Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ቄራን ከመሀል ከተማ ለማንሳት ብድር ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ቄራን ከመሀል ከተማ ወደ ፉሪ ሐና ለማዘዋወር ከፈረንሣይ ልማት ድርጅት ብድር መገኘቱ ታወቀ፡፡

ሰሞኑን ለሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ መሀል ከተማ የነበረውን የቄራ ድርጅት ወደ ፉሪ ሐና ለማዘዋወር 70 ሚሊዮን ዩሮ ከፈረንሣይ ልማት ድርጅት በብድር መልክ ተገኝቷል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከተቋቋመ 60 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ ቄራው የሚገኝበት ቦታና ሁኔታ ቄራውን ለማደስ አመቺ እንዳልሆነ በሰነዱ ተጠቅሷል፡፡ ቄራው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማይጠቀም በመሆኑ ደረጃውን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በመስጠት፣ ሥጋና ተረፈ ምርቶችን በሚፈለገው መጠን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደማይቻል ተጠቁሟል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ ባለመሆኑም የአካባቢ ብክለት እያስከተለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የሚገነባው ቄራ የኤክስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲሱ ቄራ አምስት ዘመናዊ የእርድ መስመሮች እያንዳንዳቸው 100 ከብቶች በሰዓት የሚያርዱ፣ ሦስት ዘመናዊ የእርድ መስመሮች እያንዳንዳቸው 450 በጎችና ፍየሎች በሰዓት የሚያርዱ፣ እንዲሁም ለእርድ እንስሳት እንክብካቤ አገልግሎት የሚውል በረት እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅም ዘመናዊ የእርድ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የአገሪቱን የወጪ ንግድ የሚያሳድግ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ከፈረንሣይ ልማት ድርጅት የተገኘው 70 ሚሊዮን ዩሮ ብድር የወጭ ድልድል በተመለከተም ለሲቪል ግንባታ፣ ለመሣሪያ አቅርቦት ግዥና ለገጠማ ሥራዎች 95.2 በመቶ፣ ለኢንጂነሪንግ ጥናት፣ ለክትትል፣ ለማማከርና ለአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ ሥራዎች 4.1 በመቶ፣ ለአቅም ግንባታና ለሰው አመራር 0.7 በመቶ እንደሚውል ታወቋል፡፡

በብድር የተገኘው ገንዘብም ወለድ ተፈጻሚ የሚሆነው ዓለም አቀፍ ምጣኔ (Effective Global Rate) መሠረት፣ በየወቅቱ ማስተካከያ በማድረግ እንደሚሆንና ቋሚ የወለድ መጠኑ በዓመት 1.7 በመቶ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድር ገንዘብ ላይም እስከ 0.25 የሚደርስ የግዴታ ክፍያ (Commitment Fee) እንደሚፈጸም በስምምነት ሰነዱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ የተገኘው ብድር የሰባት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ25 ዓመታት ተከፍሎ የሚያልቅ እንደሆነ ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች