Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አልበዛም እንዴ?

እነሆ መንገድ! ከሽሮ ሜዳ ወደ አራት ኪሎ። ‹‹አንተ ልጅ ይኼን የማጅራት ገትር ክትባት ተከትበሃል ለመሆኑ?›› ሾፌሩ ነው ወያላውን የሚጠይቀው። ‹‹ኤድያ እኛ እኮ የሚያስፈልገን የማጅራት መቺ ክትባት ነው!›› ብለው ጣልቃ የሚገቡት ደግሞ አንዲት ወይዘሮ ናቸው። ‹‹ምነው እማማ? የማጣት ልክፍቱን ሴት ሲላከፍ የሚያባርር የሚመስለው በእርስዎም ደረሰ እንዴ?›› ሾፌሩ ሊግባባቸው ይጀምራል። ‹‹ተወኝ እስኪ! እኔ የማወራው ስለገበያው ነው። ምን ይለክፈኛል እንደ ቀትር ጋኔን ያላልኩትን አለች ሊለኝ፤›› ተበሳጩ ወይዘሮዋ። ከወትሮ የታክሲ መያዣ ሥፍራው ተፈናቅሎ አዲስ ፌርማታ የተጠቆመው መንገደኛ በሌላ ጥግ ያጉረመርማል። ‹‹ኧረ የት እንድረስላቸው? እንደ ዳማ ድንጋይ ቦታ እያቀያየሩ ከሚያንገላቱን ምናለበት የትራንስፖርቱን ችግር ቢያቃልሉልን?›› ሲል አጭር ከትከሻው ጎበጥ ያለ ወጣት አጠገቡ ለተቀመጠች መለሎ፣ ‹‹እነሱ ማናቸው?›› ብላ ታሾፍበታለች።

‹‹እኔን ያልገባኝ ግን የእኛን ቦታ እያፈራረቁ ታክሲ መሳፈር ተደምሮ ነው የመተካካት ስትራቴጂው ግቡን የሚመታው? ወይስ ምንድነው?›› ሲለኝ ደግሞ አጠገቤ የተሰየመ ጎልማሳ፣ ከኋላችን የተቀመጠ ብልጣ ብልጥ ወጣት ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ወንድሜ እባክህ ‘አቤት ማለት ከላይ መብረር፣ ለምን ማለት ክንፍን መስበር’ ያለውን ገጣሚ አዳምጠው፤›› አለው። ስንቱን ሰምተን እንችላለን ግን እናንተ? የወዲያ ወዲሁን የሽሙጥ ቅብብል በአጭር ጊዜ አድምጦ የተዋሀደው አዲስ ተሳፋሪ መጨረሻ ወንበር ላይ ራሱን እያመቻቸ፣ ‹‹አቤት እኛ ግን! አሁን ምን አለበት አንድ ላይ ተሰብስባችሁ አንድ ነገር ከምትሆኑብኝ፣ በተን በተን ብላችሁ የሚመጣውን በፀጋ ተቀበሉልኝ፤›› የሚል አሳቢ መንግሥት ስናገኝ ብናመሰግን? እንዲያው ምን እንደሚሻለን፤›› ይላል። ለዚህ ተሳፋሪ ማንም መልስ አይሰጥም። ቀናም ብሎ ያየው የለም። ቀና ማሰብና ነገርን በመልካም ጎኑ መፍታት የአጎብዳጅና የአስመሳይ ፀባይ ነው ተብሎ የተደመደመ ይመስላል። እናም እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ ስሜት በሕይወት፣ በአገር ማቅናት፣ ድህነትን በማሸነፍ ጎዳና… ልባችን ተከፋፍሎ አብረን እንጓዛለን። ግን የት ድረስ እንዘልቅ ይሆን?

ታክሲያችን ሞልታ እየተንቀሳቀሰች ነው። ጎልማሳው ይቀደዳል። አንድ የሚያውቀው የሞባይል ስልክ ጠጋኝ አግኝቶ ወደ መጨረሻ ወንበር ተንጠራርቶ በመዞር፣ ‹‹ኧረ በፈጠረህ ይኼን ስልክ አንድ በልልኝ፤›› ይለዋል። ቴክኒሺያኑ ‹‹ምን ሆነ ደግሞ?  12 ሺሕ ብር መገዛቱን ረስቶ በወር ከምናምኑ ተበላሸ?›› በነገር ሊወጋው ያሰበ ይመስላል ዋጋውን ያሰላበት። ከፊታችን መካከለኛው ወንበር ላይ የተቀመጡት ወይዘሮ፣ ‹‹ህም 12 ሺሕ ብር?›› ሲሉ ጆሮአችን ይቀልባል። ወሬ አነፍናፊነቴን እንዳላጋልጥ ሌላ ሌላ ላስተውል ስሞክር ደግሞ፣ ‘ኩራት ራታችን ባይሆን ኖሮ እንደ ዳይኖሰር በጠፋን ነበር’ የሚል ጥቅስ አነባለሁ። ጥጋ ጥጉ ሁሉ በነገር ድር መተብተቡ ብሶም አይደል? ‹‹ምን ይሆናል ‘ኢቢሲ’ ሰለቸኝ ብዬ የ‘ቢቢሲና የአልጄዚራ’ ዜና በሞባይል እንዲደርሰኝ ባደርግ የባሰ ሆነብኝ እኮ። እንዴ የጠገበ ድብድብ የተራበ ድብድብ! ከሶማሊያ እስከ የመን የጦር ዜና ብቻ? ምነው ይኼን ያህል ባንለማም ለማን፣ ገና ብዙ ቢቀረንም አደግን የሚሉን የመልካም ምኞት ቅዠት አይሻልም እንዴ?›› ሲለው ጎልማሳው ወጣቱ ሳቀ።

ወዲያው ስልኩን ተቀብሎ ስሜት የሚረብሹ ዜናዎች እንዳይደርሱት ለማድረግ ሲጎረጉር፣ ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠ ሌላ ወጣት ስልክ በጩኸት ታክሲዋን አደበላለቀው። ‹‹በስመ አብ! ምናለበት ቀነስ ብታደርጉት ድምፁን? ከሶሪያ መጥተህ አታነሳው?›› ይላሉ ወይዘሮዋ። ተቀምጣም የታክሲዋን ጣሪያ በአናቷ የምትታከክ መለሎ ተሳፋሪ ደግሞ፣ ‹‹ምንድነው ግን ጩኸት ብርቃቸው የሆኑ ሰዎች በዙ?›› ትላለች። ይኼኔ አጠገቧ የተቀመጠ የእንግሊዝኛ መጽሔት የሚያነብ ወጣት (የአገርኛውንማ የት አግኝተነው ይመስልበታል) ‹‹በ‘ሳይለንት ሙድ’፣ በሒደት ነገሮችን ለማስተካከል ትዕግሥትና ዕውቀት ያጣው ስለበዛ አይመስልሽም?›› አላት። ዘንድሮ ለመባባል የሚቀረን ያለን አንመስልም!

ወጣቱ ስልኩን አንስቶ፣ ‹‹ሃሎ!›› ላይ ነው። ‹‹ማን ልበል? ማነህ አንተ? እ? የት ነው የምታውቀኝ? ማነህ አንተ?›› እየደጋገመ ይህንኑ ይጮሃል። ‹‹ኧረ ቀስ ብለህ አውራ በለው! ምንድነው ነገሩ?›› ሾፌሩ ተቆጣ። ወያላው እያላገጠ፣ ‹‹አትጩህ ወንድሜ! አለበለዚያ እንጠቁምሃለን! ማሸበር ማጋየት ብቻ አይደለም እየተባልክ ነው፤›› አለው። ልጁ ግን የሚሰማ አልሆነም። ‹‹ማነህ አንተ? እንዳልዘጋው ስልኩን!›› ይላል። ‹‹አቤት አቤት! በስንት ፀሎትና መንጠራራት፣ ተጋድሎና ሰማዕትነት የሚገኝን ‘ኔትወርክ’ እንዲህ ባለመደማመጥና ባለመግባባት ሊዘጋ? አይደረግም!›› ትላለች አንዲት ቆንጅዬ ተሳፋሪ፣ እኔስ ከተረቡ ለምን ይቅርብኝ ዓይነት አፏን በነገር ስታሟሽ። ‹‹ምን…  የመደማመጥን፣ የመጠያየቅን፣ ተነጋግሮ የመተማመንን ‘ኔትወርክ’ እንደ ሾተላይ ልጅ በአጭር ማስቀረት በእሱ አልተጀመረ . . .  ለቀቅ ብታደርጉት፤›› ብለው ወይዘሮዋ የቅኔ መዋጮውን ይቀላቀላሉ።

ወያላው ‹‹ወይ ጉድ!›› እያለ በለስላሳ ፈገግታው እየዳሰሰን ሒሳብ ይቀበለናል። ‹‹ተውኝ እስኪ (የጎነተሉት ይመስል የነገረኛ ተግደርድሮ ነገር የማድራት ስልት ናት ይህች ይህች አማርኛ) አሁን ይህች አገር ናት ‘ኔትወርክና’ ሰው የሚወጣላት? ከዚህ ሁሉ ትርምስና ዋጋ ክፍያ በኋላ?›› ብሎ ሳይጨርስ ጎልማሳው የተቃዋሚዎቹን ጎራ አጠናክሮ አረፈው። አንዳንዱ ደርሶ በየሄደበት ጠላት ማፍራት ሲቀናው፣ ‹‹ኧረ ጭፍን ተቃዋሚውና ጨለምተኛ አላስቀምጥ አለን!›› ሲል አንዱ፣ ከሴቶቹ አንዷ ቀበል አድርጋ ‹‹እሺ የእኛስ ይሁን የመጪውን ትውልድን ዕጣ ፈንታ በዛሬ የለውጥ ሕመም ዝለን እንዴት እንተነብያለን?›› ብላ ጎልማሳው ላይ አፈጠጠችበት። ጎልማሳው፣ ‹‹ጉድ ፈልቶ! ጭራሽ ተብሎ ተብሎ ታክሲ ውስጥም የምርጫ ቅስቀሳ ተጀመረ?›› ብሎ ያጉተመትማል። ከምንሰማው በላይ የምናየውን ላለማመን እስከወዲያኛው የማልን ሳንበዛ አልቀረንም። ወትሮስ ይኼ አይደል ከጥራት የብዛት ጣጣው አትሉም?!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጋቢና የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ስለኳስ በስሜት ያወራሉ። ሁለቱም የአርሰናል ደጋፊዎች ናቸው። ‹‹የእግር ኳስ ፓርላማ ቢኖር ኖሮ መቀመጫው ስንት ይደረግልን ነበር ይሆን እናንተ?›› ጋዜጣ የሚያነበው በምፀት ይጠይቃል። ‹‹ወይኔ አርሰናል! ሌላው ላይስ ይሁን ጠላታችን ሞሪኒሆ ፊት ያዋርደን?›› ሲባባሉ ልጆቹ፣ ‹‹ኧረ ጠላታችን ድህነት ነው የተባለውን አትርሳ በለው፤›› ትላለች ቀይዋ ልጅ። ‹‹ዋንጫ የሚባል ሳናነሳ ከአሥር ዓመት በላይ ሊሆነን እኮ ነው?›› ሲሉ አሁንም የወዳጁን ስልክ አስተካክሎ የጨረሰው ሞባይል ጠጋኝ፣ ‹‹ሦስት ሺሕ ዘመን ሙሉ የብልፅግናንና የታላቅነትን ዋንጫ አለማንሳታችን ከአርሰናል ዋንጫ ማጣት በላይ ሊያስቆጨን አይገባም ነበር?›› ይላል።

ታክሲያችን ውስጥ ማኅበራዊ ሂሱ እንደ ምትትሮሽ ኳስ እዚህና እዚያ ይለጋ ያዘ። ‹‹አሁን አልን ለማለት ነው እንዲህ የምትነታረኩት? ወይስ ከልባችሁ ነው?›› ብለው ተመፃዳቂዎቹን ወይዘሮዋ ሲታዘቡ ማንም አያዳምጣቸውም። በእኔ አውቃለሁ፣ እኔን ስሙኝ የትዕቢተኞች ገመድ ጉተታ የደመቀው ጎዳና ለአፍታ ራስን ለመመልከትና ለመጠየቅ ዕድል የሚሰጥ አይመስልም። እዚያም በራስ እውነትና ዕውቀት ብቻ መታጠር፣ እዚህም እንደዚያው ከራስ እውነትና ዕውቀት አንፃር ብቻ ዓላማ መር ሕይወት መሪ መስሎ መታየት ሆኗል ፋሽኑ። ጋቢና ያሉት ወጣቶች፣ ‹‹አሁን ያለን አማራጭ በቃ ቬንገርን ከአሠልጣኝነት መንበር ማንሳት ብቻ ነው፤›› እየተባባሉ ታክሲዋን አስቁመው ሲወርዱ ከለንደን ‘ደብል ዴከር ባስ’ የሚወርዱ የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ የቦርድ አባላት እንጂ፣ መሀል አዲስ አበባ ለዕለት እንጀራቸው የሚሯሯጡ ባለጉዳዮች አይመስሉም። አይደንቅም?!

ጉዟችን ወደ መጠናቀቁ ነው። ሾፌራችን ስለምንለየው ይመስላል ቶሎ ከአንዱ ኤፍኤም ጣቢያ ጋር ለመላመድ ሬዲዮን ይጎረጉራል። ጋዜጠኛው ስለየመን ነውጥ ይተነትናል። ‹‹አንቺ ዓለም! መቼ ይሆን ሥልጣን በጠመንጃና በኃይል ተነጥቆ የሚያዝብሽ መሆንሽ ታሪክ ሆኖ የምናስታውሰው?›› ሲል ጋዜጣ አንባቢው ወጣት ነገር ለኮሰ። ‹‹ምን እኛን ትጠይቀናለህ? ዕድሜ ልክ መግዛት የሚያምራቸውን አምባገነን መሪዎችን ጠይቃቸው!›› ብሎ ጎልማሳው መለሰ። ‹‹የሚያሳዝነው እኮ በጨለማ እንኳ ከጨረቃ ላይ ፎቶ ሲነሳ፣ ከሌሎች አኅጉሮች እኛ ብቻ ጨለማ ካረፈበት ፀጥ ካለው ባህርና ውቅያኖስ ጋር መመሳሰላችን ነው። ምናለበት 20፣ 30 እና 40 ዓመት ሲገዙ መብራት እንኳ ቢያበሩልን?›› ስትል ደግሞ ረጅሟ ወጣት፣ ‹‹ውይ ውይ! የመብራትንስ ነገር አታንሺው ይቅር! ከጨረቃ ላይ ፎቶ ሲነሳ የሚታይልን የመብራት ብርሃን ቀርቶብን እኛን ራሳችንን እርስ በርስ የሚያስተያይ የ40 ሻማ አሞፖል ኃይልም ሳይቆራረጥ ካገኘን ትልቅ ነገር ነው፤›› አለች አጠገቧ የተቀመጠች ፍልቅልቅ ወጣት። ታክሲያችን ቦታ ይዛ ሾፌራችን ‹‹አውርድ›› ሲል ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን በረገደው። ጎልማሳውና ወይዘሮዋ ቀድመውን ተከታትለው ወረዱ። ወደኋላ ከቀረነው ወጣቶች መሀል አንዱ፣ ‹‹መኖር ደግ ነው። ዕድሜ ከሰጠን የዴሞክራሲውም የመብራቱም ብርሃን ፈክቶ ማንም የማያጨልምብን ዘመን ይመጣል፤›› አለን። ‹‹እኮ መቼ?›› ብትለው መለሎዋ ልጅ፣ ‹‹አንድ ቀን!›› ብሏት ጠፋ። እኛም በየፊናችን ተበታተንን። ‹‹አንድ ቀን መቼ ይሆን?›› ብሎ አንዱ የጎዳና ላይ ወግ ሊጀምር ሲቃጣው ሌላው፣ ‹‹አልበዛም እንዴ?›› አለው፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ብለን ብለን ቀን ቆጠራ እንጀምር ደግሞ? አልበዛም እንዴ? መልካም ጉዞ! 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት