የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢሕገ መንግሥታዊ ነው የሚል ክርክር የቀረበበትን የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ በ13 ድምፀ ተአቅቦ አፀደቀ፡፡
ኢሕአዴግ በሚመራበት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ መሠረት የፓርላማ አባላት ከፓርቲው የበላይ አካል የተሰጡ ውሳኔዎችን መቃወም እንደ ዲስፕሊን ጥሰት የሚቆጠር በመሆኑ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቃውሞ ክርክር ያቀረቡ አባላትና ሌሎችም በተቃውሞ ድምፅ ከመስጠት ይልቅ ድምፅ ተአቅቦ ማድረግን መርጠዋል፡፡ አንድ ረቂቅ አዋጅ በ13 የኢሕአዴግ አባላት ድምፅ ተአቅቦ ሲፀድቅም የመጀመርያው ሊሆን እንደሚችል ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ድምፀ ተአቅቦ የቀረበበት የደን ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ በ2009 ዓ.ም. ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለፓርላማ የቀረበ ሲሆን፣ በረቂቅ አዋጁ ሕገ መንግሥታዊነትና ደረጃውን አለመጠበቅ ቢነሳበትም እስካሁን ከፓርላማው በተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እጅ ማሻሻያዎች እየተደረገበት ቆይቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ማክሰኞ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ግን፣ የፓርላማው አባላት ቀደም ብለው ያነሱትን የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ መመለስ ያልቻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በመሆኑም የፓርላማ አባላቱ በድጋሚ ጥያቄዎቻቸውን በዚሁ ጉዳይ ላይ አንስተዋል፡፡
የተቃውሞ ክርክሩ መነሻ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ከሕገ መንግሥታዊው ድንጋጌ በተቃራኒ፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ሥልጣን ውስጥ ገብቶ የደን ልማትና አስተዳዳር ሥራ እንዲያከናውን የሚፈቅድ አንቀጽ በመያዙ ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱ የተፈጥሮ ሀብቶችን የማስተዳደር ሥልጣን በግልጽ ለክልሎች፣ እንዲሁም ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለፌዴራል መንግሥት መስጠቱን የጠቀሱ የምክር ቤቱ አባላት፣ በዚህ አዋጅ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የተጠሰ ሥልጣንን ወደ ጎን ትቶ እንዲያስተዳድር መፍቀድ ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡
ሕጉን ያረቀቀው አካል በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው ማብራርያ ምንድን እንደሆነ እንዲነገራቸውም ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ረቂቁን ተመልክቶ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረበው ቋሚ ኮሚቴ ግን፣ ከሚመለከታቸው የክልል ባለሥልጣናትና ሕጉን ካረቀቁ የሕግ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቶ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይቃረንም የሚል ምላሽ ስለማግኘቱ እንጂ እንዴት እንደማይቃረን አላስረዳም፡፡
ውይይቱን የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በቂ ማብራርያ እንደተሰጠበት ገልጸው ወደ ማፅደቅ ሲያመሩ፣ እስከ ዛሬ ባልተለመደ መንገድ በርካታ የድምፅ ተአቅቦ እጆች የኦሕዴድ አባላት በሚቀመጡበት ረድፍ በመታየታቸው የፓርላማው ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እንዲቆጥሩላቸው ጠይቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት ረቂቅ አዋጁ በ13 ድምፀ ተአቅቦ ፀድቋል፡፡ ፓርላማው ሌላው ያፀደቀው ረቂቅ አዋጅ የፌዴራል ሠራተኞች አዋጅ ነው፡፡