Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጥበብን ገበያ ለማውጣት

ጥበብን ገበያ ለማውጣት

ቀን:

እጁ የተቆረጠው ታጋይ በወደቀበት እስከ ወዲያኛው አሸልቧል፡፡ ሕይወቱን በጦርነት ስለማጣቱ ከጎኑ የተተከለውና በውድቀቱ ያነሳው ባንዲራ ምስክር ነው፡፡ አገሪቱን ከወራሪው ጣሊያን ለመታደግ ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉ የዐድዋ ጀግኖች የከፈሉትን ዋጋ ማስታወስ የሚል መልዕክት ያለውን ክዋኔ የተጫወተው የ24 ዓመቱ ወንዱ ጉዲሳ ነው፡፡

ወንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመልቲ ሚዲያ ቴአትር የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎቹን ለኅብረተሰቡ የማቅረብ ፍላጎት ቢኖረውም፣ እንዴትና በምን አይነት ሁኔታ የሚለው ጉዳይ ያስጨንቀው ነበር፡፡ ብዙ ተመልካች ባለበትም ሥራውን አቅርቦ አያውቅም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በምን አይነት መልኩ ስራዎቹን ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንዳለበት ፍንጭ አግኝቷልና የራሱን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ዕቅድ አለው፡፡

መድረኩ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዲገናኝ መንገድ የከፈተለት እንዲሁም ከተወሰኑት ጋር ደግሞ ተጣምሮ እንዲሠራ ዕድል የሰጠው ነበር፡፡ በብሪቲሽ ካውንስል አስተባባሪነት በሲዮናት ሆቴል በተዘጋጀው የአምስት ቀናት የስልጠና ፕሮግራም ተሳታፊ ከነበሩ ወጣቶች መካከል ወንዱ ይገኝበታል፡፡

በጥቁርና ነጭ ቀለም የተነደፈውን የአድዋ ጀግኖችና ሌሎች ታሪካዊ ፎቶግራፎችን ወደ ባለቀለም ምስል የሚለውጠው ወጣትም ከወንዱ ጋር ተጣምሮ ሥራዎቹን አቅርቦ ነበር፡፡

ሌላው ወጣት የ26 ዓመቱ ነስረዲን መሐመድ ነው፡፡ በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉ ጀግኖችን ከሌላው ጋር የሚያነፃፅር ሽሙጥ ያዘለና ፈገግ የሚያሰኝ (ሚም) ነበር ያቀረበው፡፡ የዲጂታል ማርኬቲንግ ባለሙያው ነስረዲን ነገሮችን በሚምስ መግለፅ ሌሎች በጉዳዩ ፈገግ እንዲሉ ከማድረጉ ባለፈ ጥበብ መሆኑን ይናገራል፡፡ በስልኩ ከሚገኙ የግል መረጃዎች መካከልም ሚሞች ይበዛሉ፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሚሞች የሚያቀርቡ እንደ አቤና ከቤ፣ ሣርካዝም፣ ሣድካዝምና ሌሎችንም ገፆች ተከታይ በመሆን ሚምች ይሰበስባል፡፡ የራሱንም ያዘጋጃል፡፡

 የሚምች ዓውደ ርዕይ ለማቅረብ ሐሳብ እንዳለው ይናገራል፡፡ አውደ ርዕዩ በቅርቡ በሚጠናቀቀው በፈረንጆች 2017 በዓመቱ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ ትልልቅ ክስተቶች ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዓውደ ርዕይ ያልተለመደ በመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነት ምን ዓይነት እንደሚሆን እርግጠኛ አልነበረም፡፡ ዓውደ ርዕዩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉና መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዲሁም መከተል ያለበት የአሠራር ሒደት ምን እንደሆነም መረጃው አልነበረውም፡፡

እሱና ሌሎች መሰሎቹ እንዴት ተጣምረው መሥራት እንዳለባቸው፣ አንድ ሁነት ለማዘጋጀትም የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችና እንዴት መከናወን እንደሚችሉ ብሪትሽ ካውንስል ባዘጋጀው መድረክ በጠኑም ቢሆን እንዲረዱ ዕድል ፈጥሯል፡፡ እርስ በርስ በሐሳብ ስለሚረዳዱም ሁነቶች የማህበረሰቡን ቀልብ በሚስቡ መልኩ እንዴት መዘጋጀት እንዳለባቸው እንዲሁም የሚኖረውን ተቀባይነት ከዚሁ እንዲገምቱ ዕድል የሰጣቸው እንደሆነ ነስረዲን ይናገራል፡፡

በብሪቲሽ ካውንስል ክራኤቲቭ ፊውቸር ፕሮጀክት የኮሙኒኬሽን አማካሪው አቶ መላኩ ተኮላ እንደሚሉት፣ በብሪቲሽ ካውንስል፣ ጐተ ኢንስቲትዩትና በአይስ አዲስ ትብብር የሚተገበር ሲሆን፣ ከአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል፡፡ ከሙዚቃ ውጪ ባሉ የጥበብ ሥራዎች ማለትም ሥዕል፣ ፎቶ ግራፍ፣ ግራፊክስ ዲዛይን፣ ፋሽን፣ ጌሚንግ የመሳሰሉት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል፡፡

በእነዚህ የጥበብ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ተገናኝተው የሚወያዩበትና እርስ በርስ የሚማማሩበት መድረክ በማዘጋጀት አዳዲስ ሐሳቦችን እንዲያፈልቁ ዕድል የሚፈጥርላቸው ነው፡፡ የተገኘውን ሐሳብም ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያዳብሩ ያደርጋል፡፡ በየዘርፉ ከሚሳተፉ ወጣቶች መካከልም የተሻሉት ተመርጠው ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ውስጥ እንዲገቡና በሙያቸው እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡

በዚህ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል በፋሽን ዘርፉ ዲዛይነር ማህሌት አፈወርቅ አንዷ ነች፡፡ በጌሚንግ ረገድም ጨዋታ አዋቂ የተባለ በጌም ዙሪያ የሚሠራ ቡድን ተመርጦ በዓለም ላይ በሚገኙ ከተለያዩ ጌም ኩባንያዎች ጋር አብረው እንዲሠሩ መደረጉን አቶ መላኩ ይናገራሉ፡፡ ጨዋታ አዋቂ ‹‹የጊዜ ጦርነት›› የሚል ኢትዮጵያዊ ጌም ሠርተዋል፡፡

‹‹በእነዚህ የጥበብ ዘርፎች ላይ ያለው ደካማና ጥሩ ጎን ምንድነው የሚለውን በተመለከተ ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ በጥናቱ ወጣቶቹ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን ከመሥራት ባለፈ ሥራቸውን ለገበያ ማቅረብና በሥራቸው ተጠቃሚ መሆንን በተመለከተ ክፍተት አለባቸው፤›› የሚሉት አቶ መላኩ ዋናው ጉዳይ ሁነት የማዘጋጀት (Event Organize) ክህሎት ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በሲዎናት ሆቴል ለአምስት ቀናት በተዘጋጀው መድረክም ወጣቶቹ እንዴት ሥራዎቻቸውን ለማኅበረሰቡ ማቅረብ እንዳለባቸውና እንዴት መድረኮችን ማዘጋጀት እንደሚችሉ ሰልጥነዋል፡፡ ከ20 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ያሳተፈው ይህ ፕሮግራም ዓይናቸውን የገለጠ መሆኑን ወንዱ ይናገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...