Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የካቲት ፐልፕና ወረቀት በ1.9 ቢሊዮን ብር ዘመናዊ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ፋብሪካው ከ70 ከመቶ በላይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ይተካል ተብሏል

ወደ ግል ከተዛወረ ሰባት ዓመታት ያስቆጠረው የካቲት ፐልፕና ወረቀት ማምረቻ ድርጅት፣ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚያስገባ አስታወቀ፡፡

የየካቲት ወረቀት ሥራዎች እህት ኩባንያ የሆነው የካቲት ፐልፕና ወረቀት ማምረቻ ድርጅት፣ ቻይና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተባለው መንግሥታዊ ተቋራጭ ጋር ባደረገው የዲዛይን፣ የግዥ እንዲሁም የግንባታ አጠቃላይ ሥራ ስምምነት መሠረት፣ አዲሱ ማምረቻ ፋብሪካ በዓመት 70 ሺሕ ቶን ልዩ ልዩ ዕቃዎች ማሸጊያ ካርቶኖችንና 15 ሺሕ ቶን ለደብተርና ለልዩ ልዩ ውጤቶች ማምረቻ የሚውል ለስላሳ ወረቀት እንደሚያመርት ይጠበቃል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ዓለሙ ስሜ ማክሰኞ አመሻሹ ላይ በማሪዮት ኤክሲክቲቭ አማርትመንት ሆቴል በተካሄደው የግንባታ ስምምነት ወቅት እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ በየዓመቱ ከ200 ሺሕ ቶን በላይ የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ምርት ፍላጎት አለ፡፡ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ከ2.6 ቢሊዮን ብር ወይም ከ130 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ወጭ እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳ በአገሪቱ 120 ሺሕ ቶን ወረቀትና የወረቀት ምርቶች እንደሚመረቱ ቢገለጽም፣ ከፍላጎቱ አኳያ ፍላጎትን ማሟላት እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ ይልቁንም በአምስት ዓመት ውስጥ የአገሪቱ የወረቀት ምርቶች ፍላጎት መጠን ከ400 ሺሕ ቶን በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በአገሪቱ እየተቋቋሙ ያሉት የወረቀት ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት አልፈው ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ እንደሚጀምሩ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

የየካቲት ወረቀት ሥራዎች የፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለሙ እንደገለጹት፣ በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለው የፋብሪካው ግንባታ፣ በኦሮሚያ ገላን ከተማ በ50 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ በመጀመሪያው የፋብሪካው የግንባታ ምዕራፍ፣ 210 ቶን ጥቅል ወረቀት በቀን ማምረት የሚቻልበት ግንባታ ይካሄዳል፡፡

በምዕራፍ ሁለት ግንባታ ደግሞ 45 ቶን ለስላሳ ወረቀት በቀን ማምረት የሚያስችል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በያመቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን 12 ሺሕ ቶን ደብተር በአገር ውስጥ ለማምረት እንደሚያስችል አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ በምዕራፍ ሦስት ለሚገነባው የፐልፕ ማምረቻ መስመር ግን መንግሥት የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት የሆነውን ምጣጭ (ባጋስ) በተገቢው መንገድ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱ እየተስፋፉ የሚገኙት የስኳር ፋብሪካዎች የባጋስ አቅርቦትን እንደሚያሻሽሉት ጠቅሰው፣ ይህም ሆኖ ተረፈ ምርቱ የሚካሄድበትን የግብይት ሥርዓት ፈር የማስያዝና የግብይት ሥርዓት የመዘርጋት ሚናም የመንግሥት ድርሻ መሆኑን አቶ ዮናስ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ለታደሙት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴና ለሌሎችም ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ዕውን እንደሚሆን የሚጠበቀው ፕሮጀክት፣ ወደ ኬንያ፣ ሱዳን እንዲሁም ወደ ሌሎች ጎረቤት አገሮች በያመቱ ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን እንደሚልክ፣ በአንፃሩም ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስወጡ የነበሩ ምርቶችንም በአገር ውስጥ በማምረት ለመተካት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት 70 ከመቶ ከውጭ በሚመጡ ምርቶች ላይ ተንተርሶ የወረቀትና የወረቀት ምርቶች በማምረት ላይ እንዲገኝ የየካቲት ወረቀት ሥራዎች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐቢብ መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከ2500 ላላነሱ ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል፣ 7000 ለሚደርሱትም መደበኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል የተባለው የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ በያመቱ ከ2.6 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገቢ እንደሚያስገኝም አቶ ሐቢብ ገልጸዋል፡፡

የካቲት የወረቀትና የፐልፕ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት በ1960ዎቹ መጀመሪያ ሰሞን የተመሠረተ ሲሆን፣ እህት ኩባንያው የካቲት የወረቀት ሥራዎች ድርጅትን ጨምሮ በ2002 ዓ.ም. በ47 ሚሊዮን ብር ወደ ግል ተዛውሯል፡፡ ድርጅቱን ከመንግሥት የገዙት አቶ ጎበዝአየሁ ዘርይሁን እና ወ/ሮ ምሥራቅ አየለ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ሁለቱ ባለአክሲዮኖች በትዕዛዙ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ የተባለ ኩባንያም ማቋቋማቸው ታውቋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች