Sunday, June 23, 2024

[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ስልክ ይደውልላቸዋል]

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሮ እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ነህ?
 • ዊኬንድ እንዴት ነበር?
 • ይኼ የኳስ ነገር ሲበጠብጠኝ ነበር፡፡
 • እርስዎም ተጎዱ እንዴ?
 • ጉዳት ቢሉህ ጉዳት ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እግር ኳስ ማለት እንደዚህ ነው እንዴ?
 • ምንድነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • ጨጓራዬ እንደዚሁ ሲላጥ ነበር፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔም እንደዚሁ ስቃጠል ነበር፡፡
 • እግር ኳሱን እኮ ጦርነት ነው ያደረጉት፡፡
 • እሱማ ተባሉ ማለት ይቻላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ ጨዋታው በሰላም የሚያልቅም አልመሰለኝም ነበር፡፡
 • እግር ኳስ የሰላም መሆኑ እኮ የቀረ ነው የሚመስለው፡፡
 • ለማንኛውም በጣም ነው የተቃጠልኩት፡፡
 • እኔ ግን መንግሥት ትልቅ ዕርምጃ መውሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡
 • መንግሥት? የምን መንግሥት?
 • ይኸው ራስዎ የኳሱን ችግር እየነገሩኝ አይደል እንዴ?
 • ልማታዊ መንግሥታችን እዚህ ሥራ ጠፍቶበት የእንግሊዝ ኳስ ውስጥ ይግባ እያልከኝ ነው?
 • ምንድነው የሚያወሩት?
 • ቅዳሜ አርሰናል 3ለ1 መሸነፉ እኮ ነው ያናደደኝ፡፡
 • ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አሉ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እኔ የማወራው ስለአገራችን ኳስ እኮ ነው፡፡
 • እዚህ አገር ኳስ አለ እንዴ?
 • ለነገሩ ኳስ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የምታወራው?
 • ለማንኛውም የአገሪቷ ኳስ የፖለቲካው መገለጫ እየሆነ ነው፡፡
 • ኳስና ፖለቲካ ምን አገናኘው?
 • እዚህ አገር ከተገናኙ ሰነባበቱ፡፡
 • እንዴት ሆኖ ነው የተገናኙት?
 • በአገሪቱ የሚታዩት ፅንፈኝነትና ክፍፍል በኳሱም እየተንፀባረቁ ናቸው፡፡
 • የምን ክፍፍል ነው?
 • ይኸው የኳስ ደጋፊዎችም በብሔር ተከፋፍለው እየተፋጩ ነው፡፡
 • ስማ ማንኛውም ብሔር የእግር ኳስ ቡድን የማቋቋም መብት አለው፡፡
 • ማቋቋማቸው አይደለም ችግሩ?
 • ታዲያ ምንድነው ችግሩ?
 • ደጋፊዎች በብሔር ተከፋፍለው እየተጋጩ ነው፡፡
 • እ…
 • ክቡር ማኒስትር ይኼ የብሔር ፖለቲካ በቃ ጦፎ ይኸው ኳሱ ላይ እየተንፀባረቀ ነው፡፡
 • የምታወራው አልገባኝም፡፡
 • ባንኩ በብሔር ነው፣ ቢራው በብሔር ነው፣ ቲቪው በብሔር ነው፣ ኳሱ በብሔር ነው፡፡
 • እና ብሔር ብሔረሰቦች ይክሰሙ እያልክ ነው?
 • እንደሱ አልወጣኝም፡፡
 • ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • አንድነታችንን ዘንግተን ልዩነታችን ላይ ካተኮርን በኋላ ዕጣ ፋንታችን መጠፋፋት ነው፡፡
 • ዝም ብለህ ጨለምተኛ አትሁን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ያፈጀ ምክንያታችንን ትተን ለሕዝቡ ችግር በአፋጣኝ መፍትሔ ብናመጣ ይሻላል፡፡
 • ምን ይፈጠር እያልክ ነው?
 • የሰላምና የአንድነት መድረክ የሆነው እግር ኳስ ሳይቀር የብጥብጥና የጥላቻ መድረክ እየሆነ ነው፡፡
 • ስማ ፖለቲካና ኳስ የተለያዩ መሆናቸውን አታውቅም?
 • ክቡር ሚኒስትር ብጥብጡ እየተከሰተ ያለው ስታዲየም ውስጥ ሳይሆን ከዚያ ውጪ ነው፡፡
 • መንግሥት ምን ያድርግ ታዲያ?
 • ይኼ እኮ የፖለቲካ ሥርዓቱ ዝቅጠትን ማሳያ ነው፡፡
 • አሁን በግልጽ እየዘለፍከን ነው፡፡
 • እንዲያውም የፕሪምየር ሊጉ ስም አንደኛውን ቢቀየር ይሻላል፡፡
 • ምን ይባል?
 • የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሊግ!

[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ስልክ ይደውልላቸዋል]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • እንዴት ነህ ጎረምሳው?
 • አለሁ ጋሼ፡፡
 • ዛሬ ከየት ተገኘህ?
 • አንድ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • ሰሞኑን መንግሥት ያወጣውን መግለጫ አልሰማህም?
 • የትኛውን መግለጫ?
 • ይኸው ራሳችሁን አጋልጡ እየተባለ ነው፡፡
 • ሙሰኞችን ነው?
 • በሌላ ቋንቋ ሙስኛ በለው፡፡
 • ታዲያ አንተ የምን ሙስና ውስጥ ገብተህ ነው?
 • ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላችሁ ራሳችሁን አጋልጡ እየተባለ ነው፡፡
 • አንተ ታዲያ ከዚህ ጋር ምን አገናኘህ?
 • ረሳኸው እንዴ ጋሼ?
 • ምኑን?
 • አንተ እኮ ነው የገዛህልኝ፡፡
 • ምኑን?
 • ዲግሪዬን፡፡
 • ምን?
 • ቤት ለምን ትቀመጣለህ ስትለኝ ነጥብ አልመጣልኘም ስልህ አትጨነቅ ብለህ እኮ ነው የገዛህልኝ፡፡
 • ለአንተ ነው እንዴ ያስመጣሁት? ለወንድምህ መስሎኝ?
 • ለእሱም አስመጥተህለታል ጋሼ፡፡
 • ታዲያ እሱ አልተጠየቀም?
 • እሱማ ውጭ ስለሄደ ማን ይጠይቀዋል?
 • ምን ላድርግልህ ታዲያ?
 • እኔም እኮ ላማክርህ ነው የደወልኩት፡፡
 • አሁን አንተን ጠይቀውሃል?
 • መጠየቄ አይቀርም፣ ሰሞኑን ደግሞ ጥሩ ትምህርት አለህ ብለው አሳድገውኛል፡፡
 • ማን ነው አንተን የሚጠይቅህ?
 • የሰው ኃይል አስተዳደሩ ነዋ፡፡
 • በቃ እደውልለታለሁ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የሰው ኃይል አስተዳደሩ ጋ ደወሉ]

 • ሄሎ ማን ልበል?
 • ማን ልበል ይላል እንዴ?
 • ይቅርታ ስላላወቅኩዎት  ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • በጣም ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ ትንሽ ተበሳጭቼ ነው፡፡
 • ምንድነው ያበሳጨህ?
 • ሰሞኑን መንግሥት ያወጣው መግለጫ ትርምስ ፈጥሯል፡፡
 • የትኛው መግለጫ?
 • ይኼ ስለሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የወጣው፡፡
 • ለምን?
 • እንዴ ይኸው በቃ ሁሉም ሠራተኞች ማለት ይቻላል ሐሰተኛ ማስረጃ ነው ያላቸው፡፡
 • እ…
 • እነዚህ ሠራተኞች ይባረሩ ቢባል በቃ ሥራ ማቆማችን አይቀርም፡፡
 • ሥራማ እንዴት ይቆማል?
 • ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?
 • በቃ ሠራተኞቹን መምከርና ከዛ ማስረጃቸውን እንደ ትክክለኛ ማስረጃ መቀበል ነው፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ምን የጨረቃ ቤቶች ራሳቸው ሕጋዊ ይሆናሉ አይደል እንዴ?
 • ይኼማ ትልቅ ወንጀል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም እኔም የደወልኩልህ የእህቴ ልጅ ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት ነው፡፡
 • የምን ችግር ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱም ሐሰተኛ ማስረጃ ነው ያለው፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው ታዲያ?
 • በቃ ምከሩት እያልኩ ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም ልጁ ግን ማን ነው?
 • ሰሞኑን እንዲያውም ዕድገት የሰጣችሁት ኢንጂነር ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እሱ እኮ የተሰጠው ኃላፊነት ትልቅ ተጠያቂነት ያለበት ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አዲስ የሚገነባውን ግዙፍ ሕንፃ በአግባቡ መቆጣጠር ካልቻለ የሚያደርሰው አደጋ ከባድ ነዋ፡፡
 • ምን እዚህ አገር የቀን ሠራተኛ ራሱ ሕንፃ የሚቆጣጠርበት አገር አይደል እንዴ?
 • የእሱ ግን ከዚህም ያለፈ ነው፡፡
 • ማለት?
 • ልጁ የብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን ሌላ አደገኛ መስመር ውስጥ ገብቷል፡፡
 • የምን መስመር ነው?
 • እንዲያውም ልጁ ሲቪል ኢንጂነር አይደለም እየተባለ ነው፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የተማረው?
 • የሙስና ኢንጂነሪንግ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በግምገማ የወጣ የመንግሥትና የፓርቲ ባልደረባቸውን ሆስፒታል ያገኙታል]

 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር እዚህ ምን ያደርጋሉ?
 • ሆስፒታል ቤቴ ከሆነ ሰነባበትኩ እኮ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አሉ የሚባሉ በሽታዎች በጠቅላላ አሉብኝ፡፡
 • በሞትኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከጨጓራ ጀምረህ እስከ አስም፣ ደም ግፊትና ስኳር ተሸክሜ ነው የምኖረው፡፡
 • አይዞኝ አይዞኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን አለፋህ የበሽታ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሆኛለሁ ብልህ ይቀለኛል፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር አሁንም ይቀልዳሉ አይደል?
 • ስማ በሽታዬን ከማወቄ የተነሳ ለራሴ መድኃኒት የማዘው ራሴው ነኝ፡፡
 • እንዴት?
 • የፓርቲ ግምገማ ላይ ስቀመጥ የስኳር መድኃኒት ነው የምወስደው፡፡
 • እሺ፡፡
 • የመንግሥት ግምገማ ከሆነ የደም ግፊት ነው የምወስደው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከለጋሽ አገሮች ጋር ስንገናኝ ደግሞ አስሜ ይነሳብኛል፡፡
 • ይገርማል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከግሉ ዘርፍ ጋር ስገናኝ ደግሞ ጨጓራዬ ነው የሚላጠው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ብቻ በአጠቃላይ በሽታዬን አውቀዋለሁ ለማለት ነው፡፡
 • ታዲያ ለእርስዎ እኮ የክብር ዶክትሬት ሳይሆን ትክክለኛው ዶክትሬት ነበር የሚገባዎት፡፡
 • ወድጄ አይደለም፡፡
 • ሰሞኑን በየሚዲያው ስለእርስዎ የምንሰማው ምንድነው?
 • ይኸው እኔም ተደናግጬ ቁጭ ብያለሁ፡፡
 • ግምገማው ከባድ ነበር?
 • ልባረር፣ ነፃ ልውጣ አላውቅም፤ አምባሳደር ልሁን አማካሪ የማውቀው ነገር የለም፡፡
 • ይኼን ያህል አስጨነቅዎት?
 • በፀሎት ላይ ነው ያለሁት፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • እርስዎ አንድ ባለሰባት ፎቅ ሌላ ደግሞ ባለዘጠኝ ፎቅ አለዎት አይደል እንዴ?
 • እሱማ አለኝ፡፡
 • ታዲያ በቃኝ ብለው ለምን አያስቀጥሉትም?
 • ምኑን? የታላቁ መሪ ራዕይን ነው?
 • ኧረ ኢንቨስትመንቱን፡፡
 • እንዲህ በቀላሉ አይለቁኝማ፡፡
 • ምን ያደርጉኛል ብለው ነው?
 • መቀጣጫ ሊያደርጉኝ ይችላሉ፡፡
 • እንደዚያ ከሆነማ መግባት ነዋ፡፡
 • የት? ገዳም ነው?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ታዲያ የት ነው የምገባው?
 • ጫካ!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...