Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለቅርሶች ጥበቃ ተስፋ የተጣለበት ዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት

ለቅርሶች ጥበቃ ተስፋ የተጣለበት ዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት

ቀን:

‹‹ካልቸራል ሔሪቴጅ ኢንቨንተሪ ማኔጅመንት ሲስተም (CHIMS)›› በመባል የሚታወቀው የባህላዊ ቅርሶች የምዝገባና ቁጥጥር ሥርዓት፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በቅርቡ ይፋ ያደረገው ዳታቤዝ ነው፡፡ ቅርሶች በዲጂታል መንገድ የሚመዘገቡበት ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረውን በእጅ ጽሑፍ የመመዝገብ (ማንዋል) አሠራር ያስቀራል ተብሏል፡፡ ዳታቤዙ በየክልሉ ያሉ ቅርሶች ተመዝግበው የሚቀመጡበት በመሆኑ፣ በቅርስ መዝጋቢዎች፣ ገምገሚዎችና አፅዳቂዎች የሚሞላ ፎርም ያካትታል፡፡ ተንቀሳቃሽ፣ የማይንቀሳቀስ ወይም የማይዳሰስ ቅርስ ለመመዝገብ ሲቀርቡ፣ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች መካተታቸው እስከሚረጋገጥ በተጠባባቂነት የሚቀመጡበት የዳታቤዙ ክፍል አለ፡፡

አንድ ቅርስ ከተመዘገበ በኋላ፣ ስለ ቅርሱ ምንነት፣ መገኛና ሌሎችም መረጃዎችን ያካተተ ክፍል በዳታቤዙ ተካቷል፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዋነኛነት የሚቆጣጠረው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ በየክልሉ ያሉ ቢሮዎች ደግሞ ቅርሶቻቸውን መዝግበው ያስተላልፋሉ፡፡ ከቅርሶች ደኅንነት ጥበቃ አንፃር ሁሉም መረጃ ይፋ ባይሆንም፣ የተመዘገቡት ቅርሶች ለተመራማሪዎችና ለሕዝቡም በድረ ገጽ ተደራሽ ይሆናሉ፡፡

 

- Advertisement -

ሰዎች የቅርሶችን መጠሪያ ስም አልያም ዓይነታቸውን በመጻፍ ከዳታቤዙ ስለ ቅርሶች መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ቅርሶቹ የሚገኙበትን ቦታ በካርታ ያሳያቸዋል፡፡ ቅርሶቹን አደጋ ላይ የማይጥሉና ማንኛውም ሰው ሊያውቃቸው የሚችል መረጃዎች ያቀርባል፡፡ ሰዎች ስለ ቅርሶቹ አስተያየት የሚሰጡት ክፍልም አለ፡፡

ባለፉት ዓመታት ቅርሶች ይመዘገቡበት የነበረውን ሒደት ያዘምናል የተባለው ዳታቤዝ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶችን ሁኔታ የሚጠቁም ክፍል አለው፡፡ ስለ ቅርሶቹ ተጨማሪ መረጃ መስጠት ሲያስፈልግ አልያም በቅርሶቹ ዙሪያ ሪፖርቶች ሲቀርቡም ይካተታሉ፡፡ ዲጂታል አሠራሩ፣ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶች ከመለየት ባሻገር፣ የቅርሶችን ሕገወጥ ዝውውር ለመቆጣጠር እንደሚጠቅም የሚናገሩት፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ቁጥጥርና ደረጃ ምደባ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አበራ አንጁሎ ናቸው፡፡

የቅርስ ዘረፋ መቆጣጠርን አዳጋች ካደረጉ መሰናክሎች መካከል፣ ቅርሶች በተገቢው መንገድ አለመመዝገባቸው ይገኝበታል፡፡ የትኛው ቅርስ፣ በየቱ አካባቢ እንደሚገኝ በአግባቡ አለመታወቁ፣ በጥበቃ ረገድ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት እየተሠራ የነበረውና በዚህ ዓመት በክልል ከተሞች ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀው ዳታቤዝ ለዚህ መፍትሔ እንደሚሆን አቶ አበራ ይናገራሉ፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት አንድ የውጭ አገር ድርጅት ተመሳሳይ ሶፍትዌር ቢያዘጋጅም፣ ከአገሪቱ የቅርስ ምዝገባ መስፈርቶች ጋር በማይጣጣም መልኩ በመቅረቡ ውጤታማ አልሆነም፡፡ ሶፍትዌሩ በሐረር ከተማ በተወሰነ ደረጃ በተግባር ቢውልም፣ በሌሎች አካባቢዎች ሳይስፋፋ መቋረጡን ይናገራሉ፡፡

 

 

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አይሲቲ ዳይሬክተር ዘለዓለም ወጋየሁ እንደሚናገሩት፣ 1.2 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሶፍትዌር፣ በማዕከላዊነት በመሥሪያ ቤቱ ቢቀመጥም፣ በሁሉም ክልሎች ይተገበራል፡፡ ለመነሻነት በአማራ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋና ሐረር የሚተገበር ሲሆን፣ ለየክልሉ ባለሙያዎች ሥልጠና የመስጠትና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሒደት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ ቅርስ የሚመዘገብበትን መስፈርት በመጠቀም በማንዋል ይሠራ የነበረውን ዲጂታይዝ አድርገናል፡፡ ሁሉም ክልሎች በቀጥታ በዳታቤዙ ቅርሶች እየመዘገቡ፣ መረጃው በማዕከላዊነት በባለሥልጣኑ ይከማቻል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በማንዋል የተመዘገቡ ቅርሶችን ወደ ዳታቤዙ የማስተላለፍና ከዚህ በኋላ የሚገኙ አዳዲስ ቅርሶችን በዲጂታል መንገድ የማከማቸት ሥራ እንደሚጠብቃቸውም ያክላሉ፡፡

አቶ አበራ እንደሚሉት፣ ኤክሲድ የተባለ የሶፍትዌር ድርጅት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ምደባ ክፍል በሥራው ተሳትፈዋል፡፡ ‹‹ቅርሶችን በአንድ የመረጃ ቋት በሳይንሳዊ መንገድ በመመዝገብ የቅርሶቹን ብዛትና ሥርጭት ለማወቅ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገርና ለቱሪስቶች ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ክልሎች ቅርሶችን የመመዝገብ ድርሻ ስላላቸው፣ ዳታቤዙ በሁሉም አካባቢዎች በተግባር እንዲውል አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን በቅድሚያ ማሟላት እንዳለባቸውም ያክላሉ፡፡

ዳታቤዙ፣ ቅርሶች በማንዋል በሚመዘገቡት ወቅት የነበሩ መስፈርቶችን ማለትም ከቅርሶች ስያሜ አንስቶ፣ ምድባቸውን፣ መገኛቸውን፣ ዓይነታቸውንና ሌሎችም መገለጫዎችን ያካትታል፡፡ የቅርሶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ለቅርሶች የሚሰጠው ኮድም አብሮ ይመዘገባል፡፡ ቅርሶች ቢዘረፉ፣ በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተከታትሎ ለማስመለስ ኮዱ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ያሉበትን ቦታና ሁኔታ በዲጂታል መንገድ መመዝገብ የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር መረጃ በመለዋወጥ ሕገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመግታት እንደሚውልም ያክላሉ፡፡ ቅርሶች ባሉበት ቦታ ጉዳት ሲደርስባቸው ወይም ጥገና ሲያስፈልጋቸው ለማወቅም ዳታቤዙ ያግዛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ቅርሶችን የተመለከቱ አዳዲስ መረጃዎች ለማካተትና መረጃዎቹን ለሚፈልጉ አጥኚዎች ለማቅረብም አመቺ ይሆናል፡፡

‹‹ዳታቤዙ ቅርሶች ቢሰረቁ፣ ቢቃጠሉ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ቢዘዋወሩ ስለሚያሳይ አፋጣኝ እርምጃ እንወስዳለን፤›› የሚሉት አቶ አበራ፣ ባለፉት ጊዜዎች ቅርሶች ያሉበትን ቦታና ሁኔታ በአግባቡ አለመመዝገብ የችግሩ መንስኤ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቅርሶች የት እንዳሉ አለማወቅ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ላልታወቀ ቅርስ ክትትል ለማድረግ ያስቸግራል፤›› በማለት ለቅርሶች ክትትል ለማድረግ የተሻለው አማራጭ ዲጂታል ምዝገባ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ቅርሶችን ባጠቃላይ በአንድ መረጃ ቋት ማኖር፣ ቅርሶችን በአግባቡ ለመጠበቅና ለመንከባከብ አመቺ ነውም ይላሉ፡፡

ባለንበት የመረጃ ዘመን፣ በርካታ አገሮች ቅርሶችን ለመመዝገብ፣ ለመጠበቅና ለጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግም ዲጂታል መንገድ ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በእጅጉ መዘግየቱ አያጠያይቅም፡፡ ዲጂታል አሠራሩ ዘግይቶም ቢሆን መጀመሩ መልካም ቢሆንም፣ በየአካባቢው ተስፋፍቶ በአግባቡ ሥራው እስከሚከናወን ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡

ዳታቤዝ መኖሩ ቅርሶችን ለመመዝገብ ቢረዳም፣ አዳዲስ ቅርሶችን ፈልጎ ወደ ዝርዝሩ የማስገባት ሒደት አሁንም የዘርፉ ባለሙያዎች ድርሻ ነው፡፡ ቅርሶች ያሉበትን ቦታ ማወቅና በዲጂታል መንገድ መመዝገብ ብቻውን ቅርሶችን ከዘረፋ ያድናል ማለት አይቻልም፡፡ በተያያዥም፣ ቅርሶችን ለመጠበቅና ጉዳት ሲደርስባቸው ለመጠገንም ሶፍትዌር ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ዳታቤዙን ሒደቶችን ለማፋጠን መጠቀም ቢቻልም፣ በቅርስ ጥበቃ፣ ጥገናና ሕገ ወጥ ዝውውርን ለመግታት ዳታቤዝ ብቻውን ውጤታማ አይሆንም፡፡

አቶ አበራ የቅርሶች ዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት መዘግየቱንና ብቻውን ለውጥ ያመጣል ብሎ መደምደም እንደማይቻልም ይስማሙበታል፡፡ ቅድሚያ ሊጠሰው የሚገባው ቅርሶች ያሉበትን ቦታና ሁኔታ ማወቅ እንደሆነና በቀጣይ መዝግቦ፣ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚከተል ያስረዳሉ፡፡ አሠራሩን ወደ ክልሎች በማውረድ በኩል መሰናክል ከሚሆኑ መካከል የኢንተርኔት አገልግሎት ውስንነት ይጠቀሳል፡፡ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ያለውን የእውቀት ክፍተትን መሙላት ቢቻልም፣ ለሥራው የሚሆኑ መሣሪያዎች ካልተሰራጩ ብዙ ርቀት መጓዝ አይቻልም፡፡

ከኢንተርኔት ውስንነት ጋር በተያያዘ ላለው ችግር አንደ መፍትሄ የሚያስቀምጡት፣ ያለ ኢንተርኔት (ኦፍላየን) ቅርሶቹን በኤክስኤል መዝግቦ፣ ኢንተርኔት ሲገኝ ወደ ማዕከላዊው ሥርዓት መላክን ነው፡፡ ‹‹የአገሪቱን ቅርሶች በማወቅ፣ የሥጋት አቅጣጫዎችን በመጠቆም፣ ለተመራማሪዎች፣ ለተማሪዎች ለሕዝቡ በየደረጃው መረጃ በመስጠትም ያገለግላል፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ለየክልሉ ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥተውና መሣሪያዎችን አከፋፍለው በአገር አቀፍ ደረጃ ሥራ እንደሚጀምሩም ይክላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...