በታረቀኝ አ.
የአገራችን ሰው የኑሮ ሁኔታ ይታወቃል፡፡ የሕዝቡ ሥራ፣ የገቢ ምንጭና መጠን፣ መተዳደሪያው፣ የሚበላውና የሚጠጣው ሁሉም ነገር በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ዘይት ጠፋ ብሎ የሚጨነቅ፣ ስኳር ጠፋ ብሎ የሚሠለፍ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሮ እየከበደውና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት የሚመራ ዓይነት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ዘይት ከቀበሌ ሦስት ሊትር 71 ብር ነጋዴ ገዝቶ ውጭ 120 ብር ሲሸጥ፣ ኑሮ በጣም የከበደው ሕዝብ ላለመሠለፍ ብሎ እንኳ ጨምሮ ከነጋዴው የሚገዛበት አቅም የለውም፡፡
በየገበያ ቦታው ብንሄድ፣ በየወፍጮ ቤቱ ብንገባ የሕዝቡን በኑሮ ላይ ያለውን ምሬት መረዳት ይቻል ነበር፡፡
ይኼንን ሁሉ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ እናት የልጆቿን ደኅንነት፣ አቅምና፣ ብቃት እንዲሁም ችሎታ በቅርብ ሆና እንደምትረዳው ሁሉ፣ በሕዝብ ተመረጥኩ ብሎ የተቀመጠው የሕዝብ እንደራሴም በአካባቢው ያለን ዜጋ ኑሮና የመቻልና ያለመቻል ወሰን ጠንቅቆ ሊረዳ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ያልቻለ አስተዳዳሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ሕግ ሲዘጋጅና ደንብም ሲወጣ ሁሌም በጥናት ተደግፎ የሕዝቡ አቅም ተጠንቶ መሆን አለበት፡፡
ይኼንን ለማለት ያነሳሳኝ አንዱን ልጅ፣ አንዱን የእንጀራ ልጅ አድርጎ በጣም እያሳዘነ ያለውንና ግማሹን ነዋሪ ለደም ግፊት ሌላውን ነዋሪ ደግሞ ዓመቱ ደረሰ ምን ልከፍል ነው ለሚል ሰቀቀን የዳረገውን የመሬት ሊዝ ጉዳይ ነው፡፡ ግማሹን ልጅ አደረገ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው? የመሬት ይዞታ ማረጋገጫቸው ከ1983 ዓ.ም. በፊት የሆኑ ወይም ሲገብሩ የቆዩ ከሆኑ ካሬ ሜትር በሦስት ብር ሒሳብ በሊዝ መልሰው ሲወስዱ፣ እስከ 500 ካሬ ሜትር በዚህ ክፍያ እንዲጠቃለልላቸው ይደረጋል፡፡ ይህ ማለት አንድ ከ1983 ዓ.ም. በፊት የተያዘ መሬት ሆኖ በቀበሌው ከዚያ በፊት ሲገብርበት እንደነበር መረጃ ማቅረብ የቻለ ግለሰብ፣ 500 ካሬ ሜትር በ1,500 ብር ከፍሎ የራሱ ማድረግ ይችላል ማለት ነው፡፡
ሌላውስ ካልን ሌላው የእንጀራ ልጅ የሆነውማ ለምሳሌ ከ1983 ዓ.ም. በፊት የገዛና 500 ካሬ ሜትር ያለው ሰው፣ 250ውን ከፍሎ ከሸጠ ለምን የተገዛው በ1985 ዓ.ም. አይሆንም? አሁን በአዲሱ ሊዝ 150 ካሬ ሜትር በ217 ብር ይታሰብና ቀሪው እንደ ቦታው ደረጃ ዝቅተኛው 3,667 ብር በካሬ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህ ማለት 400 ሺሕ ብር መክፈል ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ይኼ ታዲያ ከባንክ ጋር አያይዘው ባንኩ የሚቆልለውን ወለድ ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዋናው ነጥብ እዚህ ላይ ነው፡፡ ይኼ ቦታ 500 ካሬ ሜትር እያለ ሕጋዊ ሰነድ የነበረው ሲሆን፣ ተከፍሎ የተሸጠውም አዲሱ የመሬት አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የተገበረበትም ማስረጃም እያለ፣ ተከፍሎ ከተሸጠ የመሬት አስተዳደሩ መሬቱን የሚያስተናግደው እንደ አዲስ ቦታ ነው፡፡ ለዚያውም በ1997 ዓ.ም. በወረራ ተያዘ ተብሎ ከሚታሰበው ቦታ እኩል ማለት ነው፡፡
ከላይ ለምሳሌ ያነሳሁት 250 ካሬ መሬት ባለቤት ካርታ ለማግኘት በመጀመርያ አሥር በመቶ ወይም 40 ሺሕ ብር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ያንን ከፍሎ ካርታ ከያዘ በኋላ ደግሞ ቦታውን ለሌላ ወገን ማስተላለፍ ከፈለገ፣ በቅድሚያ ዕዳውን መክፈል እንዳለበት የስምምነት ሰነዱ ያሳያል፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ ይህ ነው፡፡ ምናልባት የዚህ ቤት ባለቤት በወቅቱ መሬቱን በቀላል ገንዘብ የገዙና ትንንሽ ቤቶችን ሠርተው በማከራየት የሚተዳደሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመጀመርያ አሥር በመቶ ከየት አምጥተው ይከፍላሉ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ መልሱ ከየትም ከሆነ 150 ካሬ ሜትር ወስደው 100 ካሬ ሜትር ለመሬት ባንክ ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ መክፈል ሳይችሉ የቀሩ ዜጎችን መንግሥት ቦታ እንዲሰጣቸው ተመዝግበው ለሚጠብቁ ኪሳቸው ጠጠር ባሉ ሰዎች ለጨረታ እንዲያቀርበው ሲሆን፣ 100 ካሬው በቂ ሆኖ ካላገኘው ወደ መሬት ባንክ ይግባ ሲባል ለአሻሻጥ በሚመቸው መንገድ ከ150 ካሬው ላይ ሊወስድ ይችላል፡፡
እንግዲህ አስቡት ይኼንንም ሰጥቶ ማለት ነው ግለሰቡ አሁንም ለ150 ካሬ ሜትር 32 ሺሕ ብር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ነው የሕዝቡ ኑሮ እየታወቀ፣ የሚበላውና የሚጠጣው እየታወቀ ይኼ ሁሉ ክፍያ ለዚያውም ለመኖሪያ ቤት መጫን አለበት ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳሁት፡፡ ሕዝቡ አገሩን ጥሎ የት ይሂድ? ተሳክቶለት መሸጥ የቻለ እንኳ ማኅበራዊ ሕይወቱን፣ ኑሮውንና የለመደውን አከባቢ ጥሎ ነው ወደ ሌላ አካባቢ የሚሰደደው፣ በዚያ ላይ ገዥውም ቢሆን መሬቱ ዕዳ አለበት በሚል ሰበብ ለባለቤቱ ጥሩ ዋጋ አይሰጠውም፡፡ እንዲያው ጥሩ ዋጋ ቢያወጣ እንኳ ቀድሞ የቤት ባለቤት የነበረው ሰው በቤት ኪራይ ከመኖር ውጪ ከዕዳ ነፃ የሆነ ቦታ ሊገዛ የሚያስችል ገንዘብ አይኖረውም፡፡
ይኼ ሁሉ ዜጋ ቤት ተመዝግቦ ዕጣ አልደርስ ብሎት በቤት ኪራይ በሚሰቃይበት አገር፣ ጭራሽ ቤት ኖሮት እንደ ምንም የኑሮ ገመናውን ከልሎ የሚኖረውን ዜጋ ቤት አልባ ለማድረግ የሚደረግ ሩጫ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ካላሰበ ምኑን አስተዳዳሪ ሆነ? ይኼ ወልዶ ከመጣል፣ ወይም እኔ ካገኘሁ እነሱ የደረሱበት ይድረሱ ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡
አንድ በእጄ ላይ ያለ መረጃ ልንገራችሁ፡፡ የቦታው ስፋት 497 ካሬ ሜትር ነው፡፡ የተገዛው በ1983 ዓ.ም. ነው፡፡ ቤት የተሠራበት ደግሞ በ1988 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ መብራት የገባለት በ1992 ዓ.ም. ነው፡፡ ውኃ ደግሞ በ1998 ዓ.ም. ገብቶለታል፡፡ ከሻጮቹ የቢል ቁራጭ ተቀብለው ለቀበሌያቸው መሬት አስተዳደር ደጋግመው ቢያስገቡም፣ ተከፍሎ የተገዛ ቦታ የመጀመርያውን ቦታ ማስረጃ ተካፍሎ መጠቀም አይችልም በሚል ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የተገበረበት መረጃ ቢቀርብም፣ በ1988 ዓ.ም. በተነሳ የአየር ካርታ ላይ ቤቱ ስለማይታይ ተቀባይነት የለውም ተብሎ የቦታው ጉዳይ የታየው ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ በመሬት ወረራ ወቅት የተያዘ በሚል ነው፡፡ አስቡት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የተገበረበትና መብራት በ1992 ዓ.ም. የገባበት ማስረጃ እያለ ማለት ነው፡፡
ይኼንን ቦታ ሕጋዊ ለማድረግ በአጠቃላይ የተተመነው ገንዘብ 1,303,597.12 ብር ሲሆን፣ ቅድመ ክፍያው ደግሞ 130,387.71 ብር ነው፡፡ እንግዲህ አስቡት ገንዘቡ ሚሊየን ቤት ነው፡፡ ቅድመ ክፍያው ደግሞ አሥር በመቶ በመቶ ሺሕ ቤት ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በወቅቱ ቦታውን ሲገዙ በቀላል ገንዘብ ገዝተውታል፡፡ ይኼንን ቦታ ሲኖሩበት እንጂ ሲነግዱበት ስላልኖሩ ከየት አምጥተው ነው ለዚህ ቦታ በሚሊየን ቤት የሆነ ገንዘብ ሊከፍሉ የሚችሉት? የሚገርመው ደግሞ ይኼ አይደለም፡፡ መንግሥት የቦታውን የሊዝ ክፍያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አያይዞታል፡፡ ካርታ የሚወሰደውም አሥር በመቶውን ቅድሚያ ክፍያ ንግድ ባንክ ሄደው ተዋውለው ሲያስገቡና የውል ማስረጃ ሲያመጡ ብቻ ነው፡፡
ውሉ ደግሞ ከላይ እንዳልኩት መሬቱን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ከተፈለገ በቅድሚያ ሙሉውን ክፍያ መከፈል እንዳለበት ጠቅሶ ውል ያስገባል፡፡ ደግሞ ክፍያው ለ40 ዓመት የሚከፈል ይሆናል ይልና መጨረሻ ላይ አንድ ገጽ አለ፡፡ የ40 ዓመቱ ክፍያ ሁኔታ የተቀመጠበት ይህ ሰንጠረዥ እንደሚያሳየው፣ የዚህ ቦታ ባለቤት በመጀመርያው ዓመት ከነወለዱ 140,788.49 ብር፣ በሁለተኛው ዓመት 138,002.05 ብር፣ በሦስተኛው ዓመት 135,215.62 ብር እና እያለ እያለ በ40ኛው ዓመት 32,117.36 ብር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ የዛሬ 40 ዓመት ክፍያውን ሲጨርስ 3,458,117.36 ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 2,284,879.50 ብር ወለድ ነው፡፡
አስቡት እንግዲህ እነዚህ ግለሰቦች ይኼንን ቤት ለመኖሪያ ቤትነት እየተጠቀሙ ከላይ የገለጽኩትን ያህል ክፍያ መክፈል እንደማይችሉ የማያውቅ መንግሥት ልጆቿን ወልዳ ከምትበላ ድመት በምን ይለያል? ከባንክ ጋር ማያያዙስ ለምን አስፈለገ? እንደሰማሁት ከሆነ ባንኩ ሦስት ዓመት ድረስ ሳይከፈል ከቆየ ልክ እንዳበዳሪ ሁሉ በሐራጅ ሸጦ በውሉ የተጠቀሰውን ገንዘብ ይወስዳል፡፡ እና ዜጋችንን ምን እያደረግነው ነው?
ለዚህ ጉዳይ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እኔ እንኳን አስከማውቀው በየካ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎች፣ በተለያዩ ጊዜያት የሊዝ ዋጋ ይቀነስ፣ ወለድ ይቅርልንና ሌሎችንም በማለት ተሰባስበውና ፊርማ አሰባስበው በየቀበሌያቸው መሬት አስተዳደርና ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ቅሬታ ቢያስገቡም ቅሬታው መሬት ሊነካ አልቻለም፡፡ በየጊዜው ኃላፊዎቹ የበላይ ውሳኔ ነው፣ የሚቀየር ነገር የለም ከማለት ውጪ መፍትሔ አልሰጡም፡፡
አሁንም አሥር በመቶውን ከወዳጅ ዘመድ ተበዳድረው የከፈሉና ካርታ የወሰዱ ነገር ግን ጉዳቸውን ከውሉ በኋላ የተረዱ የመሬት ባለቤቶች ደግሞ ዓመቱ ደረሰ፣ የት እንድረስ? ከየት አምጥተን እንክፈል? እያሉ በከባድ ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አንዲት ሴት የመጀመርያውን ዓመት ክፍያ ለመክፈል ሦስት ቀናት አሳልፋ ሄዳ 200 ብር ቅጣት መክፈሏንም በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ እናስ ምን እየተካሄደ ነው? በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍላተ ከተሞች የሚኖሩና ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የተዘፈቁ ነዋሪዎችስ የመፍትሔ አባታቸው ማነው?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡