የግል ባንኮች ወደፊት በሚቀመጥላቸው የጊዜ ገደብ የካፒታል መጠናቸውን ማሟላት የማይችሉ ከሆነ፣ ወደ ውህደት ማምራታቸው የማይቀር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ገለጹ፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ባንኮች እንዲጠናከሩ ከዚህ በኋላ ካፒታላቸውን ማሳደግና አገልግሎታቸውን ማስፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ካፒታል ማሳደግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው የተገለጸላቸው መሆኑን ያስታወሱት ገዥው፣ ከዚህ በኋላ ካፒታላቸውን ምን ያህል ማድረስ እንደሚገባቸው በመንግሥት ውሳኔ መሠረት እንደሚገለጽ አመልክተዋል፡፡ የሚጠበቅባቸውን ካፒታል በምን ያህል ጊዜ ማሟላት እንዳለባቸው ጭምር ከታወቀ በኋላ፣ በዚያ ጊዜ ውስጥ የሚጠቀሰውን የካፒታል መጠን ካላሟሉ እንዲዋሀዱ ሊደረግ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም ለመፍጠር ከተፈለገ ውህደት የማይቀር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተክለወልድ፣ ‹‹አዲስ እየተጠና ያለው ጥናት ከተጠናቀቀና ውሳኔ ከተሰጠው በኋላ ውህደት ግዴታ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ከአገሪቱ ባንኮች አፈጣጠር አኳያ አንዱን ከአንዱ ማዋሀድ እንዴት ይቻላል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተክለወልድ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ እነዚህን የፋይናንስ ተቋማት የሚያውቃቸው እንደ አንድ አትራፊ ሼር ኩባንያ ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት እንዲህ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ተጠናክረው እንዲወጡ ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አንፃር፣ ባንኮች የያዙት ገንዘብም የሕዝብ መሆኑ መታወቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ባንኮች በአሁኑ ወቅት በቁጠባ የሰበሰቡት ገንዘብ ከ467 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የመንግሥትም ሆነ የግል ባንኮች በድምሩ ያላቸው ካፒታል 30 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የካፒታል ገንዘብ ሲቀነስ ቀሪው 437 ቢሊዮን ብር የሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ገንዘብ በተገቢው መንገድ እንዲሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና መንግሥት ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
መንግሥት ወደዚህ ዕርምጃ ሊገባ የሚችለው ግን አዲስ በተጠናው ጥናት መሠረት፣ ባንኮቹ ሊደርሱበት ይገባል ተብሎ የሚወሰነውን የካፒታል መጠን በተቀመጠው ጊዜ ማሟላት ካልቻሉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ባንኮች ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ አለባቸው የተባለ ሲሆን፣ ለዚህ ግን ቀነ ገደብ አልተቀመጠም፡፡ በአዲሱ ጥናትም ባንኮች መድረስ የሚገባቸውን የካፒታል መጠን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ይሁን አይሁን አቶ ተክለወልድ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ሆኖም አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ውህደት ይኖራል ተብሏል፡፡ የውጭ ዜጎች፣ የውጭ ኩባንያዎች፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዲገቡ ሊፈቀድ የሚችል ቢሆንም፣ ጊዜው አሁን አለመሆኑን ከአቶ ተክለወልድ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡