Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅትን የሚተካ ጂኦ ስፓሻል ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅትን የሚተካ ጂኦ ስፓሻል ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

ቀን:

  • ለኢንሳ የተሰጠው ተመሳሳይ ኃላፊነት አልተነሳም
  • የክልል ወሰኖችን የማመልከት ኃላፊነት ይኖረዋል

ላለፉት 74 ዓመታት የተለያዩ መንግሥታትን እያገለገለ የቆየው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅትን የሚተካ፣ የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው፡፡

ኤጀንሲውን የሚያቋቁመው ረቂቅ የሕግ ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅት በ1946 ዓ.ም. ተመሥርቶ የንጉሡን፣ የደርግንና የኢሕአዴግ መንግሥታትን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

የዚህ ተቋም አደረጃጀትና ቁመና ከአገሪቷ አጠቃላይ ልማት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተለይም ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወሳኝ ግብዓት የሆውን የጂኦ ስፓሻል መረጃ ፍላጎት ከማሟላት አኳያ የሚያስችለው ባለመሆኑ፣ በአዲስ አደረጃጀትና ስያሜ እንዲቋቋም ማስፈለጉን ረቂቁ የሕግ ሰነዱ አባሪ ማብራርያ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ በሚል ስያሜ እንዲጠራ ያስፈለገበት ምክንያት፣ ተቋሙ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በአሁኑ የዲጂታል ኢንፎርሜሽን ዘመን ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን በሚል ጥቅል ስያሜ የሚጠሩ በመሆኑና የካርታ ሥራም በዚህ ውስጥ የሚጠቃለል አንድ የሥራ ዘርፍ ብቻ በመሆኑ ነው ተብሎ በማብራርያው ቀርቧል፡፡

‹‹ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን›› ማለት ወቅታዊ ሆኖ በአየር ፎቶግራፍ፣ በቅየሳ፣ በካርታ አነሳስ፣ በሪሞት ሴንሲንግና ጂአይኤስ ዘዴዎች የሚሰበሰብ፣ የሚቀናበርና ለተጠቃሚዎች የሚቀርብ ከጂኦግራፊያዊ ማጣቀሻ ጋር የተዛመደ የቦታ መረጃ መሆኑን ሰነዱ በትርጓሜው አስቀምጦታል፡፡

በመሆኑም አዲስ የሚደራጀው ተቋም በራሱ አነሳሽነትም ሆነ በሌሎች ጥያቄ መነሻነት የጂኦ ስፓሻል መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ማምረት፣ ማከማቸት፣ ማስተዳደርና የማሠራጨት ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ድንበርና የክልል ወሰኖች በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሲወሰኑ በካርታ ላይ ማስፈር፣ እንዲሁም አግባብ ባላቸው አካላት ማለትም፣ የማመላከትና የማስተዳዳር ሥራዎችን በተመለከተ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚሰጥ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ያመለክታል፡፡

አዲስ የሚቋቋመው ኤጀንሲ ወታደራዊና አገራዊ ደኅንነትን በሚመለከቱ የጂኦ ስፓሻል መረጃዎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን የሕግ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ የተቋሙ ተጠሪነት ለኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የጂኦ ስፓሻል መረጃዎችን የመሰብሰበና የመተንተን ሥልጣኑ የሚቀጥል ይሆናል ማለት ነው፡፡

የፓርላማው አባላት ረቂቁን የማፅደቅ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለመሆኑና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ፣ በዝርዝር እንዲያየው የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ አጽንኦት ሰጥቶ እንዲያጣራ ጠይቀዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ረቂቁ ለኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት ተመርቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...