Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበውዝግብ የተሸበበው የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ዋዜማ

በውዝግብ የተሸበበው የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ዋዜማ

ቀን:

በአሜሪካ ለፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት መታደም ከምንም በላይ እንደ ክብር ይቆጠራል፡፡ በበዓለ ሲመት ወቅት በሚኖር ዝግጅት ለመዝፈንና ለመዘመር የሚመረጡትም ዝናን ያተረፉና ዕውቅ አርቲስቶች ናቸው፡፡ ከፖለቲከኞች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ እንዲሁም ከጦር ኃይሉ የተመረጡና ጥሪ የተደረገላቸውም ይገኛሉ፡፡ ከ800 ሺሕ እስከ 900 ሺሕ ሰዎች ይታደሙበታል በተባለው ዝግጅት ተገኝቶ መዝፈንም ሆነ መዘመር፣ እንዲሁም ወታደራዊ ማርሽ ማሰማት ክብርና ዝናም ነው፡፡ በበዓሉ የታደሙም፣ በመድረክ የዘፈኑም፣ ወታደራዊ ማርሽ ያሰሙም በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ ‹‹በፕሬዚዳንት … በዓለ ሲመት ተገኝቼ ይህን አድርጌያለሁ…›› ሲሉ ይኖራሉ፡፡

በበዓለ ሲመቱ ለመታደም የማይጓጓና የጥሪ ወረቀት እንዲደርሰው የማይመኝ ታዋቂ ሰውም የለም፡፡ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚደረገው የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ጆን ትራምፕ በዓለ ሲመት ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩ ልማዶች የተለየ ሆኗል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለመታደም የሚጓጓለት ሳይሆን፣ ጥሪ ከተደረገላቸው ታዋቂና ዝነኛ የሚባሉት እንደማይገኙ የገለጹበት ነው፡፡ ፖለቲከኞች በበዓለ ሲመቱ እንደሚገኙ ቢያሳውቁም፣ መድረኩን ያደምቃሉ የተባሉ ዝነኞች ለትራምፕ ባላቸው ተቃውሞ የተነሳ በመድረክ ላለመገኘት ወስነዋል፡፡ በአሜሪካ የቱንም ያህል የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖርም በጥላቻ ታጅቦ አይገለጽም፡፡ ከነልዩነት አብሮ መሥራት፣ በአንድ መድረክ ተገናኝቶ መወያየትና በአንድ ድግስ መካፈል ያለ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. የ2016 ምርጫ አስከትሎ የመጣው ክስተት የተለየ ሆኗል፡፡ ሲኤንኤንም ‹‹ከዚህ ቀደም ከነበሩ የፕሬዚዳንት በዓለ ሲመቶች ታዳሚዎች የተከፋፈሉበት፣ ፍጹም የተለየ፤›› ብሎታል፡፡

ምርጫው ከተከናወነ ከሁለት ወራት በኋላ በፖለቲከኞች፣ በዝነኞችና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጭምር በትራምፕ በዓለ ሲመት መታደም ወይም አለመታደም መከራከሪያ ሆኗል፡፡ በበዓሉ መታደም ለትራምፕ ፖለቲካዊ ድጋፍ ማድረግና የሚያነሱዋቸውን አጀንዳዎች መደገፍ ነው የሚሉ ሲኖሩ፣ በበዓለ ሲመቱ አለመገኘት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርንና የአሜሪካን ዴሞክራሲያዊ ባህል አለመደገፍ ነው የሚሉም ተደምጠዋል፡፡ ትራምፕ ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ከነበሩት ሒላሪ ክሊንተን አንስቶ እስከ ሆሊውድ ዝነኞች ድረስ ያከራከረው በበዓለ ሲመቱ የመገኘትና ያለመገኘት ውሳኔ በመከፋፈል ተደምድሟል፡፡

ቢልና ሒላሪ ክሊንተን በትራምፕ በዓለ ሲመት እንደሚገኙ ካሳወቁት ይጠቀሳሉ፡፡ ሙዚቀኛ ጃን ቻምበርሊን ደግሞ፣ ‹‹በትራምፕ በዓለ ሲመት መገኘትና መዘመር ቤተ ክርስቲያን ለትራምፕ ድጋፍ አላት የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ይፈጥራል፤›› በማለት በበዓሉ እንደማትገኝ አሳውቃለች፡፡ በኅብረ ዝማሬ ተሳታፊ የሆነችው ክርስቲ ብራዛ ግን ትራምፕን ባትደግፍም በበዓሉ በሚኖረው ኅብረ ዝማሬ እንደምትሳተፍ ገልጻለች፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጿም፣ ‹‹በበዓለ ሲመቱ እዘምራለሁ፡፡ ዓላማዬ የሰዎችን ልብ ማራራት ነው፣ ድልድይ በመሆን ልዩነቶችን ማጥበብ ነው፣ ግንኙነትና ጓደኝነትን መፍጠር ነው፤›› ብላ ማስፈሯንም ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ የ‹‹ቶኒ አዋርድ›› ተሸላሚዋ ጄኒፈር ሆሊዴይ ጥሪ ተደርጎላቸው እንደማይገኙ ከገለጹት መካከል ትገኝበታለች፡፡ ድምፃዊ ሆሊዴይ እንደምትገኝ አሳውቃ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ግን ሐሳቧን ቀይራለች፡፡ አድናቂዎቿ በፈጠሩባት ጫና ውሳኔዋን የቀለበሰችው ሆሊዴይ፣ ‹‹በበዓለ ሲመቱ በመገኘት የማቀርበው ዘፈን የግል እምነቴን የሚሽር ነው ብዬ አላመንኩም ነበር፡፡ ዘፈኔ በሁለት ፅንፍ የተሠለፉትን ጎራዎች አንድ የሚያደርግ ብሎም ከተገባበት የፖለቲካ ጥላቻ የሚፈውስ መስሎኝ ነበር፤›› ብላለች፡፡

የትራምፕ ቃለ መሃላ ከተካሄደ በኋላ በዋይት ሐውስ የወታደራዊ ማርሽ ሥነ ሥርዓት የሚኖር ሲሆን፣ በዚህም የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እንዲሁም ጂሚ ካርተር ይገኛሉ፡፡ ሒላሪ ክሊንተንም የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በነበረው ልማድ መሠረት ከሳምንት በፊት የስንብት ንግግራቸውን ያደረጉት ተሰናባች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይታደማሉ፡፡

ከ40 በላይ ዴሞክራቶች በበዓሉ እንደማይገኙ ሲያሳውቁ፣ ትራምፕ ዘረኛ ናቸው ብለው ያመኑም እንደማይታደሙ ተናግረዋል፡፡ የትራምፕ በዓለ ሲመትም በመድረክ ላይ የሚዘፍኑ ዝነኞች እጥረት ሊገጥመው ይችላል ተብሏል፡፡ ሆኖም ትራምፕ ይህ አላሳሰባቸውም፡፡ ዝነኞች ለሒላሪ ክሊንተን ምን አደረጉላት? ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ የፕሬዚዳንት ምርጫዎች ብዙ አከራካሪ ነጥቦች ተነስተው የነበረ ቢሆንም፣ የምርጫ ውጤት ከታወቀ በኋላ አጀንዳዎች ይረግባሉ፣ ሥራዎች ለቀጣዩ ፕሬዚዳንት ይተላለፋሉ፡፡ ዜጎችም ይህንንም ያህል በተመረጡ ፕሬዚዳንቶች ሲወዛገቡ አይከርሙም፡፡ የፖለቲካው ትኩሳትም ሆነ የነበሩ አጀንዳዎች ከበዓለ ሲመት ጋር አይያያዙም፡፡ በአሜሪካ ባህል የሥልጣን ሽግግር በኩርፊያ ሲታጀብም አልተስተዋለም፡፡ ባቀረበው ሐሳብ ያሸነፈ ፖለቲከኛ ከተሸነፈው ጋር አገሩን  ለማሳደግ ይሠራል፡፡ የታሪክ ጸሐፍትም ምርጫን፣ መመረጥንና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን በበዓለ ሲመት ካለመታደም ጋር አቆራኝቶ ፖለቲካ ማድረግ በአሜሪካ ያልተለመደ ክስተት ይሉታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2001 የጆርጅ ደብሊው ቡሽ በዓለ ሲመት ከመከናወኑ አስቀድሞ ብዙዎች ምርጫው ዳግም ቆጠራ እንዲካሄድበት ጠይቀው ነበር፡፡ ሆኖም ቡሽ ዴሞክራቱን ምክትል ፕሬዚዳንት አልጐር በልጠው ነበር የተገኙት፡፡ ውዝግቡ ተጠናቆ የቡሽ በዓለ ሲመት ሲከበር ግን በበዓለ ሲመቱ አልገኝም ያለ ዴሞክራት አልነበረም፡፡ በወቅቱም ቅድሚያ የተሰጠው ‹‹የአሜሪካዊነት ስሜት›› ነበር፡፡ የበዓለ ሲመት ታሪክ አዋቂው ጂም ቤንዳት በበዓለ ሲመት መገኘት የግል ውሳኔ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ በዓለ ሲመቶች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ዝነኞች በመድረክ መገኘታቸውን፣ የታዋቂዋን የሪፐብሊካን ደጋፊ አቀንቃኝ ኢተል መርማን እ.ኤ.አ.  በ1961 የዴሞክራቱ ጆን ኤፍ ኬኔዲ በዓለ ሲመት ላይ መገኘትን በምሳሌ አስታውሰዋል፡፡

ሰላሳ ተማሪዎች በበዓለ ሲመቱ የሚያቀርቡትን ኅብረ ዝማሬ የሚመሩት ቤን መክሊጆን፣ የፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ካለቀ በኋላ በሚኖሩ ዝግጅቶች መሳተፍ ሙያን ለማሳየት እንጂ ፖለቲካውን የመደገፍ ወይም ያለመደገፍ ጉዳይ አይደለም ይላሉ፡፡ ‹‹እኛ ተመራጩ ፕሬዚዳንት አይደለንም፡፡ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ወይም ፖሊሲ አውጭም አይደለንም፡፡ እኛ በሰባት ወይም በ12 ቡድን ተከፍለን፣ ወይም ከትምህርት ቤት መጥተን ኅብረ ዝማሬ የምናቀርብ ነን፤›› ሲሉ፣ በበዓለ ሲመቱ  ላይ መገኘት ወይም አለመገኘት የመደገፍ ወይም የመቃወም ሳይሆን፣ በሙያ የአሜሪካን የሥልጣን ሽግግር ባህል በሰላማዊ መንገድ የማስቀጠል አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

ውዥንብር በበዛበት የበዓለ ሲመት ዋዜማ ከጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት አሜሪካን የሚመሩት ትራምፕ፣ ከበዓለ ሲመታቸው ጎን ለጎን ‹‹አሜሪካን መምራት ይችላሉ? ወይስ?›› በሚለው ጉዳይ ፖለቲከኞችን አከራክረዋል፡፡ አብዛኞቹ አሜሪካውያን ትራምፕ አገሪቱን የመምራት አቅም አይኖራቸውም የሚል ጥርጣሬ ማሳደራቸውም ተዘግቧል፡፡ ሌሎች ደግሞ የትራምፕ የመምራት አቅም የሚፈተነው፣ ባለፈው አንድ ዓመት በምርጫ ቅስቀሳ በነበረው ሒደት ሳይሆን፣ አገር መምራት ከሚጀምሩበት ቀን አንስቶ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ያደረጓቸው ንግግሮችና በተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ ለማድረግ ባቀዷቸው ለውጦች ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ትራምፕ ከአሜሪካ የስለላ ድርጅት ጋር የገቡት እሰጥ አገባ፣ ከሚዲያው ጋር ያላቸው ውዝግብና እምነት ማጣት፣ ለሩሲያ ያላቸው ለዘብተኛ አቋም፣ ከሜክሲኮና ከቻይና ጋር የገጠሙት የንግድ ግጭትና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት ችግር ይሆንባቸዋል ተብሏል፡፡ ትራምፕ ግን በትዊተራቸው አንድ ነገር አስፍረዋል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት መገለጫ ወሬ ብቻ ነው፣ ተግባር የለውም፤›› ብለዋል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ውዝግቦች የተሸበበው ፕሬዚዳንትነት ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ቢነገርም፣ ትራምፕ ላለፈው አንድ ዓመት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ማለፋቸውና ማንነታቸው፣ ዓላማቸውና ፍላጎታቸው ቀድሞ መታወቁ ሌሎች ከእሳቸው ጋር እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ያስተማረ በመሆኑ ችግር ላይሆን ይችላልም ተብሏል፡፡ ትራምፕ በበዓለ ሲመታቸው ዋዜማ ከዚህ ቀደም ያነሷቸው የነበሩ ጉዳዮችን ዳግም ማውሳታቸው በተለይ አውሮፓውያኑን አስቆጥቷል፡፡ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ‹‹እርባና ቢስ ነው፣ ብዙ አገሮችም 28 አባላት ካሉት የአውሮፓ ኅብረት መላቀቅ አለባቸው፤›› ማለታቸው የኅብረቱን አባላትም አነጋግሯል፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድ፣ ‹‹የአውሮፓ ኅብረት ከውጭ ምክር አያስፈልገውም፤›› ሲሉ፣ የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል፣ ‹‹የአውሮፓ ዕጣ ፈንታ በእኛ እጅ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ትራምፕ ከታይምስ ኦፍ ለንደን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንደሌላቸው ፍንጭ ከመስጠታቸውም በተጨማሪ፣ ሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን እንደሚያነሱና በኑክሌር መሣሪያቸው ጫፍ የደረሱት አሜሪካና ሩሲያ የኑክሌር መሣሪያዎቻቸውን እንዲቀንሱ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡

ከመመረጣቸው አስቀድሞም በኔቶና በአባላቶቹ ላይ በቂ መዋጮ አይከፍሉም በማለት የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ የከረሙት ትራምፕ፣ ‹‹የቀድሞዋን ሶቪየት ኅብረት ለመቆጣጠር የተፈጠረው ጥምረት አያስፈልግም፣ ሽብርንም ሲዋጋ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ ሩሲያ በሶሪያ ያላትን የጦር ጣልቃ ገብነት ‹‹አላስፈላጊ፣ በጣም መጥፎና የሰብዓዊ ኑሮን ያመሰቃቀለ…›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ መጪው የአሜሪካ አስተዳደር በካዛኪስታን በሚኖረው በሶሪያ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሶሪያን  ቀውስ ለማርገብ በኦባማ አስተዳደር ከነበረው ጊዜ የተሻለ ትብብርና ፍሬ ያለው ውጤት እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸውም ላቭሮብ ገልጸዋል፡፡

ትራምፕ በኔቶ ላይ ያላቸው አቋም በሩሲያ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ የአውሮፓ መሪዎችን አስቆጥቷል፡፡ በተለይ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ከኅብረቱ መልቀቅ አለባቸው የሚለው በአውሮፓ የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ተብሎ አስተችቷቸዋል፡፡ ተሰናባቹ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ፣ ‹‹ትራምፕ ሥልጣን ሲረከብ በአውሮፓ ላይ የሰነዘረውን ትችት ለማርገብ መሥራት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ዋልተር ስቲንሚየር በኔቶ ላይ የተሰነዘረው ትችት የፖለቲካና የመከላከያ ጥምረቱ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

የጀርመን ምክትል መራሔ መንግሥትና የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሲግማን ጋብሬል፣ ‹‹ትራምፕ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ቢሮ ሲይዝ ከእሱና ከመንግሥቱ ጋር አብረን መሥራትና ዴሞክራሲያዊውን ምርጫም ማክበር አለብን›› ብለዋል፡፡ ትራምፕ የራሳቸው ምልከታ እንዳላቸው የተናገሩት ጋብሬል፣ አውሮፓ በትራምፕ አመለካከት መሸማቀቅ እንደማይገባት፣ ይልቁንም በራስ መተማመን እንደሚያስፈልግ፣ አውሮፓውያን የበታች ሳይሆኑ የራሳቸውን አጀንዳ ወደ ጠረጴዛ ማምጣት የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ትራምፕ ስለ ኔቶ፣ አውሮፓ፣ ንግድና ሌሎች ጉዳዮች የግል አመለካከት አላቸው፡፡ አውሮፓውያን ደግሞ በራሳቸው አመለካከት ሊመኩና ሊተማመኑ ይገባል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው በሚሰጡት አስተያየት ውዝግብ እየፈጠሩ ቢቆዩም፣ አሁን በበዓለ ሲመታቸው ዋዜማ ላይ ሆነው አሜሪካንና ዓለምን ወዴት አቅጣጫ ይዘው እንደሚነጉዱ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...