Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገራዊ ፋይዳ ያላቸው መረጃዎች

በጌታቸው አስፋው

አንድ ፈላስፋ አንድ ጊዜ ለጓደኛው ብዙ ገጽ ደብዳቤ ጽፎ የደብዳቤው መጨረሻ ላይ፣ ‹‹ጓደኛዬ ይቅርታ አድርግልኝ ብዙ ገጽ ደብዳቤ የጻፍኩልህ ጊዜ ስላጣሁ ነው፤›› አለው፡፡ ማሰቢያ ጊዜ አጥቼ ዝባዝንኬውን ሁሉ በማተት ጻፍኩልህ ማለቱ ነው፡፡

ለመንግሥት የሚሠሩ የኢኮኖሚ ባለሟሎች ምን ሠርተው ጊዜ እንደሚያጥራቸው ባይታወቅም፣ ጊዜ አጥሯቸው ለባለሥልጣናት የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች የተመረጡ ጥቂት ሆነው ነገር ግን ብዙ ነገሮችን የሚገልጹ አይደሉም፡፡ በሥራ አስኪያጅ ደረጃ የሚወሰኑ ዝባዝንኬ የግል ኢኮኖሚ ጉዳዮች ይበዛባቸዋል፡፡

ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ተሿሚዎች የኢኮኖሚ ዝባዝንኬዎችን (Economic Jargons) ማወቅ አይጠበቅባቸውም፡፡ የተመረጡና የተጠቃለሉ ጥቂት መረጃዎች ለፖሊሲ ውሳኔና ለፖለቲካ ፍጆታ ያህል ቢያውቁ በቂ ነው፡፡

እነኚህ ተመርጠው የተጠቃለሉ ጥቂት መረጃዎችም በመገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ በባለሥልጣናት ሲቀርቡ፣ ለባለሙያም ስለሚደርሱና ሲተነተኑ ደግሞ አገራዊ ፋይዳ የሌላቸውና ኢሳይንሳዊ ሆነው ትዝብት ላይ እንዳይጥሉ የኢኮኖሚ ባለሟሎች ኃላፊነት ነው፡፡

አንዳንዴ ደግሞ እጅግ የተጠቃለሉ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውና ለኢኮኖሚ ባለሟሎች ለራሳቸውም ሾላ ድፍን የሆኑ የብሔራዊ ኢኮኖሚ መረጃዎችን ለሕዝብ ንግግር እንዲያደርጉ ይሰጧቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በሰሞኑ ንግግር ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት አርባ በመቶ የሚሆነው መዋዕለ ንዋይ ወይም አዲስ ካፒታል ነው የሚል ይገኝበታል፡፡ ጥሩ ነው አሁን መነጋገር እንችላለን፡፡

የመዋዕለ ንዋይ መጠኑ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተገናዝቦና በሥሌት ተተምኖ ያመጣው ለውጥ ካልተለካ፣ ጥቅሙና አገራዊ ፋይዳው አይታወቅም ብለን እንሟገታለንAnchor፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፣ ከአገር ውስጥ ምርታችን አርባ በመቶውን ለመዋዕለ ንዋይ አውለን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቢገጥመን አይገርምም ሌሎች አገሮችም በእኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በነበሩ ጊዜ አጋጥሟቸው ተወጥተውታል፡፡ ለእኛም ጊዜያዊ ችግር እንጂ የሚያስፈራ አይደለም የሚል ነበር፡፡

 እኔም ያስፈራል አያስፈራም በሚለው ላይ የተለየ አቋም ለማንፀባረቅ ሳይሆን ከእምነቱ ባሻገር መፍትሔም እንዳለ ለመግለጽ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉም መዋዕለ ንዋይ ምን እንደሆነና መጠኑ ለኢኮኖሚው ዕድገት ምን አንድምታ እንዳለው የማውቀውንና የማስበውን ለማካፈል እሻለሁ፡፡

ስለሆነም ሾላ በድፍኑ ሆኖ ለቀረበው ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት አርባ በመቶው መዋዕለ ንዋይ ነው፡፡ መረጃ በባለሙያ ደረጃ ብቻ ሊታወቁ የሚችሉ መዋዕለ ንዋይን የተመለከቱ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዝባዝንኬዎችን ግልጽ ላደርግ እፈልጋለሁ፡፡

እነሱም በቅደም ተከተል ሁለቱ የመዋዕለ ንዋይ ዓይነቶችና ትርጉማቸው፣ የመዋዕለ ንዋይ ዕድገት ለምን ይጠቅማል? በውጭ ኢኮኖሚ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና በውስጥ ኢኮኖሚ የመዋዕለ ንዋይና ቁጠባ ጉድለት መስተጋብር፣ የሚሉ ናቸው፡፡

ሁለቱ የመዋዕለ ንዋይ ዓይነቶች

በብሔራዊ ኢኮኖሚ መዋዕለ ንዋይ በሁለት ዓይነት ሲከፈል አንዱና ዋናው ቋሚ ካፒታል ምሥረታ (Fixed Capital Formation) እና ሁለተኛው ከዘንድሮ ለከርሞ የተላለፈ ሳይሸጥ የቀረ ምርትና ግብዓተ ምርት ወይም በከፊል የተፈበረኩና ጥሬ ዕቃዎች ክምችት (Inventories) ናቸው፡፡ ቋሚ ካፒታል የሚፈለግና የሚታቀድ መዋዕለ ንዋይ ሲሆን፣ የቀረ ምርትና ግብዓተ ምርት ግን የማይፈለግና የማይታቀድ መዋዕለ ንዋይ ነው፡፡

ስለዚህም የኢኮኖሚ ትንታኔ በሚሰጥበትና ዕቅድ በሚታቀድበት ጊዜ የታቀደ መዋዕለ ንዋይና ትክክለኛ መዋዕለ ንዋይ (Planned and Actual Investment) የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች መሆናቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡

ለመሆኑ ከአርባ በመቶው መዋዕለ ንዋይ ውስጥ የቋሚ ካፒታሉና ሳይሸጥ የቀረው ጥሬ ዕቃና በከፊል የተመረተ ድርሻ፣ በባለሟሎቹና ዕቅድ አውጪዎቹ ይታወቅ ይሆን? አውቃለሁ የሚል ይናገር፡፡

የመዋዕለ ንዋይ ዕድገት ለምን ይጠቅማል?

መዋዕለ ንዋይ ወይም አዲስ ካፒታል የወደፊቱን ምርት ዕድገት መጠን ለማሥላት ይጠቅማል፡፡ የካፒታልና የምርት ጥምርታም (Capital – Output Ratio) በለውጥ አምጪ ምክንያቶችና በለውጥ መካከል በሚፈጠር ውስጣዊ መስተጋብራዊ ሒደት አማካይነት፣ የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት የሚተነበይበት ሥሌት ነው፡፡

አንድ ለረጅም ጊዜ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ ሥራ በኃላፊነት ያገለገለ ጓደኛዬ እንዳጫወተኝ ከሆነ፣ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በደርግ ጊዜ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን ለመተንበይና ለማቀድ በእያንዳንዷ ተጨማሪ ካፒታል ምን ያህል ተጨማሪ ምርት እንደሚመረት (Incremental Capital-Output Ratio (ICOR) ይለካ ነበር፡፡

በዚህ ዘመን የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትን ለመተንበይና ለማቀድ የካፒታልን ምርታማነት ወይም የቀጣይ ካፒታል ቀጣይ ምርታማነት (Marginal Productivity of Capital) ተለክቶ አይታወቅም፡፡ 11 በመቶ አገራዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ይገኛል ለማለት በኢሳይንሳዊ መንገድ የግብርና ምርት መጠን ጆንያ መቁጠር ነው የሚቀድመው፡፡ ለንደን ኢኮኖሚክስን ተምሮ ጆንያ ቆጥሮ ዕቅድ ማቀድ እንዴት ይሆናል?

ስለዚህም ስለ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ሲናገሩ ከጥሬ መረጃ ባሻገር የለውጥ ምክንያቶችና የለውጥ መስተጋብራዊ ተዛምዶን፣ በመጠንና በዋጋ ተምኖ እውነቱን ከነምናምኑ መናገር አገርን ከጉዳት ያድናል፡፡

በውጭ ኢኮኖሚ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና በውስጥ ኢኮኖሚ የመዋዕለ ንዋይና ቁጠባ ጉድለት መስተጋብር

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያጋጥመው በዋናነት በቁሳዊና በአገልግሎት ሸቀጦች ኤክስፖርት ኢምፖርት ክፍተት ሲሆን፣ በሚዘረጋላቸው የዕርዳታ እጅ የሚተማመኑ ታዳጊ አገሮች በዕርዳታ ማነስም ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ይጋለጣሉ፡፡ የኤክስፖርት ኢምፖርት ክፍተት በዕርዳታ ሊሸፈን ካልቻለ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ይሆናል፡፡

የውስጥ ኢኮኖሚ ጉድለትም በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ መካከል ያለ ክፍተት ነው፡፡ የውስጡ ጉድለት ለውጩ ጉድለት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የውጪውም ጉድለት ለውስጡ ጉድለት ምክንት ይሆናል፡፡

የውጭ ኢኮኖሚ ክፍያ ሚዛን ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና የመዋዕለ ንዋይና ቁጠባ ክፍተት የውስጥ ኢኮኖሚ ጉድለትም በመጠን እኩል ናቸው፡፡ የውጭውን ጉድለት በውስጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስተካከል፣ የውስጡን ጉድለትም በውጭ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስተካከልም ይቻላል፡፡

ስለሆነም በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ በምንዛሪ መጣኝ፣ በታሪፍ፣ በኮታ ወይም በኤክስፖርት ማነቃቂያ የሚወሰድ ዕርምጃ በውስጥ ኢኮኖሚ፣ በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ በውስጥ ኢኮኖሚ መሻሻል የውጪውን የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ለማስወገድም ቁጠባን ከመዋዕለ ንዋይ ማስበለጥ ያስፈልጋል፡፡

መዋዕለ ንዋይ ከጥቅል የአገር ውሰጥ ምርት 40 በመቶ ሲሆን፣ ቁጠባ ግን 22  በመቶ ብቻ ስለሆነ የመዋዕለ ንዋይና የቁጠባ ክፍተት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ያህል ክፍተት ቁጠባን በማበረታታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀረፋል ብሎ ማሰብም ይከብዳል፡፡

ቆጣቢዎችና መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች መንግሥት ወይም ግለሰቦች ስለሚሆኑ፣ የየትኛው አካል ቁጠባ ወይም መዋዕለ ንዋይ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም በሚገባ መጠናት አለበት፡፡

የግል ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ በፍላጎትና አቅርቦት በገበያ ውስጥ የሚወሰን ስለሆነ፣ በኢኮኖሚው ውስጣዊ ኃይል ግፊት የሚመራ (Autonomous) ነው፡፡ የመንግሥት ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ ግን የፖሊሲ ውጤት (Policy Driven) ነው፡፡ እንደ ግል የሚቆጠሩት የመንግሥት ድርጅቶች መዋዕለ ንዋይ ወጪም በአብዛኛው የፖሊሲ ውሳኔ እንጂ በገበያ ውስጣዊ ኃይል የሚመራ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ አውቆ በውስጡ ኢኮኖሚ መስተካከል የውጩን ጉድለት እናስወገድ? ወይስ በውጭ ኢኮኖሚ መስተካከል የውስጡን ጉድለት ማስተካከል ከሚሉት አማራጮች ተስማሚውን መምረጥ ወይም ሁለቱን ማጣመር ያስፈልጋል? የውጩን ኢኮኖሚ ለማስተካከል ብዙ ዓመት ተደክሞ ያልሆነ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም የውስጡን ኢኮኖሚ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ መዋዕለ ንዋይ ከቁጠባ ስለሚበልጥ ወይም መዋዕለ ንዋይን መቀነስ ወይ ቁጠባን ማሳደግ ያስፈልገል፡፡

የውጭ ጉድለቱ በውስጥ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ ካልተስተካከለ የውጭ ዕዳ ይቆለላል፡፡ ይኼም አበዳሪን ያሸሻል፡፡ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይንም ያባርራል፡፡ ምናልባትም እንደ አራጣ አበዳሪ የሆዷን በሆዷ ይዛ ቻይና ብቻ ልትሆን ትችላለች አባብላም ላበድራችሁ የምትለው፡፡

 ሰሞኑን በመገናኛ ብዙኃን በተነገረ ወሬ ምዕራባውያን አገሮች በመረጡት ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸው የመመልከት አዝማሚያ ምክንያት፣ እ.ኤ.አ. የ2017 የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገትም ከቻይና የማበደርና የመርዳት በጎ ፈቃድ ጋር እንደሚያያዝ ምሁራኖቻቸው ይገምታሉ፡፡ 

      ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles