Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልስሜትና ሙዚቃ

ስሜትና ሙዚቃ

ቀን:

ሙዚቃ የጾታ፣ የዕድሜ፣ የዘር፣ የኢኮኖሚና ሌሎችም የሰው ልጆች በየጎራው የሚከፋፈሉባቸው ልኬቶችን አልፎ የማስተሳሰር ጉልበት እንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሙዚቃ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጥረውን የስሜት መለዋወጥ ያስተዋሉ ተመራማሪዎች ምክንያቱን ለማወቅ ለዓመታት ተመራምረዋል፡፡ ሰዎች አንዱን ሙዚቃ ከሌላው በተለየ የሚወዱት፣ የሚመርጡትስ ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም ሞክረዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት ከተሠሩ ጥናቶች አንዱ የተጠነሰሰው እንዲህ ነበር፡፡ ቶሮንቶ የምትኖር የሥነ ልቦና ተማሪ ሕይወቷ ትርጉም አልባ እንደሆነ ይሰማትና ከራሷ ጋር ለመነጋገር ከከተማ ትወጣለች፡፡ አንድ ኮረብታማ ቦታ መኪናዋን አቁማ ሕይወቴን በምን መንገድ ብመራ ደስተኛ እሆናለሁ? ስትል ራሷን ትጠይቃለች፡፡ ምላሽ ለማግኘት አለመቻሏ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ ከቷት ነበር፡፡ አረፍ ለማለት መኪናዋ ውስጥ ገብታ ሬዲዮ ስትከፍት ክላሲካል ሙዚቃ ገጠማት፡፡ ልትገልጸው በማትችል መልኩ ሰውነቷ ተፍታታ፡፡ አንዳች ተስፋ ሰጪ ነገር እንደምታገኝ ይሰማትም ጀመር፡፡ በቀጥታ ትማርበት ወደነበረው ተቋም ተመለሰችና የሰው ልጆች ለሙዚቃ የሚሰጡት ምላሽ መነሻ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ጀመረች፡፡

ዶ/ር ቫለሪ ሳሊምፓር ከሦስት ዓመት በፊት ይፋ ያደረገችው ጥናቷ የተሠራው ለሰዎች የማያውቁትን ሙዚቃ አሰምቶ በአዕምሯቸው የሚሰራጨውን መልዕክት በመመዝገብ ሊወዱት ወይም ሊጠሉት የሚችሉበትን መንገድ ለመገንዘብ ነበር፡፡ የጥናቷ መነሻ ሰዎች የሚወዱትን ሙዚቃ በሚሰሙበት ወቅት ከፍተኛ ሐሴት ሲሰማቸው ዶፋሚን ንጥረ ነገር መለቀቁ ነው፡፡ ዶፋሚን የናረ የደስታ ስሜት ሲኖር ለምሳሌ ምግብ ሲበላና ወሲብ ወቅት እንደሚለቀቅ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

- Advertisement -

የመረጠቻቸው ሰዎች ሰምተው የማያውቋቸውን ሙዚቃዎች እንዲሰሙና ሲጨርሱ ሙዚቃውን ከወደዱት በሁለት ዶላር እንዲገዙ የሚያስችል ሥርዓት ዘረጋችና ጥናቱ ተጀመረ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቀድሞ የሚወዷቸውን የሙዚቃ ዘዬዎችና ከልጅነታቸው ጀምሮ የነበራቸውን የሙዚቃ የመስማት ልምድ የሚያስረዳ መጠይቅ ሞልተው ነበር፡፡ በጥናቷ መደምደሚያ ብዙዎቹ ሰዎች ከጥናቱ በፊት ከሚወዷቸው የሙዚቃ ዓይነቶችና ተሞክሯቸው ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሙዚቃዎችን ለመግዛት ፈቃደኛ ሆነው ተገኙ፡፡ እንደ ተመራማሪዋ ገለጻ፣ ከግኝቷ በተቃራኒው ተቀራራቢ ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች የተለያየ ዓይነት ሙዚቃ የሚመርጡበት አጋጣሚም አለና ጥናቱ በሌላ ዕይታም መቀጠል አለበት፡፡

እንደ ተመራማሪዋ ሁሉ ስለ ሰዎች የሙዚቃ ምርጫ የሚጠይቁ ብዙ ናቸው፡፡ ሙዚቃ ስናዳምጥ የምንፈልገው እሴት ምንድነው? የሙዚቃ ምርጫችን ከአንዱ ወደ ሌላው የሚያጋድለውስ በምን ምክንያት ነው? አንዳንዶች የሕይወት ተሞክሯቸውን ተመርኩዘው መሰል ይዘት ያለውን ዘፈን ይመርጣሉ፡፡ አንዳች ሁነትን ካዩበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ለሚያቀርብላቸው ሙዚቃ ቦታ የሚሰጡም አሉ፡፡ ሙዚቃን ባገኙት አጋጣሚ ብቻ የሚሰሙና እስከዚህም ትርጉም የማይሰጣቸው መኖራቸው ባይካድም፣ እንደ አንድ የሕይወት አንኳር ነገር የሚወስዱትም አሉ፡፡ አበረታች፣ ቀናና የሕይወትን በጎ ገጽታ የሚያሳይ ሙዚቃን የሚሹ በሌላ በኩል ሐዘንና ጥልቅ የስሜት መሰበር እንዲቀነቀንላቸው የሚፈልጉም ይገኛሉ፡፡

ወ/ሮ የምስራች ገብሩ ሙዚቃ በጎ መልዕክት አዘል ሲሆን ከሚመርጡት ወገን ናት፡፡ ‹‹ሙዚቃ ስሰማ የመልዕክቱ ጥልቀት ያመዝንብኛል፤›› ትላለች፡፡ ምንም እንኳን ዜማውም ሳቢ መሆን አለበት ብትልም፣ አንድ ሙዚቃ የሚያጠነጥንበትን ርዕሰ ጉዳይ ካላመነችበት አትሰማውም፡፡ በተለያየ ዕድሜ ላይ ሳለችና አሁንም ካለችበት ስሜት አንፃር የተለያየ ዘዬ ያላቸው ሙዚቃዎች ብትሰማም ቅድሚያ የምትሰጠው ቀዝቀዝ ላሉ ዘፈኖች ነው፡፡ ‹‹ምን እየተባለ እንደሆነ ለመስማት ዕድል ማግኘት እፈልጋለሁ፤›› ትላለች፡፡

ጠዋት ለልጆቿ ቁርስ እያዘጋጀች፣ ምሳ እየቋጠረች፣ ወደ ሥራ ስትሄድ መኪናዋ ውስጥ፣ ከሥራ ስትመለስና ቤት አረፍ ስትልም ሙዚቃ ታዳምጣለች፡፡ ‹‹ጃዝና ሐውስ ሚክስ በአብዛኛው እሰማለሁ፡፡ በሙዚቃው ስለሚነሳው ጉዳይ የመፍትሔ ሐሳብ ሲቀርብ ደስ ይለኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተስፋ ሰጪ ሙዚቃ ያነቃቃኛልም፤›› ትላለች፡፡

ሙዚቃ አነሳሽ መሆን እንዳለበት የምታምነው ወ/ሮ የምስራች፣ በተለይም ሰዎች ተስፋ በቆረጡበት ወቅት አፅናኝ ቢሆን ትመርጣለች፡፡ ሰሞኑን ደጋግማ እየሰማችው ያለው የጆን ሌጀንድ ‹‹ላቭ ሚ ናው›› ቤተሰብ ውስጥ ካለ ፍቅር አንስቶ እንደ ጦርነት ባለ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሰዎችም የፍቅርን ተስፋ ሰጪነት ያሳያል ትላለች፡፡

በእሷ እምነት፣ ሙዚቃ ካለችበት የስሜት ሁኔታ የምታልፍበትን መሣሪያም ነው፡፡ ሐዘን ሲሰማትም ይሁን ስትደሰት ስሜቷን የሚገልጹላት ሙዚቃዎችን መስማት ካለችበት ሁኔታ ጋር ራሷን እንድታስማማ ኃይል ይሆናታል፡፡ በሕይወቷ የሚገጥማትን ወደ ኋላ መለስ ብላ ለማስታወስም ሙዚቃን ትመርጣለች፡፡ ‹‹በሰው ላይ የሚፈራረቁ ዋና ዋና ስሜቶች ከምንም በበለጠ የሚገለጹት በሙዚቃ ነው፡፡ ሙዚቃ በሕይወቴ ትልቅ ድርሻ ስላለው የማዳምጠውን ስመርጥ በጥንቃቄ ነው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ዓለም ላይ በሚካሄዱ ክንውኖች ውስጥ ሙዚቃ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ለውጥን በመሻት የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን በማነሳሳት እንዲሁም በማፋፋምም ሙዚቃ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ በጥቁር አሜሪካውያን የሰብዓዊ መብት ትግል ሙዚቃ የነበረውን ድርሻ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንና ሌሎችም ትግሎችን በማጣቀስ ለለውጥ የሚያነሳሳ ሙዚቃ እንደሚወዱ የሚገልጹት አቶ ጥላሁን አስናቀ ናቸው፡፡

አቶ ጥላሁን ከወጣትነታቸው ጀምሮ አገራዊ ይዘት ላላቸው ሙዚቃዎች ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ‹‹በተለይም ከሕዝብ ለሕዝብ ወዲህ ትኩረቴ የሕዝቡን እውነታ የሚያንፀባርቁ፣ ለሕዝብ አንድነትና ኅብረትን የሚሰብኩ ዘፈኖች ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ በአብዮቱ ጊዜ የተሠሩ የሙዚቃ ካሴቶችን እንደ ‹‹ዓይን ብሌኔ እጠብቃቸዋለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ሙዚቃ ከሌሎች የኪነ ጥበብ ዓይነቶች በበለጠ ለሰው ልጅ ስሜት ቅርብ እንደሆነ በመግለጽም፣ ሙዚቃ ለውጥን መስበክ አለበት ይላሉ፡፡

በእሳቸው እምነት፣ በሰው ልጅ የዕለት ከዕለት ሕይወት የሚገጥሙ መሰናክሎች፣ በማኅበራዊ መስተጋብር ያሉ ፈተናዎችና የአገር ፖለቲካዊ ሥርዓትም በሙዚቃ መፈተሽ አለበት፡፡ የጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድና ጠለላ ከበደ ዘፈኖች ከሚጠቅሷቸው ጥቂቱ ናቸው፡፡ በሰምና ወርቅ ግጥም የማኅበረሰቡን እውነታ የሚያሳዩ ሙዚቃዎች ዘመን ተሻጋሪ እንደሆኑም ያምናሉ፡፡

የጥላሁን ገሠሠ ‹‹ጥሩ ሰው ፈልጌ ጓደኛ የሚሆነኝ፤ ፈልጌ ለማግኘት በምርመራ ላይ ነኝ›› የሚለው ስንኝ የሰዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት ያጠይቃል ይላሉ፡፡ የጠለላ ከበደ ‹‹ሎሚ ተራ ተራ የእማምዬን ነገር ጎረቤት አደራ፤›› የወቅቱን ሥርዓት ተቺ በመሆኑ ድምፃዊቷ እስከመታሰር እንደደረሰችም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ፍትሕና እኩልነት፣ ሰላምና ፍቅር ላይ የሚያተኩሩ ሙዚቃዎች የዘወትር ምርጫዬ ናቸው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

ሰዎች ዘወትር አውቀው የሚወዱትን ሙዚቃ ይለያሉ ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡ ጠቃሚ የሚባል መልዕክት ያለውን ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ያለ ምንም ምክንያት ዘፈን የሚመርጡም አሉ፡፡ ሙዚቃን ከይዘቱ ጋር ብቻ ማያያዝ እንደማይቻል የሚያምኑ ሰዎች፣ በተለያየ ቋንቋ የሚሠሩ ዘፈኖች ስለምን እንደሆኑ እንኳን ሳይታወቅ ሊወደዱ እንደሚችሉ ያጣቅሳሉ፡፡ ሰዎች እንዳሉበት ግላዊና ማኅበራዊ ሁኔታ የሚወዷቸው ዘፈኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለዋወጡም ይችላሉ፡፡

‹‹የሚያሳዝኑ ወይም ስለ ሐዘን የሚገልጹ ዘፈኖች እወዳለሁ፤›› የምትለው ሔራን ፍሬው፣ ሙዚቃዎች ከሷ ሕይወት ጋር የሚገናኝ ነገር ባይኖራቸውም ልብ የሚሰብሩ እስከሆኑ ድረስ ታዳምጣለች፡፡ እነዚህን ሙዚቃዎች ልውደዳቸው ብላ ባትሰማቸውም ሳታውቅ ምርጫዋ ሆነው ታገኛቸዋለች፡፡

በእሷ እምነት፣ ሐዘን ከስሜት ሁላ ጠንካራ ነው፡፡ ከፍቅር ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሐዘን ደግሞ የበለጠ ጥልቅ ይሆናል፡፡ ‹‹አገኘሁ ብሎ ከመደሰት አጣሁ ብሎ ማዘን የበለጠ የሚሰማን ይመስለኛል፡፡ ብሉዝና ጃዝ ሆነው ይህንን ስብራት የሚያንፀባርቁ ሙዚቃዎች ደስ የሚሉኝ ለዚሁ ነው፤›› ትላለች፡፡ ዘፈንን ለመውደድ ከሚያጠነጥንበት ጉዳይ ጋር መተሳሰር እንደማያስፈልግ ታክላለች፡፡ ሙዚቃን ጨምሮ ሌሎችም ጥበባዊ ሥራዎች ስሜት ገላጭነታቸውን ወይም ምስል ከሳችነታቸውን ማየት እንጂ ከአድማጭ ወይም ከተመልካች ስሜት ጋር ምን ያህል ተሳስረዋል? መባል አለበት ብላ አታስብም፡፡

የግርማ በየነ ‹‹ከሴቶች አብልጬ›› እና የኢታ ጄምስ ‹‹አይ ውድ ራዘር ጎ ብላይንድ›› ሔራን ከምትወዳቸው ሙዚቃዎች መካከል ትጠቅሳቸዋለች፡፡ የግጥምና ዜማ ደራስያኑ ሐዘንን የገለፀበትን መንገድም ታደንቃለች፡፡ ‹‹ስሜቶቹ ጠንካራ ስለሆኑ ባለሙያዎቹን አጭረው ያልፋሉ፤›› ትላለች፡፡ ሆኖም እሷ ሐዘን ሲሰማት ፍፁም ፀጥታ ስለምትመርጥ ዘፈኖቹን መስማት አትፈልግም፡፡

ሰአዳ ቃሲም ካንትሪ፣ አር ኤንድ ቢ፣ ጃዝ፣ አምባሰል፣ ትዝታ፣ ክላሲካልና ሌላም ዓይነት ሙዚቃ ትሰማለች፡፡ አንድን ሙዚቃ ስትሰማ አስቀድማ ዜማው ላይ ታተኩራለች፡፡ ዘፋኙ ምን እያለ እንደሆነ ልብ ሳትል ረዘም ላለ ጊዜ አንድ ሙዚቃ ልትሰማ ትችላለች፡፡ ‹‹ሙዚቃውን ስሰማው ልዩ ስሜት ስለሚሰጠኝ ስለምን እንደሆነ ሳላውቅም ልወደው እችላለሁ፤›› ትላለች፡፡

ከጠዋት እስከ ማታ አንዳንዴም ለሊትም ኤርፎን ከጆሮዋ አይጠፋም፡፡ ሙዚቃ መስማት የሚሰጣት እርካታ ከሰዎች ተለይታ ብቻዋን ብትሆንና፣ ምግብ ባትበላም ባዶነት እንዳይሰማት እንደሚያደርጋት ትናገራለች፡፡ ስትሠራ፣ ስትጓጓዝና ስትተኛም ከምትወዳቸው ሙዚቃዎች መለየት አትፈልግም፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ስትሰማ እልም ካለ እንቅልፍ ትነቃለች፡፡ በሙዚቃ ተመስጣ ባለችበት ልትቆም ወይም የእምርጃ ፍጥነቷ ሊጨምር ይችላል፡፡ በገለጻዋ ከሙዚቃ መሣሪያዎቹ ለሚወጣው ድምፅ ብቻ የምትሰጠውን ቦታ መረዳት ይቻላል፡፡

ሙዚቃን ከግጥሙ ወይም ከዜማው አንፃር ብቻ ነጥሎ ከመመልከት ይልቅ የሁለቱን መጣጣም የሚሹም አሉ፡፡ ሙዚቃን ሙዚቃ የሚያደርገው በሁለቱ መካከል የሚፈጠረው ውህደት ነውም ይላሉ፡፡ ‹‹ብዙ ሰው ትርጉም አልባ የሚላቸው እኔ ግን የምወዳቸው ዘፈኖች አሉ፡፡ እኔ በየጊዜው አዲስና ታዋቂ ሙዚቃዎችን ደጋግሜ እሰማለሁ፡፡ መስፈርቴ አዝናኝ መሆናቸው ነው፤›› ይላል ሚሊዮን ካሳ፡፡

በምድር ላይ አዲስ ነገር አይፈጠርም የሚለው ሚሊዮን፣ ነገሮችን ልዩ የሚያደርጋቸው የሰው ልጅ ዕይታ እንደሆነ ያምናል፡፡ ሙዚቃ የሚያውቀውን ነገር በተለየ መንገድ እንደሚያቀርብለት ይገልጻል፡፡ ‹‹ጓደኝነት፣ ስደት፣ ሞት፣ ጋብቻ ወይም ሌላም ሁነትን ባልተገነዘብኩበት መንገድ የሚያቀርብ ሙዚቃ ደስ ይለኛል፤›› ይላል፡፡ ሆኖም በሙዚቃ የሚነሳ ጉዳይ ትልቅና ትንሽ አለው ብሎ አያስብም፡፡

አሜሪካዊቷ ገጣሚና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማያ አንጀሎ ‹‹ሙዚቃ መሸሸግያዬ ነው፡፡ በኖታዎቹ መካከል ተጠቅልዬ ለብቸኝነት ጀርባዬን እሰጣለሁ፤›› የሚል አባባል አላት፡፡ ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ ‹‹ያለ ሙዚቃ ሕይወት ስህተት ትሆናለች፤›› ይላል፡፡ ፈረንሳዊው ጸሐፊ ቪክተር ሁጎ ሙዚቃ በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ ነገር ግን መባል ያለባቸውን ይገልጻል ሲል ተናግሯል፡፡ እንደየሰው የተለያየውን የሙዚቃ አመራረጥና አተረጓጎም ያመለክታሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...