Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጉምቱዎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተዘከሩበት ዓውድ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለየት ያለ ክስተት መታየት ጀምሯል፡፡ ለአገርም ሆነ ለፋይናንስ ኢንዲስትሪው ዘርፍ መልካም ሠርተዋል ለተባሉ ሰዎች ዕውቅና የመስጠት  ጅምሮዎች እየታዩ ነው፡፡

 ሐሙስ ጥር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጡ ለቆዩ ሁለት አንጋፋ ባለሙያዎች ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡

እንዲህ ያለው ፕሮግራም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀውን ፕሮግራም ያስታውሳል፡፡ አቶ ጌታሁን ናና በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የግል ባንኮች እንዲስፋፉ ያደረጉት ጥረት ዕውቅና ተሰጥቶት በክብር መሸኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከዚያ ፕሮግራም በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ባለውለታዎችን የሚያመሠግን ፕሮግራም ከተፍ ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ባለሟሎችን በአግባቡ የመዘከር ተግባር እንዲለመድ ፍላጎቱን ገልጾ ነበር፡፡ ይኸው መድረክም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደገም አድርጓል፡፡

 ከደርግ ውድቀት በኋላ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች ጀርባ ትልቅ ቦታ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ሁለት የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢዎች ዕውቅና እንዲሰጣቸው ገዥው ባንክ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉና የሚመሩት አስተዳደር፣ ለ25 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን በቦርድ አባልነትና በቦርድ ሰብሳቢነት ላገለገሉት አቶ ነዋይ ገብረአብ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ከአንጋፋው የኢኮኖሚ ባለሙያው ከአቶ ነዋይ ባሻገር፣ ባንኩን በሰብሳቢነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ፋንታዬ ቢፍቱንም በዕውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ ያደረገ ነበር፡፡ ሁለቱ ጉምቱዎች ከብሔራዊ ባንክ ጋር በነበራቸው የሥራ ግንኙነት  ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ የሠሯቸው ሥራዎች የተብራሩበትና ለዚህ አገልግሎታቸውም  ዕውቅና የተሰጠበት ፕሮግራም ተስተናግዷል፡፡

 ፕሮግራሙን በማሰናዳት ቀዳሚ የሆነው ብሔራዊ ባንክ ሲሆን ገዥው አቶ ተክለወልድ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢነትና ከመንግሥት ኃላፊነታቸው በቅርቡ በጡረታ ስለተገለሉት አቶ ነዋይና ለዕውቅና ስላበቃቸው ምክንያትም አብራርተዋል፡፡

ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የብሔራዊ ባንክ የቦርድ አባልና ሰብሳቢ ሆነው ካበረከቱት አስተዋጽኦ በላይ፣ አገሪቷ ለደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አጋዥ የሆኑ አገራዊ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ በማድረግና በትግበራቸውም ላይ የአቶ ነዋይ አሻራ ከፍተኛ እንደነበር አቶ ተክለወልድ አስረድተዋል፡፡

አቶ ነዋይ ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት አስተዋጽኦ ካበረከቱ ጥቂት ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ናቸው ያሉት አቶ ተክለወልድ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የነፃ ገበያ ሥርዓት ከጀመረበት 1984 ዓ.ም. ጀምሮ በጦርነት የደቀቀውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራና ሥር የሰደደው ድህነት እንዲቀንስ በማድረግ ሥራዎች ውስጥ ጎልተው ከሚጠቀሱ ባለሙያዎች ተርታ ይመደባሉ፡፡ የአገሪቱ የዕዳ ጫና እንዲቀንስ፣ የሕዝብ ገቢ እንዲያድግ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲገባና እንዲስፋፋ በማድረግም ስማቸው ተሞካሽቷዋል፡፡ የአገሪቱን ፈርጀ ብዙ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚመለከቱ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎችን ከመቅረጽ ጀምሮ እስከ ትግበራቸው ሒደት የላቀ ተሳትፎ በማድረጋቸው፤ ይህም ውጤት በማስገኘቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል በማለትም ስለ አንጋፋው ባለሙያ መስክረዋል፡፡

አቶ ነዋይ በአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስክርነት የሰጡት የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ለይኩን ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ዕዳ ለማስቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ የአሪቱን የወደፊት የኢኮኖሚ አቅጣጫ ለማመላከት ብዙ ስለመሥራታቸው በመጥቀስ አቶ ነዋይን በብዙ ገልጸዋቸዋል፡፡

የዕዳ ስረዛ

በወርሃ ግንቦት 1983 ዓ.ም. የደርግ ውድቀት ሲታወጅ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሚታሰበውም በላይ የተንኮታኮተበት ጊዜ ነበር፡፡ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ስለአገሪቱ ኢኮኖሚ ሲገልጹ ደርግ ምንም የተወው ነገር እንዳልነበረ፣ ትቶ የሄደው ባዶ ካዝና ነው የሚለው ንግግራቸው ይታወሳል፡፡

ችግሩ ባዶ ካዝና መረከቡ ሳይሆንና ያለቅጥ የተከማቸው የአገሪቱ የውጭ ብድር ዕዳ ለአዲሱ ሥርዓት ትልቅ ፈተና እንደነበር ሲገለጽ ይታወሳል፡፡ የዕዳው ስሌት ኢትዮጵያ በነበረችበት የዳሸቀ የኢኮኖሚ አቅም ተከፍሎ የሚያልቅ እንዳልነበረ ግልጽ በመሆኑ፣ አንዱ አማራጭ ለአገሪቱ የተለመነውን ያህል ዕዳ እንዲሠረስ መማፀን ነበር፡፡

በደርግ ጊዜ ለጦር መሣሪያና ለሌሎች ግዥዎች የዋለው ብድር ጫፍ ላይ የወጣበት ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተክለወልድ፣ ይህ ዕዳ ካልተቀነሰ አገሪቱን ማልማትም ሆነ ለልማት የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ስለማይቻል ይህንን ፕሮግራም ይዞ ተደራድሮና ተወያይቶ ማስቀነስ ትልቁ ተግባር ሆኖ እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡ አቶ ተክለወልድ እንዳሉት፣ ከ25 ዓመታት በፊት አገሪቱ የነበረባትን ዕዳ ለማሠረዝ የሚሠራ ግብረ ኃይል ሲቋቋም፣ የዚህ ቡድን አባል በመሆን የተሳተፉት አቶ ነዋይ እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ አጥናፉ ገለጻ፣ አቶ ነዋይ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች ውስጥ ካሳረፏቸው አሻራዎች መካከል የአገሪቱን ዕዳ ለማሠረዝ ያደጉት ውጤታማና ትልቅ ተግባር የሚጎላ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ለዕዳ ስረዛ በያቅጣጫው ጉዞ ተደርጓል፡፡ በዚህ ‹‹ጉዞ ዕዳ ስረዛ›› መርሃ ግብር ተሳታፊ ከነበሩ አባላትና በዕለቱ ፕሮግራም ላይ ከተገኙት የወቅቱ የሥራ ኃላፊዎች መካከል አንዱ አቶ ሱፊያን አህመድ ነበሩ፡፡

አድካሚ በነበረው የዕዳ ስረዛ ዘመቻ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ዕዳ ከነበራቸው አገሮች አንዷ ሰሜን ኮሪያ እንደበረች አቶ ሱፊያን አስታውሰዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከምትከተለው ርዕዮተ ዓለም አኳያ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ሲቀየር ሸሪኳን ካጣጭው ከዚህች አገር ጋር ዕዳ እንድትቀንስ ለመደራደር መጓዝ የቱን ያህል ከባድ እንደበነር የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አስታውሰዋል፡፡ አቶ ለይኩንም ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር የነበውን አታካች ድርድር በአሸናፊነት ለመወጣት የአቶ ነዋይን አስተዋጽኦ ዘክረዋል፡፡

የአበባ ዘርፍና አቶ ፋንታዬ

ኢትዮጵያ ለወጪ ንግድ ከምታቀርባቸው ሸቀጦች ውስጥ አበባ የተካተተው የዛሬ 16 ዓመታት ግድም ነው፡፡ አበባ የአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ሊሆን እንደሚችል ሲጠነሰስ፣ ሐሳቡንም ተቀብሎ ሥራ ላይ ለማዋል ይደረግ በነበረው ዝግጅት ወቅት ይካሄዱ የነበሩ የሐሳብ ፍጭቶች ይታወሳሉ፡፡ በተለያዩ መድረኮችም ደጋግመው ተንፀባርቀዋል፡፡ ለአበባ ምቹ እንደሆኑ ከታሰቡትና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ውስጥ ቦታ ለማግኘት የነበረው ትርምስ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ አበባ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ስለመሆኑ ቀድሞ እምነት ከነበራቸው ጥቂት የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል አንዱ አቶ ፋንታዬ ቢፍቱ ነበሩ፡፡

አቶ ፋንታዬ የአበባ ልማት በኢትዮጵያ እንዲጀመር ሐሳቡንም መንግሥት እንዲቀበለው ለማድረግ ሲሞግቱ ቆይተዋል፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ተግባር እንዲገባ በማድረጉ ሥራ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸው፡፡

በእርግጥም የአበባ ልማት ዛሬ ላይ ከሚገኙ ከአገሪቱ አሥር ዋና ዋና የወጪ ንግድ ሸቀጦች ውስጥ አንዱ ሆኗል፡፡ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱም ቢሆን ከ220 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል፡፡ ቀድሞ እንደታሰበውና ተስፋ የተደረገበትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ባያስገኝም፣ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ለአበባ ዘርፍ መጎልበት የአቶ ፋንታዬ አስተዋጽኦ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል፡፡ አበባንና የአቶ ፋንታዬን ጥረት ወደኋላ መለስ ብለው ያስታወሱት አቶ ተክለወልድ፣ ‹‹አቶ ፋንታዬ የአበባ ልማት እንዲጀመር ብዙ የታገለ፣ በኋላም የተሳካለት ሰው ነው፤›› ብለዋቸዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ መብቃት የአቶ ፋንታዬ አስተዋጽኦ እንደታከለበት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በሽግግሩ መንግሥት ጊዜ በኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ለመሥራት ወደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጽሕፈት ቤት በማቅናት ሥራ ቀድመው በመጀመር የሚታወቁት አቶ ነዋይና አቶ ፋንታዬ መሆናቸውም ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ጀርባ የነበራቸውን ትልቅ ሚና እንደሚሳይ ተነግሮላቸዋል፡፡

በዕለቱ አንጋፋዎቹን ለመዘከር በተጠራው መድረክ ከታደሙ የፋይናንስ ባለሙያዎች መካከል 80ኛ የልደት በዓላቸውን በቅርቡ የሚያከብሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ሌላኛው ተናጋሪ ነበሩ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ከአቶ ነዋይና ከአቶ ፋንታዬ ጋር አብረው ተምረዋል፡፡ አብሮ መማር ብቻም ሳይሆን፣ በወቅቱ ይካሄዱ በነበሩ የተማሪዎች ንቅናቄዎች ውስጥ አንዳቸው ፕሬዚዳንት ሌላኛው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነዋይ ደግሞ ጸሐፊ ሆነው ስለማገልገላቸውም አስታውሰዋል፡፡ እንዲህ ያለው የዕውቅና መድረክ መልካም ጅምር መሆኑን የገለጹት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ዕውቅና የመስጠት ልማዱ በሌሎችም መስኮች ሊቀጥል እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከኢኮኖሚና ፋይናንስ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ባለሥልጣናት የተካፈሉበት ነበር፡፡ አቶ ሱፊያን አህመድን ጨምሮ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ማንያዘዋልን ጨምሮ በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሠሩ የነበሩ መሪዎችም  ታድመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች