Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበአንድ እጅ ማጨብጨብ ይቁም!

በአንድ እጅ ማጨብጨብ ይቁም!

ቀን:

በልዑል ዘሩ

“አገር የሚገነባው በምሁራንም ሆነ በፓርቲዎች ይባል በመንግሥታት ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ በምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎና ሁለንተናዊ ርብርብ ነው፡፡ ሕዝብ በንቃት ያልተሳተፈበትና በፍትሐዊነት ያልተጠቀመበት (በመኖርና አለመኖር ውስጥ እየቆዘመ ሕይወትን የሚገፋበት) የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ምንም ቢሆን ሊሳካ አይችልም የመባሉ እውነታም ከዚሁ ይመነጫል፤›› የሚለውን ሐሳብ የአልበርት አንስታይን ኢንስቲትዩት መሥራች ጄን ሻርፕ በተለያዩ ጽሑፎች ሲያነሳው ይደመጣል፡፡

ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣም የአባባሉን ጥርጥር የለሽ እውነትነት እንገነዘባለን፡፡ ይነስም ይብዛም ሕዝብ በተሻለ ተነሳሽነትና አጋርነት የተሳተፈባቸው ሉዓላዊነትን የማስከበር  ትግሎች፣  የበረሃ ተጋድሎዎች፣ የልማት ሥራዎችም ይሁኑ  የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጭላንጭል ጥረቶች አመርቂ በሚባል ደረጃ ሲሳኩ ተመልክተናል፡፡ በተቃራኒው ሕዝቡ የተቃወማቸው፣ የተጠራጠራቸውና የእኔ ጉዳይ አይደሉም ብሎ ከዳር የቆመባቸው ጉዳዩች መጨረሻቸው ውድቀትና ክስረት እንደሆነም  ግልጽ ነው፡፡ እንኳን በመንግሥት ሥራ በቤተ እምነት ጉዳይም ቢሆን ሕዝብ ካልፈቀደ ዳር የሚደርስ ነገር የለም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገራችን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳዳርና የፖለቲካ መብት ጥቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈረጠሙ  መጥተዋል፡፡ ይህ የፍላጎት ማደግም ይባል የሕዝቡ ግንዛቤ እየቀደመ መሄድ የፈጠረው የለውጥ መሻት፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተካሄደ ያለ ቢሆን ይበል፣ ይጠናከር የሚያስብል ነው፡፡ ወይም ከዜሮ ድምር የፖለቲካ ጨዋታ በራቀና የተገነባውን በማይንድ የአዲስ ትውልድ የለውጥ ግፊት ላይ ቢመሠረትም እሰየው ነበር፡፡

በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እየታየ ያለው ክስተትና አየሩን እየሞላው የመጣው ሀቅ ግን፣ ከላይ ከተጠቀሰው በተቃራኒ ከመንጎድም አልፎ ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄዱም የሚያሠጋ ነው፡፡ ነገሮች እየተረጋጉ ነው በሚባልበት ወቅትም በቅርብ የሚታየው ዘላቂው ሰላምና መደማመጥ ሳይሆን፣ በሁሉም በኩል አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ማድፈጥ ነው፡፡ ወይም አሸንፎ ለመውጣት መቋመጥ እንጂ፣ ተቀራርቦ ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ለማስፈን አይመስልም፡፡ 

አሁን አሁን እየታየ እንዳለው ቢያንስ ባለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የሰላም መደፍረስ ታይቷል፡፡ በዚህ መዘዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፣ ብዙዎችም ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የህሊና ቁስለኛ የሆነውም ትንሽ አይደለም፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የአገርና የሕዝብ ሀብት እሳት ተለቆበት ወድሟል፡፡ ዜጎች በማንነታቸው ሳቢያ ወደ መጋጨትና መጠቃቃት በግልጽ ሲገቡ ታይቷል፡፡

ይህ በመሆኑም አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እናቴ በሚላት አገሩ በየትኛውም አካባቢ ተዟዙሮ ሊሠራ የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናው ፉርሽ እየሆነ ይመስላል፡፡ ይህንን ሀቅ በምንም መንገድ ከማድበስበስና ከመሸፋፈን ይልቅ ፊት ለፊት ተጋፍጦ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መታገል ሲገባ፣ ራሱ መንግሥትም ምንም እንዳልተፈጠረ አሁንም ስለመቻቻልና ዴሞክራሲያዊ የሚለውን ብሔርተኝነት እየሰበከ ነው፡፡ 

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ደጋግመው እንደሚሉት፣ የግጭትም ይባል የሕዝቡ እምቢተኝነት መነሻ ውጫዊ ምክንያት ብቻ እንደሆነ መገለጹም አሳሳች እሳቤ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ ጽንፈኛ ተቃዋሚ በሚባለው ኃይል ግፊት፣ በሻዕቢያና በግብፅ መንግሥት ረዳትነት “ለሽብር” የተሠማሩ ወጣቶች የክስተቱ ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው ተደጋግሞ ሲነገር፣ በመላው አገሪቱ በሥርዓቱ ላይ ቅሬታ ያላቸውን ወገኖች እስካለመኖራቸውም እንደ መቁጠር የሚታይ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ በመንግሥት በኩል በመልካም አስተዳዳርና በውስጥ ኢኮኖሚያዊ ችግር ሕዝቡ አለመርካቱ ይነሳና እየታደስን ስለሆነ በትዕግሥት ሊጠብቀን ይገባል የሚል አንድምታ ያለው ሰበብም ይደረደራል፡፡

ምንም ተባለ ምን በአገሪቱ መለስ ቀለስ የሚለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ግን  መንስዔዎቹ የተለያዩ እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት ሥርዓቱ ያስገኛቸው ቱርፋቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የወዘፏቸው ችግሮችና ለዓመታት ያልመለሷቸው ጥያቄዎችም ሕዝቡን እንዳማረሩት ይታመናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን በአፈጻጸም ያጋጠሙት ችግሮች የሚያስከፉት ብዙኃኑ ሕዝብ (Majority Group) እንደሚኖር አለመገመት አዳጋች ነው፡፡

በእነዚህና መሰል የውስጥና የውጭ መዘዞች ምክንያት ባለፉት ጊዜያት በአገራችን ለወራት ያህል ተከስተው የነበሩት ሁከትና ትርምሶች ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ ለአገር ሰላም ዋነኛው ምሰሶ ሕዝብ ነው፡፡  ሰላሙን፣ መረጋጋቱን፣ ልማቱንና ዕድገቱን ጠብቆ የሚያስቀጥለው የአገሩ ባለቤት፣ መሪና አሳዳሪ የሆነው ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ከሕዝብ ውጪ የሚታሰብ ሰላምም ሆነ ልማት የለም፡፡ ለዚህም ነው አሁን ሕዝቡ ሰላሙ እንዲቀጥል ቢፈልግም፣ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ባለመመለሳቸው ምክንያት የሚከሰትን የሰላም መታወክ ወይም ሁከት እንደ ቅቡል ገቢር (ሥጋት ማሳደሩ ባይቀርም) ወደ መቁጠር የመሄድ ዝንባሌ እያሳየ የሚገኘው፡፡ መነሻዎቹን አንድ በአንድ ለማየት እንሞክር፡፡

መንግሥት መገንዘብ ያለበት

መንግሥት የሕዝቡ መብቴ ይከበርልኝ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን የገለጸው የውስጥ ችግርን ለመፍታት የሚያስፈልገው  ውጫዊ ሰበብ መደርደር ሳይሆን፣ ዘላቂና ተከታታይ እንዲሁም ትውልዱንና ወቅቱን የሚመጥን መፍትሔ ማፈላለግ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዘግይቶ ወይም በድሮ በሬ ለማረስ በመሞከሩ ሕዝብ መቆጣቱ አይቀሬ እየሆነ መምጣቱን መገንዘብ አለበት፡፡ በዚህ መዘዝም በተፈጠረው ግርግር ተጠቅመን፣ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደፍርሰን፣ የዓረቡን ዓለም የመፍረስ አብዮት ወይም የአፍሪካውያንን ቀውስ በኢትዮጵያ ዕውን እናደርጋለን የሚሉ ጥብቅ ተቀናቃኞች ቢነሱ የሚደንቅ አይሆንም፡፡

‹‹ውሻ በቀደደው . . . ›› እንዲሉ ሌሎችም በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ጭምር ሰፊ ዘመቻ ከፍተው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና የጥላቻ ንግግር በመዝራት የሚዘምቱት፣ በእኛው አገራዊ ክፍተት ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ ለዓመታት ከአንድነትና ከኅብረት ይልቅ ቀለል ያለ ንፋስ የሚያናውጣቸውን የልዩነት ሕንፃዎች በድቡሽት ላይ ለመገንባት የተደከመው ድካም ሥልጡኑን ፌዴራሊዝም ለአደጋ አጋልጦታል፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ቱባ የሚባሉት የመንግሥት ባለሥልጣናት እንኳን አገራዊ ስሜትን የሚገዛ አንድነታዊ ንግግርን ከማድረግ ይልቅ፣ በብሔርና በመንደር ጭልፊት ክንፍ ላይ ሠፍረው ውቅያኖስን ለማቋረጥ ያህል ሲመኙ በእጅጉ እያዘንን ነው፡፡ 

ይህ ሁኔታ ተስፋ ሰጪውንና የኖረውን የሕዝቦች አብሮነት ቀስ በቀስ እየሸረሸረ፣ አገራችንን ለሚጠሉዋትና ሥርዓቱን በኃይል ማፍረስ ለሚሹ ኃይሎች ሴራ ሥጋት ዳርጎታል፡፡ በመሠረቱ ባለፈው ዓመትም ሆነ በቅርቡ እንደታየው መዘዝ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ያለው የተረጋጋና የሰከነ ሰላም በቦታው አይኖርም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብ ሥጋትና አለመረጋጋት እንዲከሰት በር መከፈቱን አመላካች ነው፡፡

መንግሥት አሁንም አገር የማስተዳዳር ኃላፊነት የተጫነበት እንደመሆኑ ሰበብ እየደረደረ ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ›› ከማለትም ሆነ፣ ትናንት ሞተዋል ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች (ኦነግን ልብ ይሏል) ‹‹ወጣቱን ቀስቅሰውት ነው›› እያለ በማሳበብ ትዝብት ላይ ከመውደቅ መውጣት ይኖርበታል፡፡ በመሠረቱ በዕድሜ አፍላ የሆነውንና በስሜታዊነት በቀላሉ የሚማረከውን ወጣቱን በመልካም ሥነ ምግባርና አገር ወዳድነት የመቅረፅ ተግባር የመንግሥትና የማኅበረሰቡ ኃላፊነት ነው፡፡ ይኼ ትውልድ የታላላቅ አባቶችና እናቶች ምክርና ተግሳጽ፣ ሽምግልናና ዳኝነትን ትቶ እንደፈለገው ለጥፋት የሚነዳ ከሆነ ክፍተቱና ተስፋ መቁረጡ የት ጋ ነው ተብሎ መታየት ያለበት ወደ ውስጥ ነው፡፡

ወጣቱ አገር ለመገንባትም ሆነ ለማፈራረስ የተዘጋጀ ትኩስ ኃይል ስለመሆኑ፣  ከእኛም አልፎ የብዙ የዓለም አገሮች ተሞክሮዎችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ እነ  ሶሪያ፣ ሊቢያና የመን በጽንፈኞች ተገፋፍተው ለአመፃ በተነሱ ወጣቶች ፈራርሰዋል፡፡ የየራሳቸው ዜጎች አገራቸውን ባዶ አውድማ አድርገዋል፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ተገድለው፣ የተቀሩትም ተሰደው በስቃይ ሕይወት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህን የመሰለ በጥላቻና በስሜታዊነት የተሞላ ጥፋትና ወድመት በኢትዮጵያ እንዲደርስ የሚፈልግ ዜጋ ይኖራል ባይባልም፣ እንደ ቀልድ ነገሮች ከእጅ አምልጠው ሥርዓት አልበኝነት ከተንሰራፋ ግን መመለስ አዳጋች ነው፡፡

እንዲያው ለነገሩ መንግሥት ምንም ምክንያት ይስጠው ምን፣ እንደሚባለው ወጣቱ ተገፋፍቶም ሆነ ተነሳስቶ እንዴት ለራሱና ለማኅበረሰቡ የሚጠቅመውን ልማትና የግለሰቦች ንብረት ሊያወድም ይችላል የሚለው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ የሕዝብና የመንግሥት የሆነ ንብረት ማውደም፣ ማቃጠል በደሃ አገር አቅምና ኢኮኖሚ የተገነቡ የልማት አውታሮችን ማጋየት፣ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ አምቡላንሶችን፣ የትራንስፖርት መኪናዎችን፣ ፋብሪካዎችን በተደጋጋሚ ማቃጠልና ማንደድ፣  በሕዝቡ ውስጥ እንዴት ያለ ተስፋ መቁረጥና የእኔ አይደለም አስተሳሳብ ቢያቆጠቁጥ  ነው ብሎ ሳይታይ በደፈናው የፀረ ልማት ዕርምጃ ተካሄደ ማለት መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ነገሮችን አድሮ ጥሬ የሚያደርግ የፖለቲካ አካሄድም ነው፡፡

በእርግጥ ባለፈው ዓመት የግብ ደኅንነት ኃይሎች ከጀርባ በመሩትና ባቀናበሩት በቢሾፍቱው የእሬቻ በዓል ላይ በሰላማዊው ሕዝብ ሁከት ስለመቀስቀሱ የሚታዩ ምልክቶች ነበሩ፡፡ መንግሥት በመረጃ እንዳረጋገጠው ሃይማኖታዊውንና ለፈጣሪ ምሥጋና የሚቀርብበትን መድረክ ወደ ፖለቲካዊ ተቃውሞ እንዲለወጥ፣ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር ያደረጉ ኃይሎች ድጋፍ ያገኙት ከዚያች አገር የደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደነበርም አስታውቌል፡፡ ይሁንና ለአመፃው መቀስቀስ ዋነኛ ተዋናዮች  የነበሩት የእኛው ልጆችና ወንድሞቻችን መሆናቸው ሊሸሸግ የሚችል አይደለም፡፡  ስለዚህ ቀዳሚው ትኩረት መሆን ያለበት ጣትን ወደ ውጪ መቀሰር ሳይሆን፣ ወደ ውስጥ በማማተር ጓዳን መፈተሸ መሆን አለበት፡፡  

ከዚያም ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ ማዕዘናት ተደጋጋሚ ችግሮች ተፈጥረው በሰላም ተፈቱ ሲባሉ ዳግም ሲያገረሹ ዓይተናል፡፡ አሁን በአገሪቱ ያለው መንግሥት ጠንካራና ሁነኛ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ ነው ከተባለ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት አቅም ያለው አስተዋይ መንግሥት መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የችግሩን ሰንኮፍ ፈጥኖ መለየትና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ግድ ይለዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀሰቀሱ ችግሮች በግለሰቦችና ኃላፊነት በጎደላቸው ሰዎች ቆስቋሽነት የሚነሱ መሆናቸው ቢረጋገጥ እንኳን፣ ሕዝቡ አምርሮ እንዲታገላቸው መደረግ አለበት፡፡

መንግሥት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ብልጭ ድርግም እያሉ የሚነሱ ችግሮችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን ዘለቄታዊ መፍትሔ የመስጠት ሚናውን ሲወጣ አይታይም፡፡ እንዲያውም በዚህ ረገድ አንዳንድ ክልሎች (ኦሮሚያና አማራን ይመለከቷል) የተሻለ ጥረት ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመልካም አስተዳዳር፣ በልማትም ሆነ በዴሞክራሲ ረገድ ያለውን አገራዊ ድክመትና ጥንካሬ በግልጽነትና በታማኝነት መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በመሠረታዊነት የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ታውቀው የጋራ መፍትሔ መስጠትም ይገባል፡፡ 

በመሠረቱ በሕዝቡ ውስጥ ከፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ጋር የሚነሳው መሠረታዊ  ጥያቄ፣ በፌዴራል ሥርዓቱ አፈጻጸም ላይ የሚታየው ልዩነትን የማጥበቅ ዝንባሌ፣ እንዲሁም የጠበባው የፖለቲካ ምኅዳር ሁሉ በጥልቀትና በቅንነት መፍትሔ መሻት ተመልካች ካላገኘ በምንም ተዓምር ዘላቂ መፍትሔ ሊገኝ አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ከመንግሥት በተሻለ የአንበሳውን ድርሻ የሚወጣ ሊኖር አይችልምና መንግሥት ሊያስብበት ይገባል እላለሁ፡፡

በሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት በኩል

በአንድ አገር ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ዘላቂ ለውጥ ውስጥ ከሕዝቡና ከመንግሥት በተጨማሪ የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራትን የመሳሰሉ የማኅበረሰቡ ነፃ ተቋማት ሚናቸው የሚናቅ አይደለም፡፡ እነዚህ ተቋማት ግን ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት በአንድ በኩል ገለልተኛና ነፃ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ፍትሕና ርትዕ የሰፈነባቸውና ሕዝቡ ሙሉ እምነት የጣለባቸው የሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

በተለይ የሃይማኖት መሪዎች ለሰማዩ መንገድ እንዲያበጁ ብቻ ሳይሆን በምድር  የሕዝቦች እኩልነት፣ ፍትሕና ሰላም እንዲረጋገጥም ኃላፊነታቸው ቀላል አይደለም፡፡  ይህም በብዙ የዓለም አገሮች በሚገኙ ጠንካራ ቤተ እምነቶች ሲንፀባረቅ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ አገር ግን በቀደመው ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሥርዓተ መንግሥቱ ባላቸው ትስስር፣ አሁን አሁን ደግሞ የሁሉም ቤተ እምነት መሪዎችና መንግሥት ባላቸው ቁርኝት (ምንም እንኳን በሕገ መንግሥቱ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ቢሆንም)፣ ቤተ እምነቶቹ ለምድራዊው አገዛዝ የማደርና እምብዛም ለብዙኃኑ መብትና ጥቅም ያለመታገል፣ ብሎም በውስጣቸው የመሻኮት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡

ያለፈው አልፏል ቢባል እንኳን ከዚህ በኋላ ግን የእምነት ተቋማቱም ሆኑ ሲቪክ ማኅበራቱ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ለፍትሕና ለእውነት የቆሙ መሆናቸውን ማረጋጋጥ አለባቸው፡፡ በተለይ ቤተ እምነቶቹ በተለያዩ ጊዜያት በአገር ደረጃ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብሚያስተላለፉት መልዕክትና አስተምህሮ፣ ብሎም በገቢር የሚያደርጉት  እንቅስቃሴ ሰላምን፣ አንድነትንና መከባበርን የሚያስተምር መሆን አለበት፡፡ የሰማዩ ብቻ ሳይሆን የምድሩ ዳኝነት አስታራቂና ሸምጋይ መሆን የሚችሉት በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱት ተደጋጋሚ  ግጭቶች እንደታየው የሰው ሕይወትና ንብረት ከጠፋ በኋላ፣ የሃይማኖት መሪዎች የተሰማቸውን ሐዘን የሚገልጽ መልክት ማዥጎድጎዳቸው ግን ተራ ፖለቲካ ከመሆን አያልፍም፡፡ የመደማመጥና የእርቅ መንፈስን የማይሰብክ ወግም ሁሉንም አያዛምድም፡፡ ወይም እርቅን ለማስፈን አያስችልም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን መንግሥትና የመንግሥት አካላት ምንም ያህል ቢያጠፉ የማይገሰፁ፣ በሕዝብ ላይ ሲሆን ግን ዘለፋን የሚያዥጎደጉዱና ግልጽ የሆነ አድሏዊ ዲስኩር የሚያሰሙ፣ ብሎም የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በእምነት ካባ ውስጥ የሚያራምዱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መወገዝና መከልከል አለባቸው፡፡ አሁን ላለው የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድም የሚመጥን ተግባር እያከናወኑ አለመሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡

አልፎ አልፎም ቢሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮችየኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መሪዎችብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ማቅረብ የሚኖርበት በሰላማዊ መንገድ መሆን እንዳለበት ማስተማራቸው መልካም ጅምር ነው። በዚያው በነካ እጃቸው ግን  መንግሥትም ከኃይል ዕርምጃ ወጥቶ፣ ፖለቲከኞችም በሠለጠነ መንገድ ተነጋግረው የሕዝቡን ጥያቄ አቅም በፈቀደና በፍጥነት መመለስ አለበት ማለት አለመቻላቸው ግን፣ ያው የምድሩ አድርባይነትና የራስ ጥቅምን የማስከበር ጣጣ እያናወዛቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ እየተደረገ ደግሞ አባቶቹም፣ ቤተ እምነቶቹም ተከብረው በፈጣሪ ቃል ሥር ማደራቸውን ለማመን አዳጋች መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ከዓመታት በፊት አስተዋይ መንግሥታት በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ተው ባይ የሃይማኖት አባቶቻቸውና ዴሞክራሲያዊነት ያላቸው ማኅበራትም በጨቋኝ ሥርዓቶቹ በመሳደዳቸው፣ ወይም ጭራሽ ሳይፈጠሩ በመጨንገፋቸውና በመዳከማቸው በሰሜን አፍሪካና በመካካለኛው ምሥራቅ አንዳንድ አገሮች የሆነውን እያየን ነው፡፡  

ወጣቶች ያለምንም ዓይነት ተው ባይነት በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቀስቅሰው፣ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ግፊት ሴራ ተነድተው፣ ለውድ አገራቸው መፈራረስ ምክንያት እንደሆኑ አይዘነጋም። እስካሁንም የአገራቸውን ህልውና ከአደጋ ማዳን፣ የደፈረሰ ሰላማቸውን ማጥራትና ዳግም ወደ ነበሩበት መመለስ ሳይችሉ የቆዩ አገሮችና ሕዝቦች መኖራቸውን ልብ ይሏል።

ያኔ ቆም ብሎ ማሰብና የሰከነ መንገድ መከተል ቢችሉ ኖሮ መንግሥታቸው እንደ መንግሥት ሳይቆም፣ ኢኮኖሚያቸው እንደ አገር ሳይጠነክር፣ ፖለቲካቸው ከውጭና ከአገር ውስጥ ጠላቶች ተፅዕኖ ሳይላቀቅ፣ ሕዝቦቻቸው በሥጋት ደመና ውስጥ ተሸሽገው መራብ፣ መጠማትና መሰደድ ዕጣ ፈንታቸው አድርገው እንዲኖሩ ባልተገደዱ ነበር። ለዚህ ግን ሁነኛ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት፣ እንዲሁም እነሱን የሚያከብር ሕዝብና ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን እሴቶች ማጣት ፍጻሜው ጥፋት ብቻ ነው መባሉም ለዚህ ነው፡፡  

እኛ ኢትዮጵያውያን የጎረቤቶቻችንን ይኼ ዓይነቱን አስከፊ መንገድ የምንመርጥ መሆን የለብንም። ያለፍናቸውን ረዥም ጊዜያት ስናስታውስና አሁን እኛም ሆንን አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስናጤነው ምርጫችን ሰላምና አንድነት ብቻ መሆን አለበት። ሰላማችንን በማረጋገጣችን ተጠቃሚዎች ሆነናል። ቢያንስ ራሳችንን እየቻል ለአገራችን ዕድገትና ልማት ተርፈናል። የጎደለንን ለማሟላት ሁላችንም ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን መሥራት እንጂ በማይረባ መንገድ ቆመን ጊዜያችንን የምናጠፋበት፣ እየወደቅን እየተነሳን የምንባክን መሆን የለብንም። ለዚህ ደግሞ ሕዝብ፣ መንግሥት፣ የእምነት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራትና ሌሎችም ሚናቸውን እየተወጡ በጋራ የሚቆሙ ንጂ፣ በትርኪ ምርኪ ትርፍ በአንድ እጅ የሚያጨበጭቡ ሊሆኑ አይገባም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...