Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጂቡቲ መንግሥት 70 በመቶውን የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ዕቃ የማስተናገድ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች የወደብ አማራጮችን መፈለጓን እንደማይቃወም ገልጿል

የጂቡቲ መንግሥት በዓመቱ የሚያስተናግደውን የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ዕቃዎች እስከ 70 በመቶ ለማስተናገድ የሚያስችሉትን መሠረተ ልማቶች በማሟላት ላይ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ዕቃ ለማስተናገድ አቅም እየገነባ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

የጂቡቲ ንግድ ምክር ቤትን 110ኛ ዓመት ምሥረታና የመጀመርያውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ለመዘገብ ወደ ጂቡቲ ላቀናው የጋዜጠኞች ቡድን እግረ መንገዳቸውን በጽሕፈት ቤታቸው ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የጂቡቲ ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ደዋሌህ፣ አገራቸው አብዛኛውን የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች ለማስተናገድ የሚያስችል የወደብ፣ የመንገድና የባቡር መስመሮች ግንባታን ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር እየገነባች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ የኢትዮጵያን ገቢና ወጪ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ለማስተናገድ ያላት አቅም ገና በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች ወደቦች መጠቀሟን እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ቢሆኑ ኑሮ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በቀጣናው ከጅቡቲ ባሻገር እየመጡ ያሉት አማራጭ ወደቦችን በሚመለከትም ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ በሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ፣ በሱዳን የሚገኘውን የፖርት ሱዳን እንዲሁም ወደፊት በኤርትራ የሚገኘው የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ አማራጭ ወደቦች እንደሆኑ አስውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ጂቡቲ በውድድር ሳይሆን፣ ክፍተትን የሚሞላ አጋር ሆና መታየት እንደምትፈልግ፣ አገሮች በሮቻቸውን ለዓለም ክፍት በማድረግ በተወዳዳሪነት የመሥራት አለያም በሮቻቸውን ለውጭ ውድድር በመዝጋት የሚያራምዱት ፖሊሲ እንዳለ አብራርተው፣ ጂቡቲ ግን በሯን ለሁሉም በመክፈት መሥራትን እንደምትመርጥ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዘመዳም አገሮችም ጂቡቲ አጋዥ ሆና እንደምትቀርብ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከሌሎች አገሮች ይልቅ ጂቡቲ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላትን የወደብና የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ እያካሄደች መገኘቷን ሲያብራሩም፣ የጂቡቲ መንግሥት የተበደረውን የ500 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ጠቅሰዋል፡፡

ይህን ገንዘብ በመበደር ጂቡቲ ኢንቨስት ለማድረግ የደፈረችው በኢትዮጵያ እያደገ የሚገኘው የገቢና ወጪ ዕቃዎች ፍሰት በሚገባ ለማስተናገድ እንደሆነ ተናግረው፣ መንግሥታቸው ይህንን ታሳቢ ባያደርግ ኑሮ ከባቡር መንገድ ይልቅ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚያገናኙ መንገዶችን ቢገነባበት ይመርጥ እንደነበር አስውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ዶራሌህ ያሉ ፈርጀ ብዙ የወደብ ግንባታዎችን ለማካሄድ ከ12 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ መመደቧን ይነገራል፡፡ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳም አገራቸው መበደር ከምትችለው የብድር ጣሪያ ላይ መድረሷን ተናግረዋል፡፡

የዓለም ባንክ ባንክ እ.ኤ.አ. የ2016 ሪፖርት መሠረት የጂቡቲ ሕዝብ ብዛት ከ940 ሺሕ በላይ ሲሆን፣ የኢኮኖሚው አቅምም (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በሁለት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ይህም ሆኖ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የጂቡቲ ወደብ አገልግሎት ለኢትዮጵያ የሚቀርብ እንደመሆኑ መጠን ለአገሪቱ በቀን ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝላት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች