆኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ይልቅ በ50 ከመቶ ጭማሪ የታየበት የመኪና ቁጥር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከ110 ሺሕ ያላነሱ መከኖች መግባታቸው ይጠቀሳል፡፡

መንግሥት በተሽከርካሪዎች ላይ የጣለው ቀረጥና ታሪፍ ከገቢ ምንጭነት ባሻገር በትራንስፖርት መስክ የሚታየውን አሸማቃቂ የመጓጓዣ ዕጦትን ለመቀነስ እንዲቻል የሚጥለውን የቀረጥ መጠን እንዲከልስ የሚጥይቁ አካላት እንደሚገልጹት፣ ይህን በማድረግ አቅሙ ያላቸው በርካታ ሰዎች በዚህ መንገድ የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍ እንዲችሉ መንግሥት ዕገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይናገራሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ወደፊት የድንበር ተሻጋሪ፣ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቶችን ማፅደቅና መተግበር ስትጀምር ከቀረጥ የሚገኘው ገቢ በእጅጉ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል በማሰባሰብ ከወዲሁ ሌሎች አማራጮች መታሰብ እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡ ይሁንና መንግሥት ከታክስና ከቀረጥ ከሚሰበስበው ገቢ ውስጥ ከግማሽ ያላነሰውን ከውጭ ከሚገቡ ዕቃዎች ላይ ከሚጣለው ግብር የሚሰበስብ ሲሆን፣ እንደ ተሸከርካሪ ያሉትና ዛሬም ድረስ የቅንጦት ዕቃዎች ተደርገው በሚታሰቡት ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጥሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች