Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቀኑስ እንዴት ይገፋ?

እነሆ መንገድ! ከሽሮሜዳ ወደ ላይ ወደ እንጦጦ ልንወጣ ነው። ታክሲያችን ውይይት የምትባለዋ ናት። የመንገደኛው ብዛት በአካባቢው አገልግሎት ከሚሰጡ ታክሲዎች ጋር ስለማይመጣጠን፣ ወያላው ጥርሱን እየፋቀ እጁን ኪሱ ከትቶ በወጭና ወራጁ ይደበራል። አንዳንድ እያልን ከተሳፈርነው መሀል ከመሀል ከተማ አካባቢ መጡ አንዳንድ ሰዎች፣ ‹‹ይህቺ ታክሲ አሁንም አለች ወይ ውይይት! ውይይት ቀርቶ እንደ ዛሬ ወሬ ሳይገን የወጣ ድንቅ ስም…›› እየተባባሉ ያዳንቃሉ። ‹‹ቢቻልማ የከተማውን መጓጓዣ ጠቅላላ ውይይት ማድረግ ነበር። ሰው እኮ ሐሳብ ለሐሳብ የመደማመጥና ተከራክሮ የመተማመን ባህሉ ዜሮ ሆነ ማለት ይቻላል፤›› ትላለች አንዲት ወጣት ተሳፋሪ። ‹‹ተወያየን አልተወያየን ደግሞ። ዋናው መወሰን መቻል ነው። ሐሳብን በተግባር መግለጹ ላይ ዳር ቆመን እየተመለከትን ተወያየን አልተወያየን ምን ዋጋ አለው?›› ይላታል ከፊት ለፊቷ አንዱ ኮፍያውን እያስተካከለ፡፡ ‹‹ወይ ጉድ በሕዝብ ተሳፍትፎና ርብርብ አሸባሪ እንጂ አገር ሲለማ አላየንም ስትሉ ብቻ መንግሥት እንዳይሰማችሁ!›› የሚሉን ደግሞ ከበሩ አጠገብ የተቀመጡ ወይዘሮ ናቸው።

‹‹ጠጋ ጠጋ! ሥጋ ያላችሁ ደግሞ ደቀቅ ደቀቅ ያሉትን ብትታቀፉዋቸው ደስ ይለኛል። አዎ ‘ብቻህን አትብላ’ ይላል ቅዱስ ቃሉ!›› በወያላው ድፍረት ተሳፋሪዎች ከመበሳጨት ይልቅ ይዝናናሉ። ‹‹ጭራሽ እንተዛዘልላችሁ? እሱ ነው የቀራችሁ፤›› ሲሉ አንድ አዛውንት፣ ‹‹መቼ ከሰው ይቆጥሩናል። እንኳን እነሱ ሌላው ቢሆን እኮ ግድ እየሆነበት መሄጃ ሲያጣ ነው ቁጥራችንን ጨምሮም ሆነ ቀንሶ የሚቆጥረን። እንጂ እኮ ሰይጣን ሳይቀር እንደ ሰው እያየ የሚያደባብን ያህል ሊጥሉን የሚፈልጉ በስማችን የሚነግዱ ሳይቀሩ ከሰው አይቆጥሩንም፤›› አለች አንዲት ወጣት። ይኼን ጊዜ ወያላው የምፈልገውን ያህል ጠጋ ጠጋ አላላችሁም በሚል ከረር ያለ ውዝግብ አስነሳ። ‹‹የት እንሂድልህ ከዚህ በላይ?›› ሲለው አንዱ ሌላውን ተቀብሎ፣ ‹‹ወይኔ አገሬ! እውነት ይኼን ሕዝብ ወያሎች የሚመሩትን ያህል ሌሎች ይመሩታል?›› ብሎ ይተቻል። ትችቱ እንደተሳካለትና እንዳልተሳካለት ሊያጣራ ዙሪያ ገባውን ይቃኛል። ለምንድነው ግን ዙፋን በተቸን ቁጥር ስቴዲዮም የተሰበሰበ ሕዝብ ጩኸት የምንጠብቀው?

ከስንት ጭቅጭቅና ንትርክ በኋላ ወያላው ሊቀመንበራዊ አቀማመጡን ያዘና ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረች። በትርፍ ሰዓቱና በትርፍ ገንዘቡ ወያላው ገዝቶ የለጠፋቸውን ጥቅሶች በማንበብ ሰው ‘ቢዚ’ ሆኗል። ‹‹መተዛዘን ጠፍቶ ግራ ስንጋባ፣ የስሙኒ እንቁላል ሦስት ብር ከሃምሳ ገባ!›› ብሎ አንድ ተሳፋሪ አንዱን ጽሑፍ ጮክ ብሎ አንብቦልን ሲያበቃ፣ ‹‹ወይ አዲስ አበባ! እንዳልተኖረብሽ፣ አራዳ ለአራዳ ተዛዝኖ እየበላ፣ ዛሬ አደገች ይሉሻል ወንድም ወንድሙ ላይ ቤቱን ሲዘጋ’ ልበል ደግሞ እኔ?›› ሲል ተናገረ። ‹‹ይቅርታ ማስተካካያ መጨመር ይቻላል?›› አንዷ እጇን አወጣች፡፡ ‹‹ይቻላል! የማይቻል ነገር የለም። ካለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲን በአገራችን ማስፈን ይመስለኛል። ቀጥይ እስኪ…›› ተባለች።

‹‹ቤቱን ሳይሆን ኪራይ ቤቱን ቢባል ለማለት ነው። እርስ በርስ እያደር የባሰብን መጨካከንና ራስ ወዳድነት እኮ በተያዘ የራስ በሆነ ነገር ቢሆን ጥሩ ነበር፤›› ብላ ሐሳቧን ግልጽ ሳታደርግ አንዱ ጣልቃ ገብቶ የጨዋታውን መስመር ይቀይሳል። ቁልቁል ወደምናያት መዲናችን እየጠቆመ፣ ‹‹ተመልከቷት እስኪ አዲስ አበባን! ኦ አዲስ አበባ በስምሽ ስንት ታሪክ ተሠራ?›› አለ ሁሉም እየሰማው። ‹‹ያ እዛ ጋ የማያው የሊስትሮ ሳጥን የመሰለ ነገር ምንድነው?›› ወይዘሮዋ አጨንቁረው በመስታወት እያዩ ይጠይቃሉ። ‹‹ኮንዶሚኒየም ነው እማማ!›› አጠገባቸው ነጠላ ተከናንባ  የተቀመጠች ወጣት የስላቅ ሳቅ እየሳቀች መለሰችላቸው። ‹‹በሞትኩት! ይቅር በሉኝ አደራችሁን፡፡ ከዚህ ሲያዩት ስለሚመስል ነው እንጂ ከነጉድ ጉድጓዳችን የቻለንን ኮንዶሚኒየም ልሳደብ አልነበረም፤›› ሲሉ እንደማፈር ብለው ተራ በተራ ቃኙን። ‹‹ኧረ አይዞዎት! ያሻዎትን መናገር ሕገ መንግሥታዊ መብትዎ ነው፤›› ሲላቸው አንዱ፣ ‹‹እሱማ መቼ ጠፋኝ ሕጉን እኖር ብዬ ፅድቁ እንጂ እየጠፋኝ፤›› አሉትና አፋቸውን በነጠላቸው ከለል አድርገው የትዝብት ሳቅ ሳቁ። ቅኔያቸው የገባውም ፈገግ!

እየተጓዝን ነው። ‹‹እኔ ምለው ይህቺ አሮጌ መኪና ይኼን ተራራ እንዲህ ከወጣች ባቡር ያቅተዋል እንዴ?›› አዛውንቱ ናቸው እየጠየቁን ያሉት። ‹‹ኧረ አያቅተውም፤›› አንድ ወጣት መለሰላቸው። ‹‹ታዲያ ለምንድነው ከስንቱ በፊት ተቆርቁራ ዛሬ አዲስ አበባን አዲስ አበባ ያደረገችው ሽሮሜዳ ባቡር ጥሩንባውን እየነፋ ሳያደምቃት ሌሎችን ያደመቃቸው? እንጦጦ ባትኖር ዛሬ አራት ኪሎ ትኖር ነበር?›› አሉ። አጠገባቸው የተቀመጠው ወጣት አለሳልሶ  ያስረዳቸዋል። ‹‹ጊዜው ሲደርስ ከብዙ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት በኋላ ሽሮሜዳ ወደ ቀድሞ ዝናዋና ክብሯ መመለሷን አይጠራጠሩ፤›› አላቸው እንደ መፈክር እያደረገው። ‹‹እኮ በማን ስም ነው አንተ ቃል እየገባህ ያለኸው?›› በተቃራኒው አቅጣጫ የተየሰመ ጎልማሳ አፈጠጠበት። ‹‹በራሴ ነዋ ምነው?››  ልጁ ግራ ገባው።

‹‹ተው እባክህ እኛ የግል ዕጩና የግል ሐሳብ ወንዝ ሲያሻግር አላየንም። ሳይመሽብህ ቶሎ ከአንዳቸው ብትቧደን ይሻልሃል፤›› አለ ጎልማሳው ኮስተር ብሎ። አዛንቱ ጨዋታው ባልፈለጉት አቅጣጫ እንዳያመልጣቸው፣ ‹‹ለማንኛውም…›› ብለው ጣልቃ ገቡ። ‹‹በማንም ስም ተናገርክ አየህ እኛ የሽሮሜዳ ሰዎች ትልቅ ታሪክ ያለን ሰዎች ነን። ምሳሌ ብንሰጥህ ዛሬ የቧንቧ ውኃ ሦስት አራት ሳምንት እልም ብሎ ሲጠፋ ውኃ አይጠማንም። ይኼን ታውቃለህ? የሽሮሜዳን ሰው የቧንቧ ውኃ ለምን አይጠማውም ብለህ ብትጠይቅ እምዬ ምኒልክ ራሳቸው ይጠጡት ከነበረው የንጉሥ ወንዝ ብዙ ዓመት ስለጠጣ ነው መልሱ። እንግዲህ ንጉሥ ከሚሰጠው ውኃ የሚጠጣ ድጋሚ አይጠማም’ ልትለው ትችላለህ። አዎ! ሌላው ዛሬ ፀሐይ እንደምታያት ጨርቃችሁን አውልቃችሁ እርቃናችሁን ካልሄዳችሁ ስትለን የሽሮሜዳ ሰው ጋቢ ለብሶ በቀትር ሲጓዝ ታየዋለህ። ባቡር ከማንም ቀድሞ ለእኔ ስላልተዘረጋ ልማት ላይ የወጣችው ፀሐይ እኔን አትሞቀኝም ብሎ ነው ብለህ በአሸባሪነት እስክትከሰው ድረስ። ይታይህ! ግን ለምን በቀትር ጋቢ ለብሶ ይጓዛል? ካልክ እዚያ እንጦጦ ተራራው ላይ ውጣና መልሱን ድረስበት። የሙቀት ጠላቱ ንፋስ፣ የሥራ እንቅፋቱ ወሬ ሆኖ ታገኘዋለህ። እያሉ ጥቂት አዝናኑን። የአንዳንዱ ሰው ጨዋታ እኮ!

ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። ወያላው ገንዘቡን ትኩረት ሰጥቶ እንደመሰብሰብ ወሬያችን በልጦበት አፍ አፋችንን ያየናል። ‹‹እንካ እንጂ ተቀበል! ሒሳብ ተቀበሉን ስንል በልመና፣ ስሙን ስንል ልመና፣ አገርን ያህል ነገር ግንባታ ይዘው ስለዘነጉት መርቴሎ ስንጮህ ልመና፣ ምንድነው የሚሻለን ግን?›› አለ ጎልማሳው ለወያላው ብሩን እያቀበለው። ይኼን ጊዜ ጋቢናውንና እኛን የሚለየንን መስታወት ተደግፋ ውሽቅ ብላ የተቀመጠች ልጅ እግር አንገቷን ብቅ አድርጋ፣ ‹‹የሚሻለውማ መመነን ነው። የሰው ልጅ ወደመጣበት ወደዛች ኤደን ገነት እስካልተመለሰ ድረስ እዚህ ምድር ላይ ፍትሕ ልትሰፍን አይቻላትም። እውነትም እርቃኗን ሐሰትም የእውነትን ልብስ እንደለበሰች ነገር ሁሉ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፤›› አለችው ጎልማሳውን ከሌሎቻችን ይልቅ እያስተዋለች።

ወያላው ይኼኔ እሷን ሒሳብ አለመቀበሉ ትዝ አለው። ‹‹እሺ አልሰጠሽኝም፤›› አላት በትህትና። ‹‹ምንድነው የምሰጥህ? ወደ ገነት እየሄድኩ ሒሳብ ክፈይ ትለኛለህ? ወደ ክርስቶስ እየሄድኩ ከሽሮሜዳ እንጦጦ የሄድሽበትን ክፈይ ትለኛለህ? እውነት ማን ነው በዚህች ምድር የተጓዘባትን ሜትር የሚመጥን ሐሳብ ሲያወራርድ ያየኸው? ማን ነው? ለእውነት፣ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለሰብዓዊነት ከልባቸው የታገሉና ረጂም ርቀት የተጓዙ የተመለሰላቸው መልስ የተወራረደላቸው ሒሳብ ይመጥናቸዋል? ንገረኛ?›› ስትለው ሁላችንም በልጅነቷ ሁናቴ ደንግጠን እንተያያለን። ‹‹ሴትዮ ፍልስፍናውን አቆይና ሒሳቡን ስጭኝ፤›› ቢል ወያላው እጅግ ተኮሳትሮ የወረደበት ስድብና የእንቢ ባይነት መልስ የማይነገር ሆነ። ከመሀላችን አንዱ፣ ‹‹በቃ እኔ ልቀጣ፤›› ብሎ ወያላውን ዝም ባየሰኘው ኖሮ ብሶት የወለደው የሒሳብ ሥሌት ምን እንደሚያሳየን መገመት ከባድ ነበር። ምነው እንዲህ ሁሉም ነገር ለግምት ከብዶን ውረድ እንውረድ በቁልቁለቱ ሆነብን ነገሩ?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንደኛው ተሳፋሪ ‹‹መንገዱ ነፃ ቢሆን አዲስ አበባ እኮ አሁንም ጠባብ ከተማ ናት!›› ብሎ ወሬ ጀመረ። የወዲያኛው ተቀብሎ፣ ‹‹አንተን የሚገርምህ የከተማው አለመስፋት ብቻ ነው? አስተሳሰባችንና አመለካከታችንስ? ስንት ያልተነካ ስንት ያልተሠራ ሥራ እያለ ልክ እንደ መኪና መንገዱ ጥቂት የሥራ ዘርፎች ላይ መጣበባችንስ?›› ይለዋል። ‹‹የሚያሠራ ሲኖር ነዋ! ሙስና መንገዱን ሁሉ ዘግቶ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በሥራ ተነሳሽነት ስሜታችን ላይ እየተጫወተበት፣ እጠቆር ይሆን እያልን፣ እባልን ፈርተን፣ እታማን ተሳቀን ይኼን ያህልም መታተራችን ሊደነቅ ይገባዋል። ተሳሳትኩ? ምንድነው ‘ፌስቡክ’ ላይ ብቻ ነው ‘ላይክ’ ማድረግ የምትወዱት?›› ብሎ ሁሉም እየሰማው የሚጮኸው አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ ነው። ‹‹ታዲያስ ጉዟችን ረጂም! የምንጠበቀው ሩቅ! ይኼው ግን እንደምትሉት በረባ ባልረባው ተፋፍገን በቢሮክራሲ ጣጣ ተተብትበን በኤሊ ፍጥነት እየተሳብን ‘ከመቆም ይሻላል’ እንላለን፤›› ብላ ቆንጂት አስተያየቷን ሰጠች። ወያላው ወርዶ መንገዱ የተዘጋጋበትን ምክንያት አጣርቶ ሲመጣ፣ ‹‹ግጭት ነው። የሚቸኩል ካለ ወርዶ ማዝገም ይችላል›› ብሎን አረፈው። አብዛኞቻችን የሆዳችንን በሆዳችን ይዘን ወረድን። ትንሽ ብንራመድ ትንሽ ብናሰፋ ምን እንዳይለን? ምንም! ‹‹በነገራችን ላይ እንዲህ የሆድ ሆዳችንን ስናወጋ የሕይወት ማስተዛዘኛ ይሆንልናል፡፡ አለበለዚያ ቀኑም አይገፋ…›› እያሉ ወይዘሮዋ ለብቻቸው ሲናገሩ ሁሉም በየአቅጣጫው ነጎደ፡፡ መልካም ጉዞ!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት