ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አገሮች በተለይም አውሮፓ በበረዶ በሚሸፈኑበት በአሁኑ ወቅት ምግብ ለማግኘት የሚቸገሩ ወፎች ይሰደዳሉ፡፡ ቅዝቃዜውን መቋቋም ያልቻሉ ወፎች ስደታቸው በቡድን ሲሆን፣ የብዙዎቹ መዳረሻም አፍሪካ ናት፡፡ የበረራ መስመራቸው ስምጥ ሸለቆ በመሆኑ፣ ብዙዎቹም ኢትዮጵያን ይረግጣሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስደት የሚያሳለፉት ወፎች ታዲያ የቱሪስት መስብህም ናቸው፡፡ ሰሞኑን የኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ ይዞት የወጣው ጥናት፣ ስደተኛ ወፎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከዚህ ቀደም ስደት ይጀምሩበት ከነበረው ወቅት ቀድመው መሰደድ ጀምረዋል ብሏል፡፡
በአምስቱ አህጉር በሚገኙና በመቶዎች በሚቆጠሩ የወፍ ዝርያዎች ላይ የተደረገን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ የአየር ንብረት ለውጡ ወፎች ምግብም ሆነ የወፍ ጎጆ የሚሠሩበት ቦታ እንዲያጡ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ ያለጊዜያቸው እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ የመፈልፈያ ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ ወደ ሥፍራቸው እንዲመለሱ ስለሚያደርግ፣ ወፎቹ እንዲመናመኑ ብሎም እንዲጠፉ ሊያደርግ እንደሚችል ጥናቱ ጠቁሟል፡፡