ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገርና ለመደራደር በጎ ፍላጎት ማሳየታቸው ሰሞኑን ተደምጧል፡፡ በተለይ የአገሪቱን ፓርላማ መቀመጫዎች ከአጋሮቹ ጋር መቶ በመቶ የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ሰላማዊና ሕጋዊ ከሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በሚደረገው ውይይትና አካሄድ ላይ የቅድመ ውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ጥሩ ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ መድረክ ከመጠን በላይ በመዘግየቱና በጣም ብዙ አስከፊ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት መሆኑ የሚገባቸው አገር ወዳድ ዜጎች፣ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ሊቸሩት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለምን ቢባል? ይህች አገር ካሁን በኋላ ሥልጣን በጉልበት የሚቀባበሉባት፣ አሸናፊው ሁሉንም ጠቅልሎ ተሸናፊው ደግሞ በዜሮ የሚወጣባትና በዚህ የተነሳ ግጭት ተቀስቅሶ ሕዝቧ ለጉዳት መዳረጉ በፍፁም እንዲቀር ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች ድርድራቸውን ሲያከናውኑ ሕዝብ ማዕከል እንዲሆን መትጋት አለባቸው፡፡
እንደሚታወቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሚቻለው የዴሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች ማሟላት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አራቱ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች ማለትም ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሚዲያው በሚገባ የሚናበቡበትና እርስ በርስም ቁጥጥር የሚደራረጉበት ሥርዓት ሲኖር በሕዝብ፣ ለሕዝብና የሕዝብ የሆነ መንግሥታዊ ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ ይህ ሥርዓት የሕዝብ ከፍተኛ ተሳትፎና ተጠያቂነት ያለበት ይሆንና የሕግ የበላይነት ይረጋገጣል፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ተቀዳሚው አጀንዳ ይሆናል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ የልሂቃን ስብስብ የፈለገውን ያህል ስለሕዝብ የበላይነት ቢለፍፍ፣ በሕዝብ ስም እየማለ ቢገዘት፣ ከሕዝብ ይሁንታ ውጪ ለሥልጣን ቢሯሯጥ፣ ወዘተ ተፈጥሮው ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ የትም አይደርስም፡፡ ለጊዜው ይሳካለት ይሆናል እንጂ ዘለቄታ አይኖረውም፡፡
ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም የሚቀድም ነገር የለም፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመወያየትና ለመደራደር ሲቀመጡ፣ የድርድሩ የመጨረሻ ግብ የሕዝብ ተጠቃሚነት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለድርድሩ ተዘጋጅተናል ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የድርድር ነጥቦችን ማዘጋጀታቸው እየተደመጠ ነው፡፡ በእርግጥም ለውይይትም ሆነ ለድርድር የተዘጋጀ አካል የራሱን አጀንዳ መቅረፁ ተገቢ ነው፡፡ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዋነኛ ገጽታ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መደራደር መቻል ሲሆን፣ ለዚህም ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የመደራደሪያ አጀንዳቸውን ሲቀርፁ ግን ሕዝብን ማዕከል ስለማድረጋቸው ደግመው ደጋግመው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ከአሁን በኋላ በሕዝብ ስም እየነገዱ የተለያዩ ኃይሎች ወይም ፍላጎቶች ወኪል መሆን፣ ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ ያጨናግፈዋል እንጂ ሕዝብን አይወክልም፡፡ ሕዝብን በተለያዩ መድረኮች ወይም ቤት ለቤት በሚደረግ ቅስቀሳ መድረስ አለመቻል በራሱ ችግር ነው፡፡ ይኼም በመሆኑ ነው ባለፈው ጊዜ የታየው የሕዝብ ቁጣ ከፓርቲዎች ቁጥጥር ውጪ ሆኖ አገሪቱን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠው፡፡ ስለዚህ አሁን ሕዝብ ይቅደም፡፡
የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድሩ ወቅት ከይስሙላና ከታይታ አቀራረቦች መታቀብ አለባቸው፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መደራደር ልዩነቶችን እያጋነኑ በተራ ምክንያቶች ከመፋረስ ያድናል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ቂሞችን፣ ጥላቻዎችን፣ በክፉ መፈላለግና ሌሎች አላስፈላጊ ድርጊቶችን አስወግዶ በቀና መንፈስ መነጋገር ሕዝብን ማክበር ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አጀንዳ ቀርፀው ለድርድር መዘጋጀታቸውን ሲያስታውቁ፣ ከሕዝብ ፍላጎት የሚጣጣም ፍሬ ነገር ይዘው መምጣታቸውን በብርቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ይህ እጅግ በጣም የተከበረ ሕዝብ የሚፈልገው የሚወዳት አገሩ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትመራለት ነው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመለካከትም ሆነ በመሳሰሉት የሚከፋፍሉትንና አገሩን የሚያበላሹትን ሳይሆን፣ ለሕግ የበላይነት ተገዝተው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት የሚያበለፅጉትን ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር የሚጥሩትን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚፈልገው ቁመና ላይ መገኘት የግድ ይላል፡፡ ጊዜ ያለፈባቸውን ንትርኮች ወደ ጎን በማለት በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲና ተቀናቃኞቹ የሚገናኙበት የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ሰላማዊና ለሰጥቶ መቀበል መርህ አመቺ እንዲሆን፣ የበላይነትና የበታችነት አጉል የአስተሳሰብ መንፈስ ሊወገድ ይገባል፡፡ አንዱ ሌላውን እየወነጀለ ወይም እያንኳሰሰ የተለመደው አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት ለማንም አይጠቅምም፡፡ ይልቁንም የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር እንዲከፈትና ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ግንባታ መሠረት ለመጣል፣ ጊዜ ካለፈባቸው ጉንጭ አልፋ ሙግቶችና ጭቅጭቆች ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዘመን ሥልጣኔ ጣሪያውን የነካበት፣ ትውልዱ በአመዛኙ ቀለም የቀሰመበት፣ የሕዝቡ ንቃተ ህሊና በጊዜ ሒደት እየጎለመሰ የመጣበት፣ ወዘተ በመሆኑ በተለመደው አሰልቺ ጭቅጭቅ ጊዜ ማጥፋት ለአገሪቱም ለሕዝብም አይበጅም፡፡ አንዱ ገድሉን የሚያቅራራበት፣ ሌላው ብሶቱን የሚያስተጋባበት መድረክ ከሆነ ውይይትም ድርድርም አይኖርም፡፡ ይልቁንም ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ህልውና ሲባል በሠለጠነና በዘመናዊ አስተሳሰብ መደራደር ያለፈውን አስከፊ ምዕራፍ ለመዝጋት ይረዳል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳልነው ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሴራ ከመጎንጎንና ድክመትን ከመሸፋፈን በመውጣት፣ ሕዝብን የሚያሳምን ተግባር ማከናወን አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ እኔ ብቻ ከሚለው የበላይነት ስሜት ራሱን በማላቀቅ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶችን ብቻ ከማስተጋባትና እርስ በርስ በጠላትነት ከመተያየት አባዜ ተላቀው፣ ለትልቁ ምሥል ኢትዮጵያዊነት ራሳቸውን ያስገዙ፡፡ በትምክህት መወጠርም ሆነ በቁጭት መብሰልሰል ለዚህች አገር ምንም አይጠቅማትም፡፡ ይልቁንም ይህንን የተከበረ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በማስቀደም፣ ውይይቱንም ሆነ ድርድሩን ውጤታማ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለይስሙላና ለታይታ ሳይሆን በተጨባጭ ውጤት የሚገኝበት ይሆን ዘንድ አስፈላጊው መስዕዋትነት ሁሉ መከፈል አለበት፡፡ ወደዱም ጠሉም ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር መራራቃቸውን ማመን አለባቸው፡፡ ከሕዝብ ጋር የሚታረቁት ወይም የሚቀራረቡት ፋይዳ ያለው ተግባር ሲያከናውኑ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስኪረሱ ድረስ በቅርቡ የደረሰውን አደገኛ ክስተት የሚገነዘብ ማንኛውም ዜጋ ይህንን ሀቅ አይስተውም፡፡ አሁን ሕዝብ የሚፈልገው የሚወዳትን አገሩን የሚታደጉለትን ልጆቹን ነው፡፡ ይህ ድርድር በዚህ መንፈስ ሊከናወን ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲደራደሩ ሕዝብን ማዕከል ያድርጉ የሚባለው ለዚህ ነው!