Wednesday, May 22, 2024

ሚኒስትሮች በዘፈቀደ የውጭ ጉዞ ማድረግ ይችላሉ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ዓመት ተፈጥሮ ከነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ በኋላ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ሰኞ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ሚዲያ ብቅ ብለዋል፡፡

በዕለቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመጠየቅና ማብራሪያ ለመስጠት ብቻ መቅረባቸውን ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚመሩት ፓርቲና መንግሥት እያደረጉት ነው ስለተባለው በጥልቀት መታደስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ በአገራችን ልማታዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ብዙ ሥራዎችን የሠራ ድርጀት ነው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹በየጊዜውም ይኼንኑ ዓላማ ለማሳካት ራሱን በራሱ እያረመና እያስተካከለ ከራሱ አፈጻጸሞች እየተማረ የዘለቀ ድርጅት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሚመራውም መንግሥት ራስን በራስ የማረም መርህን ተከትሎ እየሠራ የሚገኝ መሆኑን፣ በቅርቡ የተካሄደውም የተሃድሶ እንቅስቃሴ በዚሁ መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአንድ የፖለቲካ ድርጅትና ራሱ ለሚመራው መንግሥት ወሳኝ ነገር የአመራር ሥርዓቱ መሆኑን በማመን፣ በቅርቡ በተደረገው በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል፡፡

የአገሪቱ ጥረት በሒደት የካፒታሊስት ሥርዓትን መገንባት መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ይኼንኑ መሠረት በማድረግም ሥርዓቱን የሚያጋግሙ አደጋዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በዚህ የመታደስ ሒደት መለየቱን ጠቁመዋል፡፡

ከሚያጋጥሙ አደጋዎች አንዱ የሚመራው አካል ቀስ በቀስ የራስን ሕይወትና ኑሮ የማሻሻል፣ የግል ብልፅግናውን የመፈለግ እንዲሁም የቆመለትን ዓላማ እየሸረሸረ መሄድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይኼ መጣመም በፍጥነት እስካልተቃና ድረስ በሒደት በተግባር የሚገለጽ ሌብነት ውስጥ እንደሚገባ፣ ይህም አገሪቱን አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ደረጃ ከፍተኛ አመራሩ ራሱን የገመገመው የመንግሥትን ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት ማዋል ሲገባውና ሌት ተቀን ተረባርቦ ውጤት ማምጣት ሲገባው ኑሮውን፣ ቤተሰቡንና ሕይወቱን በመምራት ዙሪያ እንደተጠመደ በይፋ አምነዋል፡፡

የሚያገኙትን ሕጋዊ ጥቅማ ጥቅሞች በመጠቀም አመራሩ በስንፍና መቀመጡን፣ ከዚህ አንስቶ እስከ ስርቆት ድረስ የመሄድ አዝማሚያ በግምገማው ወቅት እንደተጋለጠና ውይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል፡፡

መስዋዕትነት ከመፈለግና ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ መዝናናትን የመምረጥ፣ ቢሮ አለመገኘት፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ አለመሥራት፣ እንዲሁም የተለያዩ ጉዞዎችን የማብዛት በከፍተኛ ችግርነት መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ሥልጣንን ለኅብረተሰብ ለውጥ ብሎ ለወሰነ ፓርቲ የማይገቡ ሥነ ምግባሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በእነዚህ ችግሮች ላይ በጥልቀት ውይይት እንደተካሄደ፣ ከዚህ በኋላ ፓርቲው የማይታገሳቸው ጉዳዮች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

በፓርቲው በጥልቀት የመታደስ ሒደት በዋነኝነት ከተነሱት ችግሮች መካከል፣ አንዱ የአመራሩ መዝናናት ላይ መጠመድና የውጭ ጉዞ ማብዛት ይገኝበታል፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የውጭ ጉዞ የሚያደርጉት እንዴት ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዞ የማወቅ ኃላፊነት የለባቸውም? የሚኒስትሮቹ ሕጋዊ ተጠያቂነት እስከምን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ መንሸራሸር ጀምረዋል፡፡

የውጭ ጉዞ ለምን ዓላማ?

ይኼንኑ በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአሠራር ሥነ ሥርዓት መመርያ፣ ስለሚኒስትሮች የውጭ ጉዞ ዝርዝር ድንጋጌዎቸችን አስቀምጧል፡፡

መመርያው ሚኒስትሮች ከመንግሥታዊ ኃላፊነታቸው ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚያደርጉት ጉዞ ለአገር ጠቀሜታ ያለው መሆኑ የተረጋገጠና በአግባቡ ለመምራትና ሥርዓት ለመከተል የሚያገለግል መሆን እንዳለበት ያስረዳል፡፡ ሚኒስትሮች ማለትም በሁሉም ደረጃ ያሉትን እንደሚያጠቃልል ያስቀምጣል፡፡

በዚህም መሠረት ማንኛውም ሚኒስትር የውጭ ጉዞ የሚያደርግበት ዓላማ የአገርንና የመንግሥትን ተልዕኮ ለመፈጸም፣ አገርን በመወከል የአገርን ጥቅምና ስም የሚያስጠብቁ ተግባራትን ለማከናወን፣ ለአገርና ለወገን ጠቀሜታ የሚውል ልምድና ተሞክሮ ለማግኘት መሆኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአሠራር መመርያ ያብራራል፡፡

ሚኒስትሮች ከላይ ለተገለጸው ዓላማ ብቻ በመንግሥት አገልግሎት ስም የውጭ ጉዞ ማድረግ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈቃድ ማግኘት እንዲሁም ተፈቅዶላቸው ከተጓዙ በኋላ አጭር፣ ግልጽና በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባቸው መመርያው ይደነግጋል፡፡

የጉዞ ፈቃድ

ማንኛውም ሚኒስትር የውጭ ጉዞ ለማድረግ ሲያስብ አስቀድሞ የጠቅላይ ሚኒትሩን ፈቃድ በጽሑፍ ማግኘት እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ጉዞ ለማድረግ የሚፈልግ ሚኒስትር ከጉዞው መነሻ ቀደም ብሎ ስለጉዞው ዓላማና አስፈላጊነት፣ ለጉዞው የሚያስፈልገው ጊዜ፣ አብረው የሚጓዙትን የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከነሥራ ኃላፊነታቸው በማቅረብ ማስፈቀድ እንዳለበት ይገልጻል፡፡

ጉዞው የሚደረግበት አገር የጉዞውን ሙሉ ወጪ የሚሸፍን መሆኑን ወይም አለመሆኑን በመግለጽ የጉዞ ፈቃድ እንዲሰጠው ማስፈቀድ ይኖርበታል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ ከተገኘ በኋላም በቀረበው የጉዞ ዕቅድ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቶ አስፈላጊውን መመርያ እንደሚሰጥ በመመርያው ተደንግጓል፡፡

የሚኒስትሮች የዓመት ጉዞን አስመልክቶ ከሚያስነሳቸው ጥያቄዎች መካከል ጉዞ የሚደረግባቸውም ከተሞች ዝርዝር፣ በጉዞው ወቅት በምን ጉዳዮች ከነማን ጋር ውይይት ለማድረግ እንደታቀደ፣ ወጪውን የሚሸፍነው ሦስተኛ ወገን ከሆነ ማን እንደሆነና በምን ሁኔታ እንደሚሸፈን ማሳወቅ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የሚኒስትሮች የግል ጉዞ

ሚኒስትሮች ግለሰባዊ መብቶች ያሏቸው ቢሆንም፣ ከሕዝብና መንግሥት አገልጋይነታቸው የመነጨ ገደቦች ሊጣልባቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህም አንዱ በዘፈቀደ የውጭ ጉዞ ማድረግ ይገኝበታል፡፡

በዚህም የተነሳ ሚኒስትሮች ለግል ጉዳዮቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቅድሚያ በማስፈቀድና የተመደቡበት የመንግሥት ሥራ እንዳይበደል አስፈላጊውን ሁሉ በማመቻቸት፣ በራሳቸው ወጪ የውጭ ጉዞ ማድረግ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ ለመንግሥታዊ የሥራ ዓላማ ወደ ውጭ የተጓዘ ሚኒስትር፣ የተጓዘበትን የመንግሥት ሥራ በተግባር ካጠናቀቀ በኃላ የግል ጉዳዩን ለማከናወን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቅድሚያ በማስፈቃድ የመመለሻ ጊዜን ማራዘም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ለተራዘመው ኃላፊነት ተጨማሪ ጊዜ ወጪውን በራሱ የመሸፈን ኃላፊነት እንዳለበት ይገልጻል፡፡

ከሚኒስትሮች ጋር ስለሚጓዙ ቤተሰቦች

ከሚኒስትሮች ጋር ወደ ውጭ የሚጓዙ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አብረው ሄደው አብረው መመለስ እንዳለባቸው መመርያው ይገልጻል፡፡

ሚኒስትሮች ወደ ውጭ በሚጓዙበት ጊዜ የሚከፈሏቸው አበልና ሌሎች ወጪዎች በየጊዜው እየተጠና በመንግሥት እንደሚሸፈን ተቀምጧል፡፡

ከሚኒስትሮች ጋር ስለሚጓዙ የቤተሰብ አባላት አስመልክቶ በሚገልጸው ክፍል፣ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍቀድ እንዳለባቸው መመርያው ይገልጻል፡፡

‹‹ሚኒስትሮች የቤተሰብ አባላት አብረዋቸው እንደሚጓዙ የሚያቀርቡትን ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሁኔታው እያየ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ወጪውም እንደ አግባቡ እየታየ በመንግሥት እንዲሸፈን ሊፈቅድ ይችላል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

አጠቃላይ የውጭ ጉዞ ዓላማና መንፈሱ የተገለጸው ቢሆንም፣ በተለምዶ አጋጣሚዎች ሚኒስትሮች በዘፈቀደ ከመጓዝ እንዳልታቀቡ እንዲሁም ለምን ዓላማ እየተጓዙ እንደሆኑ እንደማያሳውቁ ይነገራል፡፡

ከላይ የተገለጸው መመርያ በ1996 ዓ.ም. የወጣና አሁንም ድረስ የሚኒስትሮች የምክር ቤት አሠራር የሚመራበት ቢሆንም፣ የውጭ ጉዞን በተመለከተ የተደነገገውን ማንም እየተጠቀመበት አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የሚኒስትሮችን ጉዞ በተመለከተ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጠውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን እያስፈቀዱ መጓዝ የሚገባቸው ቢሆንም፣ በዚህ መሠረት ነገሮች እየተፈጸሙ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሞኑ መግለጫቸው በግልጽ ተናግረዋል፡፡         

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -