በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት የፓርላማ አባላት ጥር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መልስ በሰጡበት ወቅት የትራፊክ አደጋ ከመቼውም በላይ አስከፊነቱ እየጨመረ መሄዱን በመጠቆም ይህን ችግር ለመቅረፍ በኤችአይቪ ላይ የተደረገው ዓይነት ጠንካራ ዘመቻ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገሪቱ አስከፊ እየሆነ የመጣው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ መደረግ ካለባቸው ነገሮች መካከል የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን ጠበቅ ማድረግ አንደኛው እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገቢው ልምምድና ብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፈቃድ ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ መንጃ ፈቃድ መያዝ ተመራጭ አካሄድ እየሆነ እንዳለም ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደትን ጠበቅ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረግጠዋል፡፡
የትራፊክ አደጋውን ሲገልጹ የመንገዶች በሥራ ሰዓት መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ብቻም ሳይሆን በመደበኛ ጊዜዎች ላይ እየተጨናነቁ መሆናቸውም ሌላ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የቀረበ ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ቁጥር ከሌሎች አገሮች በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ ነገር ግን አነስተኛ ተሽከርካሪ ባለበት ሁኔታ እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ ብዙ ነው፡፡ ለትራፊክ አደጋ ከሚቀመጡ ምክንያቶች በፍጥነት ማሽከርከርና ቸልተኝነት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ የሥልጠና መጓደል፣ ጠጥቶና ቅሞ ማሽከርከርም ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸው በጥናቱ ተቀምጧል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 2007 ዓ.ም. ላይ በትራፊክ አደጋ በቀን አሥር ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 31 ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በ2007 ዓ.ም. 3,847 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ 5,918 ከባድ 6,508 ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚሁ ዓመትም ከ668 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም መውደሙን ከትራንስፖርት ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መንጃ ፈቃድ አሰጣጥን ማሻሻል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአገሪቱ የተጭበረበረ የመንጃ ፈቃድ በስፋት እየዋለ በመሆኑ እንደሆነ የባለሥልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወቃል፡፡ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን ከማሻሻል በተጨማሪ ፈቃዶቹ በማዕከላዊ ጣቢያ እንዲመዘገቡ ማድረግ እንደ መፍትሔ ተጠቅሶ ነበር፡፡