ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ በድንጋይ፣ በመካነ መቃብርና በሐውልት ላይ በመጻፍ የሥነ ጽሑፍ ታሪኩ የተጀመረው ግእዝ ቋንቋ፣ ከ1,500 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በብራና መጻሕፍት ላይ ሃይማኖታዊ ድርሳኖችን፣ የዜማና የፍልስፍና፣ የአገርና የሕዝብ፣ የነገሥታትም ታሪክ ሲጻፍበት ኖሯል፡፡ በተለይ በዘመነ አክሱምም ሆነ በመካከለኛው ዘመን በአመዛኙ ከግሪክና ከዐረቢኛ ከተተረጐሙትና በእናት ቋንቋቸው ጠፍተው ከግእዙ ተመልሰው መተርጐማቸው፣ ግእዝ ለዓለም የሥነ ጽሑፍና የነገረ መለኮት ጥናት የራሱን ትሩፋት ማበርከቱን ያመለክታል፡፡ በማሳያነትም መጽሐፈ ሔኖክ ፈሳሊጎስ ይጠቀሳሉ፡፡
ግእዝን ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በላቀ መልኩ ትኩረት በመስጠት በየተቋሞቻቸው እያስተማሩበት እየተመራመሩበት የሚገኙ የአውሮፓና የአሜሪካ፣ የመካከለኛ ምሥራቅ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በግንባር ቀደምትነት የጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች እነሐምቡርግ በርሊን ይጠቀሳሉ፡፡
መሰንበቻውን በካናዳ የሚገኘው የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ከሺሕ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የሥነ ጽሑፍ ክምችት ያለው ግእዝን ማስተማር ጀምሯል፡፡
ትምህርቱን ለማስጀመር የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ፕሮፌሰር ማይክል ገርቨርስ 50,000 ዶላር ሲሰጡ፣ በተመሳሳይ በመድረክ ስሙ ‹‹ዘዊኬንድ›› የሚባለው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬም አበርክቷል፡፡ ፕሮፌሰሩ በተለይ በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን በሚገኘው የጉንዳጉንዶ ገዳም በርካታ ብራና መጻሕፍትን በዲጂታል መልኩ መቅዳታቸው ይታወቃል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ያሉት 200 ብራናዎች ጥቅል ገጽ 35,000 እንደሚደርስ በዘገበው ቶሮንቶ ስታር ዶት ኮም አገላለጽ፣ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የትውፊት፣ የታሪክና የሃይማኖት ዕውቀቶች ያከማቸው ግእዝ ቋንቋን በመማርና በማስተማር የተዘለለውንና ክፍተት ያለበት ታሪክና ዕውቀት ይበልጥ ለማጥናት ያስችላል፡፡
በመጀመሪያው ሴሚስተር አምስት የቅድመ ምረቃና አምስት የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች በሴሜቲክ ቋንቋዎች ጥናት በተካኑት ፕሮፌሰር ሮበርት ሆልምስቴድ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡
የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ዘመን ጥናት ማዕከል ዳይሬክተሯ ሱዛን አክበሪ በባህሎች፣ በንግድና በቋንቋዎች አንፃር ለሚደረጉ ጥናቶች ኢትዮጵያ ዓይነተኛ ቦታ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ከታሪክ አኳያ የአፍሪካን እይታ ለመገንዘብ ግእዝን ማዕከል ያደረገው የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም መከፈቱ ለቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይበጃልም ብለዋል፡፡