Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቱርክ ትምህርት ቤቶች በሽብር ከሚጠረጠረው የፌቱላህ ጉለን እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ እንደሌላቸው በመግለጽ...

የቱርክ ትምህርት ቤቶች በሽብር ከሚጠረጠረው የፌቱላህ ጉለን እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ እንደሌላቸው በመግለጽ የይዘጉ ጥያቄዎችን ውድቅ አደረጉ

ቀን:

– የትምህርት ቤቶቹ ስያሜ ሊቀየር እንደሚችል ይጠበቃል

ነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ ኢንተርናሽናል በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ላለፉት 12 ዓመታት ሲንቀሳቀሱ የቆዩት ትምህርት ቤቶች፣ በቱርክ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ውስጥ እጃቸው አለበት ከሚባሉት ፌቱላህ ጉለንና በእሳቸው ስም ከሚንቀሳቀሰው የጉለኒስት ወይም የሒዝመት እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ በቱርክ መንግሥት የቀረበባቸውን የይዘጉልን ጥያቄ እንደማይቀበሉ የትምህርት ቤቶቹ ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡

የነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች የትምህርት አስተባባሪና የአይናክ ትምህርትና ሕክምና አገልግሎቶች ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰሊን አይዲን ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ ኩባንያቸውም ሆነ ትምህርት ቤቶቹ በቱርክ መንግሥት በሽብር ተግባር ከሚጠረጠረው የፌቱላህ ጉለን እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ቢሆንም፣ የቱርክ መንግሥት በፍረጃ ውንጀላ እያቀረበባቸው  ይገኛል፡፡

የቱርክ መንግሥት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲ በኩል ከፌቱላህ ጉለን እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የትምህርትና የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ መጠየቁን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ይህ ጥያቄ ግን በኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ አይዲን እንደሚሉት፣ ትምህርት ቤቶቻቸውም ሆኑ የንግድ ኩባንያቸው የኢትዮጵያን ሕግ አክብረው በኢትዮጵያ እየሠሩ የሚገኙ፣ ታክስና ሌሎችም ዕዳዎችን በአግባቡ የሚከፍሉ፣ መንግሥትም ምንም ዓይነት ችግሮች ያላገኘባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎችና ወላጆች በመሆናቸው ከሃይማኖት ነፃ የሆነ ትምህርት ውጪ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊና ሌሎች ፖለቲካ ላይ ያጠነጠኑ የትምህርት አሰጣጥ እንደሌላቸው ሚስተር አይዲን ገልጸዋል፡፡ ላለፉት 12 ዓመታትም ትርፍን መሠረት ያደረገና የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት ያከበረ የትምህርት ሥርዓት ሲተገበር መቆየቱንም  ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት አካባቢ፣ በሲኤምሲ፣ በሳር ቤት እንዲሁም በዓለም ገና 1,700 ገደማ ተማሪዎችን በመቀበል እያስተናገደ እንደሚገኝ ሚስተር አይዲንን ጨምሮ ሐሳን ኮላክና ፋቲህ ጋንኮግሉ የተባሉት የትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የ38 አገሮች ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ከ320 ያላነሱ መምህራንና ሌሎች ደጋፊ ሠራተኞችም እንዲሁ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከቱርክና ከሌሎች አገሮች የተውጣጡ በመሆናቸው በቱርክ መንግሥት እየቀረበባቸው ያለውን ውንጀላ ውድቅ የሚያደርገው እንደሆነ ሦስቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቱርክ መንግሥት ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ምን እንደሆነና በትምህርት ቤቶቹ ላይ ስላለው አቋም ከትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ሪፖርተር ሞክሮ፣ ጉዳዩን ያውቃሉ የተባሉ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ በመሆናቸው መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

የቱርክ መንግሥት በበኩሉ ከወራት በፊት ከተቃጣበት የመፈንቅለ መንግሥት መከራ ጀርባ በአሜሪካ የሚኖሩትና በመላው ዓለም በርካታ ቱርካውያን ተከታዮች እንዳሏቸው በሚነገርላቸው ሙሐመድ ፌቱላህ ጉለን የሚመራ አንጃ፣ መንግሥቱን በኃይል ሊንድ እንደሞከረ ደጋግሞ ሲገልጽና እንቅስቃሴውንም በአሸባሪ ቡድን እንደፈረጀ ይታወሳል፡፡ በርካቶች የተገደሉበት የግልበጣ መከራውን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ የጉለን ደጋፊዎችና ተባባሪዎች መታሠራቸው ይታወቃል፡፡

የቱርክ መንግሥት ማሪፍ ፋንውዴሽን የተባለውን መንግሥታዊ ተቋም በቅርቡ በመመሥረት ከፌቱላህ ጉለን እንቅስቃሴ ጋር ንከኪ ያላቸውን ትምህርት ቤቶችና ተቋማት ለመተካት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ በኢስታንቡል በተካሄደው የቱርክና የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ወቅትም ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ይህንኑ ጥያቄያቸውን ለአፍሪካ መሪዎች አቅርበው ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶቹን በማሪፍ መተካት ካልተቻለም ተፎካካሪ በመሆን እንዲቀናቀኑ ለማድረግ የቱርክ መንግሥት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሳዑዲ ዓረቢያና በኢስላሚክ ባንክ በኩል ተቀባይነት ማግኘቱም ተሰምቷል፡፡ የአሥር ሚሊዮን ዶላር መዋጮ እንደተደረገለትም የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

ፋውንዴሽኑ መመሥረቱ ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ቢጀምር፣ ምናልባት የኢትዮ-ተርኪሽ ትምህርት ቤቶች የስም ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ፣ ይህም ቱርክ የሚለውን ቃል ከስያሜቸው ሊያነሱ እንደሚችሉ ሚስተር አይዲን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...