– ለተጓተቱ ፕሮጀክቶች ጥፋተኛው ተለይቶ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቢያ ተሰጠ
በአነስተኛ ካፒታል የተቋቋሙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ካፒታላቸውን ለማሳደግ ዕቅድ ተያዘ፡፡ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚቆዩ ነገር ግን በአነስተኛ ካፒታል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ካፒታል በማሳደግ ምርታማነታቸው እንዲጨምር ለማድረግ መታቀዱ ታውቋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትሩ አቶ ግርማ አመንቴ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ አነስተኛ ካፒታል ያላቸውን የልማት ድርጅቶች ካፒታላቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አቶ ግርማ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡
አነስተኛ ካፒታል ካላቸው የልማት ድርጅቶች መንግሥት ጠቀም ያለ ፋይናንስ እንዲያገኙ አድርጎታል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ጎልተው የወጡት የስኳርና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች መዘግየት ናቸው፡፡
እነዚህ ከ15 በላይ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ላይ መንግሥት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢያፈስም፣ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠናቀቃቸው መጠነ ሰፊ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት በርካታ ምክንያቶች ቢነሱም በዋናነት የቀረቡት ግን፣ በቂ ፋይናንስና የመንገድ አውታር ሳይኖር ወደ ሥራ መግባት፣ የቦታ አመራረጥ ስህተትና በተገቢው መንገድ የአዋጭነት ጥናት አለማካሄድ ናቸው፡፡
አቶ ግርማ እንደገለጹት፣ ለእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጠያቂው ማነው በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኖቹ? ወይስ ግንባታውን የሚያካሂዱ ኮንትራክተሮች ናቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡
አቶ ግርማ ጨምረው እንደገለጹት፣ የሚካሄደው ምርመራ ሲጠናቀቅ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘው አካል ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከነባር ስኳር ፋብሪካዎች በተጨማሪ 11 ስኳር ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከአዳዲሶቹ ስኳር ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ በደካማ የሥራ አፈጻጸም ሒደት ውስጥ የሚገኙና እጅግ የተጓተቱ ናቸው፡፡ ከስኳር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳሉ ተብለው የተጀመሩት የማዳበሪያ ፋብሪካዎችም ግንባታ በጣም መዘግየቱ ይታወሳል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በስኳርና በማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ላይ ለታየው ከልክ ያለፈ መጓተት ተጠያቂ አካላት ተለይተው ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡