Monday, February 26, 2024

ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ መማር ማስተማር ሥራቸው የመመለስ ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ማዕረግ ሞላ (ሙሉ ስሟ ተቀይሯል) ተወልዳ ያደገችው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ካሉ ወረዳዎች አንዱ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እናቷ ጠላ እየጠመቁና እየሸጡ በሚያገኙት ገቢ እንዳሳደጓት፣ አባቷ በሕይወት ቢኖሩም ከእናቷ ጋር ከመለያየታቸው ባሻገር ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማያደርጉላት ታስረዳለች፡፡ የእናቷን ውለታ ለመክፈል በማሰብም ለትምህርቷ ትኩረት በመስጠቷና በማጥናቷ ጥሩ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ነጥብ አግኝታለች፡፡ ዘንድሮ በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ መሆኗንም ትገልጻለች፡፡

በ2010 ዓ.ም. የሁለተኛ ዓመት ትምህርቷን ለመከታተል ወደ መቱ ዩኒቨርሲቲ ብትገባም፣ በዩኒቨርሲቲ እንዳለፈው ዓመት ጥሩ የመማር ማስተማር ሒደት እንዳልገጠማት ታስረዳለች፡፡ የሦስት ዓመት ቆይታዋን አጠናቅቃ ሥራ ለመያዝና ለብቻቸው ያሳደጓትን እናቷን ለመርዳት ዕቅድ ቢኖራትም፣ አሁን ያለው የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሒደት እንዳሳሰባት ትናገራለች፡፡ ከሁለት ሳምንታት በላይ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት እንደገና ቢጀመርም፣ ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቋርጦ መዋሉን ገልጻለች፡፡

ትምህርት በመቋረጡም ጭንቀት ውስጥ እንደገባች አስረድታለች፡፡ በ2010 ዓ.ም. በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ሳቢያ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ለምን ዜጎች ይሞታሉ? ለምን ከቀዬአቸው ይፈናቀላሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያነሱ እንደቆዩም ታብራራለች፡፡  በተፈጠረው ግርግርም የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው መቆየታቸውን ታስታውሳለች፡፡ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የመውጫ ፈተና እንደሚኖር ከገለጸ ወዲህ፣ ተማሪዎች ጥያቄ በማንሳትና ጉዳዩን በመቃወም የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋርጦ እንደነበር ትናገራለች፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር ከተማሪዎች ጋር ባደረገው ተከታታይ ውይይትም የመማር ማስተማር ሒደቱ ተጀምሮ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ነገር ግን ኅዳር 25 እና 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የመማር ማስተማሩ ሒደት እንደተቋረጠና ይህም በእጅጉ እንደሚያሳስባት ተናግራለች፡፡

በ2010 ዓ.ም. መጀመርያ አካባቢ በኦሮሚና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ፣ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የክልሉ ተማሪዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወደዚያ መሄድ የለባቸውም የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የክልሉ መንግሥትም የተማሪዎችን ጥያቄ በማጤን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዳቀረበና ትምህርት ሚኒስቴርም ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ ምላሽ እንደሰጠ ይታወቃል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) የሁለቱ ክልሎች ተማሪዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተደለደሉት በሚኒስቴሩ ተነሳሽነት እንደሆነ ቢገለጹም፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገሪቱ ከትምህርት ተደራሽነት አንፃር ብዙ ሥራዎችን እንዳከናወነች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙና ከእነዚህ መካከል ደግሞ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ናቸው፡፡ በአገሪቱ በትምህርት ተደራሽነት ስኬታማ ሥራ ብታከናውንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርቱ ዘርፉ እየታዩ ያሉ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ከትምህርት ሽፋኑ ጋር የሚመጣጠን ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡ ሌላው በተቋማቱ ውስጥ ብሔር ተኮር ጥያቄዎች መነሳታቸው እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት እየተፈጠረ መሆኑን ማሳያዎች እንዳሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎችን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደብ፣ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ የሶማሌ ክልል ተማሪዎችን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደብ፣ በአገሪቱ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከሁለት ሳምንት በፊት ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታም ይህ ተገቢ እንዳልሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹የሁለቱን ክልሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደየክልሎቻቸውና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደብን አላምንበትም፤›› ብለው ነበር፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭትና ትምህርት ሚኒስቴር ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዕጩ ምሩቃን ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት መውጫ ፈተና ይወስዳሉ ብሎ አዲስ መመርያ ካወጣ ወዲህ፣ በዩኒቨርሲቲዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ባሉ የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች መማር ማስተማሩ እንደተቋረጠ ታውቋል፡፡ በሐሮማያ፣ በጅማና በመቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሒደት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ ሰንብቷል፡፡

በመቱ ዩኒቨርሲቲ ከብሔር ጋር ተያያዞ በተነሳ ጥያቄ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአማራ ብሔር ተወላጆችም ተመሳሳይ ጥያቄ ሲያቀርቡ ከቆዩ በኋላ፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከክልሉ አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይት ከአውቶብስ መናኸሪያ መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡

በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩ ሒደት ከተጀመረ ወዲህ ዳግመኛ እንደተቋረጠ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ለመቋረጡ ምክንያትም ከሳምንት በፊት በአርሲ ነገሌ ተከስቶ በነበረበው ግጭት ከሃምሳ በላይ ተማሪዎች፣ በተለይም የአካባቢው ተወላጆች በመሄዳቸውና እነሱ መምጣት አለባቸው የሚል ጥያቄ በመነሳቱ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሒደቱ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተቋርጦ መቆየቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፍቅሬ ለሜሳ (ዶ/ር) ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ተናግረዋል፡፡ የተወሰኑ ዲፓርትመንቶች ትምህርት እንደጀመሩ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ የማስተማር ሒደቱ ሙሉ በሙሉ እንዳልተጀመረ አክለው ገልጸዋል፡፡ ለትምህርቱ መቋረጥ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ የሚጠቀሱት ደግሞ፣ በተመሳሳይ በመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚያነሷቸው እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ2010 ዓ.ም. በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ባሉ ውስን ዩኒቨርሲቲዎች ያለው የመማር ማስተማር ጤናማ እንዳልሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው  መግለጫ አስታውቋል፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ውስን ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ከመውጫው ፈተና ጋር በተያያዘ ባነሱት ጥያቄ መስተጓጎል ተፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ የመውጫ ፈተናው (Exit Exam) ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሰጠቱ እንደማይቀር ተናግረው ነበር፡፡ አገሪቱ ከዚህ በፊት በሕግና በሕክምና ትምህርቶች የመውጫ ፈተና በመስጠት የተሻለ ውጤት እንዳስመዘገበች፣ ከዚህም አንፃር ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩና ለሚመረቁ የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተርም የመውጫ ፈተናውን በተመለከተ ከዚህ በፊት መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተናውን ለመስጠት ያቀደበት ዋነኛ ምክንያት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሆነ ገልጿል፡፡

አገሪቱ በትምህርት ተደራሽነት ስኬታማ ሆናለች ቢባልም፣ ከጥራት አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ የሚያነሱ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ አበበ ዓለሙ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የትምህርትን ጥራት ማስጠበቅ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግሥት መሥራት ያለበት አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ሳይሆን ገና ከጀምሩ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ደግሞ፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሲባል መውሰድ ያለበት ዕርምጃ በዚህ ወቅት እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ሌላ እሳት መጫር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከተፈለገም የትምህርት ፖሊሲው እንደገና መፈተሽ አለበት፡፡ ተማሪዎች መመረቂያ ጊዜያቸው ሲደርስ የመውጫ ፈተና ለመስጠት ማቀዱ ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አበበ በአገሪቱ እየተስተዋለ ላለው የመልካም አስተዳደር ችግር አንዱ ምክንያት በትምህርት ጥራት ዝቅተኛ መሆን ነው ይላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በበኩላቸው፣ ‹‹በትምህርት ጥራት መጓደል አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳች ነው፡፡ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መሠረት የትምህርት ጥራት በመሆኑ፣ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ክፍተት እንደገና ቢፈተሽና ቢያስተካከል መልካም ነው፤›› ብለዋል፡፡  

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ውስን ዩኒቨርሲቲዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ሦስት ገጽታ ያላቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ አንደኛው  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር፣ ሁለተኛው ከመውጫ ፈተናው ጋርና ሦስተኛው ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ድክመት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ የተማሪዎችን ጥያቄዎች በተገቢው ማዳመጥና ምላሽ መስጠት ደግሞ የመንግሥት የቤት ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጨመዳ ፈኔንሳ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ የሐረማያ፣ በምሥራቅ ሐረርጌና በሌሎች ወረዳዎች ያሉ ዜጎች ተማሪዎችን በማግባባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ እስከ ፊታችን ሐሙስ ትምህርት ይጀመራል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሒደቱን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፍቅሬ ለሜሳ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹በጅማ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ተቋርጦ ነበር፡፡ በዋናነት የመውጫ ፈተና ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ይኖራል በሚል ነው፡፡ እሱን አንወስድም የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ላይ ሰፊ ውይይት ሲደረግ ነው የነበረው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ ስለዚህ በአንዱ ጥያቄ እሱን ነው የሚያነሱት፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በኦሮሚያና በሶማሌ ወሰን ግጭት ብዙ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ምንድነው በመንግሥት የተሠራው? አሁን እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ግጭት አለ፡፡ ይኼ ነገር መቆም አለበት የሚሉትን ያነሳሉ፤›› ብለዋል፡፡

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ ‹‹በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው በመጀመርያ አካባቢ፣ በሁለቱ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ወሰን ላይ በተከሰተው ችግር  የኦሮሚያዎቹ ወደ ሶማሌ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶማሌም ወደ ኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች መሄድ የለባቸውም የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ ለዚያ መፍትሔ ተሰጣቸው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በሁለቱ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ወሰን አካባቢ በተከሰተው መፈናቀል ላይ ጥያቄ ተነሳ፡፡ አዎ ችግሩ ተከስቷል፡፡ ችግሩን ግን የሁለቱ ክልሎች መንግሥታትና የፌዴራል መንግሥት እየሠሩበት በመሆኑ፣ ምላሽ ይሰጣችኋል ትምህርታችሁን እንድትቀጥሉ የሚል አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡ እንደገና ከዚያ በኋላ የሁሉም የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄ የነበረው ዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ሆነ፡፡ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ በርካታ ጊዜያት ተስተጓጉለዋል፡፡ ችግሮቹ ቢኖሩም እንኳ ጥቄያቸውን እያቀረቡ ትምህርታቸውን መቀጠል ሲገባቸው፣ የተለያዩ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ተማሪዎች ከተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች እየወጡ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡ አገር ልትለወጥ የምትችለው በትምህርት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አበበ፣ ከመውጫው ፈተና ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ትምህርት ሚኒስቴር እንደገና ቢያጤነውና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሌሎች መመርያዎችን ቢያወጣ ተሻለ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የመውጫ ፈተና መስጠት ዋጋ ቢኖረውም ወደ ትግበራ መግባት የነበረበት ግን ከተማሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ ወደ ነበረበት መመለስ እንደሚቻል እምነታቸውን አስረድተዋል፡፡

የባከነ ጊዜ እንዳለ የጠቆሙት አቶ አበበ፣ ተማሪዎች ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱ በቶሎ የሚመለሱ ከሆነ የባከነውን ጊዜ ማካካስ እንደሚቻልና ወደ ተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መግባት እንደሚቻል አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በበኩላቸው የተማሪዎችን ጥያቄ በጥሞና ማዳመጥና ምላሽ መስጠት ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የባከነ ጊዜ አለ፡፡ አንድ ቀን ዋጋ አለው፡፡ ይካካስ ቢባል እንኳ መምህሩ በሩጫ ነው ማካካስ የሚችለው፡፡ በዚያ ላይ የተማሪዎች መጨናነቅ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ መፍትሔው አሁንም ከተማሪዎች ጋር ቁጭ ብሎ መወያየት ነው፡፡ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው ናቸውና፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ጥላዬ ችግሩን ለመፍታት የዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራርና ከአገር ከሽማግሌዎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ የወጡበት በቂ ምክንያት እንደሌለ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የሕግ የበላይነት መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባሉ ውስን ዩኒቨርሲቲዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሸጋገሩ የብዙዎች ሥጋት ሆኗል፡፡ የሐረማያ፣ የጅማና የመቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሒደት እየተስተጓጎለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ከላይ ታች እያሉ መሆኑ ታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ መማር ማስተማር ሥራቸው የመመለስ ፈተና ከባድ እንደሆነም ባለሙያዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ ወደ ቀደሞ የመማር ማስተማር ሥራቸው መመለስ ቢቻልም ጉዳዩ ከባድና ፈታኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን ከተማሪዎች ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግና መስተካከል ያለባቸውን በማስተካከል መፍታት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡                              

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -