በአፌ መትረየስ ውስጥ-አነጣጠርኩና-ፊደላት ብተኩስ
ሐረግ ባከታትል-ርእስ ብሰልስ
በምላሴ እርሳስ ላይ-የነጥብን ጥይት-ብለቀው እሩምታ
ዓላማዬ ሰምሮ-አንዷ የቃል ቀለህ-ልብሽን አድምታ
ሳትሞች አንደቆሰልሽ-ደምሽ ፈሶ ሳይያልቅ
ደረስኩልሽና
በአንቀጽ ኮሮጆዬ-ዐረፍተ ነገር-ውኃ መያዣያ
ኮዳዬን ከፍቼ
ከምዕራፍ ሬንጀር- ከዩኒፎርሜ ላይ-ፋሻዬን ቀድጄ
አቆምኩና ደሙን-ማርኬሽ ወስጄ
ግዳይ ጥዬ ፎከርኩ-አንችን ይዤ በእጄ፡፡
ታዲያ ወዲያውኑ
የድርሰት ጦርነት-የውጊያ አልባሳቴን-መሣሪያዬን ሁላ
ሸካክፌ አስሬ-ወርውሬ ጣልኩና-ከድሉ በኋላ
ክፍል ላበጅለት-ምዕራፍ ላወጣ-ታሪኩን ብገልጠው
ለካ ልቦለድ ነሽ- ገፀ ባሕርዬ-ምንሽን ልጨብጠው!?
- ደመቀ ከበደ ‹‹አንድ ክንፍ››፣ (2003)
**********
የዋልጌዎች ፍልስፍና ምንዛሪው ወሬ ብቻ
ለመሪህ ዓሳ ምሶል፣ እሺ ይበልጣል ከሺ የሚባሉት ቃላት በሙሉ የሰነፎች ቢሮክራቲክ ፍልስፍና ምንጭ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰነፍ ዋልጌ ከሥራ አለቆቹ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ሁሉ ‹‹እሺ ጌታዬ ወይም እመቤቴ›› ብሎ እጅ ነስቶ ይቀበላል፡፡ ነገር ግን በተግባር ተፈጽሞ የሚታይ ቁም ነገር የለም፡፡ ወደ አሜሪካ ተሰዶ ሲገባ ግን ባጭር ታጥቆ ለመሥራት ተፍ ተፍ ማለት ይጀምራል፡፡ ለደቂቃ እንኳን ቀና ብሎ ከሰው የሚነጋርበት ጊዜ የለም፡፡ የግል ስልክ ድራሹ አንዲጠፋ ይደረጋል፡፡ ሹክሹከታ እንኳ ክልክል ነው፡፡ ባገራችን ግን ለወሬ ሲባል ብቻ ለማኙ ሁሉ የእጅ ስልክ አለው፡፡ ለወሬ ቀኑ እንኳ አልበቃ ብሎ የዞረ ድምር ሆኖ ወደ ሌሊት ይተላለፋል፡፡ በቢሮ ወሬ በመኪናም ውስጥ ወሬ ብቻ በተለይም በሕዝብ መመላለሻ አውቶብሶችና ሚኒ ባሶች እንደ ጉሊት ገበያ የደራ ወሬ፣ በየፌርማታው በመቆም አውቶብስ ሲጠበቅ ወሬ ብቻ እንጂ አንባቢ በመብራት ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ዛዲያማ ፈረንጅ ‹‹ጥቁር ሕዝብ በተለይ ሀበሻ ምስጢርህን እንዳያውቅብህ ከፈለግህ በመጽሐፍ ጽፈህ አኑረው›› የሚልበት ምክንያት ልክ ነዋ! ምናልባት ግን ትንሽ የተሰፋ ጭላንጭል እንዲኖር ከተፈለገ የጋዜጣና የሬዲዮ መገናኛ ብዙኃን ሳያሰልስ ይህን ሁሉ የተበላሸ ሕይወት ለማስተካከል ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡
ሌላውም አስገራሚ ነገር በታላላቅ አውቶቡስና ሚኒባስ ውስጥ የሚጦፈው የደራ ወሬ ብዛት ነው፡፡ ከዚያ ሁሉ ወሬ ጋር ሾፌሮች ሙዚቃውን አለቅጡ ከፍተው ሻይ ቤት በማስመሰል የሕዝቡን የጆሮ ጅማት የሚበጥስ ድምፅ ማሰማት ይወዳሉ፡፡ ‹‹ቀንሱት›› ሲባሉም እሺ አይሉም፡፡ ነገር ግን ሰሚ የላቸውም፡፡ ሕዝቡም ያውካል የእጅ ስልኩ ያቃጭላል፡፡ በውጭ ዓለም በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካና ጃፓን ግን ይህ ዓይነቱ አሠራር በጣም አስነዋሪ ስለሆነ በሕግ ያስቀጣል፡፡ የማኅበረሰባችን ሒደት ከብልጽግና ይልቅ ወደ ባሰ ፍጹም ድህነትና ጉስቁልና የሚመራ ነው፡፡ ወደ ሥልጣኔ ደረጃ መሸጋገሪያው ድልድል ከሰማይ የራቀና እስከ መጨረሻ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኗል፡፡ ይህን አለመታደል ነው፡፡ ‹‹ለወሬ የለም ፍሬ ላበላ የለው ገለባ›› ይባላልና ነው፡፡ ይህን ሐቅ መናገር እንደ ድፍረት ይቆጠር ይሆን? አንባቢዎች ፍረዱ!
- መጋቤ አዕላፍ መክብብ አጥናው፣ ‹‹ሁለገብ ትምህርት ሰጭ የአዕምሮ ማዝናኛ›› (2005)
******
ትርጉም ላለው ሕይወት
ስኬታማ መሪ ለመሆን ሁለንተናዊ ዕውቀትን ይጠይቃል፡፡ በመሪነት ዙሪያም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ ስኬታማ መሪዎች አንባቢዎች ናቸው፡፡ «They are Leading by Reading» አእምሮአቸውን ሁልጊዜ በማንበብ ያበለፅጋሉ፡፡ ግንዛቤያቸውን በማስፋት የመሪነት ብቃታቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ስለሚያነቡ ነገሮችን ሰፋ ባለ መልኩ የማየት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ማንበብ እውቀት ይጨምራል፡፡ የሚያነብ መሪ መምራት አያስቸግረውም «To Day A Reader Tomorrow a Leader» የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ስኬታማ መሪዎች የሌሎች መሪዎችን ታሪክ ያነባሉ፡፡ የስኬታማነታቸውን ሚስጢር በማወቅ ራሳቸውን ያስተካክሉበታል ይማሩበታል፡፡ ስኬታማ መሪዎች ማንበብ ያፈቅራሉ፡፡ «The Best Leaders Love to Read» ማንበብ ራዕይን ያሰፋል፡፡ የተሻሻሉ ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ ያግዛል፡፡ ጠቃሚ አጋጣሚዎችን ለመለየት ያግዛል፡፡ ስኬታማ መሪዎች በማንበብ የፈጠራ ችሎታቸውን ያዳብራሉ፡፡ በራሳቸው የመተማመን ምንጩም እውቀታቸው ነው፡፡ የዘመኑን የመሪነት እውቀት ለመካን ሳያለሰልሱ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ መጽሔት፣ ጋዜጣ መጽሐፍ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶች በማንበብ አቅማቸውን ይገነባሉ፡፡ እንደ ቻይናውያን አባባል «Something is Learned Every Time a Book Opened» በማንበብ እውቀትን ማስፋፋት ይቻላል፡፡ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ስኬታማ መሪዎች ከማንበብ ውጭ ሕይወት የላቸውም፡፡
- መስፍን ባንታየሁ (ዶር.) “መሪነት” (2000)
********
‹‹ሌባና ውሻ በትር አያስመርረውም››
የሰው ገንዘብ ስፈልግ ዘዴ ብዬ የያዝሁት ባያዩኝ መስረቅን፣ ቢያዩኝ መሳቅን፣ ብችልም ታግዬ ሲሆን ገድዬ፣ ባይሆንም ማምለጥን ነበርና፤ ሁልጊዜ የታለልሁበት ይህ ዘዴ ዛሬ ከመዓት ላይ ጣለኝ፡፡ ነገር ግን ሞቱ ለእኔም ለእናንተም ደግ አይደለምና እንዳትገድሉኝ፡፡ ብትገድሉኝ ደሜን የሚበቀሉ መሰሎተ አሉኝ፡፡ ይልቅስ ከፍልጡና ከዱላው ይህንም ከመሳሰለው ከርግጫውና ከክርኑ ከጥፊውም ጨማምሩልኝና ወደ ሥራዬ ልሒድ አላቸው፡፡
ማን አለህና ዱላህን ቀምሰህ በፍልጥ ቀልጠህ በጥፊ ተወልውለህ ገና ወደወህን ቤት ትገባለህ ብለው ቢያስፈራሩት ዛረስ ከወህኒ ቤት አገባችሁኝ፡፡ የደንቡን ተቀጥቼና ታስሬ ከተፈታሁ በኋላ የናንተ መግቢያ ወዴት ይሆን? የማለት ዛቻ ቢዝትባቸውና በእጃቸው ወድቆ ሳለ ኋላ የተነሳሁ እንደሆነ የማለት ጉራ ቢነዛባቸው ገና ለገና ሳይሆን አይቀርም በማለት ሐሳብ ገባቸውና ሁለተኛ አይልመድህ ብለው ያንኑ ምሱን አቅምሰው ለቀቁት፡፡ መልቀቃቸው ደግ አልሆነም፤ ሌባና ውሻ በትር አያስመርረውም፡፡
- ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› (መጋቢት 22 ቀን 1935 ዓ.ም.)
***
ውጤታማ መሣሪያን ላለማጣት
በቅርቡ የሰው ቤት እየሰበሩ በመዝረፍ ወንጀል ስለታሠሩት ሁለት ስኮትላንዳውያን ሰምታችኋል? የተያዙት የአንዱን ቤት መስተዋት የሰበሩበትን ጡብ ረስተው በመሄዳቸው ተመልሰው ሊወስዱ ሲሞክሩ ነው፡፡
- አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)