Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሬቢስ በሽታን የሚከላከል የጤና ሥርዓት እየተዘረጋ ነው

ሬቢስ በሽታን የሚከላከል የጤና ሥርዓት እየተዘረጋ ነው

ቀን:

በአሜሪካው ተሰናባች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የተጀመረው ግሎባል ሴኩሪቲ ኢኒሼቲቭ በአዲስ አበባና በሌሎች ሦስት ክልሎች የእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) ወረርሽኝ ቢከሰት ምላሽ መስጠት የሚችል ሥርዓት ለመዘርጋትና ባለሙያ ለማፍራት በየአምስት ዓመቱ የሚታደስ ፕሮጀክት ቀርጾ እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ቡድን አስተባባሪና ተባባሪ ተመራማሪ አስታወቁ፡፡

ተባባሪ ተመራማሪው ዶ/ር አብርሃም ኃይሉ ይህንኑ አስመልክተው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከኢቦላ መከሰት በኋላ የተቋቋመው ይህ ኢንሼቲቭ ከቀረጸው ፕሮጀክት አንዱ ክፍል፣ ባህርዳርና መቀሌ ከተሞች ውስጥ የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ላቦራቶሪዎች እንዲኖሩ ማድረግ፣ እንዲሁም በማዕከል ደረጃ ኢንስቲትዩቱ ውስጥ የሚገኘውን ላቦራቶሪ አቅምን የሚያጠናክር ሲሆን፣ ላቦራቶሪውም አገልግሎቱን ለኦሮሚያ ክልል ተደራሽ እንዲያደርግ ታስቧል፡፡

እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ለላቦራቶሪ አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ የሕክምና መሣሪያዎችና ሪኤጀንቶች (ኬሚካል) በመግባት ላይ ሲሆኑ፣ በዚሁ ሥራ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የእብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ክትባትም ተደርጎላቸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት እንደሞላው፣ በዚህ ዓመት መጨረሻም ላቦራቶሪዎቹን የመክፈቱ ሥራ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚታመንም ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉ የእብድ ውሻ ቫይረሶች ዝርያን በተመለከተ ጥናት ለማድረግ በኢንስቲትዩቱ ዕቅድ ውስጥ የተካተተና እየተሠራበት ያለ ቢሆንም፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ ዝርያዎችን የመለየት ሥራ የሚሠራው ናሙና ወደ ውጭ አገር በመላክ ነው፡፡ የላቦራቶሪዎቹ ሥራ መጀመርም ይህንን ያስቀረዋል፡፡  

የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ክፍል ሥልጠና ተኮር የክትባት ዘመቻ ማካሄድ ሲሆን፣ ይህም በህዳር 2009 ዓ.ም. በጉለሌና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ያሉትን ውሾች በመከተብ ተጀምሯል፡፡

የዘመቻውም ዓላማ ምን ያህል ውሾች ሊከተቡ ይችላሉ? የሚል ሳይሆን ክትባቱ በዘመቻ ቢሠራ እንዴት ይከናወናል? የሚለው የተቀየሰበት ሲሆን፣ በቀጣይም ሐምሌና ነሐሴ 2009 ዓ.ም. ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ክትባቱን በዘመቻ ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል፡፡

ግሎባል ሴኩሪቲ ኢኒሼቲቭ ሊመሠረት የቻለው በኢቦላ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የጤና ሥርዓታቸው ጠንካራ መሆን አለበት ከሚል እሳቤ በመነሳት መሆኑን ዶ/ር አብርሃም ጠቁመው፣ የኢኒሼቲቩን የመጀመሪያ ዙር አቅርቦት ካገኙት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር አብርሃም እንደሚሉት፣ የውሻ በሽታ ምልክቶች ሁለት ዓይነቶች ናቸው፡፡ አንደኛው ምልክት ውሻው ተናካሽና ኃይለኛ መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ውሻው ሰው የመቅረብ፣ ዝምተኛ፣ ከኋላ እግሩ በታች ሽባ መሆንና ጨለማን መፍራት ናቸው፡፡ አፉ አካባቢ ያለው ጡንቻ የሚዝል በመሆኑም ለሃጩን ያዝረከርካል፣ አፉን ይከፍታል፣ ያስታውካልም፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች ውሻ አፉን ከፍቶ የሚቀረው አጥንት ጉሮሮው ላይ ተሰክቶ ነው በሚል እጃቸውን ወደ አፉ ይከታሉ፡፡ ውሻው በአፉ አካባቢ ያሉት ጡንቻዎች ስለሚዝሉ መናከስ ባይችልም፣ ስለሚቧጥጥ ለሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በዚህ ሳቢያም ለሞት የተዳረጉ ሰዎች እንዳጋጠሟቸው ዶ/ር አብርሃም ይናገራሉ፡፡

በተለይ ንክሻው እግር ላይ ከሆነ በሽታው ወደ ሴንትራል ነርቭ ሲስተም ሄዶ ጭንቅላት ውስጥ እስከሚገባ ድረስ ለወራት ከዛም ባለፈ ለአንድ ዓመት ሳይታወቅ ሊቆይ ስለሚችል፣ አንድ ሰው በበሽታ በተጠረጠረ ውሻ ከተነሰከ ክትባቱን መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...