Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሸገር የጎዳና እንግዶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር ተደጋግሞ የሚወሳ ነው፡፡ ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ እንደ ባቡር ያሉ አዳዲስ አገልግሎቶችና በአንዴ በርካታ ተጓዦችን የሚይዙ ተጨማሪ አውቶብሶች ወደ ሥራ የገቡ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ ሊቃለል አልቻለም፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማራመድና ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ታስበው ከተቋቋሙ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሸገር ትራንስፖርት፣ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አውቶብሶች በተጨማሪ ለከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፍ አዳዲስ የሚባሉ ግልጋሎቶች የሚሰጡ አማራጭ መጓጓዣዎችንም እያቀረበ ነው፡፡

ባለፈው ቅዳሜም በአገሪቱ የመጀመርያዎቹን የተማሪዎች መጓጓዣ አውቶብሶችና ተደራራቢ የሕዝብ ትራንስፖርት አውቶብሶችን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት በማስመረቅ ወደ አገልግሎት አስገብቷል፡፡ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ተገጣጥመው በዕለቱ ከተመረቁት 80 አውቶብሶች ውስጥ 50ዎቹ የሕዝብ አውቶብሶች ሲሆኑ፣ 30ዎቹ የተማሪዎች አውቶብሶች ናቸው፡፡ በዕለቱ የተመረቁትን ጨምሮ ሸገር አውቶብስ ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ጋር የገዛቸው 850 አውቶብሶች ዋጋ 3.4 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ናቸው ተብሏል፡፡

በተለይ አዲስ አበባ ጎዳናዎች እንግዳ የሆኑት የተማሪዎች መጓጓዣ አውቶብሶች የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመንም ሆነ የተማሪዎችን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ያግዛሉ ተብሏል፡፡

የተማሪዎች አውቶብስ ጽንሰ ሐሳብ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአሜሪካ ከትምህርት ቤት ርቀው የሚገኙ ተማሪዎችን በፍጥነት ወደ ትምህርት ገበታቸው ለማድረስ የፈረስ ጋሪን ለአገልግሎት በመጠቀም እንደተጀመረ በዕለቱ የተሠራጨው የሸገር መረጃ ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1930 ዓ.ም. ዋይኔ ኮርፖሬሽን ያመረተው የመጀመሪያው ብረት ለበስ ባለሞተር መኪና ወደ አገልግሎት እስከገባበት ጊዜ ድረስ የፈረስ ጋሪዎችና ከእንጨት የተሠሩ ባለሞተር ተሽከርካሪዎች አገልግሎቱን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካና በካናዳ ብቻ በዓመት አሥር ቢሊዮን የተማሪዎች የአውቶብስ ምልልሶች የሚደረጉ ሲሆን፣ በአሜሪካ ከኬጂ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ካሉ ተማሪዎች ግማሽ ያህሉ የተማሪዎች አውቶብስ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡

ለኢትዮጵያ አገልግሎቱ ገና አዲስ ቢሆንም ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ግን ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ከፍታ በአዲስ አበባ አገልግሎት እንዲጀምር መደረጉ አንድ እመርታ ነው ተብሏል፡፡ ከሸገር አንድ መቶ ስኩል ባሶች መካከል የመጀመሪያዎቹ 30 የሚሆኑት በፓይለት ደረጃ በተመረጡ 12 መስመሮች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ አውቶብሶች እንደሌሎች አገሮች ወደ ብርቱኳናማነት የሚያደላ ቢጫ ቀለም እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ ይህም አውቶብሶቹ ለሌሎች አሽከርካሪዎች በቀላሉ ከርቀት እንዲታዩ እንዲሁም በወጥ ቀለማቸው ሕፃናትን የያዙ አውቶብሶች መሆናቸው በሁሉም ሰዎች ዘንድ እንዲታወቅ ለማድረግ ነው፡፡

የተማሪ አውቶብስ ዲዛይኖች ሰባት ሲሆኑ፣ አብዛኞቹን አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ ከፊታቸው ሾጠጥ ብሎ የሚወጣ አካል ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡ በቢሾፍቱ የተገጣጠሙት አውቶብሶችም ይህንኑ ይዘት እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ በሁሉም የተማሪ አውቶብሶች ላይ እንደ ስታንዳርድ የሚሠራባቸው የደኅንነት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ሲኖሯቸው፣ የተማሪ አውቶብሶች ሾፌሩ በቀላሉ በውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችን እንዲሁም አካባቢውን መቆጣጠር እንዲችል የደኅንነት ካሜራ የተገጠመላቸው ናቸው፡፡ ሾፌሩ ከመቀመጫው ሆኖ እስከ ሁለት መቶ ሜትር ከኋላ የሚመጡ መኪኖችን መመልከት የሚያስችለው ነው፡፡ የእነዚህ አውቶብሶች መጀመር ፋይዳው በተለያየ መንገድ እንደሚገለጽ ሸገር ትራንስፖርት አስታውቋል፡፡ በተለይም በንፁህ አዕምሮ አዳዲስ ሐሳቦችን ለመማር ወደየትምህርት ቤቶቻቸው የሚጓዙ ተማሪዎች ማለዳ በታክሲ ጥበቃ፣ በሠልፍና ግፊያ ተሰላችተው፣ ተዳክመውና አንዳንዴም አርፍደው ክፍል እንዳይገቡ ይረዳል፡፡ በምረቃው ሥርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አማረ እንደገለጹት፣ በከተማዋ እያደገ የመጣውን የትራንስፖርት ፍላጎት ባለሥልጣኑ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑንና ለዚህም በዕለቱ የተመረቁትን ተሽከርካሪዎች ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የተማሪዎች አውቶብስ ለተማሪ አገልግሎት ብቻ ተብለው በልዩ ትዕዛዝ ዲዛይን የሚደረጉ ስለሆኑ ደኅንነታቸው ከሌሎች መኪኖች በላይ የተጠበቀ ሲሆን፣ መኪኖቹ አደጋ ቢያጋጥማቸው እንኳን ፊታቸው ላይ ሾጠጥ ብሎ የሚወጣ መጋጫ ያላቸው በመሆኑ በግጭት ወቅት አደጋን የመቀነስ አቅም አላቸውም ተብሏል፡፡

የተማሪ አውቶብሶች መጀመር እንደ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚታየው የትራፊክ መጨናነቅን በማስቀረት ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ነው፡፡ አሁንም በአሜሪካ የተማሪዎች አውቶብስ ካውንስል የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ አንድ የተማሪዎች አውቶብስ 36 ትናንሽ መኪኖችን ከትራፊክ ፍሰቱ የሚያስወጣ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ስሌት በአዲስ አበባ ሥራ የሚጀምሩት አንድ መቶ የሸገር የተማሪዎች አውቶብሶች ስንት ትናንሽ መኪኖችን ከአንድ አቅጣጫ ፍሰት እንደሚያስወጡና መንገዱንም ከመጨናነቅ እንደሚታደጉት መገመት ይችላል ይላል፡፡ እነዚህ የትምህርት ቤት አውቶብሶች የሚጠቀሙ ተገልጋዮች ክፍያቸውን በወር የሚከፍሉበት ዕድል ያመቻቸም ነው፡፡ ለከተማዋ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ይውላሉ ተብለው የታዘዙት 50 ተደራራቢ አውቶብሶች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ከላይና ከታች ተጓጓዦችን የሚይዙት ተደራቢ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተገጣጥመው ለአገልግሎት የሚበቁ ሲሆን፣ እነዚህ አውቶብሶች ጥቂቶቹ ለዕይታ ቀርበዋል፡፡  

  የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ እስካሁን ድረስ ከ8,000 በላይ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ያቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1,524 የተለያዩ አውቶብሶች ገጣጥሞ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

ከእነዚህ አውቶብሶች ውስጥ 550 ለአንበሳ የከተማ አገልግሎት ድርጅት፣ 410 ለፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት፣ 300 ለሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት ድርጅት እንዲሁም 264 አውቶብሶችን ደግሞ ለተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች አስረክቧል፡፡

በምርት ሒደት ላይ የሚገኙና ለርክክብ ካሉት መካከል የተዘጋጁ 100 የተማሪ፣ 50 ተደራራቢ፣ 700 ዘመናዊ የከተማ አውቶብሶች በቅርቡ ርክክብ ይፈጸማል፡፡ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪው ከገጣጠማቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ለአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሉ 2,374 አውቶብሶች ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች