Friday, February 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት በ110 ዕድሜው የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት አካሔደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኢትዮጵያ ኩባንያዎች አለመገኘታቸው አስተችቷል

የተመሠረተበትን 110ኛ ዓመት እያከበረ የሚገኘው የጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሰናዳው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከ250 በላይ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በርካታ የውጭ ኩባንያዎች የተሳታፉበት ይህ የንግድ ትርዒት፣ እ.ኤ.አ. በ1907 ከተመሠረተ ወዲህ ያካሔደው የመጀመሪያው እንደሆነ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ዮሱፍ ሙሳ ደዋሌህ አስታውቀዋል፡፡ በንግድ ትርዒቱ ለመሳተፍ፣ ከጃፓን፣ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከቱርክ፣ ከፈረንሳይ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሶማሊያ፣ ከሶማሌላንድ፣ ከኬንያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከሞሪሺየስና ከሌሎችም አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች በጂቡቲው ዓውደ ርዕይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ከኅዳር 24 ቀን 2010 እስከ ኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በጂቡቲ እየተካሔደ የሚገኘው ዓውደ ርዕይ፣ በቀጣናው የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ላይ ባተኮሩ ልዩ ልዩ የፓናል ውይይቶችና ስብሰባዎች የታጀበ ጭምር ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ዓውደ ርዕይ ይሳታፋሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ በጂቡቲ ሚስዮን ጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ወቅት እንደጠቀሱት፣ ስድስት ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ለንግድ ትርዒቱ ተመዝግበው ኋላ ግን በገንዘብ ምክንያት ሳይሳተፉ እንደቀሩ ጠቅሰዋል፡፡ በንግድ ትርዒቱ ለመሳተፍ የተጠየቀው የምዝገባ ክፍያ 780 ዶላር እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ኤምባሲው ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት ስለዓውደ ዕርዩ አስቀድሞ በማሳወቅ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ መጠየቁን አምባሳደር ሻሜቦ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና የጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዮሱፍ ሙሳ የመሩት ልዑክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባዘጋጀው 10ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይ ለመሳተፍና እግረ መንገዱንም በጂቡቲ ስለሚካሔደው ዝግጅት ለማስተዋወቅ በጥቅምት ወር አዲስ አበባ ተገኝቶ እንደነበር ከጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በየጊዜው ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የሚላኩ ምርቶችና የገበያ ፍላጎት እየጨመረ በሚገኝበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንዲህ ያሉትን የገበያ ዕድሎች ሊያሰፉላቸው በሚችሉ የንግድ ትርዒቶች አለመሳተፋቸው ለአዘጋጆቹ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ይህም ቢባል ግን ዓባይ ቀለም የተሰኘውና በውጭ ባለሀብቶች የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኩባንያ በብቸኝነት በዓውደ ርዕዩ ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተመረቱ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ንግድ በጂቡቲ ትልቅ ገበያ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ የፍራፍሬና አትክልት ገበያውም ትልቅ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ግንኙት 110 ሚሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ጫትን ጨምሮ አብዛኛውን ገበያ የያዘው ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የሚላከው ምርት እንደሆነም ታውቋል፡፡

በአንፃሩ ከንግድ ዓውደ ርዕዩ ባሻገር የአካባቢያዊ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ላይ ያተኮረው ኮንፈረንስ ትልቅ ቦታ የተሰጠውና እንደ ቆስጠንጢኖስ በርኹ ክርስቶስ (ዶ/ር)፣ እንደ ቀድሞው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ ያሉ ባለሙያዎች የታደሙበት መድረክም ለጂቡቲው ዝግጅት አኅጉራዊ ፋይዳ ሰጥቶታል፡፡ አገሮች የመሠረተ ልማት መዘርጋት ብቻም ሳይሆን፣ በሕዝቦቻቸው መካከል ልውውጥ ሊደረግባቸው የሚችሉ ምርቶችን ማምረት እንደሚጠበቅባቸውም በጉባዔው ከታደሙና ለምሁራኑ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡ በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ትስስርና ግንኙነት በፖለቲካዊ አንድምታው ሲታይ፣ ማለትም በፖለቲካዊ ድንበርና ጂኦግራፊያዊ መስተጋብር አኳያ መንግሥታቱ እንደሚፈልጉት ዓይነት ትስስር ገና አልተፈጠረም፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን እንዳጓተተው ተብራርቷል፡፡ በአንፃሩ ግን በኢትዮጵያና በጂቡቲ፣ በኢትዮጵያና በኬንያ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ሕዝቦች መካከል ድንበር የማይገድበው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አለ፡፡

ይህንን ያብራሩት ቆስጠንጢኖስ፣ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ግንኙነቶች ትልቅ እንቅስቃሴ እንደሚታይባቸውም አውስተዋል፡፡ ኢትዮጵያን በዓመት እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር እያሳጣ እንደሚገኝ ያጣቀሱት የቁም እንስሳት ሕገወጥ ንግድም በሶማሌላንድ በኩል እንደተጧጧፈ ተናግረው፣ መንግሥታቱ ሕዝቡ በቀደመባቸው መስመሮች በመግባት የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው ሥልቶች ሊንቀሳቀሱ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት ከ110 ዓመታት በፊት ሲመሠረት አብዛኛውን አስተዋጽኦ ያደረጉትና እ.ኤ.አ. ከ1957 እስከ 2003 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ሰዒድ ዓሊ ኩቤሽ የተባሉ ጂቡቲያዊ የንግድ ምክር ቤት መሥራች አባት ስለመሆናቸው ተወስቷል፡፡ እኚህ ግለሰብ ካደረጓቸው በርካታ የንግድ ምክር ቤቶች የአቻ ግንኙነት ውስጥ በአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ፕሬዚዳንትነት ከሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጋር የነበረው ግንኙነትም በታሪክ ማኅደርነት ለሕዝብ ዕይታ ከቀረቡት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡

የጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት በዓመት እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ የሚያገኝባቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ያሉት ተቋም ነው፡፡ በዋናነት የሚጠቀሰው ከኮንቴይነር አገልግሎት የሚያገኘው ገቢ ሲሆን፣ በአንድ ኮንቴይነር እስከ 25 ዶላር የሚያስከፍልባቸውን የኮንቴይነር መጫንና ማውረድ ሥራ በጂቡቲ ወደብ እያካሄደ ራሱን ይደጉማል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች