Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትእኛና የዓለም ኢኮኖሚ የሚዛን ጨዋታ

እኛና የዓለም ኢኮኖሚ የሚዛን ጨዋታ

ቀን:

በጳውሎስ ደሌ

የእስካሁኑ የዓለም ኢኮኖሚ የምዕራብ የበላይነት የሠፈነበት ነው፡፡ ይኼ የበላይነትም ጥሬ ዕቃና ርካሽ ጉልበት ከመቦጥቦጥ ጋር ተያይዞ ኖሯል፡፡ በዚህ ተያያዥነት የተካሄደ ኢንዱስትሪያዊ ግስጋሴና ከየትኛውም አቅጣጫ የሚጎርፍ ትርፍ፣ የምዕራብ አገሮችን የኑሮ ደረጃ ሽቅብ ሲያወጣው ቆይቷል፡፡ ይህም በተራው በእነዚህ ሀብታም አገሮች ውስጥ የተለመዱ ፋብሪካዎችን አንቀሳቅሶ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ መሸጥን አስቸጋሪ እያደረገ መምጣቱ፣ ፋብሪካዎችን እየዘጉ የምርት ወጪ ወደሚቀንስበት አካባቢ ማዛወርን በዚያው ልክ አፍጥኗል፣ አስፍቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የምዕራብ ኢኮኖሚ ይበልጥ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ በኢንዱስትሪያዊ ዕቃዎች ማሻሻያ ምርምርና ፍልሰፋ ላይ ከማተኮር ባለፈ፣ ፋይናንስን ባካተተ የተስፋፋ የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል፡፡ አዳዲስ መራቀቅ ያለባቸውን ምርምራዊና ኢንዱስትሪያዊ ክፍሎች ለራስ አድርጎ ቀደምቶቹን ርካሽ ጉልበት በሚተራመስባቸው አካባቢዎች የማዛወሩ ሒደት ግን የፀና የሥራ ክፍፍል አላስከተለም፡፡ በሒደቱ ውስጥ የቻይና በኃያልነት መመዘዝና የህንድ ፈጣን ዕድገት ለምዕራቡ የበላይነት አደጋ ደቅኗል፡፡

  1. በቻይናና በአካባቢዋ ያለው ኢንዱስትሪያዊ ዕድገት በነባርነት በሚታወቁት የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የኬሚካል፣ ወዘተ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ የተገደበ ሳይሆን ምዕራባዊያኑ ባተኮሩባቸው የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምርምር፣ ፈጠራና ፍብረካ ውስጥ እየዘለቀና እየገሰገሰ ያለ ነው፡፡ በምዕራብ የቀሩትን ኢንዱስትሪዎች ወጪ ወደሚቀንሱ አካባቢዎች ማዛወሩ ያለገደብ ቢቀጥል የሥራ መስኮች የባሰውን እየጠበቡ የሚፈጥሩት ማኅበራዊ ቀውስ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ ለአገር ውስጥ ሥራዎች የአገልግሎት መስክን መተማመኛ ማድረግ እንዳይቻልም ደቡብ እስያውያኑ በርካሽ ዋጋና በሚስብ መስተንግዶ ከጉብኝት፣ ከሕክምና፣ ከትምህርት፣ ከመዝናኛና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙትን ገቢዎች ሁሉ እየተሻሙ ነው፡፡ በሆሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ ላይ የሆንግ ኮንግና የህንድ ተቀናቃኝነት እየተጠናከረ ይገኛል፡፡
  2. በቻይናና በአካባቢዋ በተስፋፉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምዕራባውያን የውጭ ኢንቨስትመንት ቢኖርም፣ እውነታው ዋና አትራፊዎቹ ያው ምዕራብያውያን ናቸው ብሎ የሚያስደመድም አይደለም፡፡ የምዕራባውያን የትርፍ ተጋሪነት በተለያየ መልክ ቢኖርም፣ አካባቢያዊ የይዞታ መሠረት ያላቸው ኩባንያዎች በርካታ ናቸው፡፡ በአካባቢ ሳይወሰኑ ባህር ተሻግረው የሚፎካከሩ ግዙፍ ኩባንያዎችም ተፈጥረዋል፡፡ በጠፈር ምርምሩ መስክ ቻይናና ህንድ ገብተውበታል፡፡ በጠፈር ቱሪዝም ሥራ ላይም ቢሆን ቻይና የምትሠለፍበት ጊዜ ብዙ ሩቅ ላይሆን ይችላል፡፡ የጠፈር ቱሪዝም ሥራ ላይ በገባችም ጊዜ የሚከፈለውን ዋጋ የትናየት በመቁመጥ የዓለም ሀብታሞች ኪስ ዋና አላቢ እንደምትሆን (ህንድ ተቀናቃኝ ሆና ብቅ እስካላለች ድረስ) ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡
  3. የገንዘብሽን ዋጋ ከፍ ካላደረግሽ በታሪፍ ጭመራ እንከላከልሻለን የሚል ማስፈራሪያ የቻይናን የወጪ ንግድ የርካሽ ዋጋ ብልጫ እንደማያከሽፍ፣ ቻይናም ጥቅሟን በሚጎዳ ደረጃ የዩዋንን ምንዛሪ እንደማትሰቅል የሚያመላክቱ ለውጦች አሉ፡፡ ቻይና አሁን የአገር ውስጥን የፍጆቻ አድማስ አስፍታ ከቢሊዮን በላይ የሚቆጠር ሕዝቧን የኢንዱስትሪ ሸቀጦቿ አንድ ትልቅ መዳረሻ በማድረግ ላይ እየሠራች ትገኛለች፡፡

ከዚህ ሌላ ቻይና ሸቀጥ አውጥቶ ከመነገድና ዶላር እያጠራቀሙ የአሜሪካን የበጀት ጉድለት ከመሸፈን ተላልፋ በእስያ፣ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ውስጥ ያላንዳች ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ ወዳጅነት እየመሠረተች በመንግሥታዊ ብድር መልክ፣ ጥሬ ዕቃ በማሰስና በማልማት፣ በፍብረካና በግንባታ ዘርፍ ካፒታል እያሸጋገሩ ትርፍ መሰብሰብ ውስጥ ተሠማርታለች፡፡ (ለዚህ የባህሪ ለውጥ ምክንያቱ ከኢሕአዴግ በኩል እንደሰማነው ቻይና ውስጥ የርካሽ ጉልበት ችግር ስለመጣ ሳይሆን የኃይል ኢኮኖሚ ድንበር ዘለል ሚና ውስጥ በመግባቷ ነው፡፡) አብሮም በአገር ውስጥ ለሚመረቱ ሸቀጦቿ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ውጪ ባሉ አያሌ አገሮች ውስጥ ሰፊ ገበያ እያስፋፋች ትገኛለች፡፡ ህንድም በዚህ አቅጣጫ ውስጥ እየተጓዘች ነች፡፡

- Advertisement -

አሜሪካና አውሮፓ የቻይናን ምርት በታሪፍ ሰቅለው ህንድን መተኪያ እንዳያደርጉ፣ ህንድም ርካሽ የሸቀጥና የሠራተኛ ዋጋን ጥቅሟ አድርጋ የምትንቀሳቀስ ስለሆነ፣ ዞሮ ዞሮ በርካሽ ሸቀጥ ገበያቸው መወረሩና ወደ ህንድ የሚልኩት ምዕራብ ሠራሽ ዕቃ በዋጋ መክበዱ አይቀርም፡፡ ህንድም እንደ ቻይና የገንዘቧን ዋጋ ከፍ በማድረግ የርካሽ ሻጭነት ብልጫዋን መስዋዕት ማድረግ የምትሻ አይደለችም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም እጃቸውን ባስገቡበትና በሚያስገቡበት ቴክኖሎጂ ሁሉ ሊመረት የሚችለውን ሸቀጥ ዋጋ የትናየት አውርደው ገበያውን መቆጣጠር እንደሚችሉ ያውቁታል፡፡ ህንድ አሁን የያዘችው 35 ዶላር በሚሸጥ ኮምፒውተር የተጥለቀለቀ ገበያ የመፍጠር ትልም የዚህ አብነት ከመሆኑም በላይ፣ የዓለምን ኢኮኖሚ ሚዛን ገና ወደፊት እንደሚያናጉት የሚጠቁም ነው፡፡

አሜሪካና አውሮፓ ከቻይና የሚገቡ ምርቶችን በቀረጥ ጭማሪ ቢከላከሉና ለመልማት ከሚውተረተሩ አካባቢዎች የሚመረቱ ተራ የፋብሪካ ምርቶች ያለቀረጥም ይሁን በቀላል ቀረጥ እንዲገቡ ቢለቁ፣ የውስጥ ገበያ ወረራ የቅርብ ፈተና አይሆንባቸውምና የውስጥ አነስተኛ አምራችነትን መስፋፋት አያሰናክልባቸውም፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ ለውጥ አንደኛ የቻይና ኩባንያዎችን ጥቅም ተጋሪነት የሚያስቀር አይደለም፡፡ አሁንም በውጭ ኢንቨስትመንት አማካይነት ያለቀረጥ በማስገባት ዕድሎች እየተጠቀሙ ነው፡፡ ሁለተኛ ከቻይና የሚመጡ ዕቃዎችን በቀረጥ አስወድዶ ገበያ ተሻሚነታቸውን የማድከም ተግባር፣ ቻይና ውስጥ የተሰማሩ የአሜሪካውያንና የአውሮፓውያን አምራች ኩባንያዎችን ጥቅም አብሮ የሚያደክም ይሆናል፡፡

ከዚያ አልፎ ገበያ በታሪፍ የታገደበት አገር የአፀፋ ምላሽ ስለሚሰጥ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ ቻይና የሚያቀኑ ምርቶች እንደ ቻይና ያለ ሰፊ ገበያን የማጣት በቀል ይደርስባቸዋል፡፡

አሜሪካና አውሮፓ ወደ ታሪፍ ከለላ ሄዱም አልሄዱም አሁን ያለው አዝማሚያ እንደሚያሳየው የደቡብ እስያ ክልል ግስጋሴ የዓለማችን የኢኮኖሚ እምብርት (የገንዘብ ካፒታልና ዋና የቴክኖሎጂ መናኸሪያ) የመሆን የመድረሻ ውጤትን ያዘለ ነው፡፡ አዲሷ ኃይል ቻይና የደሃ አገሮችን መንግሥታት በጭፍራነት ለመሳብ ከአሜሪካና ከምዕራብ የላቀችበት ዋና ብልጠት ‹‹በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም›› በሚል ፖሊሲዋ ነው፡፡ ያለ ፖለቲካዊ መመዘኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን ታሰላለች፡፡ ‹‹በልማት አጋርነት›› ራሷን አሞካሽታ ታበድራለች፡፡ አሜሪካና አውሮፓ በሚበልጧት ‹‹ዕርዳታ›› ውስጥም እየገባች ነው፡፡ ያለቀረጥ የደሃ አገሮችን ጥሬ ምርት ወደ አገሯ እንዲገባ የመፍቀድ ሥልት መጠቀምም ጀምራለች፡፡ ኩባንያዎቿ የትኛውም የምዕራብ ኩባንያ በጨረታ ሊወዳደራቸው በማይችልበት ዝቅተኛ ዋጋ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ይገነባሉ፡፡ የማዕድን ልማት ሲከራዩም በተቆጠበ ወጪ የማምረት አቅማቸው ላይ በመተማን ተፎካካሪን የሚረታ ዋጋ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

  1. ከዓለም ሲሶ ያህል የዓለም ሕዝብ በቻይናና ሕንድ ውስጥ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የኢንዱስትሪያዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላዳረሰው ድህነት እንደልብ ነው፡፡ በዚህ ላይ ዝቅተኛ ሥራን ሳይንቅና ለችግር በቀላሉ ሳይበገር ከትንሿም ክፍያ አንጀት አስሮ የመቆጠብ ጥንካሬ ያለውን የሕዝብ ሀብት፣ የአገሮቹ አጠቃላይ መለያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ እናም በቻይናም ሆነ በህንድ ያለው ርካሽ የሠራተኛ ሀብት እስከ ከፍተኛ ሙያተኛ ድረስ በቀላሉ ተዝቆ የማያልቅ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ያለው የልማት ተዛነፍ እንደሚነግረን፣ ሥራዎችን ወደ ሌላ ማዛወር አስፈላጊ የሚያደርግ የሠራተኛ ዋጋ ውድነት የቅርብ ችግር አይሆንባቸውምና ሥራዎችን ወደ ራሳቸው መሳብና ማስፋፋት አንዱ ልዩ ብልጫቸው ሆኖ ይቆያል፡፡

ተጣጣሪነትና የገንዘብ መፍለቂያ ቀዳዳዎችን የማስተዋል ንቃት ከሕዝብ አንስቶ እስከ መንግሥት ድረስ የሚንፀባረቅ ሌላ ጥንካሬ ነው፡፡ ከአገራቸው ውጪ በደቡብ ፓስፊክም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የተሠራጩ ቻይኖችና ህንዶች ከቁጠባ ባህል ጋር የጀርባ ማንነታቸውን የማይረሱ መሆናቸው ትልቅ የዕድገት ሀብት ነው፡፡ ይኼን ለማጤን የፈለገ በቻይና የኢንዱስትሪ እመርታዊ ዕድገት ውስጥ የቻይና ክፉ ጠበኛ የምትመስለው ታይዋን ምን ያህል እጇ እንዳለ ማስተዋል ይበቃል፡፡ በአጭሩ ከዋናው የቻይና ምድር ውጪ ያሉ ቻይናውያን በኢንቨስትመንት በመሳተፍ፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገባት፣ ቴክኖሎጂ በመመገብና የውጭ ንግድ ድልድይ በመሆን የሚሠሩ ጥቅመ ብዙ አቅም ናቸው፡፡ ከእንግሊዝ ቅኝ ጋር በተለያየ ቦታ የተሠራጩት ህንዶችም ይኼን ዓይነቱን ባህርይ የተጎናፀፉ ናቸው፡፡

በተጨማሪ ቻይና ከቲቤት ጉዳይና ከውስጥ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ረገጣ ችግሯ በቀር በዓለም አቀፍ አሸባሪነት መጠመድ የሌለባት፣ እንዲያውም ለምዕራብ ጠንቅ ተደርገው በሚታዩና የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳይሆኑ በሚፈሩ አገሮች ላይ ሲመከርና ማዕቀብ ሲጣል፣ ‹‹የሚያዋጣው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ነው›› በሚል አቋም ጥርስ ውስጥ ሳትገባ የኢኮኖሚ ጥቅሟን የምታሯሩጥ ነች፡፡

እነዚህን ከመሰሉ ጠንካራ ጎኖቿ አንፃር በአፍጋኒስታን ጦርነትና መፈልፈያው በሰፋና መምጫው በማይታወቅ ዓለም አቀፍ ሽብርተኛነት የተጠመዱት፣ የሽብር ጥቃት ተወጥኗል የሚል መረጃ በደረሰ ቁጥር በጭንቀትና በልዩ ቁጥጥር የሚወጠሩት፣ እስራኤልና አሜሪካን በመርገም የምትታወቀው የኢራን የኑክሌር ባለቤት የመሆን ዕድገት የሚያርዳቸውና ከጥርስ መውጫ ብልኃቱ የጠፋቸው (ሃይማኖታዊ አሸባሪነትን በጣጥሶ ለማምከን የፍልስጤምን ችግር ፈትቶና ከጉልበተኛነት መንገድ ተቆጥቦ የተቃወሱና ከጥንታዊ ሥልተ ኑሮ ያልወጡ አካባቢዎች የልማት ሽግግር እንዲያደርጉ ሞተር የመሆን ዋነኛ መፍትሔ በተግባር አልጨበጥ ብሏቸው፣ በከሰረ ወታደራዊ መንገድ ውስጥ የሚዳክሩት) አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ ምሽግ የለሽ ቢባሉ ማጋነን አይሆንም፡፡

ወደ ትሪሊዮን ዶላር የተጠጋ የቻይና ዕዳ የተሸከመች፣ የበጀትና የንግድ ከፍተኛ ጉድለት እያለባት የሰፋ የስለላ የጦርነትና የዕርዳታ ወጪ የወረሳት፣ አንድ መዓት ገመናዋን መደበቅ ያልቻለችና በተጋለጡ ሰነዳዊ የግፍ ቅሌቶቿ የሰብዓዊ መብት ግንባር ቀደም ‹‹ታጋይነቷ›› የከሰረባት አሜሪካ ጉልበቷን እያዛለች ያለች ነች፡፡ በነፃ ገበያ አቀንቃኝነት ቀንደኛ የነበረችው አሜሪካ ዛሬ የውስጥ ገበያዋን የመከላከል ጭንቀት ውስጥ መግባቷና በአንፃሩ፣ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እ.ኤ.አ. ከ1999 እስከ 2001 ገና ማሻሻያዎች ታደርግ የነበረችው ቻይና አሁን የከለላ ተቃዋሚና የ‹‹ነፃ ገበያ›› ጠበቃ ሆና አሜሪካን ለመተቸት መብቃቷ፣ መጪውን የኃይል ለውጥ የሚናገር ትንቢት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለሞባይል ስልክ ለኮምፒዩተርና ለመሳሰሉት የሚውል በተራ የእንግሊዝኛ አጠራር ‹‹ሬር ኧርዝ›› የሚባለውንና 90 በመቶ ያህል ብቸኛ መገኛ የሆነችበትን ይኼንን ማዕድን በጥሬ ዕቃነት ለመሸጥ መሰሰቷም የነገ ፍላጎቷን ይጠቁማል፡፡

  1. በቻይና የዓለም ኢኮኖሚን የመቆጣጠር ግስጋሴ ውስጥ ሁነኛ እንቅፋት ሆነው የሚገኙት የርካሽ ዋጋ ሸቀጦቿ በገቡባቸው የደሃ አገሮች ገበያዎች ሁሉ የውስጥ አምራቾችን እየሰባበሩ የሚያከስሩ መሆናቸው፣ ከርካሽ ዋጋ ጋር ጥራታቸው የተጓደለና ሐሰተኛ ሥራዎች አብረው እየሰረጉ የሚያደርሱት ጥቃት፣ እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስተሮቿና ተቋራጮቿ ባነሰ ወጪ ብዙ የማሠራት ጥረቶች በተቀባይ አገር ተቀጣሪዎች ዘንድ የሚፈጥሯቸው ቅዋሜዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች በተቀጣጠለ ቁጣና ጥላቻ የአውዳሚ በቀል ሲሳይ ሆኖ ከመባረር ጀምሮ፣ ደንበኞቻቸው የሆኑ አገሮችን በቀውስ እስከማጠናቀቅ፣ ብሎም በሌላ ተፎካካሪ ገበያዎችን የመነጠቅ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው፡፡

አሜሪካና የአውሮፓ አገሮችም አኅጉራዊ ገበያዎችን ላለማጣት መፍጨርጨራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አሁንም የ‹‹አጋርነት›› እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው፡፡ የአሜሪካኖቹና የአውሮፓውያኑ ቀጥተኛ ኢንዱስትሪያዊ ኢንቨስትመንት እንደ አፍሪካ ባሉ የርካሽ ጉልበት አካባቢዎች ቢሰማራና ጥራትን ብልጫው ቢያደርግ በሞልጬ ብልጠትና በኮሾ ዕቃ የቆሰሉ ገበያዎችን ሁሉ ማሸነፍ አይከብደውም፡፡ ከቀረጥ ነፃ በሆነ ወይም በአነስተኛ ቀረጥ ተመልሰው ወደ አሜሪካ አውሮፓ እንዲገቡ መፍቀድም ጉዳት ሳይሆን ከራስ ወደ ራስ የሚሄድ ጥቅም ይሆናል፡፡ ዕድገት ለቸገራቸው አገሮች ፋብሪካዎችን ማምጣታቸውና የፋብሪካ ሸቀጦችን ወደ ውጪ እንዲልኩ ማስቻላቸውም፣ በራሱ ለሌሎች የጥቅም ዋስትናዎች መደራደሪያ ሊሆኗቸው ይችላል፡፡ አንድ ቢሊዮን ያህል ሕዝብ ያላት ባለብዙ ማዕድኗ አፍሪካም ይኼንን ዓይነቱን ቀዳዳ በውል ማጤንና የዓይን ማረፊያነቷን በፖለቲካ መረጋጋትና በልማት ማሳደግ ይኖርባታል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ ውድድሩና ገበያ የማጣት አደጋው በደቡብ እስያኑ ግዙፎች በኩል ለሚታየው ጮቅ አትራፊነት፣ የሸቀጥ ጥራትና የሐሰት ሥራዎች ችግር መፍትሔ ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ገና ከአሁኑም በአውሮፓና በአሜሪካ የተረፈውን የመኪና ፋብሪካ ከዋጋ ሰበራ ጋር ጠራርጎ ለመውሰድ፣ በጥራት ረገድ ጉድለትን የማስወገድ ትግሉ እየተጧጧፈ ነው፡፡ እናም አሜሪካና አውሮፓ ላይ ያንዣበበው አደጋ በቀላሉ የማይባረር ነው፡፡

  1. ይኼ ማለት  ግን ለእነ ቻይና መንገዱ አልጋ ባልጋ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ በቅድሚያ በአጠቃላይ አነጋገር የዓለም ኢኮኖሚ በአንድ አገር መዳፍ ውስጥ መግባት በየትኛውም አገር የሚፈለግ አይደለም፡፡ የኃያላኑ የገበያ ጥበቃና የሚዛን ክብደት ትግልም ውስብስብ ነው፡፡ ፊት ለፊት ቻይናና አሜሪካን ብናይም በሁለቱ ጫፎች በኩል የሚሠለፉትን አባሪዎች በአሁኑ ጊዜ በእርግጠኝነት መለየት ከባድ ነው፡፡ ‹‹ብሪክ›› የሚባለውን የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የህንድና የቻይና ቅርርብ የጎራ አስኳል መጀማመሪያ አድርጎ መገመት ቢቻልም በውስጡ ብዙ ሩጫዎች አሉበት፡፡ በብዙ ቢሊዮን ዶላሮች የአክሲዮን ድርሻ የብራዚልን የባህር ዳርቻ ነዳጅ ለማልማት ቻይና ያደረገችው የቅርብ ጊዜ ስምምነት የቻይናን መግዘፍ ብቻ ሳይሆን፣ ብራዚል በአካባቢያዊ ልማት ስም ላቲን አሜሪካን በሥሯ አድርጋ ለመመንደግ የምታደርገውን እንቅስቃሴም የሚጠቅም ነው፡፡ የህንድና የቻይና አንድ ላይ መግጠም (የሁኔታዎች ዕድገት እንደሚፈጥረው የጥቅም ሽግሽግ) ሊሆን የሚችልና ግዙፍ የሚዛን ክብደት የሚፈጥር ነው፡፡ ነገር ግን ከሶቪየት ኅብረትና ከአሜሪካ ትንንቅ ጊዜ ጀምሮ በሁለት ጎራ በኩል ጥቅምን እያስጠበቁ የመራመድ ልምድ ያላትና ዛሬ በአሜሪካ በኩል ለሚዛን መድፊያነት የጭንቅ ጊዜ አጋር ያህል እንደምትፈለግ ያወቀችው ህንድ (ባራክ ኦባማ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም.  በህንድ ፓርላማ ፊት ያደረገውም ንግግር ይኼንኑ ያወጀ ነው) ተፈላጊነቷን እስከ ጠፈር ምርምር የሰፋ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማግኘት በሚቻላት ሁሉ እንደምትጠቀምበት ግልጽ ነው፡፡

ከህንድ አመራር በኩል የተነገረውን ‹‹የአሜሪካውያንን የሥራ ዕድሎች የመስረቅ ፍላጎት የለንም›› የሚል አስሊ ንግግር ቀደም ብሎ ከተጀመረው የህንድን ሥራ ከጥራት ጋር አዛምዶ የማስተዋወቅ እንቅስቃሴ ጋር ያገናዘበ፣ ህንድ በየትኛውም ኃይል ሥር ከመቆየት ያለፈ ፍላጎት እንዳላት መረዳት ይችላል፡፡ ሩሲያ ከቻይና ጋር ጉድኝት እንዳላት ሁሉ በነዳጅና በተፈጥሮ ጋዝ ሀብት አቅርቦቷ በአውሮፓ በጣም ተፈላጊ ነች፡፡ እሷም አውሮፓን ለቴክኖሎጂ ትፈልጋለች፡፡ ስለሆነም የሩሲያ አሠላለፍ በእነዚህ ጥቅሞችና ከአውሮፓ-አሜሪካ ጋር ባላት የፖለቲካ ግንኙነት መኮስኮስና መለስለስ ጭምር የሚወሰን ነው፡፡ አሜሪካና አውሮፓም ቢሆኑ ዛሬ ከቻይና ጋር ባለ የጥቅም ትግላቸው አንድ ሚዛን ጫፍ ላይ የተቀመጡ ይምሰሉ እንጂ፣ የአውሮፓ ጀርመን ልቆ የመውጣት ፍላጎት እንዳለ ነው፡፡ የአሜሪካ ወዳጇ ጃፓንም ከእብደትና ከእሳት ራሷን ጠብቃ ከእስያ እስከ አፍሪካ ድረስ የኢኮኖሚ ወዳጅነቷን እያሰፋች ያለች አገር ነች፡፡

  1. በልዕለ ኃያልነት መውጣትና መንከባለል ከታሪክ እንደምንረዳው ለስላሳ ሒደት አይደለም፡፡ የቅርቡ የሶቪየት ኅብረት መውደቅ እንኳን ብዙ መናጋትን ፈጥሯል፡፡ የዓለም አቀፍ መገበያያና የሀብት ማከመቻቻ የሆነው የአሜሪካ ዶላር እንዳይሆን ሆኖ ዋጋው ቢወርድ እንኳን፣ ዓለምን (ቻይናን ጭምር) ምን ያህል ሊረብሽ እንደሚችል መገመት ነው፡፡ ውጤቱ ከክስረት አልፎ የዶላርን ዓለም አቀፍ ገንዘብነት እስከ ማስቀረት የሰፋ የአሜሪካ መንሸራተቻ ሌላ ምዕራፍ ሊሆን ይችላል፡፡

የበላይነትን ያለማጣት ትግሉ፣ የቻይናን የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ የውስጥ ችግር ከታይዋንና ከቲቤት ጉዳይ ጋር አጠላልፎ የሞት ሽረት መድረኩ ያደርገውም ይሆናል፡፡ (አሁንም በቻይና ስላለው የፖለቲካ ነፃነት ዕጦት በተደጋጋሚ የሚነሳው የቻይና ዜጎች የመብት ጉዳት እንቅልፍ ከልክሎ ሳይሆን ቻይና በውስጥ ቅራኔዎቿ ብትዋጥልን ተብሎ ነው) የአሜሪካ የበላይነትና ከለላ ገለል ካለ መፍቻ አጥተው ሲፍተለተሉ የቆዩ ሌሎች ቅራኔዎች ጦርነት በጦርነት ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል፡፡ ቀውስና ድውታው ወደ መልካም አቅጣጫ ሊታጠፍ ይችልም ይሆናል፡፡ ከኃያልነት በላይ የሰው ልጅን ጠቅላላ ህልውና ሥጋት ላይ የጣለው የአየር ንብረት መዛባት ችግር ገዝፎ አጥፊ አኗኗርን የሚቀይርና ለተፈጥሮ እንክብካቤ የሚሰማሙ የቴክኖሎጂ እምቅ ሀብቶችን ነፃ የሚያወጣ አረንጓዴ አብዮት በዓለማችን ቢያቀጣጥልስ? በአጭሩ መጪው ዓለም በእስያውያን የሚዘወር ቢመስልም፣ ይኼ ውጤት የማይቀር መሆኑ ግን እርግጥ አይደለም፡፡ ባለብዙ አቅጣጫ የኃያልነት ፉክክር እስካለ ድረስ ግን ታዳጊ አገሮች ካወቁበት (ገዢዎቻቸው ለሥልጣናቸው ሲሉ ከአንድ ኃይል አገር ጋር እስካላጣበቋቸው ድረስ) እሽቅድድሙን ለዕድገታቸው ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

በመጨረሻም የዶናልድ ትራምፕ አቋሞችን በድፍኑ ያልታሰበባቸውና ከአሜሪካ ጥቅም ጋር የሚጋጩ አድርጎ መቁጠር ይመጣ ይሆናል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ በወጪ ቅናሽ እየተማረኩ ከአሜሪካ የወጡ ሥራዎችን በታክስ ቅነሳ መልሼ እስባለሁ ማለት ሳይቸግር ቻይናን ነገር መፈለግ ሳይሆን፣ ትርፍ በሚዘውረው ካፒታሊስታዊ የዓለማችን መጠቃለል ውስጥ የመጣንና የበለፀጉትን አገሮች በፋይናንስ በአገልግሎትና በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ሥራዎች እያጣበበ (ኢንዱስትሪያዊ የሥራ ዕድሎችን እያኮማተረ) ያለ ተቃርኗዊ አዝማሚያን የማርገብ ሙከራ ነው፡፡ ወጪ ወደቀነሰበት የሚያስሮጠውን የትርፍ ፍላጎት አቻችሎ ሥፍራ ማስቀየር ግን ከባድ ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

ከእስያ ጋር መተናነቅንና የኔቶን ወታደራዊ ጎራ ጊዜ ያለፈበትና ለአሜሪካ የማያስፈልግ የገንዘብ ኪሳራ አድርጎ ትራምፕ ያየበትን ማዕዘን (ሥራዎችን ከማስመለስ ፍላጎቱ ጋር አገናዝቦ) ከዓለማችን መጠቃለል ያፈነገጠና አሜሪካን ከዓለም መድረክ አውጥቶ ወደ ግቢዋ የሚወስድ (አይሶሌሽኒስት) በማለት መተርጎምም ስህተት ነው፡፡ እንዲያውም የአሜሪካንና የአውሮፓን የውስጥ ገበያ በርካሽ ዋጋ እስከማበጥና የፈጠጠ የገበያ ጥበቃ እንዲያደርጉ እስከመግፋት እየዘረጠጠ የሚገኘውን የቻይናን ከርሰ ሰፊ የንግድ ጮካነት፣ ትራምፕና አሜሪካዎቹ የአሜሪካ ልዕለ ኃያላዊ ጥቅም ዋና ባላጋራ አድርገው የመገንዘባቸው ምልክት ነው፡፡ ከሩሲያ ጋር ያለ ትግልን ወደ ወዳጅነት የመቀየር የትራምፕ ዝንባሌም በግላዊ የከበርቴ ጥቅም ውስጥ አንሶ የሚብራራ ሳይሆን፣ ዘመን ከከዳው አሮጌ ባላጋራ ጋር የማያስፈልግ ትንንቅ ማካሄድን አቋርጦና ከአዲሷ ቻይና ጋር እንዳይወግንም ወደ ምዕራባውያኑ ሠልፍ ውስጥ አስገብቶ የቻይናን አስፈሪ ልዕለ ኃያላዊ ግስጋሴና የኢኮኖሚ ውጊያ በተሰበሰበ ኃይል መመከት ከሚል ንድፍ ጋር የተያያዘ ይመስላል፡፡ በ‹‹አንድ ቻይና›› ነባር መግባባት ላይ አንገራግሮ ጉዳዩን ለኢኮኖሚያዊ መደራደሪያ ለመጠቀም መፈለግም በዚህ ንድፍ ውስጥ ሊካተት የሚችል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...