Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሃያ ሦስት ሺሕ ቶን ብረት ለመግዛት የወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተሰረዘ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመከላከያ ፋውንዴሽን 23 ሺሕ ሜትሪክ ቶን አርማታ ብረት ለመግዛት አውጥቶት የነበረውን ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለመሰረዝ ተገደደ፡፡

በምትኩ ተቋሙ የአገር ውስጥ ጨረታ እንደሚያወጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡  ስድስት ያህል ዓለም አቀፍ የዓርማታ ብረት አቅራቢዎችን ሲያሳትፍ የነበረው ጨረታ የቴክኒክ ግምገማው ሲደረግ ቢቆይም፣ ተቋሙ በመጨረሻ ብረቱን ለመግዛት የሚያስችለውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ ጨረታውን መሰረዙ ተገልጿል፡፡

ዓለም አቀፍ ጨረታው ከወጣ በኋላ የአገር ውስጥ አምራቾች ተቃውሟቸው ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ተቃውሟቸውም ከዚህ ቀደም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካይነት የወጣውን ሰርኩላር ማናቸውም በመንግሥት ተቋማት የሚደረጉ የአርማታ ብረት ግዥዎች ከአገር ውስጥ አምራቾች ብቻ መገዛት አለባቸው የሚለውን የጣሰ ነው የሚል ነበር፡፡

ነገር ግን የመከላከያ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ብርጋዴር ጄኔራል ደግፌ በዲ፣ ዓለም አቀፍ ጨረታው የወጣው ከቀረጥ ነፃ መብትን ለመጠቀም በማሰብ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአርማታ ብረት ግዥው የመከላከያ ሠራዊት አባላትን የቤት ባለቤት ለማድረግ ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ለቤቶች ግንባታ ግብዓት እንዲሆን የወጣ ጨረታ መሆኑ ይታወቃል፡፡

መከላከያ ፋውንዴሽን ዓለም አቀፍ ጨረታውን ሲያወጣ የተሻለ ዋጋ ለማግኘትና የቤቱ ባለቤት ከሚሆኑ የሠራዊቱ አባላት ላይ ጫናን ለመቀነስ በማሰብ እንደሆነ ተዘግቦ ነበር፡፡

ነገር ግን ዓለም አቀፍ ጨረታው ከወጣ በኋላ የአገር ውስጥ አምራቾች በማኅበራቸው አማካይነት፣ ከብረታ ብረት ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች ጋር በጨረታው አግባብነት ላይ መነጋገራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህም ውይይትም ፋውንዴሽኑ ከዚህ በኋላ ጨረታ ሲያወጣ የአገር ውስጥ አምራቾችም እንዲሳተፉ እንዲያደርግ፣ የሚያወጣው ጨረታም ግልጽ እንዲሆን የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከአርማታ ብረት ግዥው በተጨማሪ መከላከያ ፋውንዴሽን ለቤት ግንባታ የሚያግዙ የሴራሚክ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የፅዳት ዕቃዎችን ለመግዛት ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በጨረታውም ለአርማታ ብረት የተወዳደሩትን ጨምሮ 33 ያህል አቅራቢዎች ተወዳድረዋል፡፡

የቤት ግንባታው ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ዋጋ ከሰላም ማስከበር ከሚገኘው ገቢ የሚሸፈን እንደሆነ ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች