Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየበላይ አመራሩም ይጠየቅ! ይቀጣ!

የበላይ አመራሩም ይጠየቅ! ይቀጣ!

ቀን:

የአገራችን የፖለቲካ ትኩሳትን ተከትሎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የገዥው ፓርቲና መንግሥት በጥልቀት መታደስ የሚለው ጉዳይና ይህንኑ ተከትሎ ከላይኛው የአመራር ዕርከን እስከ ታችኛው ባሉት የአመራር አባላት ዘንድ የመተካካትና የሽግሽግ እንቅስቃሴ ሲያካሂድ መታየቱ የሕዝቡን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ በሕዝቡ በኩልም የተለያየ አስተያየት እያስነሳ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሰሞኑን በሙስና የተጠረጠሩ አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው እየተነገረ ነው፡፡ ሆኖም ግን በሬ የሰረቀው ችላ ተብሎ ዶሮ የሰረቀውን ብቻ ማሳደድ፣ ከፍተኛ አመራሩን ወደ ሌላ የሥራ ምደባ በማዛወር ወይም በማሸሽ ከደሙ ንፁኅ የማድረጉ አዝማሚያ ሕዝቡን የሚያረካ ጥልቅ ተሃድሶ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም፡፡

በጋምቤላ ክልል እርሻ ለማልማት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለግለሰቦች ወደ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በብድር ወጪ ተደርጎ ሥራ ላይ ሳይውል ግለሰቦቹ ለሌላ ተግባር ማዋላቸው ከሰሞኑ አይተናል፡፡ የምርመራው ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቅረቡንም ሰምተናል፡፡ ስለሆነም ለበርካታ የልማት ሥራ ሊውል ይችል የነበረውን ይህንን ያህል የሕዝብ ገንዘብ እንዲዘርፍ በሩን የከፈቱ አመራሮች በሕግ ፊት ቀርበው ሊጠየቁ ይገባል፡፡

መንግሥት ኃላፊዎችን በመቀያየር ብቻ እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ሕዝቡ እንደ ጥልቅ ተሃድሶ ሊመለከተው የሚችል አይመስለኝም፡፡ በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የተጠያቂነት ዕርምጃ ወደ ከፍተኛ አመራሩም ሊዛመት ይገባዋል፡፡ የፌደራል ፀረ ሙስና ኮሚሽንም በቴሌቪዥን ድራማ ከማሳየት በላይ በነባራዊው ጉዳይ ላይ በመንቀሳቀስ ጥርስ ያለው አንበሳነቱን ያሳየን፡፡

(ማቴዎስ ሸመሎ፣ ከሐዋሳ)

* * * *

የችግሩም የመፍትሔውም ባለቤቶች ነን

በዛሬዋ ኢትዮጵያችን እየተስተዋለ ያለው ችግር ሁላችንም የፈጠርነው ነው፡፡ እኛው ኢትዮጵያውያን የችግሩ ባለቤቶች ነን፡፡ የችግሩ ባለቤቶች እኛ እስከሆንን ድረስ መፍትሔውም የሚጠበቀው ከእኛው ነው፡፡፡

እርግጥ ነው አንዱ ዜጋ የችግሩ ፈጣሪ ሌላኛው ደግሞ ተባባሪ እንደሆነ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ በመሐሉ የችግሩ ሰለባዎች መኖራቸውን ግን አንዘነጋም፡፡

እነዚህ በመጨረሻው ረድፍ ላይ የሚገኙ የችግሩ ሰለባዎች በቀን ሦስቴ መብላት የሚናፍቁ፣ በቂ መጠለያ የሌላቸውና በደሳሳ ጎጆ የሚኖሩ፣ በጎዳናውና በየደብሩ ጥጋጥግ የሚተኙ ምስኪኖች ናቸው፡፡ ይህንን የምንረዳው ማስተዋልን ከታደልን ነው፡፡ በዝሆኖች እርግጫ ሳሩ ይጎዳል፡፡ ቤተሰብ በፍቺ ሲለያይ ተጎጂዎቹ የወለዷቸው ልጆች ይሆናሉ ብለን የምናስብ ከሆነ እንዲህ ያለው ችግር በግልጽ ይገባናል፡፡

እነዚህ ሰዎች እስከዛሬ ድረስ በድህነት ውስጥ ሆነው የመከራ ኑሮ እንዲመሩ የየበኩላችንን አስተዋፅኦ እንዳበረከትን ማመን አለብን፡፡ ይህንን የምናውቀውና የምንገነዘበው ራሳችንን በጥልቀት ስንፈትሽ ነው፡፡ እኛ ብልጠት በሚመስለን ማጭበርበርና ለራስ ጥቅም በማድላት በሚፈጸም ኃጢዓት የተነሳ ስንቱ ሰው ይሆን በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖረው?

በአገራችን የኑሮ ልዩነቱ እንዲህ እየሰፋ የመጣው አንዳችን ለሌላችን ማሰብና መጨነቅ እየተውን በመምጣታችን ነው፡፡ ‹‹የአንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል ከእኔ ቤት፤›› የሚለው አባባልም ለኤችአይቪ ኤድስ በሽታ ብቻ የማስጠንቀቂያ ደውል ሆኖ የሚቀር እንዳይመስለን፡፡

ዛሬ በአገሪቱ ለተከሰተውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላስከተለው ችግር ግማሽ ሰበቡ የእኛው የአገሪቱ ዜጎች የግለኝነት አባዜና ‹‹ከራስ በላይ ነፋስ›› ባይነት ነው፡፡፡ ‹‹የእኔ ቤት በእሳት ካልተያያዘ የጎረቤቴ ቢነድ ምን አገባኝ?›› ማለታችንን የምንቀጥል ከሆነ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለወራት ሳይሆን ለዓመታት ይቀጥል ቢባል (አልተባለም እንጂ) አያስገርመኝም፡፡ ይህ እንዲሆን ግን የምንፈልግ አይመስለኝም፡፡ እና ምን እናድርግ?

ዜጎች በግለሰብ ደረጃ የሚጠበቅብን፣ ሁሉም ዜጋ ክቡርና ሰብዓዊ ፍጡር መሆኑን አምነን፣ ወንድሜ፣ እህቴ፣ አባቴ፣ እናቴ በመባባል፣ የጎረቤታችንን ልጅ የእኔ ልጅ ነው ብለን በመቀበል፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በመልክ ራሳችንን ሳናዋርድ በፍቅር መኖር እንጀምር፡፡

እንዲህ ዓይነት ኑሮ መኖር ስንጀምር ሕይወታችን የሰመረ ኑሯችንም የተደላደለና ሰላም የሞላበት ይሆናል፡፡ በተቋርኖ የተሞላ ሕይወትን ማጣፈጥ የሚቻለው፣ ለሌሎች ችግር መፍትሔ በመስጠትና ችግራቸው ሲቀረፍ ‹‹እፎይ›› በማለት ሲደሰቱ ስናይ ነው፡፡ (እንደ ሼክ አላሙዲን ያሉ ሰዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለተቸገሩ ሰዎች ሲለግሱ፣ በገንዘብ የሚገዛ ደስታ እንደሌለ፣ ከምቾትና ከድሎት ኑሯቸው ተገንዝበው መሆኑን መገንዘብ ይገባል)፡፡

የአገሪቱ ዜጎች በራሳቸው ላይ ሊደረግባቸው የማይፈልጉትን በወንድምና በእህታቸው ላይ እንዲሆን እስካልፈለጉና እስካላደረጉ ድረስ፣ በመካከላቸው ገላጋይና ሸምጋይ መግባት እንደማያስፈልገው የታወቀ ነው፡፡ ይህ ከተፈጸመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ቢሆን ነገውኑ ሊነሳ ይችላል፡፡ የከረሩ ነገሮችም በቀላሉ ሊረግቡ ይችላሉ፡፡

የአገሪቱ መንግሥትን ጨምሮ ሁላችንም የዚህች አገር ዜጎች ነን፡፡ ሁላችንም ኅሊና አለን፡፡ ሁላችንም እንደ ዕውቀታችን፣ እንደ ንባብ አቅማችን፣ እንደ አስተዳደጋችንና እንደ አመጣጣችን የሚኖረን ኅሊናም በዚያው ልክ ይመዘናል፡፡ ውጤቱም ከፍና ዝቅ ማለታችንን ያሳያል፡፡

የእያንዳንዳችንን የዕውቀት ርቀትና ምጥቀት እንዲሁም የጥበብ ፋይዳ መስፈሪያው ተግባር ነው፡፡ በተግባር ስንፈተሸ የእኛ መማር፣ የእኛ ፕሮፌሰርነት ቀሎ ሊገኝ ይችላል፡፡ ምናልባት ደሃ ዜጋችን ዳቦ ሲጠይቀን ጠብመንጃ ከነጥይቱ አቅርበንለት ከሆነ ምኑን አወቅነው፡፡

ጥበባችን ዜጎች እርስ በርስ ተገዳድለው የሚያልቁበትን መርዝ መቀመም ሆኖ ከተገኘም ምኑን ጥበብ ሊሆን ነው፡፡ ጥበብን በመጠቀም በእያንዳንዱ ዜጋ ኅሊና ውስጥ ፍቅርና ሰላምን መቅረጽ ቀላል እንዳልሆነ ቢገባኝም፣ በረቀቀ የተንኮል ጥበብ ግን በርካታ ዜጎች ማን ምን እንደሠራባቸውና እንዳደረገባቸው ሳይገነዘቡ የችግርና የመከራ ኑሮ ለመኖር እንደሚገደዱ ተገንዝቤያለሁ፡፡

ለችግሮቻችን የተለያየ ስያሜ ልንሰጣቸው እንችላለን፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ልንፈርጃቸው እንችላለን፡፡ እርግጥ ነው ችግሮቹን የፈጠርናቸው እኛው ነንና ስም መስጠቱ አይከብደንም፡፡ ይህ ግን የእኛን ማወቅና ጥበበኝነት አይገልጽም፡፡

ለማወቃችንና ለመጠበባችን የሚመሰከርንልና የሚጨበጨብልን ራሳችን ለፈጠርነው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ስናገኝለት ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂዎቹ የዚህች አገር ዜጎች እስከሆንን ድረስ እያንዳንዳችን ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል፡፡

መንግሥት እንደመንግሥት ለመፍትሔው እንዲያሰማራን የእኛን የተግባር ሰውነት ይሻል፡፡ ዝግጁነታችንን በተግባር ለማረጋገጥና ለመሳተፍ ከገዢው ፓርቲ አባላት፣ ከአገር ሽማግሌዎቸና ከፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ አይደለም እንቅስቀሴ የሚጠብቀው፡፡ ይህችን አገር በፎጣ ጠቅልሎ ማንም ለኢሕአዴግና ለአባላቱ አልሰጣቸውም፡፡ ይህች አገር በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አገር ናት፡፡

መልካም ዜጎች የጎረቤታቸው ቤት ሲንኳኳ በዚህ ውድቀት ማነው ያንኳኳው ብለው መብራት አብርተው፣ በራቸውን ከፍተው ያያሉ፡፡ ድረሱልኝ ተብሎ ቢጮህ ሮጠው ይደርሳሉ፡፡ በደስታና በሐዘን ከጎኑ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያውያን አብረውት የኖሩትን ጎረቤታቸውን እንደ ቤተሰባቸውና አጋራቸው የሚታዩት፡፡

የኢትዮጵያን ታላቅነቷን እንጂ ክፉዋንና ውድቀቷን የማይሻ ዜጋ አሁን በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር እኔንም ይመለከታል ብሎ ማሰብ መጀመር አለበት፡፡ ለመፍትሔውም መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከላይ የጠቀስኩትን ሐሳብ መርምሮ ራሱን ፈታሽ የመፍትሔው አካል ለመሆን መዘጋጀት አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ነው የመጪው ትውልድ ፀሐይ የማጠልቅ የምትሆነው፡፡

(መኮንን ሻወል፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...