Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በ12.2 ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቀድሞ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የኦፕሬሺን ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በትረወርቅ ታፈሰ፣ በመንግሥት ላይ የ12.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

አቶ በትረወርቅ ተጠርጥረው የተከሰሱበትን የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት፣ እ.ኤ.አ ኦገስት 17 ቀን 2012 ግብረ አበር መሆናቸው ተጠቅሶ ሁለተኛ ተከሳሽ ከሆኑትና ካልተያዙት አቶ ወንድወሰን መስፍን ጋር ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ አቶ በትረወርቅ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ወንድወሰን ሥራ አስኪያጅ ለሆኑበት፣ ትራንስ ናሽናል ኮምፒዩተር ከውጭ አገር ለሚያስመጣው “Annual Software Update and License of Support” ለተባለ አገልግሎት፣ በሐሰተኛ ሰነድ የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ኤልሲ) እንዲከፍቱ አድርገዋል፡፡ ኤልሲውን የከፈቱት ‹‹ለኤፌዴሪ ኢኮኖሚና ልማት ሚኒስቴር የሚሰጥ አገልግሎት ነው›› በማለት ያለምንም መጠባበቂያ ገንዘብ የ445,724 ዶላር ነው፡፡

አቶ በትረወርቅ የተጠየቀውን ኤልሲ ከባንኩ አሠራር ውጪ እንዲከፈት በማድረግ፣ ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ ወንድወሰን ደግሞ ለተገለጸው አገልግሎት በተከፈተው ኤልሲ መሠረት ገንዘቡ ለላኪው ባንክ ያላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

አቶ በትረወርቅ በወቅቱ በባንኩ ውስጥ በነበራቸው ሥልጣን መሠረት ገንዘቡ እንዲተካ ወይም እንዲመለስ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ሲገባቸው፣ ባለማድረጋቸው ገንዘቡ ለባንኩ አለመመለሱንም ክሱ ይጠቁማል፡፡ በወቅቱ ከባንኩ የተወሰደው 445,724 ዶላር ወይም በወቅቱ ምንዛሪ 8,456,252 ብር ሲሆን፣ ወለድ 1,534,159 ብር እና የዘገየበት ቅጣት 2,222,166 ብር በድምሩ 12,222,166 ብር መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

በመሆኑም ግብረ አበር ከተባሉት ሁለተኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 33፣ 411 (1ሐ)ንና (2)ን በመተላለፍ፣ የመንግሥትን ሥራ በማይመች አኳኋን መምራትና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሙስና ወንጀል፣ ክስ መመሥረቱን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የክስ ሰነድ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች