በግጭት ምክንያት ቀውስ ውስጥ ከገባው ደቡብ ሱዳን በየጊዜው እየፈለሱ የሚገኙ ስደተኞች፣ በጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተሰማ፡፡
ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ብድር የተበደሩ 160 የሚጠጉ ባለሀብቶች በሚገኙበት ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ የስደተኞች ካምፕ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የስደተኞቹም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ በእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጫና እየደረሰ መምጣቱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሀብቶች ገልጸዋል፡፡
በስደተኞች መስፋፋት በደረሰባቸው ጫና ምክንያት የኢንቨስትመንት ሥራቸውን አቋርጠው የወጡና አቋርጠው ለመውጣትም የተዘጋጁ ባለሀብቶች መኖራቸው ተሰምቷል፡፡
ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል አቶ አደገ ንጉሤና አቶ ጌታነህ ጥላሁን ይገኙበታል፡፡ አቶ አደገ በ2002 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ ፑኩሞ ቀበሌ 2,000 ሔክታር መሬት ተረክበው ወደ እርሻ ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡
ለዚህ እርሻ ሥራ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 21 ሚሊዮን ብር ተበድረው ጥጥና የቅባት እህሎችን ሲያለሙ መቆየታቸውን፣ ነገር ግን አዲሱ ኑኝኒያል ስደተኞች ካምፕ የክልሉ መንግሥት በሰጣቸው የእርሻ መሬት ላይ እየተገነባ ስለሆነና፣ በቀረው መሬታቸው ላይም ያለሙት ምርት በስደተኞቹ ጉዳት እየደረሰበት በመሆኑ፣ የደከሙበትን ኢንቨስትመንት አቋርጠው ለመውጣት እያቅማሙ መሆኑን አቶ አደገ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ሕግና ሥርዓት ተጠብቆ የተሰጠ የእርሻ መሬት ላይ የስደተኞች ካምፕ ሊሠራበት አይገባም፤›› ያሉት አቶ ታደገ፣ ‹‹የፌዴራልና የጋምቤላ ክልል መንግሥት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው ሊያዩት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ አደገ እንደሚገልጹት ከአንድ ሺሕ ሔክታር በላይ ጥጥ አልምተዋል፡፡ ስደተኞቹ በጥጥ ማሳ መካከል የሚበቅሉ ዕፅዋትን ለምግብነት ስለሚጠቀሟቸው፣ የጥጥ እርሻ ውስጥ በጥልቀት ስለሚገቡ እርሻቸው እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጥጥ ተክል በብዙ ዓይነት ተባዮች የሚጠቃ በመሆኑ፣ ተባዮቹን ለመከላከል የተለያዩ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ እርሻ ውስጥ ስደተኞች በብዛት የሚገቡ በመሆኑ ጉዳት ሊደርስባቸው ስለሚችል፣ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን መርጨት በማቆማቸው ምርት እያነሰባቸው መሆኑን አቶ አደገ ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት ባለመቻላቸው ላለፉት ሰባት ዓመታት የለፉበትን ሥራ ለማቋረጥ እያሰቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌታነህ የአቶ አደገን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አቶ ጌታነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጋምቤላ ክልል አቦል ወረዳ ጃዊ ቀበሌ 500 ሔክታር መሬት ተረክበው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
አቶ ጌታነህ ከወሰዱት መሬት ውስጥ 200 ሔክታር ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በብዙ ድካም ለእርሻ ሥራ ባስተካከሉት መሬት ላይ የጃዊ ስደተኞች ካምፕ በመገንባቱ ሥራቸውን ጥለው መውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹የደረሰብኝን በደል ለክልሉ ባስታውቅም ምንም ምላሽ አልተሰጠኝም፤›› በማለት፣ አራት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ያፈሰሱበት የእርሻ ኢንቨስትመንት ባዶ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ባለሀብቶች ካሳም ሆነ ተለዋጭ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን ለክልሉ ማስታወቃቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ምላሽ አልተሰጠንም ብለዋል፡፡
በተቀሩት ቦታዎች ላይ የእርሻ ሥራቸውን ለመቀጠል የፀጥታ ሥጋት እንዳለባቸውም አብራርተዋል፡፡
ኢታንግ ልዩ ወረዳ ብቻ ሦስት ካምፖች አሉ፡፡ በዚህ ዓመት በዚሁ ኢታንግ አንድ አዲስ ካምፕ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ‹‹በርካታ ትልልቅ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ነገር ግን ግንባታዎቹ በባለሀብት መሬት ላይ ስለመካሄዳቸው መረጃው የለኝም፡፡ ባለሀብቶቹ ቅሬታውን ለክልሉ ካረቀቡ ግን አጣርተን በአስቸኳይ ምላሽ እንሰጣለን፤›› በማለት የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ከስደተኞች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አቶ ኡቶው አክለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
በጋምቤላ ክልል አራት ትልልቅ የስደተኞች ካምፖች ይገኛሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ግጭት ከመርገብ ይልቅ እየባሰ በመምጣቱ የስደተኞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡
አቶ ኡቶው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር ይጋራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን መረጋጋት የተሳነውና በቀውስ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በርካታ ስደተኞች ወደ ጋምቤላ እየፈለሱ ነው፡፡ ‹‹ጋምቤላ ክልል በአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሩ 306 ሺሕ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የስደተኞቹ ቁጥር ከ300 ሺሕ በላይ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኡቶው ስደተኞች በብዛት እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹የኢፌዴሪ መንግሥት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የፈረመ በመሆኑ ስደተኞችን ይቀበላል፡፡ በእርግጥ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በክልሉ ሀብት ላይ ጫና አሳድሯል፤›› በማለት መፍትሔ የሚሻ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡