Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት የሥነ ምግባር ደንቡ ቅድመ ሁኔታ አይደለም አለ

ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት የሥነ ምግባር ደንቡ ቅድመ ሁኔታ አይደለም አለ

ቀን:

– መድረክና ሰማያዊ ተሳታፊ ናቸው

– ኢዴፓ ተቃዋሚዎች በቅንጅት እንዲደራደሩ ጥሪ አድርጓል

ኢሕአዴግ ሰላማዊና ሕጋዊ እስከሆነ ድረስ ከየትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፡፡ ከፓርቲዎቹ ጋር የሚደረገው ድርድር ቅድመ ውይይት ረቡዕ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በውይይቱ አካሄድና አጀንዳዎች ላይ ይከናወናል፡፡

- Advertisement -

በምርጫ ሕጉ አፈጻጸም ዙሪያ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት ገዥው ፓርቲንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማወያየት ኃላፊነት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 መሠረት በተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ካልሆኑ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ለማድረግ፣ ኢሕአዴግ ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ ይገልጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 21(9) ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ ሲቀረፅ በልዩ ልዩ ምክንያት ያልተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን የጋራ ምክር ቤቱ የሚያወጣውን የስምምነት ሰነድ መፈረም ይኖርባቸዋል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

በቅርብ በተካሄዱ ምርጫዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ድምፅ ያላቸው መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ ድርድር ለማድረግ ጥሪ በማቅረብ፣ ስምምነቱን አንፈርምም በማለት የምክር ቤቱ አባል ሳይሆኑ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡  

በዚህም መሠረት ኢሕአዴግ የሥነ ምግባር ደንቡን ካልፈረሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ‹‹የሥነ ምግባር ደንብን መፈረም አለመፈረምን ጨምሮ ምንም ዓይነት መሥፈርት አልተቀመጠም፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ለውይይቱ ጥሪ ያደረገላቸው አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለውይይቱ ጥሪ እንደደረሳቸው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡን ሳይፈርሙ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር መቻላቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ፍላጎት ስላልነበረው ነው እንጂ መፈረምና አለመፈረም ያን ያህል ወሳኝ ጉዳይ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡

በቅድመ ውይይቱ የውይይቱ አካሄድና አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ የተገለጸ ቢሆንም፣ ፕሮፌሰር በየነ ግን በውይይቱ ላይ የእርስ በርስ መተማመን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነና በዋነኝነት ለውይይቱ አስፈላጊ የሆነ ምኅዳር ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጅነር) እና በቅርብ በተመረጡት አቶ የሺዋስ አሰፋ መካከል ያለው የይገባኛል ጥያቄ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተመረመረ እንደሚገኝ ሪፖርተር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ ሪፖርተር ከቦርዱ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ይህ በቅርቡ እልባት ያገኛል፡፡

አቶ የሺዋስ ቅድመ ውይይቱን በሚመለከት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በሰማያዊ ፓርቲ ዕይታ ውይይቱ የድርድሩን አካሄድ ለመወሰን፣ ይህም በማን እንደሚመራ፣ መቼ እንደሚካሄድና እንዴት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ለመወሰን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ አቋም ለመያዝ እንደሆነ እንደሚያስቡ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል በመሆን ከኢሕአዴግ ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ዕድል የነበረው ኢዴፓም በቅድመ ውይይቱ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣውና ለሪፖርተር የተላከው የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ፣ ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ፓርቲውን ለውይይት መጋበዙን ያረጋግጣል፡፡

‹‹የኢሕአዴግ የወቅቱ የውይይትና የድርድር ጥሪ ካለፉት የይስሙላ ድርድሮች በተለየ ምን ያህል ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚለው ጥያቄ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ያቀረበውን የወቅቱን የድርድር ጥሪ ኢዴፓ እንደ አንድ በጎ ጅምር በማየት ተቀብሎታል፤›› በማለት በቅድመ ውይይቱ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡

ኢዴፓ በመግለጫው ኢሕአዴግ የሚካሄደው ድርድር እንዳለፉት ድርድሮች ለይስሙላና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡን ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ በሚያስችል ውጤት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እንዲደራደር ጥሪ አቅርቧል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በድርድሩ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተበታተነና ባልተቀናጀ ሁኔታ ከኢሕአዴግ ጋር የሚያደርጉት ድርድር የታሰበውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል ተገንዝበው፣ ድርድሩን በተቀናጀ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል የጋራ ምክክር እንዲያካሂዱም አሳስቧል፡፡

ኢዴፓ ‹‹የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት›› ያለው ሕዝብም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ፓርቲዎቹ በአገራዊ የኃላፊነት ስሜት ለድርድሩ ራሳቸውን እንዲያስገዙ የበኩሉን ግፊትና ጫና እንዲያደርግም ጥሪውን አቅርቧል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...