Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአንድ ወይስ ከዚያ በላይ ንጉሥ?

አንድ ወይስ ከዚያ በላይ ንጉሥ?

ቀን:

– የቅጅ መብትና የጋራ አስተዳደር በኢትዮጵያ

በሰብለ ገብረጊዮርጊስ

ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍና ሳይንሳዊ ሥራዎች የአንድ ማኅበረሰብ የጀርባ አጥንት ናቸው። ስለዚህም ነው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ያላቸው ቦታ ከፍተኛ የሚሆነው። በዚህ ረገድ አገራችን የታደለች ናት። ከጥንትም ጀምሮ ብዙ ሥራዎች በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚወጡባት ከመሆኗም ባሻገር ሕዝቧ በዚህ ሉላዊ ዓለም እንኳን የራሱን ሥራ የሚወድና የሚከታተል ነው። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ካላቸው ቦታ አንፃር ለእነዚህ ሥራዎች በሁሉም የዓለማችን አገሮች ማለት ይቻላል ጥበቃ ይደረጋል።

በሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው በሁለት ምክንያቶች ነው። የመጀመርያው የሥራ አመንጪው ሥራውን ለማመንጨት ጭንቅላቱን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱም እንዲሁም በብዙ ሁኔታዎች ገንዘቡን ፈጅቶ ለውጤት የሚያደርሰው በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለትና ከሥራዎቹም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያገኝ ይገባል የሚለው ነው። የሥራ አመንጪው ወይም መብቱ የተላለፈለት ሰው ሥራው በሌላ ሰዎች ጥቅም ላይ ሲውል በፈቃደኝነት ሥራውን በነፃ ካልሰጠ፣ ወይም ሥራው የጥበቃው ጊዜ ካላለፈበት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በቅድሚያም ፈቃድ መስጠት አለበት።

ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም በዘለለ የሥራ አመንጪው ዕውቅና ሊያገኝ ይገባል። የሥራ አመንጪው የኢኮኖሚያዊ መብቱን አሳልፎ ለሌላ አካል ቢሰጥም ባይሰጥም፣ ከሥራው ጋር ያለው ጥልቅና ግላዊ (Personal) ግንኙነት ከግምት ውስጥ ገብቶ ተጨማሪ የሞራል መብቶች በሕግ ይሰጡታል። ሁለተኛው ምክንያት የሕዝብና የአንድ አገር ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብ፣ ትምህርትና ሳይንሳዊ ዕድገቶችን ከማሳለጥና መረጃና ዕውቀትን ከማዳረስ ጋር የተገናኛ ነው። ከዚህ ጋር መረዳት የሚቻለው የቅጂ መብት ሕግ በባህሪው ሁለት ጥቅሞችን ለማጣጣም ታስቦ የሚወጣ የአንድ አገር የውስጥ ሕግ መሆኑን ነው።

በአገራችንም እነዚህ ምክንያቶች ከግምት ውስጥ ገብተው ይመስላል በ1952 ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ በተካተቱት አንቀጾች ጥበቃው ተጀምሯል። ይሁንና ይህ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ጠንካራ ጥበቃ ለማድረግ ባለመቻሉ በ1996 ዓ.ም. የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410 እንዲሻሻል ተደርጓል። የ1996 ዓ.ም. አዋጅ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ሥራዎች ዝርዝር፣ የመብት ዓይነቶችን፣ የጥበቃ ዘመንና ወሰን፣ ገደቦችን፣ መብት የሚተላለፍባቸው መንገዶች በማስፈር እንዲሁም ስለመብት ተፈጻሚነት በመደንገግ በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ጥበብና በሳይንሳዊ መስኮች ለሚወጡ ሥራዎች ጥበቃ እያደረገ ቆይቷል። ይሁና የሥራ አመንጪዎችና ተያያዥ ሰዎች ጥረቶችና ጥቅሞች በበቂ ሁኔታ ከማስጠበቅ አንፃር በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮች አሉ።

ሁላችንም እንደምናውቀው በጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ አብዛኞቹ ሙያተኞች ጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ናቸው ለማለት አይቻልም። ተገቢ ሕክምና ማግኘት አቅቷቸው ዕርዳታ የሚጠይቁ፣ እንዲሁም ሕክምናውን ሳያገኙ የሚሰቃዩና ሕይወታቸው ያለፈ መኖራቸውን እናስታውሳለን። መሰል ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርገው ዝቅተኛ የኢኮኖሚያዊ አቅም ነው። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ። በዋናነት ባለመብቶች ወይም የሥራ አመንጪዎች መብቶቻቸውን ለማስከበር በሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች፣ የሥራ አመንጪው የመደራደር አቅም ዝቅተኛነት፣ ለረጅም ዓመታት ሲሠራባቸው የነበሩ ሕገወጥ ሊባሉ የሚችሉ አሠራሮች፣ እንዲሁም የሕዝቡ የአዕምሯዊ ንብረት አጠቃቀም ግንዛቤ የሚጠቀሱ ናቸው።

የአዋጅ ቁጥር 410/1996 ይዘት ሲገመገም አጠቃላይ ድንጋጌዎችን የያዘና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በቂ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ይሁንና ይህ አዋጅ ከመብቶች አስተዳደር አንፃር የሚታዩበት ክፍተቶች አሉ። ከዚህ ውስጥ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት አመሠራረትና አሠራርን አለመደንገጉ ይገኝበታል። ከ12 ዓመታት በኋላ ቢሆንም ሕጉ ይህን አካቶ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 872/2007 እንዲወጣ ሆኗል። ይህ የሚመሰገን እንቅስቃሴ ሲሆን በኪነ ጥበብና በተያያዥ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ለሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች እጅግ ጠቃሚ ነው። ለመንግሥትም ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከዚህ ባልተናነሰ በተለያዩ ዘርፎች የሚወጡ ሥራዎች ለሕዝብ በቀላሉ፣ በተመጣጣኝ ዋጋና ሕጋዊ በሆኑ መንገዶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ ስለሚያመቻች ተደራሽነትን ያሰፋል። ይኼም የአንድ አገር የፈጠራና የጥበብ መስክ እንዲዳብር፣ እንዲያድግ፣ ሕዝቦችም ምኅዳራቸው እንዲሰፋ እንዲሁም የአገር ባህልና ቅርስ ተጠብቆ እንዲቀጥል ይረዳል።

የጋራ አስተዳደር ማኅበራት በተለያዩ ምክንያቶች አስፈላጊ ናቸው። ይህንንም ከሁለት አቅጣጫ ማየት እንችላለን። በመጀመርያ የመብት ባለቤቶች ሥራዎቻቸው በተለያዩ ቦታዎች ጥቅም ላይ እንዴት ዋሉ የሚለውን በመለየት፣ ተጠቃሚዎቹን በማሳደድና ከሁሉም ተጠቃሚዎች ጋር በመደራደር ፈቃድ ለመስጠት የማይችሉና እናድርግ ቢሉ እንኳን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣቸው በመሆኑ በጋራ ማስተዳደሩ አስፈላጊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ማኅበራት ተጠቃሚዎች ሥራዎችን በአንድ ቦታና በግልጽ በተቀመጡ ዝርዝር ሁኔታዎች የክፍያ መጠን እንዲያገኙ ያደርጋሉ። በመሆኑም የጋራ አስተዳደር ማኅበራት አመሠራረትና አሠራር በአገራችን በሕግ መደንገጉ በጀ የሚባልና ሊበረታታ የሚገባው ነው።

በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ይህ ሥርዓት ከሦስት ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜን አስቆጥሯል። ተግባራቱን ለማከናውንም የተለያዩ አደረጃጀቶች ተፈጻሚ ይሆናሉ። የቅጂ መብት የጋራ አስተዳደር ማኅበራት አደረጃጀቶች የሚያስተዳድሯቸው መብቶችና የባለመብቶቹ ዓይነቶች፣ የሕግ ማዕቀፍ (ከሚመለከተው የመንግሥታዊ አካል ፈቃድ ማስፈለግ አለማስፈለጉ፣ ከአንድ በላይ ማኅበር መፈቀድ አለመፈቀድ (በዘርፉ ወይም በአጠቃላይ በአገሪቱ)፣ የግዴታ ማኅበርና በባለመብቶች ፍላጎት የሚቋቋም ማኅበር መሆን አለመሆኑ፣ መንግሥታዊ የሆኑና የግል ማኅበራት፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚወጡ ሥራዎች ብዛት፣ እንዲሁም በሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ሊለያዩ ይችላሉ። አደረጃጀታቸው ላይ ልዩነት ቢኖርም ዋና ሥራቸው ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለባለመብቶች ጥቅም ማከናወን ነው።

በኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት ማቋቋም በሕግ ተፈቅዷል። የሕጉን ይዘት ስንመረምር በአመሠራረታቸውና በአሠራራቸው ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ልናነሳ እንችላለን። በመጀመርያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን በባለመብቶቹ ስም ሊያስተዳድር የሚፈልግ አካል በኢትዮጵያ ውስጥ ሊቋቋም የሚችለው ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ ነው። ያለቅድሚያ ፈቃድ ይህን ሥራ መሥራት አይቻልም። ይህን ማድረግ ሕገወጥ ተግባር ነው።

በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ማኅበራት የሚቋቋሙት በባለመብቶቹ ይሁንታ ብቻ መሆኑ ነው። ሦስተኛው አንድ ማኅበር ከጽሕፈት ቤቱ ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባው የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ዋናው ማኅበሩን ለመመሥረት በሥራቸው አባላትን የያዙና የተመዘገቡ ሦስትና ከዚያ በላይ የሆኑ የዘርፍ ማኅበራት ስብስብ መሆን ነው። ይህ በብዙ የዓለማችን አገሮች የተለመደ አይደለም። ለምሳሌ በህንድ ሰባትና ከዚያ በላይ እንዲሁም በናይጄሪያ 100 እና ከዚያ በላይ ባለመብቶች አቅፎ የያዘ አካል የጋራ አስተዳደር ማኅበርን ሊያቋቁም ይችላል።

ይሁንና በአብዛኛው በአንድ የመብት ባለቤቶች ወይም የመብት ዓይነቶች ላይ ፈቃድ ያገኘ ማኅበር ካለ ለሌላ ማኅበር ፍቃድ አይሰጠውም። በሌሎች የመብት ወይም የባለመብቶች ዓይነቶች ላይ ማኅበራትን ለማቋቋም የሚፈልጉ ካሉ ግን ይህን ከማድረግ አይከለከሉም። ሌሎች በአዋጁ መሠረት ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የመመሥረቻ ጽሑፍና የውስጥ ደንቦችን ማዘጋጀት፣ የአባላትን ዝርዝር፣ እንዲሁም የአባላት የሥራ ዓይነት መግለጫን ለጽሕፈት ቤቱ ማቅረብ ናቸው።

ይህንን ያሟላ ማኅበር ፈቃድ ሊያገኝ ይችላል። ከምዝገባ በኃላ የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ ሥራዎችንና እንቅስቃሴውን በውስጥ ደንቦቹ፣ በመመሥረቻ ጽሑፉ፣ እንዲሁም በአዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት ማከናወን ይጠበቅበታል። ፈቃድ ከመስጠት ውጪ ጽሕፈት ቤቱ አሠራራቸውን የሚቆጣጠርበት መንገዶች በአዋጁ ተቀምጠዋል። ተግባራቱን ለማከናወን አንድ ማኅበር የሮያሊቲ መጠንና የሮያሊቲ ቀመር አዘጋጅቶ ለጽሕፈት ቤቱ ማቅረብና ማፀደቅ አለበት። ይህ ሮያሊቲን ከመሰብሰቡ በፊት መደረግ የሚገባው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ማኅበር በላይ ያስፈልጋል? አያስፈልግም? የሚለው ጥያቄ የተለያዩ ወገኖችን የሚያከራክር ጉዳይ ሆኗል። ሕጉን ስናይ የተሻሻለው አዋጅ ከአንድ በላይ ማኅበራት እንዲቋቋሙ ይፈቅዳል። የተለመደው አሠራር ከአንድ በላይ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት በአንድ ግዛት ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን፣ ለዚህም በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። የሙዚቃ ሥራን ብንወስድ አቀናባሪዎች፣ የዜማ ደራሲዎች፣ የግጥም ደራሲዎች፣ ድምፃዊያንን እንዲሁም የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሮችን በጋራ ያቀፈ የሙዚቃ ሥራ የጋራ አስተዳደር ማኅበር ይቋቋማሉ። ይህ አሠራር በእንግሊዝ፣ ቻይና፣ ኔፓል፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊድን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ህንድ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ሌሎች በርካታ አገሮች ተግባራዊ ተደርጓል።

በሌላ በኩል የሥነ ጽሑፍ ነክ ሥራዎችን የሚመለከቱ የሪፕሮግራፊክ (የማባዛት) ማኅበራት እንዲሁም የኦዲዮቪዥዋል ማኅበራት፣ ለየብቻቸው ተቋቁመው ይሠራሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም በዚህ ሁኔታ የተዋቀሩ ድርጅቶች በሉዓላዊ አገሮች ውስጥ ለሚሠሩ አባል ማኅበራት ድጋፍ ያደርጋሉ።

ለአገራችን የትኛውን መንገድ ብንከተል ይበጃል? ብለን ስንገመግም የሕዝብ ብዛት፣ የሥራ መጠን፣ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ፣ ሊፈጠር የታሰበው ጥቅም፣ እንዲሁም የሕዝቡ አጠቃቀም ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብተን መሆን አለበት። አገራችን እስካሁን የጥበብ ችግር ወይም እጥረት የለባትም። አብዛኛዎቹን ሥራዎች ወደ አገር ውስጥ የምታስገባና በዚያ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነች አገርም አይደለችም። ሰፊና እያደገ የሚሄድ የሕዝብ ብዛት ያላትና ሕዝቡ የአገር ውስጥ ሥራዎችን በሰፊው የሚጠቀም ነው። በመሆኑም አንድ ዓይነት መብቶች፣ የመብት ባለቤቶች ወይም ተመሳሳይ ዘርፎች በጋራ የራሳቸውን ማኅበር እንዲያቋቁሙ ቢፈቀድ ቀልጣፋ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንድ ማኅበር ብቻ ይኑር ቢባል በተለያዩ የመብት ባለቤቶች መካከል ሊኖር የሚችለውን የጥቅም ግጭት በከፍተኛ ደረጃ ያባብሳል። እንዳንድ የሥራ አመንጪዎች ችላ የተባሉ ወይም ጥቅም የማያገኙ እንዲመስላቸውም ያደርጋል። አንድ ማኅበር የሁሉንም የሥራ አመንጪዎችና ባለመብቶች ጥቅም እኩል ሊያስተዳድር ይችላል ተብሎ ሊገመት አይችልም። ለዚህም በምክንያትነት ሊወሰድ የሚገባው የዘርፎቹ የዕድገት ደረጃ ነው።

ለምሳሌ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ሰፊ ተጠቃሚ ያለውና በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች የሚተላለፍ በመሆኑ፣ ባለመብቶች የራሳቸውን የጋራ አስተዳደር ማኅበር ቢያቋቁምና በዘርፉ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚሳተፉትን ባለሙያዎች እንዲጠቀሙ ቢደረግ ለሙዚቃው ኢንደስትሪ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። በተመሳሳይ በኦዲዮቪዥዋል ዘርፍ የተሰማሩ ሙያተኞች በአንድ ላይ ተሰባስበው የራሳቸውን ጥቅም የሥራው ዓይነትና ፀባይ በሚጠይቀው መንገድ ቢያስተዳድሩ፣ አሁንም ለዚህ ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆናል። አንድ ማኅበር ብቻ ይኑር ቢባል ከሞኖፖሊ ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ተያያዥ ችግሮችን ልብ ይሏል።

ከሁሉም በላይ ከአንድ በላይ ማኅበር ይኑር የሚለውን ሐሳብ አንድነትን እንደሚያፈርስና ከፋፋይ ሐሳብ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ከነባራዊ ሁኔታችን እንዲሁም ይህን መሰል ማኅበራት የማስተዳደር ካለን አቅምና ልምድ አንፃር ተያይዞ ችግሮች እንዳይባባሱ፣ በባለመብቶች ይሁንታ መሠረት የተለያዩ ማኅበራት ቢቋቋሙ የበለጠ ይጠቅማል። በጉዳዩ ላይ የበለጠ ውይይት ማድረግና የተለያዩ ሐሳቦችን ማስተናገድ ሁሉም ለቆመለት ዓላማ መሳካት ጠቀሜታው የጎላ ነው። አዋጪ የሚሆነው በመካከላቸው ጥሩ ግንኝነት ያላቸው ማኅበራት በተለያየ ዘርፎች ስም ማቋቋም ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...