Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት የተጠረጠሩ የቡና ነጋዴዎች ታሰሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ ሰዎች ስም የቡና ላኪነት የንግድ ፈቃድ በማውጣትና ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር መንግሥትን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማሳጣትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ፣ አምስት የቡና ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ታሰሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በርሔ ገብረ መድኅን፣ ዳንኤል ይህደጎ፣ መሰሉ ተፈራ፣ ፋንታሁን ስሜና ሳድቅ ሸደምሴ ረዲ ናቸው፡፡ ሁሉም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች  መንግሥትን የተጠቀሰውን ያህል የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉት፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገዙትን ቡና በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ደብቀው በመገኘታቸው መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ፖሊስ ለፍርድ ቤት እንዳስረዳው በርሔ ገብረ መድኅን፣ ዳንኤል ይህደጎና መሰሉ ተፈራ የተባሉት ተጠርጣሪዎች በተለያዩ ግለሰቦች ስም የቡና ላኪነት ፈቃድ አውጥተዋል፡፡ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋርም በመመሳጠር ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት በጀት ዓመቶች ውስጥ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 1,992.1 ቶን ወይም 19,921 ኩንታል ኤክስፖርት የሚሆን ቡና ገዝተዋል፡፡ ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ሳይልኩ በመቅረታቸውና በመደበቃቸው አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን 7,531,200 ዶላር ወይም 147,209,795 ብር የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል፡፡ ፋንታሁን ስሜ የተባሉት ተጠርጣሪ ደግሞ በ2006 በጀት ዓመት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 445.5 ቶን ወይም 4,455 ኩንታል ኤክስፖርት የሚሆን ቡና ገዝተዋል፡፡ የገዙትን ቡና በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ደብቀው በመገኘታቸው አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን 1,491,800 ዶላር ወይም 505,036,808 ብር የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ሳድቅ ሸደምሴ ረዲ የተባሉት ተጠርጣሪ ደግሞ ከግብር አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር በ2000 በጀት ዓመት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 178.5 ቶን ወይም 1,785 ኩንታል ቡና የገዙ ቢሆንም፣ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ደብቀው መገኘታቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን 500,700 ዶላር ወይም 5,292,899 ብር የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ማድረጋቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ተመሳጥረው መሆኑን እንደደረሰበት ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቶ፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች