Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርከጥገኝነት ወደ ኃላፊነት

ከጥገኝነት ወደ ኃላፊነት

ቀን:

 በዳዊት ወንድማገኝ (ዶ/ር)

አስከ መቼ በጥገኝነት እንተክዝ? የሰው ልጆች ለመኖር ሌላውን መጠጋት ግዴታቸው ቢሆንም፣ ጥገኝነት የመኖራችን መሠረት መሆኑ የማይቆረቁረን ለምንድን ነው? አሁን አሁን ሳስበው እንደ ብዙ ነገሮች ለምዶብን ይሆን እላለሁ፡፡ ይህን ጽሑፍ የጻፍኩት በሐዘንም በንዴትም አይደለም፡፡ በትካዜ ነው፡፡ ለምን?

የጽሑፉ መነሻ “የኛ” የሚለው የታወቀ የሬዲዮ ፕሮግራም እንግሊዞች ዕርዳታ ሰጪዎች ሐሳባቸውን በመቀየራቸው ምክንያት ዘላቂነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን በዜና መስማቴ ነው፡፡ ስንት ጥሩ ነገር ነው በጥገኝነት ምክንያት የሚቋረጠው ብዬ መተከዝ ጀመርኩ፡፡

- Advertisement -

ለምን ጥገኝነት ነውራችን ሳይሆን ቀረ? ለምን ጥገኝነት ተመቸን? የሚሉትን ጥያቄዎች ብመረምር ምንኛ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን እሱን መመርመር ጥቅም የለውም፡፡ በዚያ ላይ ይህን እንኳን ልመርምር ብል የዚህን ምርምር ወጪ ለመሸፈን ፈረንጅ ፍለጋ መንከራተት ብቻ ሳይሆን፣ ምርምሩንና ሐሳቡን ከዚያም ባለቤትነቱን ፈረንጆች በፈለጉት መንገድ ማስተካከሉን፣ በዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎች አካሄድ እስኪሰለቸን ድረስ የማውቀው ስለሆነ ደክሞኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር ጉዳዩ የጠለቀ ምርምር የሚፈልግ ዓይነት አይመስለኝም፡፡

በ“የኛ”  ፕሮግራም ችግር የምተክዘው በመናደድ ያልሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ ለኛ ማኅበረሰብ የሚጠቅም ሥራን ማገዝ ሲጀመር የፈረንጅ ግዴታ መሆን የለበትም፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የሴት ልጆቻችንን ሕይወት በእርጥባን ላይ ልንመሠርተው አይገባም፡፡ ጥያቄው ፈረንጆች ይህን ለምን አደረጉ ሳይሆን እኛ ለ“እኛ” ምን አደረግን? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መፈተሸ የምፈልገው ሐሳብም ይኸው ነው፡፡ ግን ቢሆንም ስለፈረንጆች አንድ ልጨምር የሆነው የተደገመ የተደጋገመ እንጂ አዲስ አለመሆኑን ለማሳየት፡፡

እኔ በምመራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ውስጥ በርካታ በውጭ ገንዘብ የሚረዱ የምርምር ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ “ኤመራልድ” የተባለ በአውሮፓ ኮሚሽን የሚደገፍ ወይም ለኮሚሽኑ ጥገኛ የሆነ የጥናት ፕሮጀክት ነበረን፡፡ ይህን ፕሮጀክት በኮሚሽኑ አሳሳቢነት በመጀመሪያ ሥራውን ሠርተን ከዚያ በኋላ ገንዘቡን እንደሚከፍሉ ተስማማን፡፡ ፕሮጀክቱ አንድ መቶ ስልሳ አምስት ሺሕ ዩሮ ያህል ከሌላ ተበድረን ከተሠራ በኋላ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኃላፊነት ወስዶ ወደ ካርቱምና ማካራሬ ዩኒቨርሲቲ ለምርምር የላከው ገንዘብ እነዚያ ዩኒቨርሲቲዎች በአግባቡ ስላላወራረዱ በማለት፣ ትልቁ የአውሮፓ ኮሚሽን ትንሹን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንና ትንንሾቹን የምርምር ኃላፊዎች በማጭበርበር ዕዳ ውስጥ ከተተ፡፡ ይህን ለማንም አቤት ማለት አልተቻለም፡፡ ይህን ዓይነት ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ይህን መጠየቅ ለምን አታስጠጉኝም ብሎ ከመበሳጨት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ እንዳውም ፈረንጆቹ የኛኑ ተረት ገልብጠው ‹‹እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች›› የሚሉን ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ወደ ራሳችን ልመለስ እኛ ለ ‘’እኛ’’ ምን አደረግን?

እኔ ‘’የኛ’’ን የምወድበትን ምክንያት ባስረዳ ስለአቀራረቡ ይዘት ብዙ አልልም፡፡ የየኛ ጉልበት ያለው ጭብጡ ላይ ነው፡፡ የሚያነሳው ጭብጥ ሊሰማንና ሊያንገበግበን የሚገባ ማኅበራዊ ቀውስን ስለሆነ ስለሴቶች መገፋት፣ መጎሳቆል፣ መበደል፣ መደብደብ፣ መሞት እንዲሁም የመከራ ሕይወትን እንደዋዛ መግፋት ወንዶችም ሴቶችም ብዙ ብለዋል፡፡ ከማለት የዘለለ ግን ምን ተሠራ? በጣም አጠያያቂ ጥያቄ ነው፡፡

የ‘’የኛ’’ ፕሮግራም የሴቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የሚያነሳው ግን የሴቶችን ጉዳይ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የሴት ልጆች ጉዳይ አይደለም ያልኩት የሴት ልጆች ጉዳይ አንኳር የማኅበረሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የሴቶችን ጉዳይ ችላ የሚል ማኅበረሰብ ራሱን ችላ የሚል ነው፡፡ ሁሉም የሠለጠኑና ከችግር ያመለጡ ማኅበረሰቦች የሚመሳሰሉበት አንድ ቁም ነገር የሴቶችን ጉዳይ አጥብቀው መያዛቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ የተባለና የሚባል ሆኖ፣ በእኛ አገርና ማኅበረሰብ ውስጥ እስካሁን ትርጉም ባለው መንገድ ሊሆን ያልቻለ ነው፡፡ ለምን?

ይህ ያልሆነበት ምክንያት የሴቶችን ጉዳይ አጥብቆ የያዘ እንደ የ‘’የኛ’’ ዓይነት ፕሮግራም በዘላቂነት ማከናወን ስላልተቻለ ነው፡፡ የሚያስፈልገው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ “የኛ” ፕሮግራሞች ሆነው፣ አንዱ እንኳን ችግር ውስጥ መግባቱ ያስተክዘኛል፡፡ እኛ ለ”የኛ” ምን እናድርግ?

የ‘’የኛን’’ ፕሮግራም ስሰማ ብዙ አስባለሁ፡፡ እናቴን አስባለሁ፡፡ እስኪ እናቶቻችንን ለአፍታ እናስብ፡፡ ለዘመናት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እናቶች ያፉበትን ሕይወት እንገምት፡፡ ፊታቸው ላይ የተሰመረው የመከራ መስመር ብዛት ይታየን ይሰማን እስኪ፡፡ እህቶቻችንንና ሚስቶቻችንንም እናስብ፡፡ የእነሱስ መከራ ችላ ሊባል የሚገባው ነው ወይ? ወይስ በደልን እንደ ጥገኝነት ለምደነው ይሆን?

ከሁሉም በላይ ግን ሴት ልጆቻችንን እናስብ፡፡ ሴቶች ልጆቻችን አድገው በእናቶቻችን ቦታ ላይ የተሰመረው የመከራና ሐዘን መስመር በእነርሱ ላይ ሲደገም ዝም ብለን እናያለን ማለት ነው?

  የኛ ፕሮግራም ይህን ለመቅረፍ ከሚያስፈልጉት ድርጊቶች አንዱን ለመፈጸም የሚጥር ስለሆነ፣ ከመውደድ በላይ የማከብረው ፕሮግራም ነው፡፡ አዘጋጆችንም ከማናቸውም በላይ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ስለተወጡ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

አሁን ወደተነሳሁበት የትካዜ ሐሳብ ልመለስ፡፡ ወደ ትካዜ የመራኝ ይህ የተጠናወተን የጥገኝነት አባዜ ነው፡፡ ከጥገኝነት የምንወጣው እንዴት ነው? ሌሎች እንዴት ነው ከጥገኝነት የወጡት? ወይስ እንዴት ነው ለመውጣት እየጣሩ ያሉት?

መቼም የተጠናወተን የቁስ ብቻ ሳይሆን የሐሳብም ጥገኝነት ስለሆነ፣ መፍትሔውንም እንኳን በግድ ከፈረንጆቹ ሠፈር ከተገኙ ሐሳቦች መቃረም ያስፈልጋል፡፡ መሆን የለበትም ይህ ይመስለኛል፡፡ ለዘላቂ የሚጠቅመው ሐሳብ ከየትም ከማንም መውሰድና መተርጎም፡፡ ላነሳ የፈለግኩት ሐሳብ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት (Corporate Social Responsibility) የሚለውን ነው፡፡ ይህ እሳቤ በግርድፉ ሲተረጎም የትኞቹም ማኅበራዊ ተቋማት ማለትም የንግድ፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት ወዘተ ከተቋቋሙበት ዓላማ በተጨማሪ፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ የሆነን ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይን የመደገፍ ግዴታ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ የትምህርት ተቋም ከማስተማር ጋር ያልተያያዘ ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይን መደገፍ አለበት፡፡ አንድ የንግድ ተቋም ከትርፍ ጋር ያልተያያዘ ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይን መደገፍ አለበት፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ አንጋፋ ተቋማት አንድን ማኅበራዊ ጉዳይ ለምሳሌም የሴቶችን ጉዳይ የመደገፍ ኃላፊነት አለበት፡፡ ባንኮችና የኢንሹራንስ መሥሪያ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች ሳይቀሩ ይህን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄ ለምን? የሚለው ነው፡፡ ተቋማት የማያገባቸውን ማኅበራዊ ጉዳይ ለምን ይደግፋሉ? ምን ያገኙበታል? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ መልሱም ቀላል ነው፡፡ ተቋማት ልክ እንደ ግለሰብ ዜግነት አላቸው፡፡ ይህም የኮርፖሬት ዜግነት (Corporate Citizenship) የሚባለው ነው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ የዜግነት መብትና ግዴታ አለባቸው፣ ሊኖርባቸውም ይገባል፡፡ ተቋማት የሚገኙበትን ማኅበረሰብ ሀብት፣ ንብረት፣ ቦታ፣ ጊዜና አካባቢ ይጠቁማሉ፡፡ እያንዳንዱ ተቋም አንድ ግለሰብ ከሚጠቀመው በላይ ማኅበራዊ ሀብትን ይጠቀማል፡፡ ይህ ደግሞ ያለ አንፃራዊ ሁኔታ ሊሆን አይገባም፡፡ ለምሳሌ አንድ ፋብሪካ በምርታማነቱ ለተጠቃሚው ምርትንና ለተቋሙ ጥቅምና ትርፍ የሚያመጣውን ያህል፣ በፋብሪካው ምርት ምክንያት ለሚከተለው የአካባቢ ብክለት ምን አስተዋጽኦ ያደርጋል?

ከማኅበራዊ ግዴታዎች በተጨማሪም ተቋማት የማይመለከታቸውን ማኅበራዊ ጉዳይ የመደገፍ የሞራል ወይም የሥነ ምግባር ግዴታም አለባቸው፡፡ ይህ የሞራል ግዴታ የሚመነጨው ደግሞ የትኛውም ማኅበራዊ ተቋም ጊዜያዊ እንደ መሆኑ ሁሉ፣ ከመጭው ዘመንና ትውልድ የተበደረውን አገርና ሀብት ሲሆን አሻሽሎ አሊያም ባለበት ጠብቆ በማቆየት ነው፡፡

ሦስተኛው የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነት መመንጨት ያለበት ግን ከራሳቸው ከተቋማት ፍላጎትና ድርጊት ነው፡፡ ይህ ከኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት መሠረታዊ እሳቤ ጋር ቢጋጭም፣ እውነቱ ተቋማትም እንደ ግለሰቦች ራስ ወዳድነት ስላለባቸው ለራሳቸው በቀጥታ የማይጠቅምን ጉዳይ መደገፍ ሊተናነቃቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ተቋማት የራሳቸውን ዘላቂ ስኬት በባዶ ማኅበረሰብ ውስጥ ማሳካት ስለማይችሉ ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ተገቢውን ድጋፍ ካልሰጡ፣ በማኅበረሰብ ዘንድ ያላቸው ተፈላጊነትም በአንፃሩ እየጠፋ ስለሚሄድ በማይፈለጉበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር እያዳገታቸው ይመጣል፡፡

በአገራችን የተለያዩ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ንግድ ተቋማት እየተስፋፉ መሄዳቸው የሚደገፍ ሲሆን፣ በአንፃሩ ግን ማኅበራዊ ዕድገታቸው እየቀጨጨና እየሳሳ ወደኋላ ማሽቆልቆሉን ልናስተውለው ይገባል፡፡ በዚህ መነጽር ነው እንግዲህ የእኛን ፕሮግራም ሁኔታ ልንመረምረው የሚገባን፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በአንዲት ሴት ላይ ሁላችንም የማንፈቅደው ጉዳትና መገፋት ሲደርስ፣ ሁላችንም ትንሽ ጊዜያዊ ጩኸት አሰምተን አልፈናል፡፡ እንደ የኛ ዓይነት ፕሮግራም ግን የሴቶችን ጉዳይ ከሥር መሠረቱ ለማጥራት በተከታታይ ሲታትር የሰነበተ ነው፡፡ የእኛ ፕሮግራም የሴት ልጆቻችንን ጉዳይ እንዳይረሳ ቢያንስ በሳምንት ጥቂት ቀናት ከተኛንበት የቸልታ እንቅልፍ ሲቀሰቅስ ቆይቷል፡፡

ሁላችንም ከሴት ተወልደን እየኖርን እንዲህ ዓይነት የሴት ልጆቻችንን የወደፊት ሕይወት ዕጣ ፋንታ ሊቀይር የሚችል ፕሮግራም ስናገኝ ልንደግፈው ይገባል፡፡ ከዚህ የበለጠም ልናደርግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ሴቶች የሚያድጉበት ማኅበረሰብ ለእነዚህ ሕፃናት የሚገባቸውን እንክብካቤ ለመስጠት ካልጣረ፣ እንደ ማኅበረሰብ መሰንበቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህን ማኅበራዊ ቀውስ ለመወጣት ደግሞ ከጥገኝነት ስሜት ወጥተን ወደ ኃላፊነት ስሜት መግባት ግድ ይለናል፡፡ ከዓለማችን ታሪክ የተማርነው አንድ ቁም ነገርም ይኼው ነው፡፡ ለዕድገታችን ኃላፊነትን ካልወሰድን ማደግ አይቻልም፡፡ ይህ መቼም ግልጽ ሐሳብ ይመስለኛል፡፡ ለመረዳት የሚቸግረን ምናልባትም ብዙውን ማኅበራዊ ተቋማት የምንመረምረው ወንዶች ስለሆንን ሊሆን ይችላል፡፡ የ“የኛ’’ ጉዳይ ግን የወንዶችም ጉዳይ ነው፡፡ “ወንዶች” ስል ግን ወንዶች ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በወንድ ስም የሚጠሩ ተቋማትንም በሙሉ ነው፡፡

ሁሉም ማኅበራዊ ተቋማት በወንድ ስም መጠራቱ በራሱ የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ እኒሁ ተቋማትን ማስታወስ የሚሻው ግን ሁሉም ማኅበራዊ ተቋማት የሚኖሩት በሴት የምትጠራ አገር መሆኑንና የሴት ልጆች መሆናቸውን ነው፡፡ በመሆኑም ማኅበራዊ ኃላፊነትን መውሰድ ብቻ ሳይሆን መወጣትም ግዴታቸው ሊሆን ይገባል፡፡

ይህ የጥገኝነት ስሜት ከመንግሥት ላይም ቢወርድ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለ አንገብጋቢ ማኅበራዊ ጉዳይን ለሌሎች እርዳታ አሳልፎ መተው ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ስለሆነ፣ ሌሎች መንግሥታት የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነትን በሕግ ደንግገው ይተገብራሉ፡፡ በእኛ አገር ይህንን የሕግ ተጠያቂነት ማምጣት ለምን አይቻልም? በጥያቄው ውስጥ መልሱ አለ፡፡

በመጨረሻ ግን ወደ ራሴ ልመለስ፡፡ ወደ ራሴ ስል ወደ እያንዳንዱ ግለሰብ ማለቴ ነው፡፡ እያንዳንዳችን እኔ መወጣት ያለብኝ አንድ ማኅበራዊ ኃላፊነት ምንድን ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ በመልሱ ውስጥ አቅማችን ከምናስበው በላይ ምን ያህል የጠለቀና የገዘፈ መሆኑን እንደምንረዳ አምናለሁ፡፡ እስኪ የ“የኛ” ሬድዮን በመደገፍ እንጀምር?!! አመሰግናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...