Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ ግል ከተዛወሩ የልማት ድርጅቶች 2.2 ቢሊዮን ብር ዕዳ መሰብሰብ አልተቻለም

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ሚድሮክ ከገዛቸው ድርጅቶች 1.7 ቢሊዮን ብር ይፈለጋል

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ባለፈው በጀት ዓመት ወደ ግል ካዛወራቸው ተቋማት መሰብሰብ የነበረበትን 2.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንዳልቻለ አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ መሰብሰብ የቻለው 611 ሚሊዮን ብር (25 በመቶ)  ብቻ ነው፡፡ ለሚኒስቴሩ ገቢ አሰባሰብ ደካማ መሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የሚድሮክ ኩባንያዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር አቶ ግርማ አመንቴ ከሳምንት በፊት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የገዙ ባለሀብቶችንና ኩባንያዎችን ጠርተው፣ በወቅቱ ክፍያ በማይፈጽሙበት ምክንያት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መሰብሰብ ከነበረበት 2.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ሚድሮክ የገዛቸው ኩባንያዎች 1.7 ቢሊዮን ብር ባለመክፈል ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ከሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚድሮክ ብዛት ያላቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ግዥ ፈጽሟል፡፡ ትልቁ ክፍያም የሚጠበቀው ከሚድሮክ ነው፡፡

‹‹ገቢ በመሰብሰብ ረገድ በአንድ በኩል ዝቅተኛ አፈጻጸም ቢኖረንም፣ ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት አክሲዮን ማኅበርን ከ11 ቢሊዮን ብር (510 ሚሊዮን ዶላር) በላይ በሆነ ዋጋ የአክሲዮን ሽያጭ ፈጽመናል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ችለናል፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ በሌላ በኩል ከፍተኛ ገቢ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ባለሀብቶቹና ኩባንያዎቹ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ እስከ ሰኔ 2008 ዓ.ም. ማጠናቀቅ ነበረባቸው ተብሏል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሦስት ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ቢጠይቁም፣ በጭማሪ ጊዜው ውስጥም ክፍያ መፈጸም እንዳልቻሉ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የገዙ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ክፍያቸውን በወቅቱ መክፈል ያልቻሉበትን ምክንያት ሚኒስትሩ በጠሩት ውይይት ላይ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሽያጭ ቢፈጽምም የወሰን ማስከበር ሥራ ባለመከናወን፣ የይዞታ ካርታ አለመኖር፣ በምርት ሒደት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አለመኖር፣ በጡረታ የሚገለሉ ሠራተኞችን ማስተናገድ አለመቻሉ፣ የውጭ ንግድ ገበያ እጥረትና አፈጻጸም ደካማ መሆን ተጠቃሽ ምክንያቶች ሆነው ቀርበዋል፡፡

አቶ ግርማ በመንግሥት በኩል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ፣ ገዢዎቹም ያሉባቸውን ችግሮች ፈተው በፍጥነት ከመንግሥት የሚፈለግባቸውን ገንዘብ እንዲያስገቡ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የይዞታ ካርታ ችግሮቻችንን ከክልሎች ጋር በጋራ የምንፈታው ነው፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተያዘው በጀት ዓመት 14 የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር አቅዷል፡፡ ከልማት ድርጅቶቹም 3.1 ቢሊዮን ብር ለማስገባት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች