Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኒያላ ኢንሹራንስ በኢንዱስትሪው የመጀመርያ የተባለለትን ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኒያላ ኢንሹራንስ በአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመርያ ነው የተባለውን  ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ይፋ አደረገ፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ዘርፍ አሁንም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ይህንን ያስታወቀው ማክሰኞ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ነው፡፡ ኩባንያው በ2009 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 137 ሚሊዮን ብር ማትረፉን፣ ይህ የትርፍ መጠን የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ከገቡበት ካለፉት ከ23 ዓመታት ወዲህ ያልተመዘገበ ከፍተኛ የትርፍ መጠን ነው ተብሏል፡፡

የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ከሚል መሐመድ  የ2009 ሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔ በተመለከተ፣ ‹‹በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያችን በ22 ዓመታት ታሪኩም ሆነ በግል የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪዎች ታሪክ ቀዳሚና እጅግ ከፍተኛ ሪከርድ የሆነ 137 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፤›› በማለት፣ ይህ የትርፍ መጠን ከ2008 ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ59.6 ሚሊዮን ብር ወይም 77 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኩባንያው ከታክስ በኋላም ቢሆን ያስመዘገው የ122 ሚሊዮን ብር የትርፍ መጠን በአገሪቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን፣ የ2009 ሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት መግለጫው አስታውቋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ደግሞ 1,000 ብር ዋጋ ያለውን አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 539 ብር አድርሶለታል፡፡ በቀዳሚው ዓመት የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ 359 ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ  17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2009 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ 1.08 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸው ተገልጿል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ ከታክስ በፊት ያገኘው አጠቃላይ ትርፍ ከአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ 11.24 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑም ታውቋል፡፡

የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው፣ ‹‹በሒሳብ ዓመቱ በኢንዱስትሪው የተመዘገበው የትርፍ መጠን ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም፡፡ ኩባንያው በተከተለው ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራርና አመራር ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ በበኩላቸው፣ ኩባንያው ለዚህ ውጤት ሊበቃ የቻለባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ ብለዋል፡፡

ለአብነት የጠቀሱት ለኢንዱስትሪው ዕድገት ወሳኝ የሆነው የአደጋ ተጋላጭነት ሥጋትን በአግባቡ መያዝ በመቻሉ ነው፡፡ ‹‹ሌላው ቀርቶ አክሳሪ ነው በሚባለው የሞተር ኢንሹራንስ ኩባንያችን አትራፊ ሆኖ የወጣው በዘርፉ ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራር በመከተላችን ጭምር ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

 ከትርፉ ባሻገር ኩባንያው በውል ሥራ እጅግ አመርቂ ውጤት አግኝቼባቸዋለሁ ብሎ የገለጻቸው የሥራ ዘርፎች ከአጠቃላይ መድን 97.14 ሚሊዮን ብር፣ ከሕይወት ዋስትና ደግሞ 26.3 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ የ123.4 ሚሊዮን ብር የውል ሥራ ውጤት (ዓረቦን) የተመዘገበ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ71.1 ሚሊዮን ብር ወይም 136 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

      በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ውስጥ በከፍተኛ መጠን በመናር ላይ ያለውን የካሳ ክፍያ ወጪ ለመቆጣጠር፣ ኩባንያው የተለያዩ አሠራሮችን ማስተዋወቅና መተግበሩ በ2009 ሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንሶ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ መድን 140.8 ሚሊዮን ብር፣ በሕይወት መድን ደግሞ የ179 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 158.8 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ለደንበኞቹ መክፈሉን አስታውቋል፡፡ ይህ የክፍያ መጠን ዓምና ከተከፈለው 176.5 ሚሊዮን ብር በ17 ሚሊዮን ብር ወይም በአሥር በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኒያላ ኢንሹራንስ ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ወይም ከ0.5 በመቶ ያልዘለለ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 17 በሚሆኑ አገር በቀል ኩባንያዎች የሚመራው ይኸው የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አገልግሎቶችንና ምርቶችን በማቅረብ ከአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ይልቅ በዋጋ ሰበራ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ የጋራ ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ እርስ በርስ ደንበኛና ሥራ በመነጣጠቅ የዓለም አቀፋዊ የንግድ ውድድርንና መርህን የጣሰ (Unethical Competition) ጎልቶ የሚታይበት ሆኖ መቀጠሉም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በ2009 በሒሳብ ዓመት የኢንዱስትሪውን አጠቃላይ አፈጻጸም የተመለከቱ መረጃዎች መሠረት ደግሞ፣ በ17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች  7.5 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ጠቅላላ ዓረቦን ገቢ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው የተገኘው ከጠቅላላ መድን ዋስትና ቢዝነሶች ሲሆን፣ ከሕይወት ዘርፍ የተገኘው ዓረቦን ግን 400 ሚሊዮን ብር ወይም አምስት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ የኢንዱስትሪው አጠቃላይ የሀብት መጠን 13.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ጠቅላላ የካፒታል መጠኑ 4.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ጋር ሲወዳደር የ21 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2009 ሒሳብ ዓመት የሀብት መጠኑ 1.05 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን፣ ከቀዳሚው ዓመት በ11.24 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል፡፡  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የኩባንያው የተከፈለ ካፒታሉ 258.4 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ፣ በ34 ቅርንጫፎችና በ11 አገናኝ ቢሮዎች በድምሩ በ45 ማዕከላት አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች