Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአዲስ አበባው ‹‹ዲዛይክ ዊክ››

የአዲስ አበባው ‹‹ዲዛይክ ዊክ››

ቀን:

እሑድ የብዙዎች የእረፍት ቀን እንደመሆኑ በመደበኛ ቀን ከሚለበሱ እንደ ሙሉ ልብስ ያሉ ልብሶች ውጪ ይመረጣል፡፡ ቲሸርት፣ ቱታ፣ ቁምጣ፣ ነጠላ ጫማና ሸበጥ ያደረጉ ሰዎች ከሌላው ቀን ሰከን ባለ መልኩ በከተማዋ ውስጥ ሲዘዋወሩ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ ጥር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ካዛንችስ አካባቢ የሚገኘው ጥላ ማዕከል የተስተዋለውም ተመሳሳይ ድባብ ነው፡፡ ብዙዎች ለሳምንቱ መጨረሻ የሚሆን ቀለል ያለ ልብስ ለብሰዋል፡፡ ስፖርት እንዲሁም ዮጋ ለመሥራት ሰውነታቸውን የሚያፍታቱና በማዕከሉ ስላሉ የተፈጥሮ መዋቢያዎች አገልግሎቶች የሚጠይቁም ነበሩ፡፡

ማዕከሉ ከጤናማ አኗኗር ጋር የተያያዙ በርካታ አማራጮች ያቀርባል፡፡ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሆን ጂምና አትክልት ነክ ምግቦች የሚስተናገዱበት ካፌው ይጠቀሳሉ፡፡ በማዕከሉ የተገኙት ሰዎችም እንደየፍላጎታቸው ከቀረቡለት አማራጮች አንዱን ያከናውኑ ነበር፡፡ በማዕከሉ አንድ ጥግ በጥሞና ዮጋ የሚሠሩ ሰዎች ይስተዋላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማሳጅ የሚደረጉና ጥፍራቸውን የሚሠሩም ነበሩ፡፡ ሰዎች በአንድነት ትኩረት የሰጡ የሚመስለው ግን በማዕከሉ እየተዋወቀ ለነበረው ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ነበር፡፡ በአብዛኛው ከአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች የቀረቡ ሲሆን፣ ለጤናማ አኗኗር ለማዳበር ጤናማ አመጋገብ ያለው ቦታም ተመልክቷል፡፡

በጥላ ማዕከል የተካሄደው በጤናማ አኗኗር ላይ ያተኮረ ዝግጅት ከአዲስ አበባ ዲዛይን ስምንት (ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ) መርሐ ግብሮች አንዱ ነው፡፡ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው የዲዛይን ሳምንት የተጀመረው ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በተለያየ ዘርፍ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች ላይ ያተኮረው የዲዛይን ሳምንት አንዱ ትኩረት ጤናማ አኗኗርን ማስተዋወቅ ሲሆን፣ በጥላ ማዕከል የተገኙ ታዳሚዎች ከአመጋገብ ጀምሮ በአካል ብቃት እንቅስቃሴና ፋሽን ላይ ያተኮሩ ክንውኖች አካሂደዋል፡፡

የማዕከሉ ሼፍ ሕይወት ይመር እንደምትናገረው፣ እንደ ዲዛይን ሳምንት ያሉ ዝግጅቶችን በመጠቀም ስለ ጤናማ አመጋገብ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ‹‹የምናቀርባቸው ምግቦች ቀላል ጨውና ቅመም ያልበዛባቸው ናቸው፡፡ ጁሶቹ ስኳር የላቸውም፡፡ የብዙ ሰው አመጋገብ ጤናማ ስላልሆነ እንደዚህ ዓይነት ምግቦች እናስተዋውቃለን፤›› ትላለች፡፡ ስለጤናማ አኗኗር ሲነሳ መነሻው ጤናማ ምግብና መጠጥ መሆን እንዳለበትም ታክላለች፡፡

ሐሳቧን የሚጋራው የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ሲሞኔ ሊፕሬ እንደሚለው፣ የብዙዎች አኗኗር ዘዬ መስተካከል አለበት ብለው ስለሚያምኑ በሚገኘው አጋጣሚ ሁሉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይሞክራሉ፡፡ ‹‹ጤናማ አኗኗር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከአመጋገብ፣ ውበትን ከመጠበቅና ከአለባበስ አኳያም ይታያል፤›› ይላል፡፡ በዲዛይን ሳምንት ላይ ለተገኙ ታዳሚዎችም ይህን መልዕክት እያስተላለፈ ነበር፡፡

የዲዛይን ሳምንት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ ሁለተኛ ጊዜው ይሁን እንጂ፣ በበርካታ አገሮች ለዓመታት የተካሄደ ዝግጅት ነው፡፡ የዲዛይን ሳምንት በየአገሮቹ መዲና ሲካሄድ ከሚካተቱት ውስጥ ፋሽን፣ ሥነ ጥበብና አኗኗር ዘዬ ይገኙበታል፡፡ በፈረንሣይ ፓሪስና በዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትሷ ዱባይ በየዓመቱ የሚካሄደውን የዲዛይን ሳምንት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአህጉረ አፍሪካ ደግሞ በጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ይካሄዳል፡፡

የኢንተር ዲዛይን ሳምንት መሥራችና ዳይሬክተር መታሰቢያ ዮሴፍ የዲዛይን ሳምንትን ወደ አዲስ አበባ የማምጣት ጥረቷ አምና እንደተሳካ ትናገራለች፡፡ አምና ከዲዛይን ጋር የተያያዙ ጥቂት ዝግጅቶች ለሦስት ቀናት ብቻ ቢካሄዱም ዘንድሮ የመርሐ ግብሮቹን ቁጥር ማሳደግ ተችሏል፡፡ የተሳታፊዎች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ‹‹ዲዛይን ሲባል ብዙዎች ከፋሽን ጋር ብቻ ያያይዙታል፡፡ ዲዛይን ከአልባሳት በተጨማሪ ከምግብ፣ ከቤት ኢንቲርየር ዲዛይንና የከተማ ዕቅድ ጋርም ይያያዛል፤›› ትላለች፡፡ የዲዛይን ጽንሰ ሐሳብ ሁሉንም የማኅበረሰብ አካል ያማከለ በመሆኑ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ቢበራከቱም መልካም ነው ትላለች፡፡

የአዲስ አበባው የዲዛይን ሳምንት በማቆጥቆጥ ላይ ያለ እንደመሆኑ ከሌሎች አገሮች ልምድ ለመቅሰም መሞከሩን ትናገራለች፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ከዲዛይን ጋር ይያያዛል፤›› የምትለው መታሰቢያ፣ እንደ ዱባይ ዲዛይን ዊክ ካሉ ዝግጅቶች ብዙ መማራቸውንም ታስረዳለች፡፡ ሐሳቡን ወደ ኢትዮጵያ ስታመጣው አጋር ድርጀቶች ማግኘት ቀዳሚ ሥራዋ ነበር፡፡ ሐሳቡ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ይህ ቀላል አልነበረም፡፡ ሆኖም ከአምና የዘንድሮው የተሻለ እንደሆነና በቀጣይ ዓመታት ዝግጅቱ የበለጠ ሲታወቅ ደጋፊዎቹ እንደሚበዙ ተስፋ ታደርጋለች፡፡ የዘንድሮው የዲዛይን ሳምንት የሰዎች እንቅስቃሴ የሚበራከትበት ማለትም በገናና ጥምቀት በዓላት መካከል የተደረገው የሕዝቡን ትኩረት ለመሳብ እንደሆነም ትገልጻለች፡፡

የዲዛይን ሳምንቱ የተጀመረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ሕንፃ ግንባታና የከተማ ልማት ተቋም ውስጥ በተካሄደ ዐውደ ርዕይ ነበር፡፡ አምስት የተለያየ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ዲዛይኖቻቸውን ለዕይታ ያቀረቡ ሲሆን፣ ስለ ቦታ አጠቃቀምና የከተማ ዕቅድም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከወቅቱ ልማትና የግንባታ መስፋፋት ጋር በተያያዘ የቦታ አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት? የሚለው ጉዳይም ተነስቷል፡፡

መታሰቢያ እንደምትለው፣ ከቤት አሠራር ጀምሮ በጥቅል የከተማ ግንባታ ላይ የማኅበረሰቡ አስተያየት የሚንሸራሸርበት መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ ‹‹ዋናው የውይይት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው እንደ ማኅበረሰብ ስንነጋገር ነው፤›› ትላለች፡፡ እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው በዲዛይን ሳምንት ከተሳተፉ ተቋሞች አንዱ አዋሽ ወይን ስለሚያካሂደው አዲስ ግንባታ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር መወያየቱን ነው፡፡

አዲስ ግንባታ ለማካሄድ ያቀደው ድርጅቱ፣ ልደታ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በመንገድ ዝርጋታና በሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ውይይት በዲዛይን ሳምንት አካሂዷል፡፡ የአዋሽ ተሞክሮ የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብን በውሳኔ ውስጥ ማሳተፍ ያለውን ጠቀሜታ ለማሳየት እንደረዳቸው መታሰቢያ ትገልጻለች፡፡

የዲዛይን ሳምንን ከፋሽን አንፃር የምትገልጸው የዝግጀቱ ፕሮግራም ማናጀር ናባይት መንግሥተአብ ናት፡፡ እሷ እንደምትለው፣ በሁለት ባለሙያዎች ስለ ፋሽን ፎቶግራፊ ወርክሾፖች ተሰጥቶ ሠልጣኞች ያነሷቸው ፎቶዎች ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡      በፋሽንና በፎቶግራፍ ዘርፍ ያሉ ጀማሪና አንጋፋ ባለሙያዎችም ሥራዎቻቸውን ያሳያሉ፡፡ ሥራዎቻቸውን ከሚያሳዩ መካከል ጂሚ ተመስገንና ሰሎሜ ክፍሉ ይገኙበታል፡፡ የፋሽን ሳምንት እስከ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ስለሚቆይ ሥራዎቹን መመልከትም ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢንቲርየር ዲዛይነሮችን የሚያሳትፍ ዝግጅትም አለ፡፡ የቀስተ ደመና ፍራሽ ፋብሪካ አዲስ ኢንቲርየር ሾውሩም ጉብኝት እንደተካተተም ትገልጻለች፡፡

ከዲዛይን ሳምንት ዓላማዎች አንዱ ጀማሪ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ የሚያስተዋውቁበት መንገድ ማመቻቸት እንደሆነ መታሰቢያ ትናገራለች፡፡ የአዲስ አበባ የዲዛይን ሳምንት ከሌሎች አገሮች የዲዛይን ሳምንቶች ጋር መተሳሰሩም ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በተለያየ የፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩና ጀማሪ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በነፃ ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩ ሲሆን፣ ዕውቅ ባለሙያዎች ግን ይካፈላሉ፡፡

ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ በማሳየት ይበረታታሉ ከተባሉት ጀማሪ ባለሙያዎች በሥነ ጥበብና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቪዲዮ አርትና ሌሎችም የሥነ ጥበብ ዘርፍ ያሉ ሥራዎቻቸውን ያሳዩ ነበሩ፡፡ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያሉ ወጣቶችም የፈጠራ ሥራቸውን እንዲያሳዩ መድረክ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዲፋይፍ የተሰኘው የጌመሮች ስብስብ በቴክኖሎጂው ከተሳተፉት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ ‹‹በጣም አስገራሚ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ሥራቸውን የሚያሳዩበት መድረክ አያገኙም፡፡ እንደ የዲዛይን ሳምንት ባለ ዝግጅት ግን ዕውቅና ያገኛሉ፤›› ትላለች መታሰቢያ፡፡

ተመሳሳይ ዝግጅቶች ሲሰናዱ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሰዎች ባለፈ ሰፊው ማኅበረሰብ ሲሳተፍ አይስተዋልም፡፡ የዲዛይን ሳምንት በታደምንባቸው ቀናት፣ ለምሳሌ ስለ አርክቴክቸርና ሥነ ጥበብ ጉዳይ ሲወሳ በሙያው ካሉት ውጪ ያሉ ተሳታፊዎች ጥቂት ናቸው፡፡ ስለ ጉዳዩ ጥያቄ ያቀረብንላት መታሰቢያ፣ ችግሩ ዝግጅቶቹን በስፋት ካለማስተዋወቅ የመነጨ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ትልቁ ድክመት ሰፊውን ማኅበረሰብ አለመድረስ ነው፤›› በማለት ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ትስማማለች፡፡ የዲዛይን ሳምንትን በማስተዋወቅና የዲዛይን ሐሳብን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ በቀጣይ እንደሚሻሻሉም ታክላለች፡፡

በሌሎች አገሮች ያሉት የዲዛይን ሳምንቶች በተሳታፊ ቁጥርም ይሁን በዝግጅት ዓይነት የተደራጁ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባው የዲዛይን ሳምንት በውጣ ውረድ ካለፉት የዲዛይን ሳምንቶች ትምህርት በመውሰድ በአጭር ጊዜ የሚያድግበት ዕድል  ሊኖረው ይችላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...