Monday, October 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ለሜጋ ፕሮጀክቶች የሰጠውን ትኩረት ያህል ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታም ይስጥ!

መንግሥት በተያዘው ዓመት መጨረሻ 30 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶችን ለባለ ዕድለኞች እንደሚያስተላልፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 131 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ እየተገነቡ መሆኑን፣ ቤቶቹም በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለፈላጊዎች እንዲተላለፉ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የተደመጠው የቤቶች ግንባታን መቀዛቀዝና እንዲያውም መቆምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባል ጥያቄ በቀረበላቸው ጊዜ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር እጅግ መሠረታዊ ከሚባሉ ፍላጎቶች መካከል የዜጎች ዋነኛ ፈተና የሆነው የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤቶች እጥረት የተነሳ ዜጎች ለከባድ ምሬት ተዳርገዋል፡፡ ለኑሮ ተስማሚ ካልሆኑ ጎስቋላ መንደሮች ጀምሮ በተለያዩ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች ከአቅም በላይ በሆነ ኪራይ መከራቸውን እያዩ ያሉ በርካታ ዜጎች፣ መንግሥት መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ይሰጠናል ብለው እየቆጠቡ ቢጠባበቁም ጉም የመዝገን ያህል ሆኖባቸዋል፡፡

እንደሚታወቀው በ1996 ዓ.ም. የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ባለፉት 13 ዓመታት ባደረገው አዝጋሚ ጉዞ፣ 140 ሺሕ ያህል ቤቶች ተገንብተው ለዕድለኞች ተላልፈዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የተመዘገቡ የመጨረሻዎቹ ነዋሪዎች ከዓመታት ቆይታ በኋላ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይስተናገዱ ተብሏል፡፡ በ2005 ዓ.ም. አንድ ሚሊዮን ለመሆን ጥቂት የቀራቸው ዜጎች በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 ፕሮጀክቶች ተመዝግበው እየቆጠቡ ነው፡፡ በ10/90 የተመዘገቡ በአጭር ጊዜ ሲስተናገዱ፣ በ20/80 እና በ40/60 መርሐ ግብሮች ውስጥ ያሉት ግን አዝጋሚውን ሒደት እየጠበቁ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት አንዳችም ምዝገባ ባለመካሄዱ፣ በአጋጣሚ ሌላ ዙር ምዝገባ ቢጀመር የቤት ፈላጊዎች ቁጥር በሁለትና በሦስት እጥፍ እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተመራቂዎች በየዓመቱ 100 ሺሕ ያህል በመድረሳቸው፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አንገብጋቢነትን የበለጠ ጨምረውታል፡፡ ሥራ የያዙ ወጣቶች የቤት ኪራይ ዋጋን መቋቋም ስለማይችሉ ሳይወዱ በግድ ከወላጆች ጋር እየኖሩ ነው፡፡ ጋብቻ እየፈለጉ በዚህ የኪራይ ዋጋ ምክንያት ብቻ በላጤነት ለመኖር የተገደዱ ብዙ ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው በደርግ ጊዜ መሬት እየተመሩ የራሳቸውን ጎጆ የሚቀልሱ፣ በአነስተኛ ወለድ በሚገኝ ብድር በማኅበራት እየተደራጁ ቤቶቻቸውን የሚገነቡ ዜጎች በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ብዙ ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘም በኋላ በማኅበራት ተደራጅተው ቤቶቻቸውን የገነቡ ብዙ አሉ፡፡ በኋላ ግን ከመሬት ድልድል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ሙስና በመስፈኑና በተጨማሪም በከተማው ውስጥ የመሬት ጥበት በማጋጠሙ ወደ ሌላ መፍትሔ ተገባ፡፡ ይህም መንግሥት መሬት እያዘጋጀና በጀት እየያዘ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ነው፡፡ ነገር ግን ያለፉትን 13 ዓመታት ጉዞ ስንቃኝ የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ የሆነ የማስተንፈስ ሥራ ቢከናወንም፣ አሁንም ችግሩ እግር ተወርች ይዟል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ቢመድብም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን 16 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ቢያደርግም፣ ተመዝጋቢዎች በየወሩ ቢቆጥቡም ፍላጎትና አቅርቦት ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡

መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እያሳተፈ ሲገነባ የተገኙ ልምዶችን ከስኬት አንፃር ብቻ ለመመልከት ከሞከረ በጣም ተሳስቷል፡፡ 140 ሺሕ ቤቶችን ገንብቶ ማስተላለፍና 131 ሺሕ ቤቶችን መገንባት በራሱ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር ትልቅ ግምት ቢሰጠውም፣ ከማኅበራዊ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ግን እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ ከወር ቀለብ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከልጆች ትምህርት ቤትና ከተለያዩ ወገብ የሚያጎብጡ ወጪዎች በተጨማሪ፣ በየወሩ እየቆጠቡ ቤት ለማግኘት በጉጉት የሚጠባበቁ ዜጎች ከእነ ቤተሰቦቻቸው በሚሊዮኖች ይቆጠራሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የኑሮ ጫና ውስጥ ያሉ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚደገፍ ቢሆንም፣ አካሄዱ ግን ዘገምተኛ በመሆኑ መፍትሔ ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው፡፡

ችግርን ከሥር ከመሠረቱ ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ አካል ነው እንደሚባለው፣ አሁን በተያዘው አካሄድ ብቻ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎትን ማሟላት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ ሰሞኑን በፓርላማ ለመጠየቅ እንደተሞከረው የገንዘብ እጥረት ትልቁ ችግር ሲሆን፣ ሌላው መሠረታዊ ችግር ደግሞ የማስፈጸም አቅም ብቃት ማነስ ነው፡፡ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም በፍፁም ግንባታ ማካሄድ አይቻልም፡፡ የማስፈጸም አቅም ማነስ ደግሞ ለጥራት መጓደል ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ በአንዳንድ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች ቤት በዕጣ የደረሳቸው ዜጎች ለማጠናቀቂያና ለማስተካከያ ሲባል ብቻ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል፡፡ የተገነቡት ቤቶች ውስጥ የተገጠሙት የኤሌክትሪክ፣ የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮችና የመፀዳጃ ቤቶች ዕቃዎች ከጥራት ደረጃ በታች መሆን በራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር እንዳለ ሆኖ በየዓመቱ ከሚፈለጉ የመኖሪያ ቤቶች ቁጥር አንፃር መንግሥት ምን ያህሉን ያሟላል? ለሚለው በጥሩ ሁኔታ ምላሽ ለማግኘት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው አጭርና ግልጽ ነው፡፡

በዚህም መሠረት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ካለው ሰፊ ፍላጎት አንፃር ወደ ግንባታ የሚገቡበትን አመቺ ሁኔታ በማጥናት የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቤቶችን እንዲገነቡ ማበረታቻና ማትጊያ ማዘጋጀት፣ ዜጎች በማኅበር እየተደራጁ የራሳቸውን የጋራ መኖሪያዎች እንዲገነቡ ዕድሉን መስጠት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የኮንዶሚኒየም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቢገነቡም፣ በውድ ዋጋ ተከራይተው የሚኖሩባቸውም ሆኑ የሚነግዱባቸው መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎቱ እየጨመረ የመጣውን የመጠለያ ችግር፣ እስካሁን በነበረው አሠራር ለመፍታት መሞከር ውጤት አያመጣም፡፡ ይልቁንም ችግሩ የበለጠ እያበጠ ሄዶ ማኅበራዊ ትርምስ እንዳይፈጥር በፍጥነት አማራጮችን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት ለሜጋ ፕሮጀክቶች የሰጠውን ትኩረት ያህል ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታም ይስጥ!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...